ኢራን በአሜሪካን ላይ የአጸፋ ጥቃት ፈጸመች

ኢራን በኳታርና በኢራቅ በሚገኙ በአሜሪካ ወታደራዊ ቤዞች ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። አሜሪካ በኒውክሌር ጣቢያዎቿ ላይ ለፈፀመችባት ጥቃት የበቀል ርምጃ ለመውሰድ እያጤነች እንደምትገኝ ኢራን አስታውቃለች። የሀገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይድ ኻቲብዛዴህ ኢራን እንዴት፣ መቼ እና በምን ያህል ደረጃ ለአሜሪካ ምላሽ እንደምትሰጥ እያጤነች እንደሆነ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ሀገራቸው ለአሜሪካ ጥቃቶች የአፀፋ ርምጃ የመውሰድ መብት እንዳላት ግልጽ ሊሆን እንደሚገባ ‹ለአልጀዚራ› ተናግረዋል። ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ርምጃ ልትወስድ እንደምትችልም ጠቁመዋል። አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የፈፀመችው ጥቃት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የጣሰ ከባድ ስህተት እንደሆነም ኻቲብዛዴህ ገልፀዋል።

ኻቲብዛዴህ እስራኤል በኢራን ላይ በምትፈፅመው ጥቃት አሜሪካ እጇን የምታስገባ ከሆነ በአጠቃላይ በቀጣናው ገሃነም እንደሚፈጠር ባለፈው ሳምንት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። ‹‹ይህ የአሜሪካ ጦርነት አይደለም›› ያሉት ኻቲብዛዴህ፣ ‹‹የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ከተሳተፉ በማይመለከታቸው ጦርነት ውስጥ የገቡ ፕሬዚዳንት ሆነው ሁልጊዜም ይታወሳሉ›› ማለታቸው ይታወቃል። የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ግጭቱን ወደ አረንቋነት እንደሚለውጠው፣ ቁጣው ተባብሶ እንደሚቀጥል እና የሚፈፀመውን ጭካኔ የተሞላበትን ጥቃት ማብቂያ እንደሚያዘገየውም ጨምረው ተናግረዋል።

የኢራን ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጀኔራል አብዶልራሂም ሙሳቪ፣ አሜሪካ የኢራንን የኒውክሌር ጣቢያዎች በማጥቃት የሀገራቸውን ሉዓላዊነት እንደጣሰች እና ጦርነቱን በቀጥታና በግልጽ እንደተቀላቀለች ተናግረዋል። ‹‹ወንጀለኛዋ አሜሪካ ሕገወጧንና ወራሪዋን ተቀጥላዋን ከመቅጣት ባሻገር በእሷ ጥቅም ላይ ያነጣጠረ ማንኛውንም ርምጃ መውሰድ እንደምንችል ማወቅ አለባት። በዚህ ጉዳይ ፈፅሞ ወደ ኋላ አንልም›› ብለዋል።

የኢራን ጦር ማዕከላዊ እዝ ቃል አቀባይ ኢብራሂም ዞልፋጋሪ በበኩላቸው፣ ‹‹አሜሪካ በኢራን ላይ የፈፀመችው ጥቃት እየሞተ ያለውን ጽዮናዊ አገዛዝ ለማትረፍ ያደረገችው ተግባር ነው። ርምጃው ጦርነቱን የሚያሰፋ አደገኛ ተግባር ነው። ትራምፕ ይህ ጦርነት ቢጀምረውም የምንጨርሰው ግን እኛ ነን›› በማለት ተናግረዋል።

አሜሪካ ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟ ይታወሳል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦራቸው በፎርዶው፣ ናታንዝና ኢስፋሃን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የተሳኩ ጥቃቶችን መፈፀሙን ተናግረዋል። ኢራን ወደ ድርድር የማትመጣ ከሆነ ከዚህ የከፉ ጥቃቶች እንደሚጠብቋትም አስጠንቅቀዋል።

ኢራን በአሜሪካ ጥቃት ከተፈፀመባት በኋላ በእስራኤል ላይ ጥቃቶችን የፈፀመች ሲሆን፣ በአሜሪካ ላይ በቀጥታ ስለምትወስደው ርምጃ ግን እስካሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ ኢራን ከአሜሪካ ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎችን እንደምትደበድብ ዝታለች። የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር አዚዝ ናስርዛዴህ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ ኢራን በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን ኢላማ ያደረገ ምላሽ እንደምትሰጥ መናገራቸው ይታወሳል።

እስራኤልና ኢራን የሚያደርጉት የአየር ውጊያ ወደ ሁለተኛ ሳምንቱ ተሸጋግሯል። እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማትና ወታደራዊ ጣቢዎች ላይ የፈፀመችውን ጥቃት እና ኢራን የሰጠችውን የአፀፋ ምላሽ ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ውጊያ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ሄዷል። ይባስ ብሎም አሜሪካ ውጊያውን ተቀላቅላለች።

እስራኤል በፈፀመቻቸው ጥቃቶች በርካታ የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ኢራንም በወሰደቻቸው የአፀፋ ርምጃዎች በእስራኤል ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። በጥቃቶቹ ሰላማዊ ዜጎችና የመኖሪያ አካባቢዎች ሰለባ እንደሆኑም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለው የቃላት ጦርነትም ተጣጡፎ ቀጥሏል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱ ሀገራት ውጊያቸውን እንዲያቆሙ ቢያሳስብም ጥሪው ሰሚ አላገኘም።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You