ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ጽሑፍ ሳነብ ጽሑፉ ውስጥ እንዲህ የሚል ሃሳብ ተመለከትኩ። ‹‹ … ሙስና በኢትዮጵያ የየዕለት ሕይወት አካል ሆኗል …›› … ሃሳቡ ሙስና በሀገሪቱ ውስጥ የደረሰበትን ደረጃ ቀላልና ግልጽ በሆነ (አስደንጋጭ ቢሆንም) አገላለፅ ለማሳየት ጥሩ እድል ይፈጥራል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከወር በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ስለሙስና/ሌብነት ይህን ተናግረው ነበር፡-
‹‹ … ሌብነት በጣም አታካች ሆኗል። በተለይም የገጠመንን ሀገራዊ ፈተናና ችግር እንደእድል የቆጠሩ ሰዎች ‹ቀይ መስመር› ያልነውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውት በነፃነት እየተንሸራሸሩበት ነው … ኢትዮጵያ ውስጥ ‹ፋይል በእግሩ አይሄድም› የሚለው ቋንቋ የተለመደ ቋንቋ ሆኗል።
”ፋይል በእግሩ አይሄድም፤ በእጅ ብቻ ነው የሚሄደው … ሌብነት የኢኮኖሚ ነቀዝ ነው፤የእድገት ነቀርሳ ነው። ሌብነት ባለበት መኖርና ማደግ ያስቸግራል … የሌቦች ስራ ድብብቆሽ ነው። ድብብቆሽ ወደ ህገ ወጥ ቢዝነስ ስለሚያመራ የተሰረቀን ገንዘብ ወደ ህጋዊነት ለማምጣት ያስቸግራል። ለዚህ ነው አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ፎቆች ባለቤት አልባ የሆኑት … በሁሉም ተቋማት ውስጥ ሌብነትን እየተለማመድን ነው። ለዚህ ነገር መፍትሄ ካላበጀን እድገታችንን ይጎዳል።
” ድሮ ‹ሳይሰሩ የሚበሉ› ነበር የሚባለው፤ አሁን ግን የሚሰራውን ሰው መርጠው የሚበሉ አሉ። እነርሱ ተቀምጠው መጠቀማቸው ብቻ ሳይሆን እየሰራ የሚንቀሳቀስን ሰው በተለያየ መንገድ ጠልፈው ይጥላሉ። ስራን ይበላሉ፤ ሰራተኛንም ይበላሉ። ይህ በሁሉም መስክ በስፋት እየታየ ያለ ጉዳይ ነው። ሌባ ሰው ቤት ይሰራ ይሆናል እንጂ ሀገር አይኖረውም፤ በሌብነት ቤት እንጂ ሀገር አይገነባም፤ ሀገር አልባ ቤት ደግሞ ዘላቂ አይሆንም። በጋራ እንደሀገር ማደግ የምንችልበት እድል እያለ፣ ‹በተናጠል ቤቴን ልገንባ› ችግር ያስከትላል …።
”በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ‹ቃለ መሃላ ገብቻለሁ፤ በገንዘብ አልሰራም› የሚሉ ፖሊሶች፣ ዓቃቤ ሕጎች እና ዳኞች አሉ። እነዚህ ሰዎች ግን በጓደኞቻቸውና በቤተሰቦቻቸው ዘንድ እንደሞኝ ይታያሉ … በቴሌግራም ግሩፕ ከፍተው ጉቦ የሚቀባበሉ ዳኞች አሉ። ጠንከር ያለ የፍትህ ስራ ካልሰራን፣ ስብራቱ ከፍተኛ ነው … ››
በጽሑፉ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ሃሳብም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሙስና ወንጀል ለመግለፅ ቢያንሱ እንጂ አይበዙም። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹በሙስና ውስጥ አለመሳተፍ እና ሙስናን መዋጋት ወንጀል ነው›› የተባለ እስኪመስል ድረስ የወንጀሉ ተሳታፊ ለመሆን የሚደረገው እሽቅድድም እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ነው።
በጉቦ፣ በምዝበራ፣ በማጭበርበና በሌሎች የሙስና መልኮች የሚፈፀመው የወንጀል ብዛትና ዓይነት ታይቶም ተቆጥሮም አያልቅም። ጉዳይ ለማስፈጸም ጉቦ መጠየቅና መስጠት ‹‹በሕግ ያልተፃፈ ግዴታ›› ሆኗል። የሚጠየቀውና የሚከፈለው የጉቦ መጠን ደግሞ ‹‹ጆሮ አይስማ›› ያሰኛል። ቀደም ሲል በረቀቀ መንገድ ሲፈፀም የነበረው ሙስና አሁን በማን አለብኝነትና በግላጭ ይደረጋል።
ያለጉቦና ዝምድና አገልግሎት ማግኘት ፈፅሞ የማይታሰብ እየሆነ ነው። በአጠቃላይ ዜጎች ጉዳይ የማስፈጸምና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው እንዲሁም የመንግሥት ሹማምንትና ሰራተኞች ደግሞ የዜጎችን አገልግሎት የማግኘት መብት የመፈፀምና የማስፈፀም ግዴታ ያለባቸው መሆኑ ጨርሶ ተዘንግቷል።
በኢትዮጵያ ያለውን የሙስና ወንጀል የከፋና አስፈሪ የሚያደርገው ደግሞ ሙስና ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተጋምዶ ሲፈፀም መቆየቱና አሁንም ተባብሶ መቀጠሉ ነው። የጎሳ መዛመድን መነሻ ያደረገ ጥልፍልፍ የሙስና ወንጀል በእጅጉ ተንሰራፍቷል። ይህም በአንድ በኩል ሙስናን ተጸይፈው የሚሰሩ ጥቂት ሀቀኛ ሠራተኞችን፣ በሌላ በኩል ወንጀሉ ያሰባሰባቸው ጎሳ አባል ያልሆኑትን ለማጥቃት ምክንያት ሆኗል።
ይህ ደግሞ ሙስና ከጉቦ፣ ከማጭበርበርና ከዝርፊያ የተሻገረ ትርጉምና ውጤት እንዲኖረው ያደርጋል። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ገንዘብ በማባከንና ጉቦ በመቀበል የሚቆም ሳይሆን እጅግ አስከፊ ወንጀሎች እንዲበራከቱ በማድረግ ሀገር እንዳትጠገን ሆና እንድትፈራርስ የሚያደርግ አደገኛ መዘዝን ያስከትላል።
ከምክር ቤቱ ማብራሪያቸው ጥቂት ቀናት በኋላ ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ ሙስና የኢትዮጵያ የደኅንነት ሥጋት እና የብልጽግና ጉዞ ዋናው እንቅፋት መሆኑን ገልፀዋል። የመንግሥትን ሙሉ አቅም በመጠቀም በተቀናጀና በተናበበ ሁኔታ ሙስና የፈጠረውን ችግር ለመቀልበስ እንደተሰየመ የተነገረለት ኮሚቴው ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን፣ መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የማስተባበር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የመለየትና ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት አለው ተብሏል።
በእርግጥ በቅርቡ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዳሉና የአንዳንድ ሹማምንትና ሰራተኞች ስም በፌስቡክ ጭምር ተለጥፎ ግለሰቦቹ የት እንደሚገኙ ኅብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ተመልክተናል። በጸረ-ሙስና ዘመቻው የአገሪቱ የጸጥታ እና የፍትህ ዘርፍ እንዲሁም የመንግሥት የመሬት አስተዳደር ቅድሚያ እንደተሰጣቸው እንዲሁም የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር፣ የፋይናንስ፣ የመንግሥት ገቢ እና ጉምሩክ ሥርዓት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ አስተዳደር እና የመንግሥት ግዢን የመሳሰሉ ዘርፎች ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ከተባሉት መካከል እንደሚገኙ ተገልጿል።
በፍትህ እና በጸጥታ ዘርፍ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም የዜጎችን ሰላም እና የሀገርን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን ተገን አድርገው በተለያዩ ሕገ-ወጥ መንገዶች ከግለሰቦች እና ከንግድ ድርጅቶች ገንዘብ እና ሀብት ለመውሰድ የተንቀሳቀሱ ተጠርጣሪዎች ተለይተዋልም ተብሏል።
ሙስናን ለመዋጋት ተብሎ ኮሚቴ ሲቋቋም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደምም መሰል ኮሚቴዎች ተቋቁመው እንደነበር ይታወሳል። ‹‹በሙስና ላይ ዘመቻ ተከፈተ›› ተብሎ ይወራና ሕዝቡም ‹‹ሙሰኛው ሁሉ ተጠራርጎ ሊገባ ነው›› ብሎ በፀረ ሙስና ዘመቻው ላይ መጠነኛ ተስፋ ሲያደርጉ ይስተዋል ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ተደጋግሞ ተደርጎ የዘመቻው ውጤት ግን ከዜሮ ያልተሻለ ሆኖ ሲገኝ ሕዝቡም ተሰላችቶ ዘመቻውን ‹‹ጉራ ብቻ›› ብሎ ሲገልፀው ነበር። ‹‹ቀደም ሲል የተቋቋሙ የፀረ ሙስና ኮሚቴዎችስ የት ደረሱ? ምን ተግባራትንስ አከናወኑ?›› ተብሎ ቢጠየቅ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አዳጋች ነው።
በእርግጥ የዘመቻ ተግባር ለሙስና ችግር ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል?! የፀረ ሙስና ዘመቻ ሙስናን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስና ከስሩ ለመንቀል ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ አይሆንም! የሀገር የደኅንነት ሥጋት ሆኗል›› የተባለ ችግር ሃቀኛና ዘላቂ በሆነ ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ እንጂ በአንድ ሰሞን ዘመቻ መፍትሄ አያገኝም። ሙስና መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ መገለጫም እየሆነ ነው።
‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› በሚል ብሂል የሚኖርና ሀቅንና መርህን ተከትሎ ስራን የሚሰራን ሰው ‹‹ሞኝ፣ ጅል›› ብሎ የሚያሸማቅቅ ኅብረተሰብም ሆነ በስርዓትና በመዋቅር ታግዞ የሚዘርፍና የሚያጭበረብር ሹመኛና ሰራተኛ በዘመቻ አይደነግጥም። ቢደነግጥም እራሱን አረጋግቶ ወደ ቀደመ ቦታው ለመመለስ ብዙ ጊዜ የሚፈጀበት አይሆንም።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንጻር ስር የሰደደ ሀገራዊ ነውር ለማስታገስ የተጀመረው ዘመቻ የሚበረታታ ቢሆንም፣ ከቀደሙት ተመሳሳይ ዘመቻዎች ተሞክሮ ወስዶ ጉዳዩን አምርሮ መያዝ ወሳኝ ነው። ዘመቻው ከዘመቻ ባለፈም በቀጣይነት ተጠናክሮ የሚሄድበትን አሰራር ከወዲሁ ማሰብ፣ መፍጠር እና ሀገራዊ ዝግጁነት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው ፀረ- ሙስና ትግሉ በስኬት ሊጠናቀቅ የሚችለው።
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 /2015