በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በአንድ ወቅት ብቅ ብለው የስፖርት ቤተሰቡን ጮቤ ካስረገጡ ታላላቅ የእግር ኳስ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነው። ከአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጫዋችነት እስከ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ድረስ ስኬታማ ታሪኮችን ያስመዘገበው ዝነኛው የእግር ኳስ ጥበበኛ መንግሥቱ ወርቁ ከ12 ዓመታት በፊት ታኅሳሥ 6 ቀን 2003 ዓ.ም ነበር ከዚህ አለም በሞት የተለየው። የአለም ሕዝብ በኳታሩ አለም ዋንጫ አስደናቂ ክስተቶች ተስቦ እግር ኳስ ከትንሽ እስከ ትልቁ መነጋገሪያ ሆኖ በገነነበት በዚህ ወቅት እኛም ከተለያዩ ምንጮች ባገኘነው መረጃ ኢትዮጵያዊውን የእግር ኳስ አርቲስት በዝነኞች ገጽ ልናስታውሰው ወደድን።
መንግሥቱ የተወለደው በ1932 ዓ.ም በቀድሞው በጌ ምድር ጠቅላይ ግዛት፣ ቋራ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነው:: ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስም ‹‹አሻግራቸው›› ነበር:: አባቱ ፊታውራሪ ወርቁ ስንቄ ፀረ-ፋሺስት አርበኛ ስለነበሩና ለፋሺስት ኢጣሊያ ባለስልጣናት በማስቸገራቸው አባቱን ለመያዝ በማሰብ ሕፃኑ አሻግራቸው ወርቁ ከእናቱ ከወይዘሮ እማዋይሽ አብተው ጋር ታሠረ:: ‹‹አሻግራቸው›› የሚለው ስሙ ወደ ‹‹መንግሥቱ›› የተለወጠው ከእናቱ ጋር ታስሮ በነበረበት ወቅት በፋሺስቶች ቢሆንም እንዴት እንደተለወጠ የሚገልፁት መረጃዎች ግን ሁለት ዓይነት ናቸው::
አንደኛው የአባቱ የፊታውራሪ ወርቁ ወንድም ፊታውራሪ ዓለሙ በፋሺስቶች ከተያዙ በኋላ ፋሺስቶች ፊታውራሪ ወርቁ ወንድማቸውን በጣም ይወዱ እንደነበር ስለሰሙ “ወንድምህን እንድንለቀው ከፈለግህ መጥተህ እጅህን ስጥ:: አለበለዚያ በወንድምህ ላይ አደጋ ይደርሳል›› የሚል መልዕክት ላኩባቸው:: ፊታውራሪ ወርቁም እጃቸውን ሰጥተው ወንድማቸውን ካስፈቱ በኋላ ከእስር ቤት አምልጠው ስለጠፉ ፋሺስቶች ‹‹መንግሥቱን (ንጉሰ ነገሥቱ በስደት እየኖሩና አገሪቱ በጠላት ኃይል እየተገዛች ስለነበር) ሊፈልግ ነው ያመለጠው›› ብለው ሕፃን አሻግራቸውን ‹‹መንግሥቱ›› አሉት የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‹‹በልጅነቱ ከእናቱ ጋር በእሥር ላይ የነበረው አሻግራቸው ጣሊያኖች ሁኔታውን ዐይተው ‹አንተ መንግሥት ለመሆን ነው የምትፈልገው› በሚል ‹መንግሥቱ› ብለው ስም እንደሰጡት የሚገልፅ ነው:: የሆነው ሆኖ ‹‹አሻግራቸው›› የሚለው ስሙ እየተረሳ በ‹‹መንግሥቱ›› እየታወቀ ሄደ:: መንግሥቱም ‹‹እንዴት ፋሺስት ባወጣልህ ስም ትጠራለህ?›› ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ስሜ የኢትዮጵያዊ እንጂ የፋሺስት ስም አይደለም፤ እንዲያውም ስሜ የአባቴን ሙያ ያስገነዝበኛል›› ብሏል::
የትምህርት ቤት ቆይታው
የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ድል ሆኖ ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ መንግሥቱ የቅኔ ትምህርት ቤት ገብቶ ዳዊት ደግሟል:: ፊታውራሪ ወርቁ ስንቄ ከጠላት ጋር ሲፋለሙ መሞታቸውን በማሰብ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሕፃኑ መንግሥቱ ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በቤተ-መንግስት እንዲቀመጥ አደረጉ:: በ1940 ዓ.ም መድሐኔዓለም ትምህርት ቤት ገብቶ ዘመናዊ ትምህርት መማር ጀመረ:: በዚሁ ትምህርት ቤትም ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተማረ::
መንግሥቱ በአንድ ወቅት ስለ ትምህርት ቤት ቆይታው ሲናገር ‹‹በ … ተማሪ ቤት እያለሁ ተማሪ ሁሉ ዘመዱ ሲጠይቀው እኔ ግን የዘመድ ጠያቂ ባለማግኘቴ እብሰለሰል ነበር:: ግርማዊነታቸው ትምህርት ቤቱን ለመጎብኘት ሲመጡ የ‹‹ወርቁ ልጅ የት አለ›› ብለው አስፈልገው አነጋግረው አስፈላጊውን ሁሉ ፈፅመውልኝ ‹በርታ› ይሉኝ ስለነበር በጣም ደስ ብሎኝ እፅናና ነበር … ›› ብሏል::
በቀለም ትምህርት ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል አንዱ የነበረው መንግሥቱ፣ በትምህርት ቤቱ በሚከናወኑ የስፖርት ውድድሮች (በመረብ ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በሩጫ፣ በእግር ኳስ … በመሳተፍ ሁለገብ ስፖርተኛ መሆኑን አሳይቷል:: በኢትዮጵያ ተማሪዎች መካከል በተደረገ የሩጫ ውድድርም በአንድ መቶ ሜትር ተወዳድሮ አሸናፊ ሆኗል:: መንግሥቱ በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ተሰጥዖ የነበረው ቢሆንም ትኩረት ማድረግ የፈለገው በእግር ኳስ ላይ ነበር::
በአንድ ወቅት ከሌሎች የስፖርት ጨዋታዎች ሁሉ ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር እንዴት እንዳደረበት ተጠይቆም ‹‹ … ከጓደኞቼ ጋር እየሆንን ጢቢ ጢቢ እንጫወት ነበር:: ያለማቋረጥ ብዙ እመታለሁ፤ በኋላ ገንዘብ አዋጥተን ትንሽ ሸራ ኳስ ገዛንና ራስ ኃይሉ ሜዳ እየሄድን ቅዳሜና እሁድ ስንፋተግ እንውላለን:: እንዲህ እዲህ እየተጫወትን ባለንበት ወቅት ሚስተር ሒውዝ የተባሉ የስፖርት መምህራችን ‹‹A››/‹‹B››/‹‹C›› የተሰኙ ቡድኖች አቋቋሙ:: እኔ በሲ ቡድን ውስጥ ተመደብኩ:: በኋላም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ጋር ውድድር ተመሰረተና በሁለት ቁጥር ቦታ እየተጫወትኩ ድሉ የትምህርት ቤታችን ሆነ … በ‹‹C›› ቡድን ጥሩ እጫወት ስለነበር በቀጥታ በቁመትም ሆነ በእድሜ አቻዬ ካልሆኑት ከ‹‹A›› ቡድን አባላት ጋር በአምስት ቁጥር ቦታ ተሰልፌ እንድጫወት ተመደብኩ:: በ‹‹A›› ቡድን ተጨዋች በነበርኩበት ዘመን አከታትለን ቻምፒዮን ሆነናል …›› በማለት የኳስ አጀማመሩንና የመድሐኔ ዓለም ትምህርት ቤት ትዝታውን ገልፆ ነበር::
መንግሥቱ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ
መንግሥቱ የመድሐኔዓለም ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ በአካባቢው ለነበረው የጉለሌ ቡድን ለመጫወት ልምምድ ጀመረ:: በወቅቱ ጉለሌ በኢትዮጰያ እግር ኳስ ያልተመዘገበ የሰፈር ክለብ ነበር:: ታዋቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊ የነበሩት አቶ ቱፋ ሻይና ተጨዋቹ ነፀረ ወልደ ሥላሴ መንግሥቱን ሲጫወት አይተውት ስለነበር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን እንዲገባ አግባቡት:: በተለይ አቶ ቱፋ ደጋግመው ስለጠየቁት ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በ1949 ዓ.ም፣ ክረምት ወቅት የቅዱስ ጊዮርጊስን ቡድን ተቀላቀለ::
በወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ወደ ድሬዳዋ ሄዶ ይለማመድ ስለነበር መንግስቱ ከቡድኑ ጋር አብሮ ተጓዘ:: ቡድኑ ከጥጥ ማህበር ቡድን ጋር ሲጫወት መንግስቱ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ተገደደ:: ያምሆኖ በጨዋታው መንግስቱ ራሱን የሚያሳይበት አጋጣሚ አገኘ። ጥጥ ማኅበር ሦስት ለ አንድ በሆነ ልዩነት እየመራ ቅዱስ ጊዮርጊስም በይድነቃቸው ተሰማ ብቸኛ ግብ እየተመራ በሚገኝበት ሰአት የፈረሰኞቹ አንድ ተጨዋች ተጎዳና መንግሥቱ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ገባ:: ሁለት ግቦችን በማስቆጠርም ቡድኑን ከሽንፈት ታደገው::
በቀጣዩ ጨዋታ ደግሞ መንግስቱ በስምንት ቁጥር መለያ ተሰለፈ:: ቅዱስ ጊዮርጊሥ ስድስት ለ ሁለት በሆነ ሰፊ ውጤት አሸነፈ:: ቅዱስ ጊዮርጊሥና መንግሥቱም ውል አሰሩ። የቅዱስ ጊዮርጊሥ ስምንት ቁጥር መለያ የመንግሥቱ ሆነ:: በዚህ የተጀመረው የመንግሥቱና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ትስስር እየጠነከረ ሄዶ በቡድኑ ታሪክ እስካሁን ድረስ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ባለታሪክ ለመሆን በቃ:: ቅዱስ ጊዮርጊስ ማለት መንግሥቱ፤ መንግሥቱ ማለት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆኑ!
መንግሥቱ ከ1951 ዓ.ም እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተጫውቷል:: በተጨዋችነት ዘመኑ የሌላ ክለብ መለያ አልለበሰም:: ከ1958 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫን፤ በ1965 እና 1966 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ጭሎ ማለፍ ዋንጫን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ጋር አሸንፏል::
የቴክኒክና ሙያ ምሩቅ የነበረው መንግሥቱ ከተመረቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ የተቀጠረው መብራት ኃይል መስሪያ ቤት ውስጥ ነው:: በወቅቱ መብራት ኃይል የእግር ኳስ ቡድን ነበረው:: መንግሥቱ ግን የሚጫወተው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ነበር:: በ1955 ዓ.ም. ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መብራት ኃይል በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ተገናኙ:: ቅዱስ ጊዮርጊስ መብራት ኃይልን አራት ለ አንድ አሸንፎ ዋንጫውን ሲያነሳ ሦስቱን የቅዱስ ጊዮርጊሥ ግቦች መብራት ኃይል ላይ ያስቆጠረው የመብራት ኃይሉ ሰራተኛ መንግሥቱ ነበር:: የመብራት ኃይል ሰራተኞች ‹‹እኛ ዘንድ እየሠራና ደመወዝ እየበላ እንዴት መጫወቻ ያደርገናል?›› ብለው ተቆጡ:: የሰራተኞቹ ተቃውሞ እያየለ ሄዶ የድርጅቱ ኃላፊዎች ‹‹ለእኛ ካልተጫወትክ አቋምህን አሳውቅ›› አሉት:: እርሱም ‹‹ለጊዮርጊሥ መጫወት አላቆምም … ጊዮርጊስንም አልለቅም …›› ብሎ ከመብራት ኃይል መስሪያ ቤት ሥራውን ጥሎ ወጣ::
መንግሥቱ ወርቁ ለሌሎች የእግር ኳስ ክለቦች እንዲጫወት ተጠይቆ ነበር:: ነገር ግን ስምንት ቁጥርንና የ ‹‹V›› ምልክት ያለበትን የቅዱስ ጊዮርጊስ መለያን ጥሎ መውጣትን እንደክህደት ስለቆጠረው የእግር ኳስ ዘመኑን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ብቻ በታማኝነት አገልግሏል:: ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ መንግሥቱ ቅዱስ ጊዮርጊሥን በታማኝነትና በትጋት እያገለገለ ምንም ዓይነት ክፍያ ጠይቆ አለማወቁ ነው:: ስለዚህ ጉዳይ መንግሥቱ በአንድ ወቅት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር …
‹‹ … የሚያጫውትህ የሕዝብ ፍቅር ነው:: ከማልያው ጋር ተዋህጄ ስለነበር ትቼ መሄድ አልፈለግሁም … ደምተህና ተፈንክተህ ቡድኑን እዚህ ካደረስክ በኋላ እንዴት ጥለህ ትሄዳለህ? ስለዚህ ‹ጊዮርጊስ አልከፈለኝም› ብዬ አንድም ቀን እንኳን ገንዘብ ጠይቄ ሰንፌም አላውቅም … ›› … መንግሥቱ ለቅዱስ ጊዮርጊሥ የነበረው ፍቅርና ታማኝነት እንዲህ ያለ ነው::
ከኢትዮጵያ የስፖርት አባት ከይድነቃቸው ተሰማ (ለ23 ዓመታት) ቀጥሎ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ረዥም ጊዜያት በመሰለፍ ሁለተኛ ሰው መንግሥቱ ወርቁ ሲሆን ለ16 ዓመታትም ክለቡን አገልግሏል:: መንግሥቱ በተጨዋችነት ዘመኑ በእግር ኳስ ችሎታውና አብዶ በመስራት በሚያሳየው ጥበብ ተማርከው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው:: እንዲያውም ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ ኃያልና የብዙ ደጋፊ ባለቤት መሆን የቻለው በመንግሥቱ ምክንያት ነው›› ብለው የሚናገሩ ወገኖች በርካታ ናቸው::
የብሔራዊ ቡድን አገልግሎቱ መንግሥቱ ከክለብ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ በመጫዋት እስከዛሬም ድረስ በማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ያልተደፈሩ ክብረ ወሰኖች ባለቤት ለመሆን በቅቷል:: ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መሰለፍ የጀመረው በ1951 ዓ.ም በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው:: በ1954 ዓ.ም ኢትዮጵያ ባስተናገደችው ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩን ኮከብ ግብ አግቢነት ክብርን ከግብፁ መሐመድ በደዊ አብደል ፋታህ ጋር በጋራ ተቀዳጅቷል:: የውድደሩ ኮከብ ተጨዋችም እርሱ ነበር:: ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ አንድ ለእናቱ የሆነውን የአፍሪካ ዋንጫዋን (1954) እንድታሸንፍ ከፍተኛውን አስተዋፅዖ ያበረከተው መንግሥቱ ነበር::
እስከ ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ የብሔራዊ ቡድኑን መለያ ለብሶ አገሩን አገልግሏል:: በአጠቃላይ ከ1951 እስከ 1964 ዓ.ም ድረስ 102 ጊዜ ለብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፎ ተጫውቷል፤ 62 ግቦችን ለብሔራዊ ቡድኑ በማስቆጠር የክብረወሰን ባለቤትም ነበር።
በሀገር ውስጥ ውድድሮች ላይም በርካታ ጊዜያት ኮከብ ግብ አስቆጣሪ መሆን ችሏል:: መንግሥቱ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ እስካሁን ድረስ ብዙ ግብ ካስቆጠሩ አፍሪካውያን ተጨዋቾች መካከል አንዱ በመሆን ከአፍሪካ ኮኮብ ግብ አግቢዎች ተርታ መሰለፍ የቻለበትን ደማቅ ታሪክም መፃፍ ችሏል:: ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በተሳተፈችባቸው የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ከመንግሥቱ በስተቀር ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀና የተሸለመ ተጨዋች የለም::
መንግሥቱ አገሩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ እንድትሆን ቢያደርግም እርካታ አላገኘም:: የአፍሪካ ዋንጫን አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ ለኢትዮጵያ ማስገኘትን አልሞ የነበረው መንግሥቱ፣ ኳስ መጫወት ለማቆም በወሰነበት ወቅት ‹‹ላሳደገኝና ለወደደኝ ሕዝብ ውለታውን ሳልመልስ ከኳስ ተጨዋችነት መገለሌ እየፀፀተኝ ነው:: ነገር ግን አገራችን ጥሩ ተጨዋቾች እንዲኖሯት በአሰልጣኝነትና በአማካሪነት ለማገልገል ከመጣር አልቦዝንም›› ብሎ ተናግሮ ነበር::
የአሰልጣኝነት ሕይወት
መንግሥቱ ከተጨዋችነቱ ባሻገር በአሰልጣኝነት ስራውም ውጤታማ መሆን ችሏል:: በአሰልጣኝነቱ ያስመዘገባቸው ስኬቶች ጎበዝ ተጨዋች በመሆኑ የተገኙ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ የስልጠና ኮርሶችን ወስዶ በአንደኛነት በማጠናቀቁም ጭምር የተገኙ ናቸው:: የእግር ኳስ ችሎታና ልምድ ብቻውን ጥሩ አሰልጣኝ እንደማያደርግ የተረዳው መንግሥቱ፣ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ፊፋና በሌሎች ተቋማት የተዘጋጁ የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን ተከታትሎ አንደኛ በመውጣት ሰርተፊኬት፣ ዋንጫና ሜዳልያዎችን አግኝቷል::
ካሰለጠናቸው ክለቦች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊሥ፣ መብራት ኃይል፣ ኢትዮጵያ መድኅን፣ አየር መንገድ፣
ባንኮች እና ወንጂ ስኳር ይገኙበታል:: ከአዲስ አበባ ከተማ 190 ኪሎ ሜትር እየተመላለሰ ‹‹ሕጻናት አምባ›› ውስጥ የነበሩ ታዳጊዎችንም አሰልጥኗል:: በ‹‹ምርጥ›› ደረጃ ደግሞ ‹‹የአዲስ አበባ ምርጥ››፣ ‹‹የሸዋ ምርጥ›› እና ‹‹የኢትዮጵያ ተስፋ›› ቡድኖችን አሰልጥኗል::
መንግሥቱ የእግር ኳስ ክህሎት ያላቸውን ልጆች የማወቅ ልዩ ተሰጥዖ እንደነበረው የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል:: ክለብ ለማሰልጠን ከመስማማቱ በፊት ከክለቡ ጋር ከፍተኛ ድርድር የሚያደርገው በደመወዝ ጉዳይ ላይ ሳይሆን በሜዳ ላይ ነው:: ቡድኑ የተስተካከለ መለማመጃ ሜዳ እንዲኖረው ግፊት ያደርጋል:: መብራት ኃይልና መድኅን ሜዳ እንዲኖራቸው ያደረገው መንግሥቱ ነው::
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆንም ሀገሩን አገልግሏል:: በአሰልጣኝነት ስራ ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀለው በ1968 ዓ.ም በረዳት አሰልጣኝነት ነው:: ቀጥሎም ዋና አሰልጣኝነቱን በመረከብና በወጣቶች የተገነባ ቡድን በመስራት ኢትዮጵያ ለ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ አድርጓል:: በአፍሪካ ዋንጫ በተጨዋችነት ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቶ በአሰልጣኝነት ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ያሳለፈ ብቸኛው ሰው መንግሥቱ ወርቁ ነበር:: ከአሰልጣኝነቱ በተጓዳኝም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኃላፊ ሆኖ ለአሰልጣኞች ስልጠናዎችን ሰጥቷል፤የቴክኒክ ኮሚቴን አዋቅሯል:: የክለቦችን ሥልጠና በንቃት ተከታትሏል::
መንግሥቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢንስትራክተር (የአሰልጣኞች አሰልጣኝ) ነው:: የአፍሪካ የእግር ኳስ አሰልጣኞች አሰልጣኝ በመሆን በናይጄሪያ፣ በታንዛኒያ፣ በኡጋንዳ እንዲሁም በስዋዚላንድ በመዘዋወር ለአሰልጣኞች ስልጠናዎችን ሰጥቷል:: በርካታ ተተኪ አሰልጣኞችንም አፍርቷል:: መንግሥቱ በኤርትራና በሱዳንም ከፍ ያለ ዝናና ተወዳጅነት ነበረው::
መንግሥቱና ‘ስምንት’ ቁጥር መንግሥቱና ‘ስምንት’ ቁጥር የተዛመዱ ናቸው:: ‹‹መንግሥቱ ወርቁ›› የሚለውም ስም ስምንት ፊደሎች አሉት:: ክለቡ ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ››ም ባለስምንት ፊደል ነው:: የሚቆርጠው ሎተሪና የሚነዳው መኪና የመጨረሻ ቁጥራቸው እንዲሁም ለክለብም ሆነ ለብሔራዊ ቡድን ሲጫወት የሚለብሰው የመለያ ቁጥር ስምንት ነበር:: በባህርይው ኮስተር ያለ (ቁጡ) እንደነበር የሚነገርለት መንግሥቱ፣ ‹‹በባህሪዬ ቁጡ ነኝ፤ አኩራፊም ነኝ:: አሁን እድሜዬ በመግፋቱ ሁሉንም ትቻለሁ:: ግን ኳስ ተጨዋች ለመሆን በትንሹ ቁጡ መሆን ያስፈልጋል›› ብሏል::
ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ካፈራቻቸውና ካየቻቸው ታላላቅ የእግር ኳስ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆነው፤ ለቅዱስ ጊዮርጊስና ለሌሎች ክለቦች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባከናወናቸው ዘመን አይሽሬ ወርቃማ ተግባራት አሁንም ድረስ በበርካታ አድናቂዎቹና የእግር ኳስ ቤተሰቦች ዘንድ ልብ ውስጥ ላቅ ያለ ቦታ ያለው ወርቃማው የእግር ኳስ አርቲስት መንግሥቱ ወርቁ፣ የጤና እክል አጋጥሞት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ፣ ታኅሣሥ 06/ 2003 ዓ.ም ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2015