ኢትዮጵያ የብዙ ሺ ዓመታት የዳበረ ታሪክና ሀብት ባለቤት ነች፤ የሰው ዘር መገኛ እና የሰው ልጆች ስልጣኔ መነሻ፤ የአትንኩኝ ባይነትና የነጻነት ፋና ወጊ መሆኗም የአደባባይ ምስጢር ነው።
ይህንን በሚቃረን መልኩም ለዘመናት እንደ ሀገር የግጭትና የጦርነት፤ ከዚህ የሚመነጭ የድህነትና የኋላቀርነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትወሰድ፤ በዚህም ከፍ ያለ ዋጋ ለመክፈል የተገደደች ሀገር ነች።
ግጭትና ጦርነት ፣ ኋላቀርነትና ድህነት የቀደመ ታሪኳን ያሳደፉባት፣ ሕዝቦቿንም አንገት አስደፍተው በዓለም አቀፍ መድረኮች ሙሉ በሙሉ ቀና ብለው እንዳይጓዙ ተግዳሮት የሆነባት ሀገርም ነች።
እንደ ሀገር የቀደመውን ታሪኳን በተሻለ ደረጃ ማስቀጠል ቢያቅታት ፤ የነበረውን ይዛ መጓዝ አለመቻሏ ለብዙ ትውልዶች ጥያቄ የሆነ ፣ በዚህ ትውልድ አዕምሮም የሚመላለስ ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ ነው።
ለዚህ ደግሞ ዘመናት ያስቆጠረው በመንግስትና በሕዝብ አስተዳደር ሥርዓቷ ውስጥ ሰርፆ የገነገነው፣ ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህላችን በዋንኛነነት ተጠቃሽ እንደሆነም የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
በሴራ፣ በጥላቻና በመጠላለፍ ላይ የተመሰረተው ይኸው የፖለቲካ ባህላችን ዛሬም ቢሆን ሀገርን እንደ ሀገር ከፍ ያለ ዋጋ እያስከፈለ ስለመሆኑ፤ ችግሩን ፈጥኖ ማረም ካልተቻለ በቀጣይ የሀገር ህልውና ስጋት የሚሆንበት ደረጃ ሊደርስ እንደሚችልም ይታመናል።
በአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት ላይ የተመሰረተው ለዘመናት የኖረ ቆሞ ቀር የፖለቲካ ባህል ፤ የቀጣይ ሀገራዊ እጣ ፈንታችን ላይ እያጠለለ ያለው ጽልመት ባለፉት አራት ዓመታት/ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገርን በብርቱ ሲፈትን የተስተዋለ ነው።
በእርስ በርስ ጦርነት አንዱ አንዱን ገድሎ፤ካልሆነም አስገብሮ መንግስት የመሆን መቶዎች ዓመታትን ያስቆጠረው ይሄው ባህላችን በቀደሙት ትውልዶች ደም ነፍስ እንደዘራ ሁሉ፤ የዛሬውን ትውልድ ደም የመጠየቁ እውነታም በእነዚህ ዓመታት ታይቷል፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞቻችን የዘመናዊ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ የባለ ብዙ ክብር ባለቤት በሆኑበት ሀገራዊ እውነታ አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ከዚህ ኋላ ቀር እና ቆሞ ቀር የፖለቲካ አስተሳሰብ አለመላቀቃቸው ለተራው ሕዝባችን ሳይቀር አጠያያቂ ነው።
አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ከዚህ ትውልድ ተሻጋሪ ችግር ራሳቸውን ከመታደግ ይልቅ አስተሳሰቡ ተጨማሪ የጥፋት አቅም እንዲያገኝ ዘር እና ሀይማኖትን የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ አድርገው መምጣታቸው፤ በሀገሪቱ ቀደምት ችግሮች ላይ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” ሆኗል፤ እያስከፈለ ያለውም ዋጋ የብዙ ዜጎችን ልብ የሰበረ ነው።
በርግጥ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ህሳቤ መሰረቱ የሕዝብ ፍላጎት እንደሆነ ይታመናል፤ከዚህ አንጻር አንዳንድ ፖለቲከኞች ቢያንስ ቢያንስ ህዝባችን ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ይዞት ለተነሳለትና ብዙ ዋጋ ለከፈለለት መሻቱ ተገዥ መሆን ነበረባቸው።
ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ሀገርና ሕዝብን በትውልዶች መካከል ብዙ ዋጋ ካስከፈለውና እያስከፈለ ካለው የሴራ፣ የጥላቻና የመጠላለፍ ቆሞ ቀር ኋላቀር ፖለቲካ ራሳቸውን ማራቅ ፤ከዚህ አጥፊ የፖለቲካ ጉዞ ራሳቸውን ማቀብ፤ ለዚህም የሚሆን ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው።
ይህን ለማድረግ ደግሞ አስተሳሰቡ በዘመናት መካከል የቱን ያህል ሀገርን ዋጋ እንዳስከፈለ ፤ ከነበርንበት የከፍታ ስፍራ የቱን ያህል ለዝቅታ ጫፍ እንዳደረገን በነጻ አእምሮ፤ ከፍ ባለ ሕዝባዊ መንፈስ እና ኃላፊነት በአግባቡ መረዳትና የጠራ ግንዛቤ መፍጠር ይፈልጋል።
ኋላ ቀር የፖለቲካ አስተሳሰብ መልኩን እየቀያየረ ዛሬም ዋጋ እያስከፈለን መሆኑንና በዝምታ ካስቀጠልነው መጪውን ትውልድ ተመሳሳይ ዋጋ ሊያስከፍል፤ ከከፋም ሀገርን ለአደጋ ሊዳርግ እንደሚችል አርቆ ማሰብን ይጠይቃል።
ችግሩ ስልጣንና ከስልጣን የሚመነጭን ተጠቃሚነት፤ ከሕዝብና ከሕዝብ ፍላጎት፤ ከትውልድና ከትውልዶች የተሻለ እጣፈንታ አሳንሶ የማየትና በተጨባጭም ያነሰ መሆኑን በተግባር አሳይቶ መገኘት፤ በዚህም ታሪክን ጽፎ ማለፍን የሚጠይቅ ነው!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 /2015