በኢሉባቡር መቱ አካባቢ በሙሉ ጤንነት የተወለደው ሕፃን ሲያድግ ለወላጆቹ የሚተርፍ ብልጽግና ይኖረዋል ብለው ነበር። ለዚህም ይመስላል ሀብታሙ የሚል ስም ያወጡለት። ሕፃኑ በተወለደ በአንደኛ ዓመቱ ግን ወላጆቹ የልጃቸው የወደፊት ሕይወት ላይ የጣሉትን ተስፋ የሚፈታተን ጉዳይ ተከሰተ። ከ40 ዓመታት ገደማ በፊት ሕፃን ሀብታሙ እግሩ ላይ ከባድ ህመም አጋጠመው።
በጉዳዩ የተጨነቁ ቤተሰቦችም ባህላዊ ህክምናዎችን ቢያማትሩም ችግሩን መፍታት አልተቻላቸውም። በወቅቱ የተሻለ ህክምና ባለማግኘቱ እና ወደጤንነቱ ባለመመለሱ የሕፃን ሀብታሙ አንድ እግር ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት። እናም ገና በጨቅላ ዕድሜው አካል ጉዳተኛ ለመሆን ተገደደ።
በጊዜው በአካባቢ የነበረው ማህበረሰብ ለአካል ጉዳተኛ ያለው ግምት እጅጉን የወረደ እና ሰርቶ መለወጥ እንደማይችል የሚታመንበት ነው። በመሆኑም ሀብታሙ ስሙ ብቻ የሀብታም ሆኖ መቅረቱን ይገምቱ የነበሩ ሰዎች በርካቶች ነበሩ። ሕፃኑ ግን ከመንደር ጓደኞቹ ጋር እየተጫወተ እነርሱ ያደረጉትን አድርጎ እያሳየና ችግሩን እየተጋፈጠ አለፈ። በዚህም አላቆመ ትምህርት ቤት ገብቶ ለአካል ጉዳተኛ በማይመቸው ቅጥር ግቢ እየተመላለሰ ዕውቀት መቅሰሙንም ተያያዘው።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ችሎታውን ፈልጎ መሰማራት እንዳለበት እራሱን አሳምኗል። አሁን ሀብታሙ ለአካል ጉዳተኛ ምቹ ባልሆነው ገጠራማ ቦታ ብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አልፎ የወጣትነት ዕደሜው ላይ ደርሷል። እግሩ እንደፈለገ የማያንቀሳቅሰው በመሆኑ ችሎታውንና አቅሙን ሲያመዛዝን ስዕል እና ቅርጻቅርጽ ላይ ቢሰራ ለእርሱ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጠር ተሰምቶታል።
ለመሞከሪያ እንዲሆን በሚል የመንደሩ አንዳንድ የንግድ ባለቤቶችን ቀለም እና መጻፊያ እንዲያዘጋጁ በማድረግ አርማ እና ስማቸውን ታፔላዎቻቸው ላይ በነፃ መጻፍ ጀመረ። በሙከራው የተደሰቱ ሰዎች የሚሰጡት ማበረታቻ ደግሞ ትልቅ ስንቅ ሆነው።
የጽሑፍ እና ቅርጻቅርጽ ሥራውን በመንደሩ እያከናወነ ሳለ ደግሞ የኢትዮጵያ ወዳጅ ካርል ሄይንዝ በም “ሰዎች ለሰዎች” የተሰኘውን የእርዳታ ድርጅታቸውን ሥራ ለመመልከት መቱ ይመጣሉ። እውቁን የእርዳታ ድርጅት መስራች ያገኘው ወጣት ታዲያ ዕድሉን ላለማሳለፍ ቆርጦ ተነስቷል። በመድረኩ የተሰየሙትን ካርልን ጠጋ ብሎ አካል ጉዳተኛ እንደሆነ እና በሙያው የድርጅቱን የታፔላ ጽሑፎች እያዘጋጀ መስራት እንደሚችል ያጫውታቸዋል። በሀብታሙ ታሪክ እና ሙያ የተሳቡት ካርልም በእርዳታ ድርጅታቸው ውስጥ እንዲሰራ ሁኔታውን አመቻቹለት።
ሀብታሙ ድርጅቱን ከተቀላቀለ በኋላ ከመቱ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተዘዋወረ የድርጅቱን የጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት እና ቢሮዎችን የማስታወቂያ ቦርድ ማዘጋጀቱን ተያያዘው። የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የጽሑፍ ሥራ ከብዙ ሰዎች ጋር እንዲተዋወቅ እና ሙያውንም እንዲያሻሽል ዕድል እንደሰጠው ያስታውሳል። ይህን ሁሉ ሲሆን ግን የሰዎች ለሰዎች ሥራውን ሳይለቅ ቤቱ ውስጥ ደግሞ በግሉ የተለያዩ አነስተኛ የማስታወቂያ ህትመት ሥራዎችን ይከውን ነበር። እየሰራም ትዳር ይዞ ሁለት ልጆችን ወልዷል።
ህልሙ ትልቅ እንደሆነ የሚናገረው ሀብታሙ ግን በወቅቱ መቱ ላይ የነበረው የማስታወቂያ ሥራው ገበያ ከእርሱ አቅም ጋር ሲያወዳድረው እምብዛም ነበረና መዳረሻውን ወደአዲስ አበባ ለማድረግ ይወስናል። ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ቤተሰቡን ይዞ አዲስ አበባ ሲመጣ ገርጂ አካባቢ ከወንድሙ ቤተሰብ የመኖሪያ ቤት ነበር ያረፈው።
የኋላ ኋላ የእራሱን ቤተሰብ ይዞ ጀሞ አካባቢ በተከራያት ቤት ኑሮውን ቀጥሏል። አቶ ሀብታሙ ተባራሪ የማስታወቂያ ሥራዎችን ለማግኘት ጊዜውን ወዲያ ወዲህ በማለት ማሳለፉ አልቀረም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በአንድ በኩል የቤት ኪራይ በሌላ ጎኑ ደግሞ የልጆች ትምህርት ቤት ወጪ ናላውን ያዞረው ጀምሯል። ምንም እንኳን የማስታወቂያ ሥራዎችን እያመጣ ማሽን ላላቸው ሰዎች እያቀረበ የተወሰነ ክፍያ ቢያገኝም የወር ወጪውን ለመሸፈን ግን ቋጥሯት ከመጣው ጥቂት ገንዘብ ላይ መጠቀም ግድ ሆኖበታል።
ለተሻለ ሕይወት የመረጣት መዲናዋ እጇን ዘርግታ ባትቀበለውም አቶ ሀብታሙ ግን ተስፋ አልቆረጠም። ይልቁንም ጥንካሬው ለማሳየት የሚችልበትን መንገድ ይፈልግ ተያይዟል። ወደመኖሪያ ቀበሌው በማምራት በአካል ጉዳተኝነቱ ምክንያት ከሥራ ወደኋላ አለማለቱን እና ተደራጅቶ የማስታወቂያ ህትመት ላይ መሳተፍ እንደሚችል ያሳውቃል። በዚህ ዕድል የመስሪያ ቦታ ይመቻችለትና ማረፊያውን ይዞ የማስታወቂያ ገበያውን ማፈላለጉን ቀጠለ።
የመስሪያ ቦታው ቢገኝም ከደንበኞች ገበያ ሲቀበል የሚያትምበት ማሽን በቢሮው ስላልነበረው ሥራውን ይዞ ወደሚያውቃቸው ማተሚያ ቤቶች እያስተላለፈ ነበር የሚሰራው። በ2007 ዓ.ም ወርሃ ሐምሌ ላይ ግን መንግሥት በአነስተኛ ካፒታል ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች የማሽን ሊዝ (የማሽን ዱቤ ግዢ) አሠራር እንዳለው በመስማቱ ማሽን ለመግዛት ዕድል እንዳለው ተረዳ። ማሽኖቹን ለመግዛት የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን አመለከተ።
ጥያቄውም ተቀባይነት በማግኘቱና ማሽን ገዝቶ ህትመቶችን በቢሮው የሚጨርስበት ዕድል ከፊቱ በመደቀኑ ሀብታሙ ተስፋው የሚመነደግበት ዕድል ተፈጠረ። ከአዲስ ካፒታል በማሽን ሊዝ ውል አምስት የጀርመን ማተሚያ ማሽኖችን በ890 ሺ ብር ሊወስድ ነው። በቅድሚያ ግን 133 ሺ ብር ክፍያ መፈጸም ነበረበትና ዘመድ እና ወዳጆቹ እንዲሁም እጁ ላይ ያለችውን ጥቂት ገንዘብ እንደምንም ጨማምሮ ከፈለ።
አሁን የወረቀት መቁረጫ፣ መብሻ፣ መጠቅጠቂያ እና ማተሚያ የተባሉ አነስተኛ ማሽኖችን ተረክቧል። በጥራት የሚያትማቸው ደረሰኝ እና የተለያዩ ወረቀቶችን ለደንበኞች እያደረሰ ገቢውን ማሳደግም ችሏል። ሰባት ሠራተኞችም ተቀጥረው ከሚገኘው ገቢ የማሽን ብድር በየወሩ መከፈል ጀመረ። ሥራው ሲቀላጠፍ ደግሞ የአቶ ሀብታሙ ድርጅት የአንድ ሚሊዮን ብር የመንግሥት ድርጅት ህትመት ሥራ አሸነፈ።
ሥራው የወረቀትና ኮፍያ እንዲሁም ቲሸርት ህትመትም የሚያጠቃልል ብዛት ያለው ትዕዛዝ በመሆኑ እና በአጭር ቀናት ውስጥ ማስረከብ ስለነበረበት ከአጋሮቹ ጋር ለመስራት ወስኗል። ህትመቱ በሙሉ ተጠናቆ ጠያቂው ድርጅት ከተረከበ በኋላ ግን ክፍያ የለ ምላሽም የለ ዝም ጭጭ ሆነ ነገሩ። ሥራው በተጠናቀቀ በ5 ቀን ውስጥ ገንዘቡ ይከፈላል የሚለውን የሥራውን ውል በተደጋጋሚ ቢያሳያቸውም በቂ መልስ የሚሰጠው ያጣል።
በሥራ ካጋጠሙት ፈተናዎች መካከል የገንዘቡ መቅረት ትልቁ መሆኑን የሚናገረው አቶ ሀብታሙ፣ የተወሰነውን ሥራ ያካፈላቸው አጋሮቹ ታዲያ ገንዘባችንን ስጠን እያሉ በየጊዜው ሲወተውቱት ይውላሉ። እርሱም ሙሉ አቅሙም አሟጦ የተረባረበበት ሥራ የሚያስገኝለት ገቢ በመቅረቱ ለማሽን ዱቤው እንኳን በየወሩ የሚከፍለውን ገንዘብ እስኪያሳጣው ድረስ አከሰረው።
ልጆቹን አነስተኛ ክፍያ ወደሚጠይቅ ትምህርት ቤቶች በማሸጋገር ወጪውን በመጠኑ ቀነሰ። የሚከፍለው አጥቶ ለአምስት ወራት የቤት ኪራይ ባይሰጣቸውም ልበ ሩህሩዎቹ አከራዮቹ ታግሰውታል። ተስፋ መቁረጥ ልምዱ አልነበረምና እንዲህ እንዲያ እያለ ከተቆራቆዘበት ለመውጣት ሥራዎችን መስራቱን ቀጥሏል። ዕዳውን መሸፈን ባለመቻሉ ቢያዝንም የሥራ ውሉን ይዞ የመንግሥት ድርጅቱ ክፍያውን እንዲፈጽም በፍርድ ቤት መጠየቁን ግን አልረሳውም። እነሆ ከሁለት ዓመታት ክርክር በኋላ ግን ለአቶ ሀብታሙ ብስራት ተሰማ። ባለመብት በመሆኑ የዛሬ ዓመት አካባቢ ሙሉ ክፍያው እንዲፈጸምለት ፍርድ ቤቱ አዘዘለት።
በተገኘው ገንዘብ የማሽን ክፍያውን ዕዳ ሙሉ በሙሉ ዘግቶ ቢሮውንም አደሰ። በአንድ ልቡ ወደሥራው ላይ ስላተኮረም በርካታ የመንግሥት እና የግል ደንበኞች አሁን እርሱን ምርጫቸው አድርገዋል።
በጥራት የሚያትማቸው ደረሰኞች እና መጽሐፎች ለሥራው እማኝነታቸውን እየሰጡ በገበያ ላይ ገበያን ጨምረውለታል። የገንዘብ ሚኒስቴርን ሙሉ የህትመት ሥራ ጨምሮ በርካታ የህትመት ሥራዎች በእጁ ላይ አሉ።
“ብዙዎች መስራት እንደምችል ስነግራቸው ፊቴ ያመኑ መስለው ዙር ሲሉ አይቀበሉትም” የሚለው አቶ ሀብታሙ፤ በርካቶች ደግሞ ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ እንደማይረዱት ይገልጻል። ከአካል ጉዳተኝነቱ ጋር ተያይዞ ብዙዎች መስራት እንደማይችል ቢያስቡም እርሱ ግን አሁን ለእራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሥራ መፍጠር እንደሚችል አሳይቷል። በድርጅቱ ውስጥ 14 ሠራተኞች አሉት። ካፒታሉን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ከማድረስ አልፎ ለመንቀሳቀሻ የምትሆን ዘመናዊ የቤት መኪናም ባለቤት ሆኗል።
ህልሙ ትልቅ በመሆኑ በቀጣይ ሰፋ ያለ ቦታ ለሥራው እንደሚያስፈልገው አቶ ሀብታሙ ይናገራል። በመንግሥት ሊዝ ፋይናንስ አማካኝነት ሁለት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተሻሉ ማሽኖች እንዲመጡለት አዟል። አሁን ካለው የህትመት አቅም በሁለት እጥፍ በማተም የገበያውን ፍላጎት ማሟላት ነው እቅዱ።
ከቀጣይ እቅዶቹ መካከል ደግሞ የማሸጊያ (ፓኬጂንግ) ኢንዱስትሪውን መቀላቀል አንዱ ውጥኑ ነው። “ጥናት ሳደርግ በኢትዮጵያ ሰፊ የማሸጊያ ምርቶች እጥረት በመኖሩ ዘርፉን ለመቀላቀል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወንኩ እገኛለሁ” ይላል።
እንደ ሥራ ፈጣሪው ከሆነ፣ የፕላስቲክ ማሸጊያዎችን ከአገር ለማስወጣት የወረቀት ማሸጊያዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በመንግሥት ሊዝ ፋይናንስ ተጠቅሞ ምርት ለማምረት የሚያስችል አቅም አለ። የመስሪያ ቦታው ተመቻችቶለት ማሽኖቹን ማስመጣት ከቻለ ከመቶ ያላነሱ ሠራተኞችን ቀጥሮ ሥራውን ማካሄድ የሚያስችል ዕድለ አለ። በተለይ የሻይ ቅጠል፣ የሻ እና የተለያዩ የምግብ እና መገልገያ ዕቃዎችን ማሸጊያዎች በቀላሉ ከአየር ንብረቱ ጋር በሚጣጣሙ የወረቀት ምርቶች የመተካት ህልምም አለው።
ማንም ሰው ከሰራ መለወጥ ይችላል፤ አካል ጉዳተኛም ቢሆን የሚለው አቶ ሀብታሙ እንደእርሱ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎቸ የሞራል ስንቅ መሆን የሚያስችል ሥራ እየሰራ መሆኑን ይናገራል። በመሆኑም አስተሳሰብን ከሚሰሩ እጆች ጋር ማጣመር ከተቻለ ማንኛውም ሰው አገሩን እና ቤተሰቡን የሚጠቅምበት ልዩ ችሎታ ባለቤት ነው። እናም አንተ አካል ጉዳተኛ ነህ መስራት አትችልም ከሚል አስተሳሰብ ወጥተን አካቢያችንን በሥራ እንለውጥ የሚለው ደግሞ መልዕክቱ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2011
በጌትነት ተስፋማርያም