በኢትዮጵያ በየዓመቱ ስለ ሲሚንቶ ችግርና እጥረት እንዲሁም የዋጋ መወደድ ይወራል። ይመከርበታል። ዛቻ የተቀላቀለበት አቅጣጫም ይሰጥበታል። ይሑንና ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ሲያገኝ ሳይሆን፤ የምርት ስርጭት ሒደቱ ሲተረማመስ እና የባሰ ምስቅልቅል ውስጥ ሲገባ የሚስተዋል፤ ይልቁንም ወግ የሌለውና ሸፍጥ የሚታይበት፣ ሁሌም ቢወቅጡት እንቦጭ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
እናም የሲሚንቶው ኢንዱስትሪ መሰል ቅርቃር ውስጥ ሲባዝን ‹‹ለምን እንዲህ ይሆናል››? በሚል ኃላፊነት የሚወስድ የለም። ሁሉም ‹‹ከደሙ ንፁህ›› ነን ባይ ነው። አምራቾች ‹‹የውጭ ምንዛሪ የሚሰጠን አጣን›› ሲሉ፤ አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች ‹‹ከተመዘገብን ዓመት ሞላን፣ ይሑንና ወረፋ አልደረሰንም›› የሚል ሰበብ ይደረድራሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ገዢው ወይንም ተጠቃሚው በሚደርስበት የተደራረበ ችግርና ጫና ምክንያት ‹‹ኧረ የመፍትሔ ያለህ›› የሚል ምሬቱን ሲገልፅ ይሰማል፡፡
ይሁን አንጂ የሲሚንቶ ገበያ ከዓመት ዓመት በዚህ መልኩ በችግር ላለመላቀቁና እጅ ከወርች ካሰረው አዙሪት መላቀቅ ላለመቻሉ የተለያዩ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ። ለአብነት፣ የግንባታዎች መበራከት እና ከአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ጋር የተያያዘው ችግር አንዱ ነው። ምርቱ ከፋብሪካው አንስቶ ተጠቃሚው እጅ እስኪገባ ድረስ ያለው የግብይት ሰንሰለት ረዥም መሆንም ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ነው። ያልተገባ ጥቅም የማግኘት ፍላጎት/ስግብግብነት እንዲሁም የኢኮኖሚ አሻጥርን አይነት ጉዳዮችም በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡
አንድም ከብቃት ማነስ ሌላም ከጥቅም ተጋሪነት የሚመነጭ የቁጥጥር መላላት እንዲሁም በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ውስጥ ባሉ ጥቂት ጡንቻማ ግለሰቦችና ከእነሱ ጋር የጥቅም ትስስር ባላቸው አካላት የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራትም ለሲሚንቶው ቀውስ ምክንያት ተብለው ከሚዘረዘሩ ችግሮች ተርታ የሚያሰልፏቸውም ብዙዎች ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ ለሲሚንቶ ምርትና ስርጭት መዛባት ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱት መሰል ችግሮች መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው በሙስና የተዘፈቁ የመንግስት ባለስልጣናት ስውር እና ረጅም እጅ ስለመሆኑም የበርካቶች እምነት ነው፡፡
ይሄን የሚሉ ወገኖች ደግሞ በቅርቡ የተገለጠውን አንድ ሃቅ አንድ ብለው እንደማሳያ ይጠቅሳሉ። ይሄም ባለንበት የታህሳስ ወር መጀመሪያ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽንና ሎጂስቲክስ ምክትል ዳይሬክተር ተስፋዬ ደሜና አራት የአገልግሎቱ ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ነው። በዚህ ረገድ ከፍትህ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃም፣ ግለሰቦቹ በአገልግሎት ስም 29 ሺ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ከሁለት ፋብሪካዎች ገዝተው ለግለሰቦች በመሸጥ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው በማዋል የተጠረጠሩበት የሙስና ተግባር መሆኑን ያመላከተበት ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በማድረግ ላይ የምትገኝ አገር እንደመሆኗ፤ ሲሚንቶ በሁሉም መስክ በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፉ የምጣኔ ሀብት አንቀሳቃሽ ሞተርና የበርካቶች የስራ ዋስትና የዕለት ጉርስ ምክንያት ነው። ይሕ እንደመሆኑ ታዲያ የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት በአግባቡ መመራት ይኖርበታል። የሲሚንቶው ገበያ ሰላም ካላገኘ የሚበላሸው ብዙ ነው። የሲሚንቶ ግብይት መስተጓጎል፣ የስርጭቱ በሕገ ወጦችና በደላላዎች መመራት እንዲሁም በስግብግብ ነጋዴዎች መከዘን በአገር ላይ የሚያስከትለው ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
ለአብነት፣ በግንባታው ዘርፍ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው የነበሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ያለ ስራ እንዲባዝኑ፣ አምራች ጉልበታቸው ያለ አግባብ እንዲባክን ያደርጋል። ሌሎች የግንባታ ቁሶችን በማቅረብ የሚተዳደሩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ስራም ይታወካል። በርካታ ለሕዝብ አገልግሎት ተብለው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ባሉበት ለመቆም እንዲገደዱ እና ተስተጓግለው መጠናቀቅ ባለባቸው ጊዜ መጠናቀቅ አልሆን እንዲላቸው ምክንያት ይሆኗል፡፡
መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የሲሚንቶው ቀውስ ‹‹ችግሩ ምን ይሆን›› በሚል ሲጠየቅ፤ ‹‹የመለዋወጫ ችግር ነው፣ ደላሎች የፈጠሩት ሰው ሠራሽ እጥረት ነው፣ የኢኮኖሚ አሻጥር ነው›› የሚል ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል። ውጤቱ በሚጠበቀው ልክ ባይሆንም መፍትሄ ያላቸውን መመሪያ እና የአሰራር ደንቦችን ማውጣት ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድም ተስተውሏል፡፡
ለአብነት፣ ሐምሌ 2014 ዓ.ም የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሲሚንቶ ዋጋን የሚቆጣጠርና በሚኒስቴሩ የሚተገበረው መመሪያ በማውጣት ገበያው ላልተወሰነ ጊዜ በነጻ የገበያ ዋጋ ላይ ተመስርቶ እንደሚወሰን ገልፆ ነበር። በመስከረም 2015 ዓ.ም ደግሞ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአገሪቱ ያለውን የሲሚንቶ ምርት የዋጋ ንረት ለመግታት አዲስ የሲሚንቶ ዋጋ ደንብ ማውጣቱን አስታውቋል። ይህም ከአንድ ዓመት በፊት ከወጣው እጅግ በጣም የራቀ ነው። የነፃ ገበያ ኢኮኖሚውን የሚወስን ነበር።
መንግስት ለችግሩ ፍቱን መፍትሄ መስጠት እንዳልቻለ ያሳያል። ሂደቱም ለችግሩ ዘላቂ ከመስጠት ይልቅ አለባብሰው ቢያርሱ ሆኖበት ችግሮችን እየተከተሉ ጊዜያዊ መፍትሄ መስጠት ላይ መጠመዱን ያሳያል። ምክንያቱም ችግሩን ለማቃለል በሚል በየጊዜው መመሪያዎችን ሲገለባብጥ ከመቆየቱም በላይ፣ ‹‹ከዚህ በላይ ሽያጭ ሲያከናውን ያገኘሁትን አልምረውም አይቀጡ ቅጣት እቀጣዋለሁ›› የሚል ማስፈራሪያ እስከመስጠት ተሻግሮም ታይቷል። ይሑንና ለመፍትሄ የሚቀርቡ ሃሳቦች ሁሉ አንድ ኩንታል ሲሚንቶን ሁለት ሺህ ብር ከመሸጥ የመታደግ አቅም አልነበራቸውም፡፡
ምክንያቱም ከስድስት ወራት በፊት በመንግስት የወጣው የሲሚንቶ ስርጭት መመሪያ ህብረተሰቡን ከደላሎች፣ አስፈላጊ ካልሆነ የዋጋ ንረት፣ ከስርቆት እና ከቢሮክራሲያዊ አሰራር ለማላቀቅ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ ባለፉት አምስት ወራት ትግበራ እንታየው ችግሮቹ እንዳልተቀረፉም። በአጠቃላይ የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት እጥረቱን ለመቀነስ፣ እንዲሁም በግብይት ውስጥ ያለውን ረዥም ሰንሰለት ለመበጠስና በየጊዜው እንደ ችግር ለሚነሱ ጉዳዮች መፍትሔ ይሆናል የተባሉ ዕርምጃዎች ይሕ ነው የሚባል ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። መፍትሄ ተብለው የሚወሰዱ መድሃኒቶች ሁሉ በአብዛኛው ለማስታገሻ የሚረዱ እንጂ ህመሙን የሚያሽሩ አልነበሩም፡፡
ሆኖም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉና አካሄዱ አላምር ያላቸው የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ምሁራን አሁን ያለውን የሲሚንቶ ችግር ለመፍታት መፍትሔው አሁንም መንግስት እጅ መሆኑን ይገልጻሉ። ለዚህም ‹‹ገበያው ከፖለቲካ ንክኪ መውጣት አለበት፣ እንደውም መንግሥት ከዚህ ወጥቶ ገበያውን ነፃ ቢያደርገው ገበያው ይስተካከላል›› የሚል እምነት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲገለፁ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ለጉዳዩ እየተሰጠው ያለው ምላሽ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› አይነት ሆኖ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ግራ የገባውን የሲሚንቶ ዋጋ ለማረጋጋትና ለመቆጣጠር ከጥቂት ወራት በፊት ያወጣውን መመሪያ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ዳግም ሽሮ በሌላ ተክቶታል፡፡
በአዲሱ ውሳኔውም ሲሚንቶ በነፃ ገበያ ዋጋ እንዲሸጥ ብሏል። በዚህ ውሳኔ ላይ ታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠበት ሲሆን፤ መግለጫውን የሰጡት የንግድ ስርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ፣ በሲሚንቶ ስርጭትና ግብይት ላይ ሲስተዋል የነበረውን ችግር ለመቅረፍ የወጣው መመሪያ ቁጥር 908/2014ን በመላ አገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገቡን የተናገሩ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውጤቶች መካከል የቆሙ የፌዴራልና የክልል የመንግስት ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ሂደታቸው መግባታቸው፣ የግብይት ሰንሰለቱ እንዲያጥር መደረጉ፣ ጠረፍ የሚባሉ አካባቢዎች በመመሪያው አማካይነት የሲሚንቶ አቅርቦት እንዲያገኙ መደረጉ፣ የፋብሪካዎችን ያልተገባ ጭማሪ ማስታገስ መቻሉ፣ ትላልቅ የግል የግንባታ ፕሮጀክቶችና ሪል እስቴቶች በቀጥታ ከፋብሪካዎች ሲሚንቶ እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በአንጻሩ በመመሪያው አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች የሲሚንቶ ምርትና ምርታማነት መቀነስ፣ እስከ መስከረም 20 2015 ድረስ ከሁለት ፋብሪካዎች ውጪ ስምንት ፋብሪካዎች ሽያጭ አለመፈጸማቸው፣ የተመረተው ሲሚንቶም በአግባቡ ያለመሰራጨት ችግር እንደነበር፣ የአንዳንድ ክልል ፕሮጀክቶች የሲሚንቶ ፍላጎት በአግባቡ ተጠንቶ እና ተደራጅቶ ለሚኒስቴሩ በወቅቱ አለመላክ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ቸርቻሪዎችን በመተካት ስርጭት እንዲያደርጉ የተመረጡት የልማት ድርጅቶች በቂ እና ተደራሽ የስርጭት ማዕከል ያለመኖር ችግርችን መስተዋላቸውን ዘርዝረዋል፡፡
አያይዘውም፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሌላ መመሪያ መዘጋጀቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአዲሱ መመሪያ መሠረትም በኬላዎች አካባቢ በሲሚንቶ ምርት ላይ የሚደረግ ማንኛውም ቁጥጥር መነሳቱ፣ ቸርቻሪዎችንና አከፋፋዮችን መምረጥ የፋብሪካዎች ኃላፊነት እንዲሆን መደረጉ፣ ያለደረሰኝ ምንም አይነት ግብይት እንዳይካሄድ መደረጉ፣ ከፋብሪካዎች የሚወጣ ማንኛውም የሲሚንቶ ምርት በቂ ሰነድ ሊኖረው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በፋብሪካዎች በር ላይ የሚደረገውን የሲሚንቶ ሽያጭ ዋጋ የመወሰን ስልጣኑን በአዲሱ መመሪያ ይዞ ቢቀጥልም፤ በየአካባቢው የሚኖረውን የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ የመወሰን ኃላፊነት ግን ወደ ፋብሪካዎች እንዲተላለፍ አድርጓል። ሆኖም መንግስት የሲሚንቶ ምርት ከፋብሪካ ለተጠቃሚዎች የሚቀርብበት ሂደት በተገቢው ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ ታውቋል። በዚህም በመንግስት የሚከናወነው የቁጥጥር ስራ የሲሚንቶ ምርትን ‹‹ነጻነትን›› የሚያግድ አይሆንም ተብሏል።
ዋናው ነጥብ ግን በወራት ልዩነት ሚኒስቴሩ እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሰበትን ምክንያት ለማወቅ ቢያስቸግርም፣ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አይነቱ ተግባር ግን የአገሪቱ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ የገባበትን ቅርቃር ግልፅ አድርጎ የማስመልከት አቅሙ ግዙፍ ነው። በእርግጥ ቀደም ሲል የግብይት ሥርዓቱን በመንግስታዊ መዋቅር ለመምራት የተደረገው ጥረት የተሳካ፣ የሕዝቡን ችግር ያቃለለ ሥራ ነበር ለማለት የሚያስደፍር ውጤት አልታየም። የሲሚንቶ ምርት በመንግሥት መዋቅሩ ቀጥተኛ ተሳትፎ እየተመራ ዋጋው መኖሩ አልቀረም። የሕገ ወጦች መጠቀሚያ ከመሆንም አልዳነም።
ከዚህ አንጻር አሁን ላይ ማሻሻያ መደረጉም እሰየው የሚያሰኝ ቢሆንም፤ አሁንም ቢሆን ሲሚንቶ በነፃ ገበያ እንደ ቀድሞው እንዲገበያይ መወሰኑ ብቻውን መፍትሔ ይሆናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በመሆኑም ሕግ፣ ደንብ እና መመሪያ ከማውጣት ባለፈ ለውጤታማ ተፈፃሚነቱ በቂ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
አሁንም ቢሆን ቀደም ሲል የግብይት ሥርዓቱን በመንግስታዊ መዋቅር ለመምራት ሲሞከር በሂደቱ የተገኘው ውጤት ምንድን ነበር? ከትርፉና ከኪሳራው የቱ በልጦ ታየ? ድክመቱስ የቱ ጋራ ይበልጥ ተስተዋለ? ብሎ መፈተሽ፤ ለስኬታማነቱ መጓደል ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን መለየት እና መቀመር የግድ ይላል። የሰሞኑ ውሳኔ ገበያውን ምን ያህል ያረጋገዋል የሚለውን ወደፊት የምናየው ይሆናል። ይሑንና ‹‹ሁኔታው ለእኔ ተመቸኝ” እንዳለው ሙዚቀኛ እንዳይሆንና የሲሚንቶ ገበያው በሕገ ወጥ ነጋዴዎችንና ደላላዎች እንዳይዘወር ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ይላል፡፡
በተለይ የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱን ከደላሎች ጣልቃ ገብነት ለማላቀቅ፣ በጥቁር ገበያ ዘዋሪዎች አማካይነት ፈር የሳተውን ግብይት ለማስተካከልና መልክ ለማስያዝ መንግሥት በአንክሮ ሊሰራ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከሌብነትና ከዘራፊነት ጋር ስማቸው የማይነሳ ህጋዊው የንግዱ ማኅበረሰብ በነፃነት ሥራቸውን የማከናወን መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የግብይት ሥርዓቱን የሚያተራምሱ ደላሎችን አደብ ማስገዛት፣ ምርት አንቀው የሚይዙትንም ሆነ የሚሰውሩትን በሕግ መቅጣት የግድ ይላል፡፡
ከሁሉ በላይ የአንድን ድርጊት ወይም ውሳኔ ተጠቃሚዎችን ‹‹beneficiary of an action›› ኖችን ለይቶ ማወቅና ማስወገድ ሊዘነጋ አይገባውም። እናም እዚህ አካባቢ በሚገባ መፈተሽና ፈጣን ማስተካከል ማድረግ ከተቻለ ሌላው ዕዳው ገብስ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ከሁሉ በላይ መንግስት በየጊዜው መመሪያ ከመገለባበጥ ጊዜ ወስዶ እና ጥናት ላይ ተሞርክዞ አጠቃላይ የሲሚንቶ የግብይት ሥርዓቱን ለማስተካከል የሚረዱ እርምጃዎችን ለመራመድ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ አሁንም በስመ ነፃ ገበያ ስም ሲሚንቶ በጥቂት ተዋናዮች እየተተራመሰ መቀጠሉ አይቀርም፡፡
በእርግጥ ግብይት እና ስርጭቱ መሄድ ባለበት መንገድ እንዲራመድ በማድረገ ረገድ መንግስት ብቻውን ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። ጉዳዩን ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው አይደለም። ሁላችንም በምን አገባኝ ስሜት የምናልፈው ሕገ ወጥ ሥራ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዋጋ የሚያስከፍለው እኛኑ ነው፡፡
በመሆኑም ሕጋዊ አሠራር ብቻ እንዲተገበር፣ ሕገ ወጥ ሥራዎች በፍጥነት እንዲታረሙ የጋራ ሚናችንን መወጣት አለብን። ለጋራ ተጠቃሚነታችን ስንል ሕግ፣ ደንብ እና መመሪያ አክባሪም አስከባሪም እንሁን። በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱም ተገቢን ድጋፍ መስጠት ይኖርብናል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 /2015