ጋዜጠኛና ዲፕሎማቱ አቶ ማዕረጉ በዛብህ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነው ከመስራታቸው አስቀድሞ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አዘጋጅ ነበሩ። በማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ በቱሪዝሙ ውስጥ ደግሞ የፕሮሞሽን መምሪያ ኃላፊ፣ ከዚያ በኋላ ትምህርታቸውን በፖለቲካው ዘርፍ በማሳደግ በጄኔቭ ቀጥሎም በእንግሊዝ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ኢትዮጵያን ከ18 ዓመት በላይ አገልግለዋል። ወደአገር ቤት ተመልሰው ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። በተጨማሪም ለረጅም ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በዩኒቱ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትን አስተምረዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ‹‹ጋዜጠኝነት ጽንሰ ሐሳቡና አተገባበሩ›› እና ‹‹በጋዜጠኝነት ሙያ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች›› በሚሉ ርዕሶች ሁለት መጽሀፍት እንዲሁም ‹‹የእኔ እንጉርጉሮ›› በሚል ርዕስ የግጥም መድብልም ጽፈው ለአንባቢያኑ አበርክተዋል። የዛሬው የወቅታዊ እንግዳችን መምህር፣ ጋዜጠኛና ደራሲም ሲሆኑ በጋዜጠኝነቱና በመገናኛ ብዙሃኑ ዙሪያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ አነጋግረናቸው እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው ጋዜጠኝነት በእናንተ ዘመን ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል በሚለው ጥያቄ ቃለ ምልልሳችንን እንጀምር?
አቶ ማዕረጉ፡- ጋዜጠኝነት እንደ ሌሎች የሙያ አይነት ሁሉ እየተቀየረ መጥቷል። በተለይ በቴሌቪዥኑ በኩል ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑ የሚታይ ነው። በእርግጥ የስራውን ጉዳይ ለማነጻጸር ያስቸግራል። እኔ የሰራሁበት የሚዲያ ዘርፍ ሕትመት ላይ ነው፤ ይህ የሕትመት ሚዲያ ውጤት አሁን አሁን በከተማችን አዲስ አበባ ውስጥ እምብዛም አይታይም ማለት ያስደፍረኛል። ለምሳሌ አዲስ ዘመንን በመዲናችን ውስጥ አይቼ አላውቅም ማለት እችላለሁ። በጥቅሉ ከተማ ውስጥ ምንም ጋዜጣ ማግኘት አይቻልም። በመሆኑም ይህ ትልቅ ግደፈት ነው ባይ ነኝ።
በአሁኑ ወቅት በስፋት እየታዩ ያሉት የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ በተለይም ቴሌቪዥን ነው። አንደኛ ብዙ የጋዜጠኝነት ስራ የሚካሄደው ቴሌቪዥን ላይ ሲሆን፣ እሱም አብዛኛውን ጊዜ ውይይት ነው። እኔ በሰፊው በዩኒቨርስቲ ውስጥ ከማስተምረው የትምህርት አይነት አንዱ ደግሞ ቃለመጠይቅ (ኢንተርቪው) ነበር። ቃለ መጠይቅ ማድረግ ትልቅ ሙያ ነው። አንድ ጋዜጠኛ አንድ እንግዳ ጋብዞ ቃለምልልስ ከማድረጉ በፊት ቃለ ምልልሱን ለማድረግ ስለጋበዘው እንግዳ በሰፊው ሊያውቅ ይገባል። ሁለተኛ ደግሞ ሊያነጋግረው ስለሚፈልገው ሙያ ጋዜጠኛው በሰፊው እውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡
አሁን አሁን እያየሁት ያለው ቃለ ምልልስ ግን በተለይ በቴሌቪዥን ላይ የሚካሄደው ቃለ ምልልስ አድራጊው እንደቀላል ነገር አውርቶ በመጨረሻም ‹‹እድል ልስጥዎት የሚጨምሩት ነገር ካለ›› ሲል ይደመጣል፤ በመጀመሪያ ደረጃ ‹‹እድል ልስጥዎ›› መባሉ በራሱ አግባብነት ያለው አባባል አይደለም። ቃለ ምልልስ የሚደረገው ሰው የጋዜጠኛው እንግዳ ነው፤ እንግዳ እስከሆነ ድረስ ተገቢውን ክብር መስጠት ተገቢ ነው። በተለይ ደግሞ አብዛኛዎቹ ቃለ ምልልስ የሚደረግላቸው ሰዎች በእድሜም፣ በትምህርትም፣ በስራም ከፍተኛ ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ስለሆኑ አክብሮትም ያስፈልጋል።
ሌላው ቃለ ምልልስ አድራጊው ጋዜጠኛ የሚጠቀመው አንድ ቋንቋ አለ፤ እሱም ‹‹መልካም›› የሚል ነው። ይህ አባባል ለእኔ አስቂኝ ነው። መልካም ማለት ልክ አንድ አስተማሪ ተማሪውን ‹‹ይህን አደረግህ እንዴ! እንግዲያውስ መልካም›› እንደሚለው አይነት ይመስላልና ‹‹እሽ! አመሰግናለሁ›› በሚባሉ ቃላት ነው መተካት ያለበት። ደግነቱ የሕትመት ሚዲያ ላይ ችግር የለም። ምክንያቱም ለተደራሲያኑ አይታይምና ነው። በቴሌቪዥን ሲሆን ግን የሚደረገው የቃለ ምልልስ መስተጋብር ስለሚታይ በዛ በኩል ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነው። ይህ አንዱ አሰራር ነው።
ሌላው የቋንቋ ግድፈቱ በጣም ያሳፍራል። ይህ በአማርኛም በእንግሊዝኛም ሳይቀር ነው። በ‹ው› ካብዕ እና በ‹ው› ሳድስ ያለው ልዩነት የማይታወቅበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ‹ምሳዬን በላሁ› ለማለት ‹ምሳዬን በላው› ይባል ተጀምሯል። እንዲህ እየተባለ ይጻፋል፤ በቴሌቪዥን ላይም በዚሁ መልክ ይነገራል። ከዚህ አንጻር የሚደረግ ጥንቃቄ የለም፡፡
በእኛ ዘመን ብዙ የተማርን ባንሆንም፤ በእውነቱ ከሆነ ጥንቃቄው በጣም የሚያስደስት ነበር። ጥናትና ንባብ በእጅጉ ይደረግ የነበረበት ዘመን ነው። እኔ አስቀድሜ እንደገለጽኩልሽ ያስተማርኩት ብዙ ዓመት ነው። የተማሩትም የት እንደሄዱ አላውቅም። አንዳንዴ ሳስብ ያስተማርናቸው ልጆች የት ሔደው ነው እላለሁ። እነዚህ ነገሮች በአግባቡ በክፍል ውስጥ ስናስተምር እንደቆየን አውቃለሁ።
በሌላ በኩል የቀደመውን ጋዜጠኝነትና የአሁኑን ለማነጻጸር ያህል አሁን ያለው እድል ከቀደመው በጣም የተሻለ ነው። በዛው ልክ ከኛ ዘመን ጋር ሲወዳደር ነጻነቱም ሰፊ ነው። የአሁኖቹ ጋዜጠኞች የፈለጉትን አይነት መጻሕፍት ያገኛሉ። ስለተለያዩ ሰዎች የሚነበብ ነገር ለማግኘት በጣም ቀላል ነው። ለምሳሌ ስለእኔ ብዙ የተጻፉ ነገሮች አሉ። እዚህ ላይ ማውራት የፈለግኩት ስለእኔ ሳይሆን ስለተለያዩ ሰዎች የተጻፉ በርካታ ነገሮች አሉና በዛው ልክ ተያያዥ የሆኑ ነገሮችን ማንበብ ይቻላል ለማለት ነው። ስለዚህ በቃለ ምልልስ አድራጊውና በተደራጊው መካከል የሚደረገው ቃለ ምልልስ ላይ የመጀመሪያው ቃለ ምልልስ መምሰል የለበትም። በዚህ ወቅት የጋዜጠኛውንም እውቀት የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡
በትምህርት ከሆነ ደግሞ የአሁኖቹ ጋዜጠኞች የበለጠ በመማራቸው እድለኞች ናቸው ማለት ያስችላል። ብዙዎች በሚያስብል ደረጃ ዲግሪ ያላቸው ናቸው። ነገር ግን ጥረታቸው ያንን ያህል አይደለም። የአሁኖቹ ጋዜጠኞች የተማሩትን ያህል ብዙ ሆነው አይታዩም። በእርግጥ አልፎ አልፎ እጅግ ጎበዝ የሆኑ ጋዜጠኞች የሉም ለማለት ግን አይደለም።
አብዝቼ የምገልጽልሽ ስለ ቴሌቪዥኑ ነው፤ ስለ ሕትመት ሚዲያውማ አስቀድሜ እንደጠቀስኩልሽ ጋዜጣ በከተማው ውስጥ ስለሌለ ምንም የማውቀው ነገር የለም ማለቱ ይቀላል። በተለይ እኔ ከዛሬይቱና ከአዲስ ዘመን በተጨማሪ በሔራልድ ጋዜጣ ላይም ሰርቻለሁ። ከዚህም የተነሳ ሔራልድ ጋዜጣን ማየትና ማንበብ እፈልጋለሁ። በቋንቋ በኩል አዲስ ዘመን እንኳን ደህና ነው።
ለምሳሌ አንድ ነገር ልጥቀስ፤ ዲፕሎማሲያችን በጦርነቱ ተዳክሟል እየተባለ ሲነገር ነበር። ዲፕሎማሲው የሚሰራው አንደኛ አንድ ዲፕሎማት ተሹሞ ወደሌላ አገር ሲሄድ የሚያነበውና የሚያዳምጠው ከሚኖርበት አገር ያሉትን የሕትመተ ውጤቶችንና በብሮድካስት የሚተላለፉትን መረጃዎች ነው። የተለያየ መረጃ የሚያገኘው ከዚያ ነው። በእርግጥ በስራ ላይም ሊያገኝ ይችላል። ነገር ግን ዋና መረጃውን የሚያገኘው በየዕለቱ ከሚወጡ ጋዜጦችም ጭምር ነው። በየዕለቱ የሚወጡ ጋዜጦች ደግሞ በአጥጋቢ መልክ ካልተዘጋጁና ደረጃቸው ከፍ ያለ ካልሆነ አያነባቸውም፤ ይንቃቸዋል። ስለዚህ የሚያዘነብለው ወደራሱ ግምትና ሰዎች ወደሚሉት ነገር ነው። ለአገሩ የሚልከው ደግሞ በዛ መልኩ ያገኘውን መረጃ ይሆናል ማለት ነው።
የእርሱ አገር ደግሞ ኢትዮጵያን የሚያውቋት እሱ በላከው ሪፖርት ነው። ያ ሪፖርት ጥሩ ካልሆነ እንዲሁም ኢትዮጵያን በጥሩ ገጽታ የማያስቀምጣት ከሆነ ገጽታዋ በእነርሱ ዘንድ ጥሩ አይሆንም ማለት ነው። ስለዚህ ይሄ የራሳችን ስህተት ነው፤ በአሁኑ ወቅት በምዕራቡ ዓለም የሚንጸባረቀው ችግር ላይ የራሳችንም ስህተት አለበት።
ምክንያቱም ተገቢውን መረጃ በአግባቡ እስካላገኙ ድረስ ማለት ነው። በዚህ ጉዳይ ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች ያፈስፈልጋሉ ማለት ነው፡፡ልክ በውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲ እንደሚሰራ ሁሉ የፕረስ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል እላለሁ። ይህን ሳየው ድክመት ያለ ይመስለኛል።
ይህን አይነቱን አካሄድ ሳየው በቀደመው ጊዜ የነበረው ጥረት ብዙ ነበር ያሰኘኛል። ሰዎች በጣም ይጥሩ ነበር። አብረውኝ ይሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች ምን ያህል ይደክሙ እንደነበር አስታውሳለሁ። ሌላው በቀደመው ጊዜ የአስተያየት ጽሑፍ ነበር። አሁን ይህ የለም ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ በእንግሊዘኛ የሚጻፍ የአስተያየት ጽሑፍ የለም። ጋዜጠኛው ራሱ ዝም ብሎ ዜና መጻፍ ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ የአስተያየት ጽሁፍ መጻፍ ይገባዋል።
አሁን ዲፕሎማሲያችን ‹‹ወደቀ›› የተባለው አንድም በዛ ነው። ቋንቋ የሚችል ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ በእንግሊዝኛ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለምን አይጽፍም? በእርግጥ የምዕራባውያን ጋዜጠኝነት የመረጃ እጦት የለበትም፤ የእነርሱ ጋዜጠኝነት በርዕዮት ዓለምና በምዕራቡ ዓለም ጥቅም ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው እንጂ መረጃ የማጣት ጉዳይ አይደለም። ቢሆንም ቅሉ የእኛ ጋዜጠኞች በቂ መረጃ ማቅረብ አለባቸው። እሱ ሳይሆን ቀርቶ የእኛ ጋዜጠኞች የሚጽፉት አነስተኛ ከሆነ ለውጪው እንዴት አድርጎ ነው የሚደርሰው? ስለዚህ አንዱም የራሳችን ችግር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ጋዜጦችን በመዲናችን አዲስ አበባ አላገኛኋቸውም ብለውኛል፤ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ማዕረጉ፡– ላለመኖራቸው ምክንያት የሚመስለኝ ስሕተት መስራት ነው፤ ምክንያቱም ጋዜጦቹ ከታተሙ መዳረስ አለባቸው። ጋዜጦቹ የሚገኙት አራት ኪሎ ብቻ ነው፤ ምሳሌ የእኔ መኖሪያ ከአራት ኪሎ በብዙ ርቀት ላይ ቢሆን ጋዜጣ ለመግዛት ብዬ አራት ኪሎ ድረስ ለመሄድ አልችልም። ነገር ግን ጋዜጣ ገዝቶ ማንበብ ደግሞ እፈልጋለሁ፤ ሳስበው የትራንስፖርቱ ሁኔታና ርቀቱ ይታየኝና እተወዋለሁ። ስለዚህ ይህ ‹ምናለ በከተማው ውስጥ በየቦታው ስርጭቱ ቢኖር› የሚያሰኝ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚያሳትማቸውን ጋዜጦች ወደተለያዩ ክልል ከተሞች ያደርሳል፤ በአዲስ አበባ ከተማም የማሰራጫ ሱቆች አሉት።ይሄ በቂ ላይሆን እና ስርጭቱም አነስተኛሊሆን ይችላል። ለዚህ ታድያ መፍትሄው ምን መሆን አለበት.?
አቶ ማዕረጉ፡- በእርግጥ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል የሆንኩት ገና በቅርቡ ነው፤ ድርጅቱን የመጎብኘት እድል አግኝቻለሁ። እየሰራ ያለው ስራ ይበል የሚያሰኝና የሚበረታታ ነው፤ በተለይ ደግሞ በተለያዩ ቋንቋዎች እያሳተማቸው ያሉ መጻሕፍትን አይቼ ተደንቄያለሁ። ከዚህ ጋር ደግሞ የጋዜጦች ማከፋፈያ ማዕከላት ማቋቋም በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የሕትመት ሚዲያ ከብሮድካስቱ የሚለይበት ብዙ መንገድ አለ። ሁለቱም የየራሳቸው ጥቅም አላቸው። የየራሳቸው ድክመትም አላቸው። የሕትመት ሚዲያው የሕትመት ውጤቱን መግዛቱ፣ መሸከሙ ብሎም ማንበቡም ከባድ ስለሆነ ውጣ ውረድ አለው። ስለዚህ የብሮድካስቱ ደግሞ በቀላሉ መስማት ያስችላሉ፤ ነገር ግን ቀሪ መረጃ በእጅ ላይ አይኖርም። ስለዚህ ፕሬስ ተጽዕኖ ሊኖረው የሚችለው ሁለቱ አንድ ላይ ሲሆኑ ነው። እውነት ለመናገር ጋዜጣ ለማሳተም መንግስት ብዙ ገንዘብ እንደሚያወጣ አያለሁ። ፕሬስ እያቀዳቸው ያሉ ትልልቅ እቅዶች አሉት፤ ከዚህም ውስጥ አንዱ ማተሚያ ቤት እንዲኖረው ይፈልጋልና ይህ ትልቅ ስራ ነው። ስለዚህ የጋዜጣ ማሰራጫ ጣቢያዎችም ያስፈልጉታል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ጋዜጠኝነት እንደሙያ ነጻ ነው ሲባል ምን ማለት ነው? በእርግጥ ምዕራቡ ዓለም እንደሚለው ነጻ ሊባል የሚችል ጋዜጠኝነት አለ?
አቶ ማዕረጉ፡– ጋዜጠኝነት በምዕራቡ ዓለም እንደሚባለው ነጻ ነው ለማለት ያስቸግራል። በመጀመሪያ ደረጃ ምዕራቡና እኛ የተለያየን ነን። በኢኮኖሚ፣ በባህልም ሆነ በታሪክ እንለያያለን። ለእነርሱ ትልቅ የተባለ ጉዳይ ምናልባት ለእኛ ያን ያህል ላይሆን ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ እኛ ትልቅ ጉዳይ የሚመስለን ነገር ለእነርሱ ምንም ላይሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ሁሉም ነገር ከእድገት ጋር ይሄዳል። እድገት የሚባለው ደግሞ ወደድንም ጠላንም በምዕራቡ ዓለም አስተሳሰብ የተቃኘ ነው። እድገት የሚለካው በኢኮኖሚ፣ በትራንስፖርት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በእነዚህ መሰል ነገሮች ነው እንጂ በታሪክና በባህል አይደለም።
ስለጋዜጠኝነት ከተነሳ በጣም ሳቢ የሆነ ጉዳይ አለ፤ ይኸውም የእኛ ጋዜጠኝነት አገር በቀል መሆኑ ነው። እንደሚታወቀው ብዙዎቹ የአፍሪካም ሆኑ የኢስያ አገሮች ጋዜጠኝነትን ያገኙት ከቅኝ ገዥዎቻቸው ነው። ለምሳሌ ኬንያን ብትወስጂ በጣም ደረጃውን የጠበቀ ጋዜጣ አላቸው። እነዚህ በምዕራቡ ዓለም የሚቃኙ ናቸው። እንደዛ ሊሆን የቻለው ምዕራባውያኑ (ቅኝ ገዥዎቻቸው) ሲወጡ ጥለውት የሄዱት መሰረት ወይም ሌጋሲ ነው። እነርሱም በቅኝ ግዛት ውስጥ ስለነበሩ ያቺኑ አስቀጥለው መሄድ ቻሉ፡፡
አሁን የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነትና የምስራቅ አፍሪካም ሆነ የምዕራብ አፍሪካ ጋዜጠኝነት የተለያዩ ናቸው። እኔ እንዳጋጣሚ ናይሮቢ ሔጃለሁ፤ ኢስት አፍሪካን ስታንዳርድን አንብቤዋለሁ፤ አይቻዋለሁ። ‹‹The Press of Africa: Persecution and Perseverance›› የዚህ መጻሕፍ ጸሐፊ የሚለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ከሌላው አፍሪካ ጋር የሚስተካከል አይደለም። ለዚህ ደግሞ በምክንያነት የሚያስቀምጠው የጃንሆይን ታሪክ ብቻ ነው ይዞ የሚወጣው የሚል ነው። ይህን ያለው ደግሞ እኔ የጻፍኩትን አርቲክል ወስዶ ነው። ይሁንና ለዛ አርቲክል እውቅና ሳይሰጠው በመጻሕፉ ላይ ያቀረበው ራሱ እንደጻፈ አይነት አድርጎ ነው፡፡አርቲክሉን የጻፍኩት እኔ ስሆን፣ የወሰደውም እንግሊዝ አገር ከሚታተም አንድ መጽሔት ላይ ነው። አርቲክሉን ሲወስድ ምንም እንኳ ጸሐፊው ማዕረጉ ነው ባይልም በተወሰነ መልኩ ብቻ ስሜን ጠቅሶታል።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ አተያይ በአሁኑ ወቅት ያሉ ጋዜጠኞች ነጻ ሆነው መስራት የሚያስችላቸው መደላድል አለ ብለው ያስባሉ?
አቶ ማዕረጉ፡- ነጻነት አንጻራዊ ነው፤ ፍጹም የሆነ ነጻነት የለም። ይህ በምዕራቡም ዓለም ቢሆን ማለት ነው። ምክንያቱም አንድ ጋዜጠኛ በሚሰራው በድርጅቱ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ መሰረት የማይጽፍ ከሆነ ይከሰሳል። ከፍ ያለ የገንዘብ ቅጣት ሊጣልበት ይችላል፤ ከስራም ሊባረር ይችላል። ስለዚህም ፍጹም የሆነ ነጻነት የለም። ስለዚህ ነጻነት ሲባል አንጻራዊ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ያለው የፖለቲካው ተጽዕኖ ብቻ አይደለም። የባህልም የታሪክም ተጽዕኖ አለ። ስለዚህም ነጻነት የሚገደበው በብዙ መልክ ነው። ከዚህ ባሻገር ጋዜጠኝነት ሲባል በራሱ እንደ ሙያ ብስለት ያስፈልገዋል። ለምሳሌ በፖለቲካው ጉዳይ የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመውሰድ መተንተን ይቻላል ብዬ አስባለሁ። ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ የሚሰራ ጋዜጠኛ እምብዛም አላይም፤ ለምሳሌ አንድ ጋዜጠኛ ስለአንድ ነገር ለመጻፍ ሲነሳ ስለጉዳዩ በአግባቡ መረዳትና ማወቅ ይገባል፡፡
ለምሳሌ ከሁለት ዓመት በፊት ባጋጠመን ጦርነት ላይ በምዕራቡ ዓለም የነበረን ምስል መንግስት ራሱ ጦርነቱን እንደጀመረው ተደርጎ ሲወራ ነበር። በእርግጥ ይህ የሆነው በአንድ በኩል ጠንካራ የሆነ የሚዲያም ድጋፍ ስለሌለ ነው። ለአብነት ያህል በሔራልድ ትክክለኛውን ዜና መጻፍና እውነታውን ማሳወቅ የግድ የሚል ነው። ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሲመጣ ደግሞ እንግሊዝኛ ቀድሞውኑ የታለና ነው ? በኛ ዘመን እንግሊዝኛ የሚነገረውም የሚጻፍበትም ከአማርኛ ጋር እኩል ነው። ለምሳሌ አንድ ወረቀት በአንድ ሰው እጅ ላይ የሚታይ ከሆኑ ከፊት ለፊቱ አማርኛ ካለ ከጀርባው እንግሊዝኛ ነው። በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝኛ የሚጽፍ ሰው የለም ማለት ያስደፍራል። እኔ ለረጅም ዓመት አርታኢ ሆኜም ስለቆየሁ አማርኛም ሆነ እንግሊዝኛ ሲሳሳት በጣም አዝናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ያሉ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው ማለት ይቻላል? ያሉበትስ ደረጃ ምን ላይ ነው ይላሉ?
አቶ ማዕረጉ፡- ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ እኔ እርካታ የለኝም። ብዙ ሊሰራ እንደሚችል እገምታለሁ። ቀደም ሲል ጥቂት ሰዎች በትንሽ ትምህርት ብዙ ነገር መስራት ችለዋል ብዬሻለሁ። በአሁኑ ወቅት ግን ከዩኒቨርሲቲ ወጣሁ የሚለው ሰው ብዙ ነው። በርካታ የተመቻቸ ነገርም አለ፤ ቴክኖሎጂው በራሱ የሚያግዝ ነው። በእኛ ጊዜ የጋዜጣውን ዲዛይን መስራቱ በራሱ በጣም ከባድ ነበር። እኔ ለምሳሌ አዲስ ዘመን ላይ አንድ ትልቅ ነገር የሰራሁት ዳሚውን (የጋዜጣውን ገፅታ ወረቀት ላይ መሰራት) የማስተምረው እኔ ነበርኩ። ምክንያቱም እኔ ዳሚ የተማርኩት ስኩል ኦፍ ጆርናሊዝም እንግሊዝ አገር ነው። አሁን ግን ዳሚውን መስራት በጣም ቀላል ነው፤ ምክንያቱም የሚሰራው በኮምፒውተር ነው። እንደዚያም ሆኖ ፎቶግራፍ ያለካፕሽን (መግለጫ) ይወጣል። መግለጫ የሌለው ፎቶ ደግሞ ምንም ትርጉም የለውም።
በብሮድካስት ሚዲያው ላይ የማየው ችግር አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የጋዜጠኛው የእውቀት ጥልቀት ችግር ነው። ሁሉንም ማለቴ ግን አይደለም። እውቀት ያላቸው ስለሚሰሩት ስራ ባለሙያ ናቸው እስከሚያስብል ድረስ የሚያውቁ አስደናቂ የፕሮግራም አዘጋጆች አሉ። ስለዚህ ጥረት ነው የሚያስፈልገው።
አዲስ ዘመን፡- የምዕራባውያን ትልልቆቹ ሚዲያዎች የአገራቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ ለአገራቸው ወግነው ይቆማሉ፤ ከዚህ አንጻር በአገራችን ላይ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ ይታያል፤ በኢትዮጵያ ያሉ ሚዲያዎች አገራቸውን ከማስበለጥና ከማዳን አኳያ ስራቸው ምን ይመስላል?
አቶ ማዕረጉ፡- ይህ በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው፤ በእውነት ከሆነ የሚያሳዝነኝ ነገር እሱ ነው። ከዚህ አኳያ በበቂ ሁኔታ አይሰሩም። ለምሳሌ የሰሜኑ ጦርነት በሚገባ አልተገለጸም። ለዚህ ደግሞ ዋናው ችግር ቋንቋ ካለማወቅ ነው። ሌላው ደግሞ በሕትመት እና በብሮድካስቱ ሚዲያ መካከል ቅብብሎሽ መኖር አለበት። በሕትመት ሚዲያው አንድ ጥሩ አርቲክል ከተጻፈ አርቲክሉ በብሮድካስት ሚዲያም መተላለፍ አለበት። በተመሳሳይ በብሮድካስት ሚዲያው ጥሩ ውይይት ከተደረገ ውይይቱ በሕትመት ሚዲያው እንዲሁ መጻፍ አለበት። ይህ ቅብብሎሽ የለም፤ ቢኖር ጥሩ ነው። ይህ ግን የሚጠቅመው ጥልቀት ያለው ጽሑፍ የሚጽፉ ጋዜጠኞች ሲኖሩ ነው፤ ከሌሉ ግን የውጭ ሰው እንዲጽፍ ማድረግ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት የመገናኛ ብዙኃኑን በነጻነት እንዲሰሩ እያደረገ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ማዕረጉ፡- አገራችን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በመመራት ላይ ትገኛለች፤ መንግስት ደግሞ አንድ ዓላማ አለው። ይኸውም ልማትና አገርን ማሳደግ ነው። ኅብረብሔርነትን መያዝ ነው፤ ምክንያቱም አገሪቷ ከዚህ አንጻር ብዙ ፈተና አለባት። እነዚህን የመንግስት ዓላማዎች የሚቃወም ሚዲያ እስካልሆነ ድረስ የሚዲያዎቹን ሐሳብ የሚገድብ መንግስት አይመስለኝም። በእርግጥ ይህንን ለማወቅ ውስጡ መሆን ይገባል። ከዚህ አኳያ የብሮድካስቱ ላይ እንደማየው የሚጠየቀው ጥያቄ ብዙ ሊያናግር የሚችል ነውና የነጻነት አለመኖር ችግር ያለ አይመስለኝም።
የነጻነት ችግርማ በእኛ ጊዜ ነበር። በጃንሆይ ጊዜ ብዙ ነገሮች ነበሩ። እያንዳንዱ ሚኒስትርም ሆነ ጄነራል አኩራፊ ነው። ጠርቶ ለምን ሆነ የሚል ነው። በደርግም ጊዜ ቢሆን እንዲሁ ነው፤ ያስፈራል። በአሁኑ ወቅት ግን እንዲህ አይነት ነገር አለ ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ነጻነቱ አለ። መነጋገር የሚገባው ያለውን ነጻነት መጠቀም ያለባቸው እንዴት ነው በሚለው ላይ ነው። ለምሳሌ መጻሕፍት እየታተመ ነው፤ ነገር ግን ቅድመ ግምገማ የሚባል ነገር የለም። ስለሆነም ነጻነቱ አለ።
አዲስ ዘመን፡- የሽግግር ወቅት ላይ ከመሆኑ አንጻር አሁን ያለውን ሁኔታ የሚገመግሙት እንዴት ነው?
አቶ ማዕረጉ፡- ይህ የመረጃ ጉዳይ ከባህልም ጋር የተያያዘ ነው። ዋናው ምክንያት ፖለቲካ ነው። ምክንያቱም አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰራ ሰው በራሱ ፈቃድ ተነስቶ ስለመስሪያ ቤቱ ወይም ስለ አንድ ጉዳይ ለመግለጽ ይፈራል። የበላይን ይፈራል። በሌላ በኩል ደግሞ እንደባህል የተያዘ ነገር አለ፤ ፊት ለፊት መነጋገርና መወያየት ብዙ አላዳበርንም፤ ከኋላ በሐሜት መልክ ነው የሚቀርበው። ስለዚህ ሰው ለቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ አይሆንም።
የአሁኑ ትውልድ ባለስልጣናቱ ማለቴ ነው በነጻነት መናገር አለባቸው፤ ግን ባህሉ እየጎተታቸው ነው፤ ሲጠየቁ እንዲያው ደስ ሊላቸው ይገባል፤ ምክንያቱም የሰሩትን ስራ ነው የሚናገሩት፤ ግን ባህል ሲጎትታቸው ይታያል፤ በአጼ ኃይለስላሴ ጊዜም ቢሆን በደርግም ጊዜ በጣም ከባድ ነበር፤ በኢህአዴግም እንዲሁ ነው፤ ማን ፈቀደልህ ይባላል፤ ሳትታዘዝ እንደፈለክ መፈንጨት አትችልም ይባላል፡፡
ከዚህ አይነት አካሄድ መውጣት የሚቻለው በማደግ ነው፤ ቴክኖሎጂው ሲያድግና ትምህርት ሲስፋፋ የሚመጣ ጉዳይ ነው። በመጀመሪያ በየቦታው ሕዝብ ውይይት ሲያደርግ ነው። አንዳንዴ ውይይቶች አሉ፤ የተወሰነ ቡድን ብቻ ከመጋበዝ ደግሞ እንደእኔ አይነቶችም አሉና ብንጋበዝ የምናበረክተው ነገር ይኖራል። ውይይቱ ሲስፋፋ ያንን ለመሸፈን ይሰራልና ሚዲያም ያድጋል።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ ከምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ የነበረው ተጽዕኖ ገሃድ የወጣ ነው፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ የምዕራቡ ዓለም የተቀናጀ ዘመቻ ነበርና ይህን እርስዎ እንዴት ነበር ያዩት?
አቶ ማዕረጉ፡- ይህ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፤ በምዕራቡ ዓለም ነጻነት አለ ይባላል፤ ነገር ግን የሚገዛቸው ነገር አለ፤ ነጻ ነን ይበሉ እንጂ ከምዕራቡ አስተሳሰብ ነጻ ሊሆኑ አይችሉም። ዓለም በምዕራቡ ዓለም ሞኖፖሊ እንዲሆን ለማድረግ የተደረገ ዘመቻ ባለፈው 50 እና 60 ዓመት በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ የምዕራቡ ሚዲያ የጦርነት አይነት ሚዲያ ነው።
የምዕራቡ ፍልስፍና፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የምዕራቡ የፖለቲካ ስርዓት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ስርዓት እንዲኖር አይፈልግም። እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ብቅ ሲሉ የሚደነግጡት ለዚህ ነው። ለምሳሌ አሁን ያስደነገጣቸው በኢትዮጵያ ያለው የአሁኑ መንግስት ነጻ ሆኖ ማሰብ የሚችል ነው። በነጻነት የሚያስብ፤ በነጻነት የሚሰራ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ከኋላ የሚያዝዘው ምንም የሌለው ነጻ የሆነ መንግስት ነው።
ምዕራባውያኑ ጠንካራ መንግስት እንዲኖር አይፈልጉም። ስለዚህም በመንግስት ላይ ትልቅ ትግል ሲያካሄዱ ነበር እንጂ የሕወሓት መሪዎች እነርሱን ስለሚጠቅሟቸው አይደለም፤ እንደማይጠቅሟቸውም ያውቃሉ። ጫናው የመጣውም ነጻ የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት ቀና ብሎ መሄድ ሲጀምር ወዴት እየሄደ ነው ከሚል ስጋት ነው፤ ምዕራባውያኑ መጫን የሚሹት ያቺኑ የእነርሱን አስተሳሰብ ነው፤ ከስሜት ነጻ የሆነ ዜና ወደዓለም እናደርሳለን የሚል አስተሳሰብ ይዘው የተነሱ ቢሆኑም ከስሜትና ከራስ ጥቅም የጸዳ አይደለም። ሌላው ቀርቶ ጦርነቱን የጀመረው ሕወሓት እንደነበር እንኳን በወቅቱ አለመግለጻቸው አንዱ ማሳያ ነው። ለምሳሌ ይህ ትልቅ ጉድለት ነው። ከእኛ ውጪ ምንም አስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም አይኑር ባዮች ናቸው። ኢትዮጵያ የምዕራቡ ዓለም መራኮቻ አይደለችም። ይህን እያወቁ መጥተዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል አራት ዓመት ሙሉ ነጻ የመሆንና የማደግ ጥረቱ አለ፤ በአሜሪካ ለሽልማት ድረስ እንዲበቁ ያደረጋቸው እሱም ጭምር ነው። የዚህ መንግስት ችግሩ በጣም ሩህሩህነት እና ደግነቱ ነው። ከዚህ በኋላ ጠንክሮ መስራትና ኢኮኖሚውንም ማሳደግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ማዕረጉ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 /2015