ልጆችን ከባድ ከሆነ በሽታ ለመከላከልና ከሞት ለመታደግ ክትባት ቀላሉ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ዘዴ መሆኑን ሁሉም ሰው መረዳት ይኖርበታል። ሁሉም ክትባቶች ለልጆች እንደ የእድሜያቸው በነፃ የሚሰጥ ሲሆን ልጆች ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ በሽታን አስቀድሞ የመከላከያ አቅማቸውን እንዲያዳብሩ ወሳኙ ዘዴ ነው። በመሆኑም ወላጆች ይህንን በመረዳት ልጆችን ማስከተብ አገርንም ወገንንም ማገዝ መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል።
ለዓለምም ሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት የሆነው የኩፍኝ በሽታ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ክልሎች በወረርሽኝ ደረጃ ተከስቷል። በተለይም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባም በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በወረርሽኝ መልክ በመታየት ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት በወቅቱ ካልተወሠደ በሽታው በፍጥነት ከልጅ ወደ ልጅ የሚዛመትና እስከ ሞት የሚደርስ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ክትባቱ በዘመቻ መልክ በመሰጠት ላይ ይገኛል ። በመሆኑም ሁሉም ኅብረተሰብ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት እና የክትባቱን አስፈላጊነት በመገንዘብ ሕጻናቱን ማስከተብ አለበት።
አገራችንም እንደ ፖሊዮና ኩፍኝ እንዲሁም ሌሎቹን በሽታዎች ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ከመደበኛው የክትባት ፕሮግራም በተጨማሪ የተለያዩ ዘመቻዎችን በማድረግ ብዙ ርቀቶችን ተጉዛለች። አሁንም ይሄንኑ የክትባት ፕሮግራም ከመደበኛ ፕሮግራም በተጨማሪ በዘመቻ መልክ እየሰጠች ትገኛለች። ክትባታቸውን ሙሉ በሙሉ ያጠናቀቁ ሕጻናት ከተለያዩ የበሽታ አይነቶች የተጠበቁ፤ የመከላከል ብቃታቸውም የዳበረ ሲሆን ያልተከተቡት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ለከባድ ህመም ተጋላጭ በትንሽ በትልቁ ችግር ውስጥ የሚወድቁም ስለመሆናቸው ጥናቶች አረጋግጠዋል።
ኩፍኝ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ያልጠፋ ከመሆኑም በላይ እስከ አሁንም በዓለም ላይ 140 ሺ የኩፍኝ ኬዞች አሉ። በአገራችንም ከአምስት ዓመት በታች ያሉ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሕጻናት ኩፍኝን ጨምሮ ከተወለዱ ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት ክትባት ያላገኙ ስለመሆናቸው ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይሁን እንጂ እስካሁንም በተለያዩ ምክንያቶች በክትባት ልንከላከላቸው የምንችላቸውን በሽታዎች የሕጻናት የጤና ችግር ሆነው ቀጥለዋል። ለሕጻናት ሞትም ምክንያት ሆነዋል።
የበሽታው ስርጭትና የመግደል መጠን ከዓመት ዓመት ከመጥፋት ይልቅ የተለያዩ መጠኖችን እያስመዘገበ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል። በዚህም እ.ኤ.አ በ 2015 ላይ 197 የነበረው የሞት መጠን እ.ኤ.አ በ 2016 ወደ 50 ዝቅ ብሎ ነበር፤ እኤአ በ 2021 ደግሞ 18 ሕጻናት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ብዙ ጊዜም ዘመቻዎች የሚደረጉት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ፣ የከፋ ሞትና ህመም እንዳይመጣ ለማስቻል ነው፤ አሁንም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የኩፍኝ ወረርሽኝ በመኖሩ ምክንያት የዘንድሮው ዘመቻ አስፈላጊ ሆኗል።
በመሆኑም ይሄንን አሳሳቢ የጤና ችግር ሙሉ ለሙሉ ከአገራችን ለማጥፋት ከመደበኛ የክትባት ፕሮግራም በተጨማሪ በዘመቻ መልክ ክትባት ለሕጻናት እንዲዳረስ ጤናው የተጠበቀ ትውልድ ለማፍራት በመላው ሀገሪቱ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል።
በያዝነው ዓመትም ከታህሳስ 13 እስከ 22 ቀን 2015 ዓ .ም ድረስ በመላው አገሪቱ በሚካሄደው የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት እንዲሁም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ወጣቶች ደግሞ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት በመሰጠት ላይ ነው። በመሆኑም ኅብረተሰቡ ለተጀመረው የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ውጤታማነት ክትባቱን ያላገኙ ሕጻናት በሙሉ ክትባት እንዲያገኙ በማድረግ የድርሻውን መወጣት አለበት ።
ይሄ የክትባት ዘመቻ ውጤታማና የነገው አገር ተረካቢ ትውልድ ጤንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን በተለይም የሃይማኖት አባቶች ፣ መገናኛ ብዙሃን ፣ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት አለመውሰድ የሚያመጣውን ችግር በማስገንዘብ ልጆች የክትባቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስተማርና ማንቃት ይገባቸዋል። የክትባት ዘመቻው ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ትልቅ አቅም መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ ማስረዳትም ይጠበቃል።
ክትባቱ እስከ ታህሳስ 22 ድረስ የሚቆይ በመሆኑ ሕጻናቱን በአቅራቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቋሟት በመውሰድ የክትባቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል። በአጠቃላይ ለዘመቻው ውጤታማነት፣ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2015