እኛ ኢትዮጵያውያን ዘመናት ያስቆጠሩ ከሰላም ጋር የተያያዙ ብዙ ባህላዊ ፣ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ እሴቶች ያሉን ህዝቦች ነን። እነዚህ እሴቶቻችን ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸሩ፣ እንደ አገርም መለያችን ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው።
የሰላም ጠንቅ የሆኑ ችግሮችን ቀድሞ ከመከላከል የሚጀምሩት እነዚህ አገራዊ እሴቶቻችን፣ የተጣሉ ግለሰቦችን፣ ጎሳዎችን፣ የማህበረሰብ ክፍሎችን ማስታረቅ፣ ቀጣይ ሕይወትን በተሻለ መንገድ በሰላማዊ መንገድ መምራት የሚያስችል አቅም ያካባቱ ናቸው።
የአካባቢ እና የአገር ሽማግሌዎችን፤ የሃይማኖት አባቶችን ፤ የጎሳ መሪዎችን በማክበርና በመታዘዝ አስተምሮ ላይ የተመሰረቱት እነዚህ እሴቶቻችን ፤ እንደ አገር ለመጣንባቸው ረጅም ዘመናት የሕዝብ ለሕዝብ ሰላም መሰረት እንደሆኑም ይታመናል።
እነዚህ እሴቶቻችን በተለይም ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ”በዘመናዊ ትምህርት እና ስልጣኔ” ስም ባጋጠማቸው ፈተና አገር እንደ አገር አደጋ ውስጥ ከገባች ውሎ አድሯል። በዚህም ለመክፈል የተገደድነው ያልተገባ ዋጋ የከፋ ስለመሆኑ የትናንቶቹ ሳይሆኑ የዛሬዎቹም ታሪኮቻችን ተጨባጭ ማሳያ ሆነዋል።
የለውጥ ኃይሉ ይህንን ታሪክ ለመቀየር ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ ለውጡ ለአገራዊ ሰላም መሰረት በሆኑ ፤ በይቅርታ እና በፍቅር እሴቶቻችን ላይ መሰረት አድርጎ እንዲጓዝ፤ በዚህም የቀደሙት ጥቋቁር የለውጥ ታሪኮቻችን እንዳይደገሙ ረጅም ርቀት ተጉዟል።
የለውጥ ኃይሉ አዲስ የፖለቲካ አካሄድም በመላው ሕዝባችን ከፍ ያለ ተቀባይነት የማግኘቱም ሚስጥር ከዚህ የመነጨ ነበር፤ ይሁንና በታቀደው መንገድ መጓዝ የሚችልበት ዕድል ባለማግኘቱ ላለፉት አራት አመታት እንደ አገርና ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ተገደናል።
መንግስት ግጭቶች ከተፈጠሩም በኋላ በሰላማዊ መንገድ በውይይት/በድርድር እንዲፈቱ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ፣ የአገር ሽማግሌዎች፤ የሀይማኖት አባቶች ፤ የጎሳ መሪዎች፤ የግጭቶች ዋንኛ ተጋላጭ የሆኑ እናቶችን ጨምሮ ጉዳዮችን እንዲሸመግሉና ሰላም እንዲያሰፍኑ ጥሯል።
ከሕወሓት ጋር የነበረውን አለመግባባት ጨምሮ ከሰላም ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮችን በእጃችን ባሉ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ እሴቶች ለመፍታት ብዙ ጥረት ተደርጓል። ከምንም ነገር በላይ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠትም ለእዚሁ እውን መሆን የሚጠቅሙ እሴቶቻችንን በተግባር እንዲውሉ ቢሞከርም ግጭቶች ማጋጠማቸው ግን አልቀረም።
አጋጣሚውን እንደ መልካም እድል የወሰዱት ታሪካዊ ጠላቶቻቻንም ለችግሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ በመሆን፤ አገርን እንደ አገር የህልውና ስጋት ውስጥ ገብታ እንደነበር የሚታወስ ነው። በሕዝባችን መካከል ፈጥሮት የነበረው ግራ መጋባትና ግራ መጋባቱ የፈጠረው ፈተና ብዙ ነበር።
በርግጥ ወደ ግጭት የገቡ ፖለቲከኞቻችን ለነዚህ አገራዊ እሴቶቻችን በቂውን ትኩረት መስጠት ችለው ቢሆን ኖሮ፤ ለውጡ ይዞት ከመጣው የለውጥ አስተሳሰብም ሆነ አስተሳሰቡ ሊፈጥርላቸው ከሚችለው ዘላቂ ተጠቃሚነት አንጻር የከፈልነውን ያልተገባ ዋጋ ከመክፈል እንድን ነበር። አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመጪው ትውልድ ፈጥረን የምናልፍበትን እድል መፍጠር እንችል ነበር።
በፌደራል መንግስት እና በሕወሓት መካከል የነበረው ግጭት /ጦርነት በደቡብ አፍሪካው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እልባት ማግኘቱ ፤ በኋላም በናይሮቢ፤ በመቀጠልም፤ በመቀሌ ያለውጪ አደራዳሪዎች የመንግስትና የሕወሓት ተደራዳሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው የመነጋገራቸው እውነታ ለራሳችን ቸግር መፍትሄው ራሳችን መሆናችንን ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።
ይሁንና አሁን ለተጀመረው ሰላም ውጤታማነት በእነዚህ አገራዊ እሴቶቻችን ላይ በመታመን ሕዝባችን እንደ ሕዝብ የሚፈልገውን እና ብዙ ዋጋ የከፈለበትን ሁለንተናዊ ሰላም ለማስፈን ሁላችንም ራሳችንን ለእሴቶቹ ተገዥ ማድረግ ይጠበቅብናል።
በርግጥ እነዚህ ዘመናት ያስቆጠሩት የሰላም እሴቶቻችን አሁን ላይ የሚታዩ አለመግባባቶችን ብቻ ሳይሆን፤ በቀጣይ ሆና ለማየት ለምንፈልጋት ሰላማዊና የበለጸገች አገር ምስረታ ከምንም በላይ አቅም መሆን እንደሚችሉ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። መጪ ትውልዶችን በእነዚህ እሴቶች በመግራት የትናንት ጥቁር ታሪኮቻችን ማከም የምንችልበትም እድል ሰፊ ነው !
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓም