ከሰባ ስምንት በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ወጭና ገቢ ንግድ የሚስተናገድበት የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል በየጊዜው በርካታ ማስፋፊያዎችንና ማሻሻያዎችን በማድረግ አቅሙን እያሳደገ ቢመጣም፤ የአስመጭዎች ኮንቴነራቸውን በወቅቱ አለማንሳት በወደቡ አሰራር ላይ ለዓመታት መፍትሔ ሳይገኝለት የዘለቀ ቁልፍ ማነቆ ሆኖ መቀጠሉን በህዳር ወር መጀመሪያ ላይ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ለዓመታት መፍትሔ ሳያገኝ እየተንከባለለ ዛሬ ላይ የደረሰው ይኸው ችግር በአሁኑ ሰዓት እየተባባሰ በመምጣቱ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ከምንጊዜውም በላይ የከፍተኛ አመራሩን ትኩረት የሚሻበት ሰዓት ላይ መሆኑንም አመላክተን ነበር፡፡
እስከ ህዳር ወር መጀመሪያ ድረስ በወደቡ ውስጥ የተለያዩ ዕቃዎችን የያዙ 14ሺ 343 ኮንቴይነሮች ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ ይህም ወደቡ መያዝ ከሚገባው የመጨረሻ አቅም ላይ እየደረሰ በመሆኑ ችግሩ በአፋጣኝ ካልተፈታ የወደቡን አጠቃላይ ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን ከወር በፊት ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች ወደቡን በጎበኘበት ወቅት በወደቡ አስተዳደር በኩል ተገልጿል፡፡ በወደቡ ተከማችተው ከሚገኙ 14ሺ 343 ኮንቴይነሮች ውስጥ 3ሺ 856 ኮንቴነር ዘይት ሲሆን፤ ይህም ያለምንም ታክስና ቀረጥ በመንግሥት ድጎማ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ነው፡፡
እኛም ለዛሬው የኅብረተሰቡን ህይወት በቀጥታ የሚነኩ በመሆናቸው ትኩረታችንን ሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ላይ በተከማቹት የዘይት ኮንቴነሮች ላይ አድርገናል፡፡ ዘይት ለኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች መካከል ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ከፍተኛ ፍላጎት የሚስተዋልበት የዘይት ምርትም ሁሌም በገበያ ላይ እጥረት ይታይበታል፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ከሌሎች ምርቶች በተለየ ዘይትን ለመሳሰሉ ምርቶች ለሚያስገቡ አስመጭዎች ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ እንዲያስገቡ የሚያደርገው፡፡ ከዚህ ባለፈም እነዚህን ምርቶች በማስመጣት ሥራ ላይ ለተሰማሩ አስመጭዎች ድጎማም ያደርጋል፡፡
ይሁን እንጅ በዚህ መንገድ በልዩ ማበረታቻ ወደ አገር ውስጥ የገቡት የዘይት ምርቶች አስመጭዎች በወቅቱ ኮንቴይነራቸውን ማውጣት ባለመቻላቸው ምርቶቹ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ለረጅም ጊዜ ወደቡ ላይ ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ በገበያ ላይ የአቅርቦት እጥረት እየፈጠረ በመሆኑ በኅብረተሰቡ ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ኅብረተሰቡ በአቅርቦት እጥረት እየተቸገረ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ግን ዘይት ወደቡ ውስጥ ተከማችቶ ይገኛል፡፡
ይህም ፍጹም ተገቢነት የሌለው ድርጊት በመሆኑ አስመጭዎች በኣፋጣኝ ምርታቸውን የማያነሱ ከሆነ መንግሥት የራሱን እርምጃ ለመውሰድ ውሳኔ ላይ መድረሱን የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ ይናገራሉ፡፡ “በዚህ መሰረት ስልሳ ቀናት ያለፋቸው ኮንቴይነሮች ሁሉ እንዲወረሱና ለኅብረተሰቡ ፍጆታ ሊውሉ በሚችሉበት አግባብ እንዲሰራጩ የሚደረጉበትን መንገድ አመቻችተናል” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ለዚህም “አለ በጅምላ” የተባለ ድርጅት ዘይቶችን ተረክቦ ለኅብረተሰቡ እንዲያከፋፍል ከድርጅቱ ጋር ስምምነት ተፈርሞ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ በስምምነቱ መሰረት በወደቡ ተከማችተው ከሚገኙት 3ሺ 856 ኮንቴይነር ዘይት መካከል አንድ መቶ የሚሆኑትን አውጥቶ ማከፋፈል ጀምሯል፡፡
በቀጣይም በገባው ቃል መሰረት የተቀሩትን ኮንቴይነሮች ለማውጣትና ለማከፋፈል እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፤ ድርጅቱ በሚፈለገው ፍጥነት ሥራውን እያከናወነ ባለመሆኑ ሂደቱ አዝጋሚ መሆኑንም ነው ኮሚሽነሩ ያመላከቱት፡፡ ስለሆነም አጥጋቢ ውጤት የማይገኝ ከሆነ መንግሥት አማራጭ ርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቷል፡፡ “ስለዚህ ሁኔታውን አይተን ኮንቴይነሮችን የማውጣትና የማከፋፈል ሥራው እኛ በምንፈልገው ፍጥነት የማይከናወን ከሆነ ግልጽ ጨረታ አውጥተን እንሸጣቸዋለን” ነው ያሉት፡፡ ምክንያቱም ጊዜው በረዘመ ቁጥር ምርቶቹ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ሊጨርሱና ከጥቅም ውጭ ሊሆኑ ስለሚችሉ ለኅብረተሰቡም ለመንግሥትም ሳይሆኑ አጉል ስለሚቀሩ ነው፡፡ ወደዚህ ርምጃ ከመገባቱ በፊትም ለሁሉም አስመጭዎች ምርቶቻቸውን እንዲያነሱ በስልክ፣ በደብዳቤና በመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ እንዲያውቁ መደረጋቸውንና ጥሪ የቀረበላቸው መሆኑንም ነው የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ያስታወቁት፡፡
እኛም አስመጭዎቹ በዚህ ዙሪያ ያላቸውን ሀሳብና የሚሰጡትን ምላሽ ለማወቅ የበኩላችንን ጥረት አድርገናል፡፡ በዚህም በሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ተከማችተው ከሚገኙት 3ሺ 856 የዘይት ኮንቴይነሮች መካከል የ1ሺህ 63 ኮንቴይነሮቹ አስመጭ ወደሆነው የደብሊው.ኤ. ዘይት አስመጭና አከፋፋይ ኃላፊነቱና የተወሰነ የግል ድርጅት ደወልን፡፡ የድርጅቱ የሎጅስቲክስ የገቢ ንግድ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ እፀገነት ጌታቸው ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ፤ ድርጅታቸው ዘይት የሚያከፋፍለው ለምስራቅ ጎጃምና ለአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ወደብ ላይ የተከማቸው ዘይት ለአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ያስመጡት መሆኑን ጠቁመው “ሆኖም ኮሚሽኑ መጋዘኔ ሙሉ ነው በማለቱ ያመጡለትን ዘይት ማውጣት ባለመቻሉ የተፈጠረ ችግር እንጂ በእኛ ምክንያት አይደለም” ይላሉ፡፡
ኃላፊዋ እንደሚሉት፤ አስመጭው ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ጋር ያለው ስምምነት እስከ ወደቡ የማድረስ እንጅ እስከ የኮሚሽኑ መጋዘን ድረስ ለማቅረብ አይደለም፡፡ ኮሚሽኑ ለአስቸኳይ አቅርቦት ወደ አራት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ አስገብቶ በመጋዘኑ አከማችቶ ስለነበረ ቦታ የለኝም በማለቱና ዘይቱን ካስመጡ በኋላ በወቅቱ ባለመረከቡ ምክንያት ኮንቴይነሮቹ እስካሁን በወደቡ ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ለአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽንና ለምስራቅ ጎጃም እንዲያቀርቡ ከንገድ ሚኒስቴር በተፈቀደላቸው መሰረት ለኮሚሽኑ ያስመጡት በራሱ ችግር ምክንያት ወደብ ላይ ከመቆየቱ በቀር የማምጣቱም የማሰራጨቱም ሥራ በአስመጭው አማካኝነት የሚከናወነው የምስራቅ ጎጃም ኮታ ላይ ግን ምንም ዓይነት ችግር አለመኖሩን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ በመሆኑም ችግሩ የአስመጭው አለመሆኑን በመታወቁ ኮሚሽኑ ከወደቡ ባለ ስልጣናት ጋር እየተነጋገረበት ይገኛል፡፡
እኛም የአስመጭውን ምላሽ ይዘን ብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊዎችን አነጋግረናል፡፡ በዚህም ወደብ ላይ ያሉትን ኮንቴነሮች ለኮሚሽኑ መምጣታቸውንና ሆኖም በመጋዘን እጥበት ምክንያት እስካሁን ማንሳት አለመቻሉን የሎጅስቲክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ አይድሩስ ሐሰን አረጋግጠውልናል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ኮሚሽኑ ለእርዳታና ለመሳሰሉት መጠባበቂያ የማስቀመጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑና በአገሪቱ በነበሩት ግጭቶች ምክንያት በርካታ ቁሳቁሶች ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ ገብተው ስለነበረ የመጋዘን ጥበት በመፈጠሩ ነው፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ አገራዊ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ከወደቡ አስተዳደር ጋር እየተነጋገረበት እንደሚገኝ የሎጅስቲክስ ዳይሬክተሩ ገልጸውልናል፡፡
በጉምሩክ ኮሚሽን የሞጆ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ጊዜያዊ ማከማቻ መጋዘንና ተርሚናል አስተዳደር ኃላፊ አቶ ተገኔ መንግስቱ በበኩላቸው፤ ተከማችተው ስድሳ ቀን ያለፋቸው ዕቃዎችን በሙሉ በህጉ መሰረት ወደቡ በጨረታ የመሸጥ ስልጣን ያለው በመሆኑ በዚህ መሰረት በአብዛኞቹ አስመጭዎች ላይ ጨረታ ወጥቶባቸው ጨረታው በሂደት ላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ጨረታ እንደወጣባቸው የሰሙ አንዳንድ አስመጭዎችም ወደ ወደቡ መጥተው ጨረታው እንዲቆምላቸውና ዕቃቸውን እንዲያወጡ በመደራደር ላይ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ሲለመኑ ዝም ብለው ተደብቀው የቆዩት አስመጭዎችም አሁን ጨረታ ወጣ ሲባል ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ምክንያቱም አይደለም በጨረታ ሂደት ላይ ከተሸጠ በኋላም አስመጭው ከመጣና ገዥው የገዛበትን ገንዘብ ከፍዬ ዕቃዬን እወስዳለሁ ካለ ህጉ ይፈቅድለታል ይላሉ፡፡ በዚህም ጨረታው እንዲቆምና ዕቃቸውን እንዲያወጡ ተፈቅዶላቸው ማውጣት የጀመሩ አስመጪዎች መኖራቸውንም ይጠቁማሉ፡፡ እስካሁን ድረስም ሦስት አስመጭዎች ወደ አራት መቶ የሚጠጉ የዘይት ኮንቴነሮችን ማውጣት ችለዋል፡፡
“ይህንን ህግ ስለሚያውቁ ነው እነርሱም የሚያስቸግሩን” የሚሉት የመጋዘን ክምችት ኃላፊው፤ ነገር ግን አስመጭው በመዘግየቱ ምክንያት በጨረታ የተሸጠበትን ዕቃ ባለቀ ሰዓት መጥቶ ማስመለስ የሚችልበትን ከላይ የተጠቀሰውን ህግ ጨምሮ ሌሎችም ክፍተት ያለባቸው ህጎችን ለማሻሻል ከከፍተኛ አመራሩ ጋር በቅርቡ ስምምነት ላይ መደረሱን ያመላክታሉ፡፡ ከዚህ በአሻገር የጉምሩክ ኮሚሽነሩ በገለጹበት አግባብ አለ በጅምላ የተባለው ድርጅት ተረክቦ ለኅብረተሰቡ የሚያከፋፍልበት መንገድ ካለና ይህም የተሻለ አማራጭ ሆኖ ከተገኘ የመንግሥት ውሳኔ በመሆኑ የወደቡ አስተዳደር የማይቃወም መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡