የፈረንጆቹ ዓመት (2022) ተጠናቆ ሌላኛውን ዓመት ለመተካት ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል። በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው በዚህ ዓመትም በርካታ አስደሳች፣ አሳዛኝ፣ አስገራሚ፣ የማይጠበቁ፣… ስፖርታዊ ክንዋኔዎች ታይተዋል። መሰል በርካታ ክንዋኔዎችን ካስተናገዱ ስፖርቶች መካከል አንዱ አትሌቲክስ ሲሆን፤ በዓመቱ አምስት ዓለም አቀፍ ውድድር ለማካሄድ ታቅዶ አንዱ ለአዲሱ ዓመት ሲተላለፍ አራቱ ተከናውነዋል።
የዓለም አትሌቲክስ በሚመራቸው ውድድሮች ላይ በስፋት ለምትሳተፈው ኢትዮጵያም በአመዛኙ ዓመቱን በአስደሳች ጊዜ አሳልፋለች። በአትሌቲክስ ስፖርት ስኬታማ ከሆኑ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከእርምጃ ቻምፒዮና ውጭ በተካሄዱት ውድድሮች የነበራት ተሳትፎ የሀገርን ስም በድል በማስጠራትና ሰንደቅ ዓላማዋን በማውለብለብ የታጀበ ነበር። ኢትዮጵያም በዘርፉ ስፖርት ከምንጊዜውም በላይ ስኬታማ ዓመት ያሳለፈበት መሆኑን ተከትሎ፣ ያለፈውን ዓመት የአትሌቲክስ ሁለቶችን በሚከተለው መልኩ ዳስሰነዋል።
የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በዓመቱ መጀመሪያ አካባቢ ከተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች መካከል አንዱ ነው። በዚህ ውድድር ላይም ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ሀገራቸው ከፍ ያለችበትን ውጤት በማስመዝገብ መመለሳቸው የሚታወስ ነው። በውድድሩ ላይ 4 የወርቅ፣ 3የብር እና 2የነሃስ በጥቅሉ 9 ሜዳሊያዎችን ያስቆጠረችው(ያገኘችው) ኢትዮጵያ፤ አሜሪካ እና ቤልጂየምን በማስከተል በቀዳሚነት ነበር የፈጸመችው። የ800፣ 1ሺ500 እና 3ሺ ሜትር ርቀቶች ደግሞ ሜዳሊያዎቹ የተገኙባቸው ርቀቶች ናቸው። ከሜዳሊያዎቹ ባሻገርም አትሌቶቹ የገቡባቸው ሰዓቶች የውድድሩ እንዲሁም የዓመቱ ምርጥ ሰዓቶች የተመዘገቡባቸውም ነበሩ።
የአሜሪካዋ ኦሪጎን አዘጋጅ በሆነችበት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተካፋይ ኢትዮጵያ በእርግጥም የሯጮች ሀገር መሆኗን ያስመሰከረችበትን ውጤት ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው። በዚህ ውድድር ላይ በወርቅ ሜዳሊያዎቿ ቁጥር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረኩ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ስታጠቃልል፤ ቀድሞ በደረጃ ሰንጠረዡ ቁንጮ በመሆን የሚታወቁትን ሀገራት በመብለጥ ነው። በዚህ ውድድር በተለይ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት ረጅም ርቀት ሩጫዎች አሁንም ድረስ ስኬታማ መሆኗን ያረጋገጠችበት ነበር። በማራቶን በሁለቱም ጾታዎች አትሌቶቿ የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቃቸው ለዚህ ማሳያ ይሆናል። በወንዶች ማራቶን አትሌት ታምራት ቶላ አሸናፊ ሲሆን ሌላኛውን አትሌት ሙስነት ገረመውን በማስከተል ነበር።
በሴቶች በኩል በማራቶን አትሌት ጎትይቶም ገብረስላሴ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ፤ ኢትዮጵያ አስቀድሞ በምትታወቅባቸው የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች በአትሌት ጉዳፍ ጸጋይ እንዲሁም በአትሌት ለተሰንበት ግደይ ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያዎች መገኘታቸው ይታወቃል። በ5ሺ ሜትር ዳዊት ስዩም ጉዳፍን ተከትላ በመግባት የነሃስ ሜዳሊያውን ስታሳካ፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል በሁለቱም ጾታዎች አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል። በወንዶች አትሌት ለሜቻ ግርማ የብር፣ ወርቅውሃ ጌታቸው እና መቅደስ አበበ ደግሞ በሴቶች ሁለት የብር እና አንድ የነሃስ ሜዳሊያዎቹ ባለቤቶችም ሆነዋል። በ1ሺ500 ሜትር ሴቶች ደግሞ ጉዳፍ ጸጋይ የብር ሜዳሊያውን በመውሰድ ባለጥምር ድል ባለቤት በመሆን ነበር ውድድሩን ያጠናቀቀችው።
በዚህ ቻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መለያ ይባል የነበረውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየጠፋ የመጣው የቡድን ስራና በጋራ የመሮጥ ባህል በዚህ ቻምፒዮና ላይ መታየቱም ከስኬቶቹ መካከል አንዱ ነበር። በተጨማሪም በሴቶች እና ወንዶች ማራቶን የውድድሩ ክብረወሰን የተመዘገበ ሲሆን፤ በርካታ የግል ፈጣን ሰዓቶች እና ብሄራዊ አዳዲስ ሰዓቶችም ታይተዋል።
ከሳምንታት በኋላ በተካሄደው ሌላኛው የአትሌቲክስ ውድድርም ኢትዮጵያዊያን ወጣት አትሌቶች ተመሳሳይ ድል በማስመዝገብ ነበር የተመለሱት። በኮሎምቢያዋ ካሊ በተካሄደው ከ20ዓመት በታች የአትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ 12 ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ኢትዮጵያ አሜሪካንን እና ጃማይካን ተከትላ ማጠናቀቋ ሕዝቡን በድጋሚ በደስታ ማዕበል ያንሳፈፈ ነበር። 6የወርቅ ሜዳሊያ፣ 5የብር እና 1የነሃስ ሜዳሊያዎች የተገኙበት ቻምፒዮና ኢትዮጵያዊያኑ ወጣት አትሌቶች ያላቸውን የወደፊት ተስፋ በግልጽ ያሳየም ነበር።
በግላቸው በተለያዩ ውድድሮች ላይ ተካፋይ የነበሩ አትሌቶች ዓመቱን ሙሉ በጎዳናም ሆነ በመም ውድድሮች የሀገራቸውን ስም ሲያስጠሩ ቆይተዋል። በስፔን በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ያስመዘገበችው 29 ደቂቃ ከ14ሰከንድ በዓመቱ የተመዘገበ የዓለም ክብረወሰን በመሆን በዓለም አትሌቲክስ ጸድቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 /2015