የአገሬው ሰው “ውሃ የሬሳ ማጠቢያ ነው” የሚል ብሂል አለው። ይህም አባባሉ አንድም ሁሉም ሰው በተፈጥሮ ያገኘውን ውሃ ሳይሰስት ለጠማውና ለታረዘ በደግነት መስጠት እንዳለበት የሚያስተምር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ሁሉን ጥሎ የሚያልፍ ፍጥረት በመሆኑ ባለው መኩራራትና መመጻደቅ እንደሌለበት ይልቁንም ያለውን ተካፍሎና ተዛዝኖ መብላት መጠጣት፤ ያለው ለሌለው ማካፈል እንዳለበት የሚያስተምር አባባል ነው።
ከዚህ የተነሳም በቀደሙት ዘመን ኢትዮጵያውያን ባህልና ወግ “ውሃ” ለጠየቀ ሁሉ የማይነፈግ ውድ የተፈጥሮ ስጦታ ነው። በሌላ በኩል ሳይንሱ ደግሞ የሰው ልጅ መላ አካሉ 50 በመቶው ውሃ ሲሆን ሁሉንም የሰውነት አካል የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ደግሞ 75 በመቶ ስሪቱ ውሃ እንደሆነ ያስተምራል። ይህም የሚያሳየው ምድር ላይ ለሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወሳኝ ከሚባሉ የተፈጥሮ ስጦታዎች አንዱና ግንባር ቀደሙ ውሃ ነው።
ዋተር ኤይድ የተባለው ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ እንደሆነች ቢነገርላትም በአፍሪካ በንፁህ ውሃ አቅርቦት ችግር በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አገራት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያ ስትሆን፤ ኤርትራ፣ ዩጋንዳ፣ ሶማሊያና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ይከተሏታል። እንደ ድርጅቱ ሪፖርትም በኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ በአቅራቢያው አያገኝም።
አገሪቱም የውሃ አቅርቦትን እያሻሻሉ ካሉ 10 የዓለም አገራት ውስጥ 7ተኛ ደረጃ ላይ ነች። በመኖሪያ አቅራቢያቸው ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከማያገኙ 10 አገራት መካከል 2ተኛ፣ በጣም ዝቅተኛ የውሃ አቅርቦት ካላቸው አገራት ደግሞ በ4ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በአገሪቱ 39 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ብቻ በመኖሪያ አቅራቢያው ንፁህ የመጠጥ ውሃ ያገኛል። ያ ማለት አብዛኛው ህዝብ ውሃ ለማግኘት ረዥም መንገድ በመጓዝ አስቸጋሪ የለት ዕለት ህይወት ይገፋል ማለት ነው።
ከዚህ አኳያ በተለይ በመዲናዋ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነትና ተደራሽነት ከሌሎች የአገሪቱ ክፍልና ከተሞች አንጻር የተሻለ ቢሆንም፤ በሀብታምና በድሆች መካከል ሲታይ ልዩነቱ የትየ ለሌ እየሆነ መጥቷል። በአብዛኛው የከተማዋ የውሃ ስርጭት ሲታይ በአማካኝ በወር አንዴና ሁለት ጊዜ፤ በዛ ከተባለ ሶስት ጊዜ ነው። በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ከፍተኛ የውሃ እጥረት በመኖሩ ምክንያት የውሀ አቅርቦቱ በወር አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ የሚሆንበት ጊዜ ያጋጥማል።
ይህንን የከተማዋ ነዋሪዎችን የውሃ ችግር የተረዱ ጮሌ ነጋዴዎች ውሃ በቦቲ ተሽከርካሪ ጭነው በየሰፈሩ እየዞሩ መሸጥ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ግለሰቦቹ በተለይ በጋራ መኖሪያቤቶች እና ከፍተኛ የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ከነዳጅ ባልተናነሰ ዋጋ ውሃን እየቸበቸቡ ይገኛሉ።
ይህ ውሀ በቦቴ የመሸጡ እውነታ ስራዬ ተብሎ ሰው ሰራሽ የውሀ እጥረት እየፈጠረ ስለመሆኑም የሚያነሱ አልታጡም። በጋራ መኖሪያቤቶች እና ከፍተኛ የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ቧንቧቸው ደርቆና ዝጎ ውሃ በቦቲ ተሽከርካሪ ጭነው ውሃ ፈላጊ እያሉ የሚቸበችቡ ግለሰቦች “ውሃ ከየት አመጡ?” የሚለውንም ጥያቄ ለማንሳት የሚገደዱም ጥቂቶች አይደሉም።
እንደውም በማስረጃ አልተረጋገጠም እንጅ በሀሜት ደረጃ በሀብታሞች ሰፈር ውሃ አትጠፋም ነው የሚባለው። በተጨባጭ ደግሞ ድሃዋና ለፍቶ አዳሪዎች እናት ግን ካለው የኑሮ ውድነት አኳያ ልጆቿን ሻይ አፍልታ ዳቦ በሻይ እንኳ የምትመገብበት ውሃ አጥታ አንድ ጀሪካን ውሃ 20 እና 30 ብር እየገዛች ኑሮዋን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ” አድርጎባታል።
አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት አካላት በቦቲ ውሃ ጭነው ለህብረተሰቡ በነጻ ሲያቀርቡ የሚስተዋልበት ጊዜ ቢኖርም፤ ውሃ ለማግኘት ባለው ከፍተኛ ሽሚያ፣ በተለይ በጋራ መኖሪያቤት አራተኛ ወለልና ከዚያ በላይ የሚኖሩ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ተሻምተው ውሃውን ለማግኘት የሚቸገሩበት ሁንታ ሰፊ ነው።
ውሃውን እንደምንም አገኙ ቢባል እንኳን ውሃውን እቤታቸው ድረስ ለሚያደርስላቸው የጉልበት ሠራተኛ ከፍተኛ ወጪ ነው የሚያወጡት። ስለዚህ ውሃውን ሲገዙ ደግሞ ወጪያቸው እጥፍ ድርብ ነው የሚሆነው።
ከዚህ ባሻገር በቦቲ ተሽከርካሪ ተጭኖ በየሰፈሩና በየሆቴሉ የሚቸበቸበው ውሃ ምን ያህል ለጤንነት ተስማሚ መሆኑ በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ተፈትሿል? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ ሌላ ችግር ነው።
ከዚህም ባለፈ በከተማዋ የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች አንዳንድ ግለሰቦች ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተው ይሆን አይሁን ባይታወቅም የከርሰ ምድር ውሃ አውጥተው ሲሸጡ ይስተዋላል። ይህስ ኅብረተሰቡ በጋራና በእኩልነት ሊገለገልበትና ሊጠቀምበት የሚገባውን የተፈጥሮ ሀብት የግለሰቦች የሀብት ማካበቻ መሆኑ ተገቢ ነው? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።
ምክንያቱም ሁሉም ማህበረሰብ በጋራ ሊጠቀምበት የሚገባውን የአገር ተፈጥሮ ሀብት አንድ ግለሰብ እየሸጠ ሀብት የሚያካብትበት ሌላኛው ደግሞ መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያቀርብለት የሚገባውን ተፈጥሮ ሀብት ባልተገባ ዋጋ ገዝቶ የሚጠቀምበት የሞራል ሆነ የሕግ ግዴታ የለበትም።
በጥቅሉ በከተማዋ የእውነት የውሃ እጥረት ስላለ ነው ወይስ ግለሰቦች በሚፈጥሩት ሰው ሰራሽ የውሃ እጥረት ህዝቡ ላልተፈለገ ወጪና ኪሳራ እየተዳረገ ነው? እንዲሁም ውሃ በቦቲ ተሽከርካሪ ጭነው ውሃ ፈላጊ እያሉ እየዞሩ የሚቸበችቡ ግለሰቦች ውሃውን ከየት አገኙት? ውሃውስ ምን ያህል ለጤንነት ተስማሚ ነው? ምን ያህል ውሃ የመሸጥ ሕጋዊ ፈቃድስ አላቸው በሚሉት ጉዳዮች ላይ ከተማ አስተዳደሩ ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ ሊያደርግ ይገባል።
በተጨማሪም ጉዳዩ ተራ ቢመስልም የሰፊውን ማህበረሰብ ውሃ ጠጥቶ የማደር ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ መንግሥት አሁን ላይ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋት በያዘው ቁርጠኛ አቋም ዘርፉን ፈትሾ የመዲናዋን የውሃ ችግር መሰረታዊ መንስኤ በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ሊያስቀምጥ ይገባል ባይ ነኝ።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓም