
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ ስደተኞችን ወደ ሦስተኛ ሀገር እንዲያባርሩ ፈቀደ። የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን ከሀገራቸው ባለፈ ወደ ሦስተኛ ሀገር ማባረር እንዲችሉ መንገዱን ጠርጓል። የታችኛው ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞች ወደ ሦስተኛ ሀገር ሲባረሩ የሚገጥማቸውን ችግር እንዲያስረዱ “ትርጉም ያለው እድል” እንዲሰጥ የወሰነውን ውሳኔ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ስድስት ለሦስት በሆነ ድምፅ ሽሮታል።
ሦስት ለዘብተኛ የፍርድ ቤቱ ዳኞች “ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ” ነው ያሉትን ብይን ተቃውመዋል። ጉዳዩ ባለፈው ግንቦት የምያንማር፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኩባ፣ ሜክሲኮ፣ ላኦስ እና ቬትናም ስምንት ስደተኞችን ወደ ደቡብ ሱዳን የሚወስድ አውሮፕላን ውስጥ እንዲሳፈሩ መደረጉን ተከትሎ የመጣ ነው ተብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞች “ከከፉትም የከፉ” ናቸው ብሏል። የቦስተን የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ ብራየን መርፊ ባለፈው ሚያዝያ ስደተኞቹ በሦስተኛ ሀገር ማሰቃየት ወይንም ግድያ ይፈፀምብናል ብለው ካመኑ ጉዳያቸውን እንዲያሰሙ እድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ ውሳኔ አሳልፈዋል። ይህም እድል ሌሎች ሕጋዊ አቤቱታዎቻቸው ውድቅ ቢደረጉ እንኳ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዳኛ ሶኒያ ሶቶማየር፣ ኢሌና ኬጋን እና ኬትማጂ ብራውን ጃክሰን ሰኞ እለት በአብላጫ ድምፅ የፀደቀውን እና ያልተፈረመውን ውሳኔ “ከባድ ጥሰት” ሲሉ ተችተውታል። የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት ሆምላንድ ውሳኔው “ለአሜሪካ ሕዝቦች ደኅንነት እና ጥበቃ ድል ነው” ብሏል። የተቋሙ ቃል አቀባይ ትሪሺያ ማክሊን “ማባረሪያ አውሮፕላኖች ያሟሙቁ” ሲሉ ከውሳኔው በኋላ ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ስምንቱ ስደተኞች በአሜሪካ ግድያ፣ እሳት ቃጠሎ እና በጦር መሳሪያ ዝርፊያን ጨምሮ “አስከፊ ወንጀሎችን” የፈፀሙ ናቸው ብሏል። የስደተኞቹ ጠበቃ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባስገቡት ማመልከቻ አብዛኞቹ ስደተኞች ወንጀለኛ ተብለው የተፈረደባቸው አይደሉም ብለዋል። ከሳሾቹን የወከለው ብሔራዊ የኢሚግሬሽን ሙግት ትብብር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ “አስፈሪ” ብሎታል።
የትብብሩ ስራ አስፈፃሚ ትሪና ሪልሙቶ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደንበኞቻቸውን “ለስቃይ እና ሞት” ያጋለጠ እንደሆነ ተናግረዋል። ትራምፕ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰዱት የታችኛው ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ ባለፈው ወር የቦስተን ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ባለመቀልበሱ ነው። በባይደን የተሾሙት ዳኛ ብራየን መርፊ የአሜሪካ መንግስት ስደተኞች ወደ ሦስተኛ ሀገር ሳያባርር የአሜሪካ የጦር ሰፈር ባለበት ጂቡቲ እንዲያቆዩ ጠይቀዋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ዓቃቢ ሕግ ጆን ሳወር ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ለአደገኛ ወንጀለኞች ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ለመመስረት ተገደዋል ብለዋል። ዓቃቢ ሕጉ አክለውም አደገኛ ወንጀለኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ሀገራት ለመቀበል ፈቃደኛ ስለማይሆኑ መንግስት ብዙ ጊዜ እንደሚቸገር፤ ይህም ስደተኞቹ “ሕግ አክባሪ አሜሪካውያንን ዳግሞ እየጎዱ” በአሜሪካ እንዲቆዩ አድርጓል ሲሉ አብራርተዋል።
የሰኞው ውሳኔ አያሌ ስደተኞችን ለማባረር ለወጠኑት የሪፐብሊካኑ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሌላ ድል ነው። ባለፈው ወር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 350 ሺህ ስደተኞች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ እና ለቬኑዚዌላ ዜጎች ተሰጥቶ የነበረውን ጊዜያዊ ጥበቃ እንዲነሳ ውሳኔ አሳልፏል።
በሌላ ውሳኔ ባለፈው ግንቦት ወር ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ የኩባ፣ ሄይቲ፣ ኒካራጉዋ እና ቬንዙዌላ ስደተኞች ለሁለት ዓመት በአሜሪካ ሲቆዩ የሚሰጣቸውን የሰብዓዊ ድጋፍ ፕሬዚዳንቱ በጊዜያዊነት እንዲያቋርጡም ወስኗል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም