የተለያዩ አገራት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ አገራዊ ችግሮችን/መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ያጋጠሙ አለመግባበቶችን/አካታች በሆነ አገራዊ ውይይት መፍታት ችለዋል። በዚህም ዘላቂ ሠላም በመስፈን የተሳካ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖላቲካዊ ለውጥ ማምጣት ችለዋል።
ለአብነት ያህል ደቡብ አፍሪካን መጥቀስ ይቻላል። ዜጎቿ አገሪቱን እንደአገር የህልውና አደጋ ውስጥ ጥሎ የነበረውን ችግር ይቅርታ እና እርቅን መሰረት ባደረገ አገራዊ ውይይት በአገራቸው ጉዳይ ተገልለው የነበሩ ቡድኖችን ጭምር እንዲደመጡ እድል በመስጠት ችግሮቻቸውን መፍታት ችለዋል።
ይሄ ደግሞ ለአገራችን ኢትዮጵያ እንደ አንድ አብነት ሊወሰድ የሚችል ተግባር ነው። ምክንያቱም አገራዊ ውይይቶች በተለይ በክልሎች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ከብዙ በላድርሻ አከላት ጋር ተወያይቶ ለመፍታት ውጤታማ ይሆናሉ። ባለድርሻ አካለት አገራዊ ውይይት በሚጠሩበት ጊዜ አላማው ብዙውን ጊዜ ፖለቲካ ተሳትፎን ማስፋት እና በሌለ መልኩ ለተገለሉ ቡድኖች ባለቤትነት መስጠት ነው፡፡
ይህ የበለጠ አካታች ሂደት እና የተሻለ ዘላቂ ውጤት ለማምጣት መንገድ ይከፍታል። ነገር ግን አገራዊ ውይይቶች አንዳንዴ በልሂቃን ለብሔራዊ ዓላማ የፖለቲካ ህጋዊነትን ለማግኘት ወይም ለማስመለስ እንደ መሳሪያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ይህም የለውጥ አቅማቸውን በመገደብ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋል።
ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረግ ምክክር ግን ከእንደዚህ አይነት ፍላጎት በጸዳ መልኩ በዕውነት ለይ በተመሰረተ ግንኙነት እና ስሜትን ተቆጣጥሮ ቁጭ ተብሎ በጥሞና በመነጋገርና በመደማመጥ ሀሳብ የሚለዋወጡበት፤ እርስ በእርስ የሚነጋገሩበት፤ የሚመካከሩበት እና የጋራ መግባባት ላይ የሚደርሱበት ነው።
አገራዊ ምክክር ደፍሞ በዚህ መልኩ ሲከወን ከአሸናፊነትና ተሸናፊነት ስሜትና እልህ ነጻ በሆነ መንፈስ ሁሉም/አገርና ህዝብ/ አሸናፊ የሚሆኑበት የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር የሚያስችል ነው። ዘላቂ ሰላምና መግባባትን በመፍጠር ዜጎችን ከግጭትና ግጭት ከሚፈጥረው ኪሳራ ለመታደግ ያስችላል።
አገራዊ ምክክር በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የተለያየ ቋንቋ፣ ሀይማኖት፣ ባሕል፣ ወግና ልማድ ወዘተ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን አካታች በሆነ ስርዓት ቁጭ ብለው ላለመግባባታቸው ምክንያት በሆኑ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ የሚመካከሩበትና ወደ መግባባት የሚሸጋገሩበት ሂደት ነው።
አገራዊ ምክክር አለመግባባቶች ወደ ግጭት ከማምራታቸው በፊት መከላከል የሚያስችል ሲሆን፤ በዜጎች መካከል አዲስ ማህበራዊ ውል እስከ መፍጠር የሚደርስ ዓላማ ሊኖረው ይችላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሕብተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር የሀሳብ ልዩነት እና አለመግባባት እንዳለ ይታመናል። ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ተስፋ የተደረገው አገራዊ ምክክሩ የተሻለ አገራዊ አንድነት ለመገንባት በሂደትም የመተማመን እና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት እንዲሁም የተሸረሸሩ ማህበራዊ ዕሴቶችን ለማደስ የሚጠቅም ነው፡፡
አገራዊ ምክክሩ ተቀባይነት እና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆንም ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ተሰይመውለት ገለልተኛ እና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ባላቸው ግለሰቦች እንዲመራ ተደርጓል። ተጠያቂነታቸውም ገለልተኛ ለሆነ አካል እንዲሆን ተደርጓል።
ምክክሩ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት፣ መተማመንን ለማጎልበት፣ እንዲሁም በመንግስት እና በህዝብ መካከል መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያስችል አዲስ አስተሳሰብና ለአስተሳሰቡ የሚገዛ ማህበረሰብ መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው።
የቆዩ አለመግባባቶችን ጨምሮ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት በመፍታት፣ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለሚደረገው ጉዞ የውይይት ባህልን ማዳበር እና ወቅታዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ይረዳል።
ሰላምን በማረጋገጥ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ መደላድል ከመፍጠር በተጨማሪ አገራዊ መግባባት በመፍጠር ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አገረ መንግስት ለመገንባት የሚያስችል መሰረት ለመጣልም የተሻለ እድል መፍጠር ያስችላል። ለዚህም ሲባል ኮሚሽኑ የውይይት አጀንዳዎችን ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር በመምከር በመምረጥ ላይ ይገኛል ።
ላለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመለየት፣ በተለዩት አጀንዳዎች ላይ አገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ስርዓት በመዘርጋት ለአገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተልዕኮ አድርጎ እየሰራ ነው። በዚህም በ2017 ዓ.ም በአገሪቱ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ተፈጥሮ የማየት ርዕይ አስቀምጧል፡፡
በዚህ ረገድ የተሳካ ብሄራዊ ውይይት ማድረግ አገሪቱ ለምታደርገው የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ መደለደልን ከመፍጠር በዘለለ ጠንካራ አገረ መንግስት ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው። በመሆኑም ለአሳታፊነቱ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያሻል። አካታች፣ ግልጽ እና ተአማኒነት ያለው የምክክር ሂደት እንዲኖረው ማድረግም ተገቢ ነው፡፡
ይህ ሲባል፣ ሰፊ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አካላት፤ ለምሳሌ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችን፣ የሲቭክ ማህበራት፣ ሴቶችና ወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የሃይማኖት እና ባህላዊ መሪዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ መንግስት እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማሳተፍ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብሄራዊ ውይይቱ የታለመለትን ዓላማ ማሳካት ስለሚችል፤ ለዚህ ዓላማ መሳካት የሁሉንም በላድርሻ አካለት ጥረት አስፈላጊ ነው።
በክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 /2015