ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ መድረክ በመወከል ቀዳሚ ከሆኑት ስፖርቶች መካከል አንዱ ብስክሌት መሆኑ ይታወቃል። እአአ ከ1956ቱ የሜልቦርን ኦሊምፒክ የሚነሳው የኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርት ተሳትፎ ከጥቂቶች በቀር እስከ 2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ድረስ ኢትዮጵያን በመድረኩ መወከል ችላ። ስፖርቱ በኦሊምፒክ መድረክ በተሳትፎ ደረጃ የሚወሳ ታሪክ ይኑረው እንጂ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአህጉር አቀፍ እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩ ነው።
በቀጣይ በፓሪስ የሚካሄደውን ኦሊምፒክ ጨምሮም በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ውጤታማ ለመሆንም የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን እየተጋ እንደሚገኝ ጠቁሟል። የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም ወልደአብ፤ የብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመወከል ከአትሌቲክሱ ቀጥሎ የሚጠቀስ ስፖርት እንደሆነ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን፤ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በዚህ ዓመት በደቡብ አፍሪካ ራይድ ጆበርግ በተሰኘ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳለያ ስታገኝ፤ በግብጽ በአዲስ መልክ በተጀመረው ናል ቱር ደግሞ የነሃስ ሜዳሊያ ማስመዝገብ መቻሉ ታውቋል፡፡
በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት እንዲሁም እአአ በ2024 በፓሪስ በሚደረገው ኦሊምፒክ ላይም ውጤታማ ለመሆን የተለያዩ ስራዎች ከወዲሁ በመስራት ላይ ይገኛሉ። እአአ 2023 የአፍሪካ ቻምፕዮና እንዲሁም የዓለም ብስክሌት ቻምፕዮና የሚካሄዱ ሲሆን፤ ተወዳዳሪዎች ባላቸው ወቅታዊ ብቃት መሰረት ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ ወደ ዓለም አቀፍ ስልጠና ማዕከላት እንደሚላኩም ኃላፊው ይጠቁማሉ። ብስክሌት ጋላቢዎቹ የሚያገኙት ይህ ስልጠና መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ባደረገው የስዊዘርላንድ የስልጠና ማዕከል ነው። በስልጠና ላይ የሚቆዩትም ለ2 ወር፣ ለ3ወር እንዲሁም ለ6 ወር ሲሆን፤ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና እንደሚሰጣቸውም እንዲሁም የማጣሪያ ውድድሮችን ጭምር እንደሚያደርጉም አክለዋል፡፡
በተያዘው ዓመትም በዚህ የስልጠና ማዕከል ሶስት ብስክሌተኞች ስልጠናውን ወስደው ተመልሰዋል። ብስክሌተኞቹ በአውስትራልያ ኦሪንጎንግ በተካሄደ የዓለም ቻምፕዮና ተሳትፈውም ጥሩ የሚባል ውጤት እንዳስመዘገቡና ስፖርቱም በተሳትፎም ሆነ በውድደር ደረጃ በተሻለ መልኩ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በተለያዩ የውጪ ክለቦች የኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ያሉ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ በአሜሪካ፣ በፈረንሳይ እና በጣሊያን ክለቦች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህም ተወዳዳሪዎች በተለያዩ የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን በመወከል ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ ኪያ ጀማል፣ ሰላም አመሃ፣ ነጋሲ፣ ጽጋቡ ገብረማርያም ከብዙ በጥቂቱ ቢሆኑም ብዙ በውጪ ክለቦች ያሉ ተወዳዳሪዎች እንዳሉ ተነግሯል።
በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከሚደረጉ ተሳትፎዎች በተጓዳኝም በመደበኛነት በአገር ውስጥ የተለያዩ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ከነዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ ቻምፒዮና በየዓመቱ በሰኔ ወር መጨረሻ ሲካሄድ፤ ለዓለም ዓቀፉ የብስክሌት ፌዴሬሽን ማሳወቅ ግዴታ ነው። በቻምፕዮናው አሸናፊ የሆነ ተወዳዳሪም በዓለም አቀፍ ክለብ ይኑረውም አይኑረውም የኢትዮጵያ አርማ ያረፈበት ጄርሲ (ማለያ) መልበስ የሚችለው የኢትዮጵያን ቻምፕዮና ተሳታፊ ሲሆን ብቻ ነው። ሌሎችም ውድድሮች ያሉ ሲሆን የክለብ ቻምፕዮና፣ የቱር ውድድሮች፣ የውጪ አገራት ተወዳዳሪዎች የሚካፈሉበት የአረንጓዴ ልማት ቱር፣ የክልሎች ውድድር፣ የታዳጊዎች ውድድር ናቸው። ይሁንና እነዚህ ውድድሮች አሁን እየተደረጉ አይደለም፤ ነገር ግን ለማስቀጠል በእቅድ ደረጃ መያዙ አብራርተዋል።
ብስክሌት የራሱ የሆነ የተሰጥኦ ስፍራ (ታለንት ኤሪያ) ስላለው በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ያለውን ተሰጥኦ አውጥቶ ለመጠቀም እየሰራ መሆኑንም ፌዴሬሽኑ ይገልጻል። እነዚህም ብስክሌት በብዛት የሚዘወተርባቸው እንደ ትግራይ፣ አዋሳና ድሬደዋ ናቸው። በአገሪቷ የመጣው የሰላም ተስፋ ለዚህም አስተወጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል። በዚህ ወቅት አስቸጋሪ የሆነው ውድድሮችን ከክልል ክልል ማድረግ ነው። ምክንያቱም ውድድር ሲደረግ መንገዶች ዝግ መሆን ይኖርበታል፤ ለዚህም ከምንም በላይ ሰላም ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት ከዓለም 42ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ደቡብ አፍሪካን እና ኤርትራን በመከተል 3ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ዓመት ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያደርግ ባቀረበው ሪፖርት ገልፆ ነበር፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 /2015