የማዋዣ ወግ፤
ኳታር ተጠባና ተጠብባ ዓለምን ጉድ ያሰኘችበት የ22ኛው የዓለም ዋንጫ ውድድር ዝግጅት ከተጠናቀቀ ቀናትን አስቆጥሯል። የቤት ሥራዋን በአግባቡና በአስደናቂ ስኬት ተውጥታ ዋንጫውን ለአርጀንቲና ቡድን ባለ ወርቃማ እግሮች ላስረከበችው ለዚያች “የበረሃ ገነት” ዛሬም ድረስ ምሥጋና እየተዥጎደጎደላት ይገኛል።
በድካሟ ጣመን ባለመራድም እንግዶቿ ገና ጠቅልለው እግራቸውን ነቅለው ከመውጣታቸው አስቀድሞ ለበዓሉ ዝግጅት “የጎዘጎዘችውን ቄጤማ” በትጋት እየጠረገች የከተሞቿን ሕይወት ወደ ወትሮው የተረጋጋ እንቅስቃሴ ለመመለስ ደፋ ቀና ማለቷም ሌላው የጥንካሬዋ መገለጫ ነው።
ዘመኑን የዋጁ ዘመንኞቹ የዓለማችን የእግር ኳስ ጠቢባን ስለደረሱበት የተራቀቀ የአጨዋወት ስልት፣ የትኛው ሀገር በምን ቴክኒክና ብቃት ይሻል ነበር? በየውድድሮቹስ ምን አዳዲስ ክስተቶች ተስተውለዋል? ወዘተ. ለሚሉት ጥያቄዎች የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በአግባቡ ሲተነትኑ ስለከረሙ እኛን መሰል “የሙያው ባእዳን” እንዲህና እንዲያ ነበር ብሎ የኳታሩን መሰንበቻ ለመሄስም ሆነ ለመተቸት እውቀቱና ወኔው የለንም።
ይህንን ያህል ሃሳብ ለመስጠት የተዳፈርነውም ከዓለም ዋንጫው መጠናቀቅ በኋላ የተከሰተን አንድ አስገራሚ እውነታ ለዛሬው ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳያችን እንደ ማዋዣ መንደርደሪያነት ለመጠቀም ፈልገን እንጂ “በአደረ አፋሽ” ፍላጎት ትዝታውን ለማስታወስ ግድ ስለሆነ አይደለም።
የውድድሩን መጠናቀቅ ተከትሎ በየሀገራቱና በዓለም ታላላቅ ብዙኃን መገናኛዎች እየተዘገበ ያለው ያ ክስተት በእጅጉ የሚያስገርም ብቻም ሳይሆን ሆቸ ጉድ! አሰኝቶ የሚያስፈግግ ጭምር ነው። የዜናው አንኳር ሃሳብ የሚከተለውን ይመስላል። “ዝነኛው ቱርካዊ የምግብ ባለሙያ ነስረት ጎክች (በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚጠቀምበት ‹የብዕር ስሙ› ሶልት ቤ) ማንም ሰው በእጁ ሊነካ ያልተፈቀደለትን ትልቁን የዓለም የስፖርት ምልክት የሆነውን ዋንጫ ሊዮኔ ሜሲን ታኮ በምን ምክንያት “በአዳፋ እጁ” ሊነካ እንደቻለ ፊፋ ጉዳዩን በጥብቅ እያጣራ ይገኛል። ”
የሀገሬ ብሂለኛ አንዳች የግራ መጋባት ስሜት ሲወረው “ጉድ በል ሸዋ!” ይሉት ዓይነት የአግራሞት መገለጫ ኃይለ ቃል ይጠቀማል። እኛም አባባሉን ተውሰን “ጉድ በል አልሰሜ!” በማለት ለተለየ አምልኮታዊ ሥርዓት ብቻ እንደሚውሉትና ከዋናዎቹና ከተመረጡ አገልጋዮች ውጭ ማንም ሰው እንደፈለገው እየተዳፈረ በእጁ እንደማይነካቸው “ነዋየ ቅዱሳት” ስለምን የዓለም ዋንጫው እንደ “ቅዱስና አይደፈሬ እቃ ሊቆጠር ቻለ?” የሚለው ጥያቄ የመደነቅ ስሜት አጭሮብናል።
ክስተቱን በሌጣው አስታወስን ለማለፍ ካልሆነ በስተቀር ሰበበ ምክንያቱ ምን ሊሆን እንደሚችል በዝርዝር ለመተንተን የጠለቀ እውቀት ስለሌለን ለጊዜው ከዚህ በላይ ለማለት አንዳፈርም። ቁመቱ 36.5 ሴ.ሜ፣ ስፋቱ 12.5 ሴ.ሜ የሆነውና ክብደቱ 4927 ግራም በሚመዝን በባለ 18 ካራት ወርቅ (አንዳንድ መረጃዎች 14 ካራት ነው ይላሉ) የተለበጠውና ግምታዊ ዋጋው 420 ሚሊዮን ዶላር የተቆረጠለት ያ ለአርጀንቲና ሞገስ የሆናት ዋንጫ ደግመን እንጠይቅና ስለምን እንደ ቅዱስና አይነኬ እቃ ሊታመንበት ቻለ?
ምናልባትም እንደ ዥረት የፈሰሰው የዓለም የእግር ኳስ ክዋክብት ላብና ድካም ትልቅ ክብርና ዋጋ ተሰጥቶት ዋንጫው የተለየ አክብሮት እንዲሰጠው ታስቦም ሊሆን ይችላል፤ ወይንም ክብሩን የሚመጥን የፀጥታ አጠባበቅና መሰል ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከበስተጀርባው በምክንያትነት ሳይኖሩ እንደማየቀር መገመትም ይቻላል።
ዋንጫውን እንዲነኩም ሆነ እንዲዳስሱ የተፈቀደላቸው ውሱን ግለሰቦች የአሸናፊው ቡድን አስልጣኞች፣ የአሸናፊው ቡድን አባላት፣ የፊፋ ባለሥልጣናትና የተወሰኑ ርእሳነ ብሔራትና መራኅያነ መንግሥታት ወይንም የተመረጡ ተወካዮች ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ውጭ “ቂል እንደሰማው ፈሊጥ፤ ውሻ እንደ ደፋው ሊጥ” ያንን ሌት ተቀን በልዩ ጥበቃ ሥር ውሎ የሚሽሞነሞነውን የወርቅ ዋንጫ “በተራ እጅ” እንዳሻው ሊዳብሰው ወይንም “በአዳፋ እጁ” ጫፉን ሊነካው ማንም ግለሰብ በፍጹም አይችልም። ይህንን መሰሉን ድፍረት የፈጸመ አልሰሜ “እጁን ለሰንሰለት፤ እግሩን ለግር ብረት” አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል የሚባለውም ስለዚሁ ነው።
ሀገሬን ያቆሸሹ የእኛዎቹ እድፋም እጆች፤
በሀገሬ ምድር በሌብነትና በጉቦ የተካኑ እጆች የእፍረትና የመሸማቀቂያ መታወቂያ መሆናቸው ቀርቶ የደፋሮች “የገቢና የመበልጸጊያ” ምንጭ መሆን ከጀመሩ ከራርሟል። ሌብነቱም ሆነ ጉቦው እንደ ቀዳሚ ዘመናቱ በድብቅና በጨለማ እጅን ዘርግቶ የሚቀባበሉት መሆኑ ቀርቶ በድርድርና በንግግር ያውም በአደባባይና በፀሐይ ፊት እስከ መፈጸም መድረሱ ፍቺ ካጡት ሀገራዊ ዕንቆቅልሾቻችን መካከል አንዱና ግዙፍ ለመሰኘት የሚበቃ ዋነኛው ብሔራዊ “እርግማናችን” ነው።
በየትኛውም መንግሥታዊም ሆነ ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ከላይኛው “ባለወንበር” እስከ ታችኛው “ባለ ብርኩማ” ድረስ እጅ እጅ ማየት፣ እጅ መንሻ መጠበቅ፣ እጃችሁ ከምን? ተብሎ በድፍረት መጠየቅ እንደ ጀግንነት ይቆጠር ካልሆነ በስተቀር ማፈሪያነቱና ማስፈሪያነቱ ከቀረ ሰነባብቷል።
ምስኪኑ ዜጋ ላቡን አፍስሶ፣ አሳሩን በልቶ የቋጠረውን “የመግደርደሪያ ጥሪቱን” እንደምን በቀን ጅቦች ሲበዘበዝ እንደኖረ አቅሙ፣ ፈቃደኛነቱ፣ ችሎታውና ቅንነቱ ያለው ተቋም የግለሰቦችን ገጠመኞች በማሰባሰብ ብቻ በጥራዝ ላይ ጥራዝ እያከታተለ ዳጎስ ያሉ ሰንዶችን ለማሳተም የሚቸግረው አይሆንም። የፍትሕ ሥርዓቱ ራሱ ጠንከር ተብሎ ቢፈተሽ ከዚህ ክፉ ደዌ የነፃ ሊሆን አይችልም። በየደረጃውና በየእርከኑ ያሉ መንግሥታዊ ተቋማትም ከዚህን መሰሉ ወረርሽኝ የጸዱ ናቸው ለማለት አያስደፍርም።
የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሥርዓትና ከላይ የጠቃቀስናቸው ተቋማት የሚዘወሩት በደላሎችና በአቀባባዮች መረብ ተጠላልፈው ስለመሆኑ ደጋግመን ጽፈናል። የመንግሥት ያለህ በማለትም እስከ መጮኽ ደርሰናል። የግፉ መብዛት የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ለማሳየት ካስፈለገ ማንኛውም ጉዳይ ያለ ደላሎችና አገናኞች ሊፈጸም እንደማይችል ተቋማቱን ፈትሾ ማረጋገጥ ብቻ በቂና ከበቂ በላይ ይሆናል።
ጨካኞቹና እድፋሞቹ የሌብነት እጆች የሚዳብሱት በላብና በደመወዛቸው የወረዛውን የተራ ዜጎችን ኪስ ብቻም ሳይሆን የመንግሥታዊና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ካዝናም ጭምር በትብብርና በምክክር መበርበሩ የእድገቱን ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ደረጃውና መጠኑ ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ያጋጠጡና ያሰፈሰፉ የጉበኞች ጥርሶች ያልነከሱት፣ ያልቦጨቁት፣ ያላላመጡትና ያላመነዠኩት አንድ ነፃ ተቋም በሀገሬ ምድር “ይገኝ ይሆንን?” በማለት እኛ ተራ ዜጎች ጥያቄ በጥያቄ ላይ እያነባበርን ጥርጥር ላይ ከወደቅን ሰነባብተናል።
ይህ ጸሐፊ ለአብነት ያህል ካሁን ቀደም በፍትሕ ሥርዓቱ፣ በሚኖርበት ወረዳ፣ በአንድ የከተማችን አገልግሎት ሰጭ ተቋም ውስጥ እና በአንድ የገቢዎች ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ውስጥ የተፈጸመበትን ያፈጠጠና ያገጠጠ “የእጅህ ከምን ጥያቄ” በተመለከተ በዚሁ ጋዜጣ አምርሮ መዘገቡ አይዘነጋም። እጅግ የሚያሳዝነውና ግርምት ላይ የሚጥለው ጉዳይ አንደኛው ተቋም ይህ ጸሐፊ “የበጎ ፈቃድ አምባሳደር” በመሆን ጊዜውንና እውቀቱን እያበረከተ ያገለገለው መንግሥታዊ መ/ቤት መሆኑ የጉዳዩን ግዝፈት ቁልጭ አድርጎ ሊያሳይ ይችላል።
ለዜጎች መታወቂያ ለመስጠት በተጀመረው አዲስ እንቅስቃሴ በተግባር ላይ በዋለው ቴክኖሎጂ ዝግምተኛነትና የተለመደም ይሁን ያልተለመደም የማሽን ብልሽት ምክንያት እየተሰጠ ለአንዳንድ ጨካኝ በላተኞቹ (ብዙዎች ለማለት ጠቅላይ አስተያየት እንዳይሆን በመስጋት መሆኑ ልብ ይሏል) ጥሩ የጉቦ በር ወለል ተደርጎ የተከፈተ ይመስላል። ከሌሊቱ ዘጠኝ ወይንም አሥር ሰዓት ሰልፍ ይዞና ያለ ቁርስና ምሣ እየዋለ በመጨረሻ የሥራ መውጫ ሰዓት ሲደርስ ሌላ ቀን ተመለስ የሚባል ግፍ የሚፈጸምበት ሌላ ሀገር ስለመኖሩ ለመመስከር አፍ ይይዛል።
ደግምን እናጸናዋለን ፤ የማንነት ማረጋገጫ መታወቂያ ለማውጣት መከራ የወደቀበት ሕዝብ ከሀገሬ ውጭ ሌላ ሀገር አጋጥሞኛል የሚል ምሥክር ይኖር ከሆነ በአደባባይ ወጥቶ ቃሉን ሰጥቶ ሊያርመን ይገባል። ይህ ማለት ግን በሕገ ወጥ መንገድ በሚታደል ተራ መታወቂያ ምክንያት በሀገሪቱ ውስጥ ሲፈጸም ለኖረው ውስብስብ ሴራ፣ ዘረፋና አመጽ ጸሐፊው ግንዛቤ የለውም፣ ጥንቃቄ በመድረጉ ላይም ተቃውሞ አለው ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል።
ይህን መሰሉ የሰሞኑ የእንግልት ብቻ ሳይሆን የዘረፋ ስልት በላይኞቹ ወንበረተኞች ይታወቅ አይታወቅ እርግጠኛ አይደለንም። ለሹሞቹም ለታሪክም ሊበጅ ስለሚችል ግን ደግመን ደጋግመን “የመንግሥት ያለህ!” እያልን በመታወቂያ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተስተዋለ ያለው ዝርክርክና “ሰው ጤፉ” መስተንግዶ በአግባቡና በጥናት እንዲተገበርና ችግሮች እንዲታረሙ “አቤት! አቤት!” እንላለን።
“ሆድ አደር” የሀገራችን ጉበኞች መብት የሆነን ጉዳይ ለመፈጸም ከባለ ጉዳይ የሚጠይቁት ጥሬ ገንዘብ ብቻም አይደለም። “የሕዝብና የመንግሥት” እየተባለ በመንግሥታዊ ሰነዶችና ንግግሮች የሚንቆለጳጰሰው ውሱን የተፈጥሮና የመሬት ሀብት በወረራ፣ በጉቦና በዘረፋ፣ “በላጉርስህ አጉርሰኝ” ብልሃትና ዘዴ ሲመዘበር ውሎ ስለማደሩ እኛ ዜጎች ለምሥክርነቱ አንሰንፍም።
ቀደም ሲል በማዋዣነት የተንደረደርንበትንና በማንም “ተራ እጅ” ሊነካ ፈቃድ የማይሰጥበትን ወርቃማውን የዓለም ዋንጫ መነሻ በማድረግ ጥቂት መሰል ተያያዥ ሀሳቦችን ለመፈነጣጠቅ እንሞክር። “ዋንጫውን እንዲነኩ የተፈቀደላቸው እነ እከሌ ብቻ ናቸው” እንደተባለው ሁሉ ለስርቆሽና ለጉቦም እንዲሁ የተፈቀደላቸው እስኪመስሉ ድረስ እጃቸውን ወደ መንግስት ሀብት ለዘረፋ የሚያሾሉና የሚያስረዝሙ በርካታ “ስሜ አይጠሬ ዝሆኖች” እንደነበሩና እንዳሉ እስኪሰለቸን ድረስ ስንሰማ ስለኖርን “መርዶውም ሆነ ዜናው” እንግዳችን አይደለም።
አንዳንዶችም በረከሰና በቆሸሸ ኅሊናቢስነት በገሃድና በግልጽ የሀገርና የዜጎችን ሀብትና ንብረት በእድፋም እጆቻቸው ተሸቀዳድመው ለመቆንጠር ሲራወጡ እየታየ ስለምን እስከ ዛሬ ድረስ ጠበቅ ያለና ተጠያቂነት የሚያስከትል ሕግና አተገባበር እውን ሊሆን እንዳልቻለ ማሰቡ ግራ ያጋባል። የህልውናችን ጉዳይ “በኳስ ጨዋታ ድል ለተገኘው ዋንጫ የሚሰጠውን ክብር ያህል” ወግ ተነፍጎት “ብሔራዊ ፈተናችን” ሆኖ መኖሩን የምንሞግተው ትናንትን በጸጸት እያስታወስን ዛሬን በምሬት እየኖርንበት ነው።
ሰሞኑን የተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴም የተረከበውን አደራ እውን ለማድረግ ምን ያህል “ኮረኮንች በሞላበት ጎዳና” እየተራመደ ውጤት ሊያስመዘገብ እንደሚችል ለመተንበይና “ጸሎታችን ተመለሰ” ብለን ፈጣሪንም ሆነ መንግሥትን ለማመስገን በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ነን። ኮሚቴው ትላልቆቹን አሳዎችና ትናንሾቹን ግልገሎች እንዴት አጣጥሞ ለመፍትሔ እንደሚሰራም ተብራርቶ አልተገለጸልንም። ምናልባት ይጠቅም ከሆነ በየመንግሥታዊ ተቋማቱ በልዩ ጥንቃቄ የሚከፈት የጥቆማ ሣጥን መዘጋጀት ቢችል ችግሩን ጥቂትም ቢሆን ይቀርፈው ይሆን? ምኞት ነው።
ሀገሬ በስንቱ እድፋም ደፋር እጆች ቆሽሻለች! በስንቱ ጉበኛ ጥርሶችስ ተላምጣለች? እድፋም እጆች ያራቆቱት ወገንስ ብዛቱና የተዘረፈበት የስልት ዓይነት ምን ያህል ይሆን? የመንግሥት ካዝና እንደ “ቅዱስ እቃ” ተቆጥሮ የሚፈራበትና ልዩ ጥበቃ የሚደረግበት ዘመን በእኔ ዕድሜ ይታይ ይሆን? የግለሰቦች ኪስና ነዋይስ ከጉበኞችና ከግፈኞች ነፃ ወጥቶ የምናይበትስ “ቅዱስ” ቀን ይመጣ ይሆን?
ተስፋችንና ምኞታችን፡- ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ከዕለታት አንድ ዓመት በእድፋም እጆች የማይዳበሱበት፣ የዜግነታቸው ክብር ተጠብቆላቸው አገልግሎት የሚያገኙበት ዘመንና ጊዜ መምጣቱ በእርግጠኝነት የሚቀር አይመስለንም። ግን መቼ? በእኛ እድሜ ወይንስ በልጆቻችን? ለተፈጻሚነቱ መዘግየትም ሆነ መፋጠን አደራውን የሚሸከሙት ፈጣሪና መንግሥት ስለሆኑ እነሆ አቤቱታችንን ለሁለቱም ይድረስ ብለናል። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 /2015