በበይነ መረብ በመጠቀም ወጪንና ጊዜን መቆጥብ፣ በፍጥነት ተደራሽ መሆን ዘመኑ የሚጠይቀው ወሳኝ ተግባር ሆኗል። ይህ የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማቃለል በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው የመረጃ መለዋወጫ ዘዴ በዓለም አቀፍ እንዲሁም በአፍሪካም በሚፈለገው ልክ ተደራሽ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዓለም ላይ 2ነጥብ 7 ቢሊዮን፣ በአፍሪካ ደግሞ 871 ሚሊዮን ሕዝብ ከበይነ መረብ ግንኙነት ውጭ ስለመሆኑም በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ተጠቁሟል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ያለው የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት 19 ሚሊዮን፣ በአሁኑ ወቅት ከ30 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አመልክተዋል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የበይነ መረብ ተደራሽነት እያደገ የመጣ መሆኑን የጠቆሙት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ተደራሽነቱ የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነና በትኩረትና በስፋት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዌር ምህንድስና ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ፊሊክስ ኢቴሳ ስለ በይነ መረብ /ኢንተርኔት/ በይነ መረብ /ኢንተርኔት/ ለመማር፣ ለምርምር እንዲሁም ለህብረተሰቡ የዕለተ ተዕለት እንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንደ ቅንጦት የሚታይ እንዳልሆነ ያመለክታሉ። በዚህ የዲጂታል ዘመን ካለ ኢንተርኔት በቴክኖሎጂ ሳይታገዙ መሥራት አዳጋች መሆኑንና በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
እንደ አቶ ፊሊክስ ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተደራሽነት በእጅጉ አናሳ ነው። የኢንተርኔትን ተደራሽነት ለማወቅ ኢንተርኔት የት የት አካባቢዎች አለ? መሠረተ ልማቱስ በሚገባ ተደራሽ ሆኗል ወይ? በየቦታው የቴሌኮሙኒኬሽን ማዕከላት አሉ ወይ? ምን ያህል ሰው ተጠቃሚ ሆኗል የሚሉት ሁሉ መታየት ይኖርባቸዋል።
ማህበራዊ ድረገጽ (ፌስ ቡክ)፣ ዩቲዩብና የመሳሰሉት የመረጃ መለዋወጫ ዘዴዎችስ (ፕላት ፎርሞች) ምን ያህል ተጠቃሚዎች እንዳሏቸው ለይቶ ማወቅ ይገባል። ዘመናዊ /ስማርት/ የስልክ ቀፎ ያለውም ቢሆን ጥቂት ሰው ነው። እንደ ሀገር የተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) ቴክኖሎጂ ከተጀመረ አንስቶ ኢንተርኔት ፍጥነቱ እያደገ አምስተኛ ትውልድ (5ጂ) ኔትወርክ ላይ የደረሰ ቢሆንም፣ የኢንተርኔት ፍጥነቱ ግን አሁንም በጣም አነስተኛ ነው።
‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ኢንተርኔት እየተጠቀምን ነው ማለት አይቻልም›› ያሉት አቶ ፊሊክስ፤ የኢንተርኔት ተደራሽነት የሚለካው በመሠረተ ልማቱ መዘርጋት ብቻ ሳይሆን፣ በፍጥነቱም ነው ብለዋል። የኢንተርኔት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በተግዳሮት ከሚጠቀሱት ዋንኛና መሠረታዊ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሚው ህብረተሰብ ስለዲጂታል ቴክኖሎጂ ያለው ግንዛቤ አነሳ መሆኑም አንዱ ነው ይላሉ፡፡
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ ባለሙያው አቶ ጥላሁን ሽፈራው የኢንተርኔት ጥቅሙ የገባቸው አንዳንድ የዓለም ሀገራት እንደ አንድ የሕይወት አካል አድርገው በመውሰድ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ይናገራሉ። የቴክኖሎጂ መኖር ብቻውን ውጤታማ እንደማያደርግም ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል ያሉት አቶ ጥላሁን፣ አጠቃቀምና የሚተዳደርበት ሁኔታ ሊታይ ይገባል ነው ያሉት። ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም መሠረተ ልማት መሟላት እንደሚኖርበት፣ ተጠቃሚውና የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ተጣምረው መሄድ እንዳለባቸው ያመለክታሉ። የኢንተርኔት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በቅድሚያ ኢንተርኔት አስፈላጊ እንደሆነ ሊታመንበት ይገባል ይላሉ፡፡
የኢንተርኔት ተደራሽነት የኮምፒዩተር ተጠቃሚነት ሰዎች እውቀት ላይ መሠረት ያደረገ እንደሆነ ያመላክቱት አቶ ፊሊክስ፤ በሀገሪቱ ያለው የዲጅታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በጣም አናሳ መሆኑን ይጠቁማሉ። መሠረታዊ የኮምፒዩተር እውቀት የሌላቸው ዜጎች በትምህርት ቤቶች፣ በእስር ቤቶች፣ የወትድርና ቦታዎችና በሌሎች መስኮች መኖራቸውንም ያመለክታሉ። በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያለው ተደራሽነት በጣም አናሳ እንደሆነም አመልክተው፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት ተስፋፍቶ ማህበረሰብ የትም ቦታ ላይ በስፋት መጠቀም መቻል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ፊሊክስ ማብራሪያ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብንመለከት መሠረተ ልማት ተዘርግቶ፣ የዳታ ማዕከላት ተገንብተው፤ መጠቀሚያ መሳሪያዎቹ በውድ ዋጋ ተገዝተው አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል። ሆኖም ግን እነዚህ ማዕከላት በባለሙያ እንዲመሩ ባለመደረጉ ጉዳት ይደርሳል። ቴክኖሎጂው ብዙ ጥቅም ሳይሰጥ አገልግሎቱ ይቋረጣል። ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ጥቅም ላይ እንዲውል ሁሉም የየድርሻውን መወጣትና ትኩረትም ማግኘት አለበት፡፡
ሀገሪቷ ወደኋላ እንድትቀር ያደረጋት የዲጂታል ቴክኖሎጂ እጥረት መሆኑን ነው አቶ ፊሊክስ የሚጠቁሙት። የዓለም ሀገራት የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ኢንተርኔት መጠቀም የግድ እንደሆነም ያስረዳሉ። ለአብነት የጃፓንን ልምድ ብንመለከት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በቀጥታ ትኩረት ያደረጉት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ላይ ነው የሚሉት አቶ ፊሊክስ። ጃፓኖች ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ መሠረት የሆናቸው በየትኛውም መስክ በግብርናም ሆነ ጤና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርገው በመሥራታቸው ነው ይላሉ። በተለይ ሀብት ሳይኖራቸው ከባህል ጋር የተዋሃደ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢንተርኔት ልክ እንደ ትምህርት ቤት ሁሉ ተደራሽነቱ በገጠሪቱ ሀገሪቱ ክፍል እንዲስፋፋ በማድረጋቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢንተርኔት ተደራሽነት ለማስፋት የዓለም ሀገራትን ተሞክሮ ወደ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ማምጣት ይገባል ብለዋል።
አቶ ፊሊክስ በዚህ አራት ዓመት በመንግሥት ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለ ኢንተርኔት ያለው ግንዛቤ በጣም ተለውጧል ሲሉ ገልጸው፣ መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ የኢንተርኔት ተደራሽነት ላይ እየሰራ መሆኑንና በዚህም ለውጦች መምጣታቸውን አመላክተዋል። ለአብነት ባንኮች በኢንተርኔት ግንኙነታቸውን እያሰፉ የምንመለከትበት ሁኔታ ለውጥ መኖሩ ማሳያ ይላሉ፡፡
ለኢንተርኔት ተደራሽነት እንደ ተግዳሮት የተቀመጡትን ችግሮች መንግሥት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው አቶ ፊሊክስ ያመላክቱት። ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ከተሰራና በፖሊሲ ከተደገፈ መሠረተ ልማቱ እየሰፋ ይመጣል ባይ ናቸው። እንደ መንግሥት ለኢንተርኔት ከፍተኛ በጀት ተመድቦ መሥራት እንዳለበት አመላክተው፤ ‹‹ኢንተርኔትን ተደራሽ ለማድረግ የተዘረጋ መሠረተ ልማትና ተጠቃሚው ካልተመጣጠነ ኢንተርኔትን አንጠቀም እንደማለት ነው። ለምሳሌ ጎግል ወይም ዩቲዩብ ቢጠፉ ኢንተርኔት አንጠቀም ማለት ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ በራሳችን የፈጠርናቸው ፕላት ፎርሞች ስለሌሉ ነው›› ብለዋል፡፡
አቶ ፊሊክስ በሌላ በኩል ቴክኖሎጂዎች ከውጭ ገብተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሲደርግ በቀጥታ እንደመጡ ከመጠቀም ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ እና ባህል ጋር አቀናጅቶ የመጠቀም ችግር መኖሩንም ይጠቁማሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በሀገር ውስጥ ለሚሰሩ አዳዲስ(ኢኖቬቲ) ፈጠራዎች ትኩረት በመስጠት በራስ ነባራዊ ሁኔታ በመቀየር ቴክኖሎጂዎችን ማሻሻል የሚቻልበት መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል። መንግሥት ከላይ ወደታች የሚሄድ አሠራር በመተው በተለይ ለባለሙያው ትኩረት ሰጥቶ በእያንዳንዱ ነገር ላይ ባለሙያውን በማሳተፍ የመረጃ እና እውቀት ክፍተት እንዳይፈጠር ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡
አቶ ጥላሁንም ህብረተሰቡ ላይ በመስራት አስፈላጊነት ላይ የሰጡት ሀሳብ የአቶ ፊሊክስን ሀሳብ ያጠናክራል። አሁን ያለንበት የመረጃ ጊዜ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፣ በመረጃ የበለጸገ ህብረተሰብ መገንባት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ፤ ቴክኖሎጂ ማምጣት ላይ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ላይ መሥራት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት። ‹‹በመረጃ የበለጸገ በእውቀት የሚመራ ህብረተሰብ ማምጣት ከቻልን ህብረተሰቡ ራሱ ኢንተርኔትን ይጠይቃል፤ ቴክኖሎጂን ይፈጥራል›› ሲሉ ያስረዳሉ።
አቶ ጥላሁን እንደሚሉት፤ ህብረተሰቡ ዘንድ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በደንብ የማስተዋወቅ እንዲሁም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በደንብ መሰራት ይኖርበታል። የኢንፎርሜሽን ኢንዱስትሪው ጥቅም እንዳለው፣ ሕይወትን መቀየር እንደሚችል ማስገንዘብና ማሳወቅ ይገባል ይላሉ። ‹‹ሰው በልቶ ማደር እንዲችል ለማድረግ በምንሰራው መጠን በእውቀት የታነጸ ህብረተሰብ ሲኖር ደግሞ በራሱ እውቀት መብላት እንዲችል መረጃዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልገው ማስተማር ያስፈልጋል›› ባይ ናቸው ፡፡
የዓለም ሀገራት ከኛ ተሽለው የተገኙት የራሳቸውን እሴት ይዘው በመገኘታቸው ነው የሚሉት አቶ ጥላሁን፤ ቴክኖሎጂዎች ስናላምድ ከቴክኖሎጂው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ነገሮች ላይ እምብዛም አልተሰራም ሲሉም ይጠቁማሉ። እንደ ጃፓን፣ ቻይና የመሳሰሉት ሌሎች ሀገሮችን የቴክኖሎጂ እድገታቸውን ብንመለከት መጀመሪያ ከራሳቸው ውስጣዊ ችግር ተነስተው ነው ምርምሮችንም ሆነ የፈጠራ ሥራዎችን የሚሰሩት የሚሉት አቶ ጥላሁን፤ እኛ ግን ያለብን ችግር በጥልቀት አንለይም እንዲሁም አናጠናም ይላሉ። ‹‹ችግራችንን የምንፈታው እነሱ የሰሩት ቴክኖሎጂ በቀጥታ ወስደን በመጠቀም ነው፤ የወደፊት መፍትሔ ሊሆን የሚገባው ችግሮቻችን በራሳችንን መፍታት የሚያስችሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን በማስፋፋት መጠቀም ስንችል ነው ብለዋል።
አሁን ኢንተርኔት ኖሮ እኮ ተደራሽ የምናደርገውና የምናገራው እንዲሁም የምንጫወትበት የመረጃ አካባቢ ሌሎች ሀገራት በሰሩት ፕላት ፎርም ላይ መሆኑን ነው ሲሉ አቶ ጥላሁን ይናገራሉ። በምንፈልገው መጠንና ልክ ኢንተርኔት ቢኖረን እንኳን፣ የትኛውን የራሳችንን ዳታ ነው ተደራሽ የምናደርገው? በየትኛው ዳታ ነው ኢንተርኔትን ተጠቅመን ለችግራችን መፍትሔ የምንፈልገው የሚለው ከወዲሁ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው ይላሉ። ስለዚህ መጀመሪያ የራሳችን የምንለውን ነገር በደንብ መገንባት፣ ከዚያ ባሻገር ደግሞ የአስተዳደሩን ሥራ መሥራት፣ ሰዎች በኢንተርኔቱ ዘርፍ ያላቸውን እውቀት በደንብ ማሳደግ ቀጣዩ ትልቁ ሥራችን መሆን አለበት ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ በቅርቡ በተካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ዘርፍ ፈጣን ለውጥ እያመጣች መሆኑን ጠቅሰው፤ የበይነ መረብ አገልግሎት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘውን የአሥር ዓመት እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ፋይዳ እንዳለው አስታውቀዋል።
‹‹በዘመነ ዲጅታል የበይነ መረብ ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በትራንስፖርት፣ በግብርና እንዲሁም በጤና እድገት ላይ ዘርፉ ያለውን አወንታዊ ድጋፍም አመላክተዋል። ኢትዮጵያ በኮቪድና በሌሎች ሰው ሠራሽ ችግሮች በተፈተነችበት ወቅት ሥራን በበይነ መረብ ማካሄድ መቻሏን አዳዲስ ፈጠራዎች እንዲበረታቱ ማድረጉንም በመልካም ጎኑ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ወደ አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ በምታደርገው ጉዞ አንድ ወጥ የሆነ ራዕይ ያስቀመጠ ብሔራዊ ዲጂታል ስትራቴጂ በሥራ ላይ ማዋሏን የጠቆሙት ዶክተር ዐቢይ፣ ስትራቴጂው መሠረተ ልማትን ማጎልበት፣ ሥርዓቶችን ማስቻል፣ ዲጂታል መድረኮችን እና የዲጂታል ሥነ-ምሕዳርን በመገንባት ላይ ያተኩራል ማለታቸውም ይታወቃል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው 17ኛው የዓለም የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ብዙም ባስተላለፉት መልእክት በዓለም አቀፍ ደረጃ በበይነ መረብ ተደራሽነት ላይ በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ መጠቆማቸው ይታወቃል። አስተማማኝና አካታች የዲጂታል ደህንነት እንደሚያስፈልግም ማስገንዘባው ይታወሳል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 /2015