የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው፡፡ ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርአያነት ሲጠቀስ የኖረም ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ሰላም መገለጫቸውና የመጀመሪያ ምርጫቸው ነው፡፡ ስለሆነም ለሰላም ሲሉ በርካታ መስዋዕትነቶችን ሲከፍሉ ኖረዋል፤ አሁንም እየከፈሉ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታትም የታየው ሃቅ ይኸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ወደማይፈልጉት ጦርነት ከመግባታቸው በፊት በርካታ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ሽማግሌዎችንና ታዋቂ ሰዎችን ጭምር በመላክ ለሰላም ያላቸውን ፍላጎት በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ሆና የሰላም ያለህ ሲሉ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ሲባል የትም ቦታ፤ በማንኛውም ጊዜ እና በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ለመወያየት ፍቃደኝነቱን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ጥረቱም ፍሬ አፍርቶ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ጥቅምት 23 ቀን 2015ዓ.ም በመንግስትና በሕወሓት መካከል ታሪካዊ የሚባል የሰላም ስምምነት ተፈርሟል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሁለቱም ወገኖች ታሪክ ጽፈዋል፡፡ አስራ ሁለት አንቀጽ ያለው የሰላም ስምምነት በመፈረም ሰላምን አውጀዋል፡፡ በፕሪቶርያ የተካሄደው ስምምነት ለዘመናት መፍትሄን በጠብመንጃ ለማምጣት ሲኬድበት የነበረውን ኋላቀር አስተሳሰብ የሰበረና ስልጡን የሆነ አካሄድን ለሀገራችን ያስተዋወቀ ነው፡፡ ስምምነቱ የኢትዮጵያን መሰረት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን የትግራይ፤ የአማራና የአፋር ሕዝቦችን እፎይታ አጎናጽፏል፡፡
ከፕሪቶርያው ስምምነት ቀጥሎ የተካሄደው የናይሮቢ ስምምነት መተማመንን የፈጠረና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም መንገድ የሚያጸና ነው፡፡ በፕሪቶርያው ስምምነትና ይህንኑ ተከትሎ በናይሮቢ በተካሄደው የማስፈጸሚያ ውል ባለፉት ሁለት ዓመታት ከደረሰው ዕልቂት፣ ውድመትና ምስቅልቅል ውስጥ መውጣት የሚያስችል ዕድል ተገኝቷል፡፡
በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሰረተ ልማቶችንና ሰብዓዊ ድጋፎችን በሚፈለገው መልኩ ማድረስ ተችሏል፡፡ እስካለፈው ዓርብ ድረስም 89 ሺ 910 ቶን ምግብ ነክ እና 8 ሺ 624 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ወደ ትግራይ የተላከ ሲሆን ከ780 ሺ 755 ሊትር ነዳጅ ተጓጉዟል፡፡ በጥሬ ብር ደረጃም ከ800ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ 80 የትግራይ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ባንክን በተመለከተም ሥራ ከጀመሩት በተጨማሪ ከ22 በላይ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችን ስራ ለማስጀመር በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከሁለት አመታት በኋላ ዛሬ ወደ መቀሌ በ ረራ ጀምሯል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በርካታ ርቀቶችን ተጉዞ ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲሰፍን ተጨባጭ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት በመንግስት በኩል የሚጠበቁበትን ሙሉ ለሙሉ ተፈፃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጭምር ወደ መቀሌ በመላክ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል፡፡
ሰሞኑን አጠቃላይ ሰላም ሂደቱ በተገመገመበት ወቅትም የሰላም ሂደቱ እስካሁን ከነበረው በተሻለ አፈጻጸም እንዲሄድ መንግስት ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አስፈላጊውን እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አረጋግጠዋል።
መስከረም 29 በተካሄደው ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አጽንኦት ሰጥተው እንዳብራሩት “የአገሪቱን ጥቅም ባስከበረ” እንዲሁም “ዘለቄታን ባማከለ” መልኩ ከሕወሓት ጋር የሚደረገውን ድርድር የፌደራል መንግሥቱ እንደሚቀጥልበት ገልጸዋል። መንግሥት “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር” ያለውን ፍላጎት በንግግራቸው ጠቅሰው “የሰላም በር አይዘጋም” ሲሉ ማረጋገጣቸው የሚታወስ ነው። የተገባው ቃልም በተግባር በመገለጥ ላይ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ አሁን ለተገኘው ሰላም መንግስት ያደረገው ግንባር ቀደምና ተምሳሌታዊ የሆነ ቁርጠኝነት ላቅ ያለ ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ነው።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 /2015