አዲስ አበባ፡- ቻይና 71 የጦር አውሮፕላኖችን ያሳተፈ በታይዋን አቅራቢያ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ ተገለጸ፡፡
ሕዝባዊ ነጻ አውጪ ጦር በመባል የሚታወቀው የቻይና ጦር በአሜሪካ እና በራስዋ በምትመራው ደሴት እየተስተዋለ ያለውን ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት በሚል እሁድ እለት “ወታደራዊ ልምምድ” አድርጋለች፡፡
ከታይዋን የመከላከያ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ወታደራዊ ልምምዱ እስካሁን ይደረጉ ከነበሩት እጅግ ትልቅ ነው ተብሏል፡፡
ሚኒስቴሩ በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ በልምምዱ 60 ተዋጊ ጄቶች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የቻይና ዘመናዊ አውሮፕላኖች እንደሆኑ የሚነገርላቸው ስድስት ሱ-30 የጦር አውሮፕላኖች ናቸው ብሏል፡፡
ከዚህም በላይ 47ቱ በደሴቲቱ የአየር መከላከያ መለያ ዞን ውስጥ ተሻግረው መግባታቸውን የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ መረጃ ያመለክታል፡፡
ይሁን እንጂ በልምምዱ ጥቅም ላይ ውለዋል ስለተባሉት አውሮፕላኖች ብዛት በቤጂንግ በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡
ታይዋን የምትኖረው ዲሞክራሲያዊት ደሴት የግዛቷ አካል እንደሆነች በምትናገረው በቻይና የማያቋርጥ የመወረር ስጋት ውስጥ መሆኑ ይታወቃል።
በፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ የምትመራው ቤጂንግ አሁን ላይ በታይዋን የምታደርገው ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዋን ከፍ ማደረጓን ደግሞ የዚሁ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
ሩስያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯ ደግሞ ቻይና በታይዋን ላይ ተመሳሳይ ነገር ልትሞክር ትችላለች የሚል ስጋት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡
አሜሪካ ለታይዋን የምታደርገው ድጋፍ ደግሞ ሌላው ቻይናን የቀጠናው ውጥረት እያባበሰ ያለ ጉዳይ እንደሆነ ይነሳል፡፡
በተለይም አሜሪካ ከቀናት በፊት ይፋ ያደረገችው ታይዋንን ለመርዳት የሚያስችል አዲስ የመከላከያ ህግ ደግሞ ቤጂንግን እጅጉን ያስቆጣ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡
ቤጂንግ የአሜሪካ ውሳኔ “በታይዋን የባህር ዳርቻ ሰላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ድንጋጌዎች” የያዘ ነው ስትል አዲሱን ህግ ማውገዟም አይዘነጋም፡፡
በጋዜጣዉ ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 /2015