ወይዘሮ ብርሃኔ ድጉማ ከጣሊያን ሰፈር ነዋሪዎች አንዷ ናቸው። የሚተዳደሩት በጥበቃ ሥራ የተሠማሩት ባለቤታቸው በሚሰጧቸው ጥቂት ብርና ደጃፋቸው ላይ ወይራን ጨምሮ ከሰልና ቄጤማ በመሸጥ ነው። ዘንድሮ ጅባው ቄጠማ ሦስት ሺህ ብር በመግባቱና ሲቸረቸር ባለማትረፉ ትተውት ወይራና ከሰል ብቻ ነው እየሸጡ የሚተዳደሩት።
ወይዘሮ ብርሃኔ መንገድ ዳር በምትገኘው ሁለት በሁለት በሆነች ቆርቆሮ ቤት ውስጥ ከባለቤታቸውና ከሦስት ልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ። ቤታቸው መንገድ ዳር ይባል እንጂ ቤታቸው መንገድ ውስጥ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚያ ላይ ለቤቱ የንፁሕ መጠጥ ውሀ አገልግሎት ስላልገባ ወይዘሮዋ የንፁሕ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ አይደሉም።
እዚህ የሀገሪቱ ዋና መዲናና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ለዚያውም ጣሊያን ሰፈርን በመሰለ መሐል ከተማ ላይ ተቀምጠው እንደ ገጠሯ እንስት በንፁሕ መጠጥ ውሃ ይሰቃያሉ ቢባል ማንም አያምንም። ግን በባለ 20 ሊትሩ ጀሪካን አንዱን አራት ብር ሂሳብ ከአካባቢያቸው በመግዛት እየተሸከሙ ነው የሚጠቀሙት። የእሳቸውንና የቤተሰባቸውን ልብስ በሚያጥቡበት ወቅት እስከ 10 ባለ 20 ጀሪካን ውሃ በመቅዳት በጀርባቸው እየተሸከሙ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል።
ውሃ ብቻ ሳይሆን ቤታቸው የኤሌክትሪክ መብራትም የለውም። ይሄንንም ማለቱ ቢከብድም ወይዘሮዋ ከነባለቤታቸውና ልጆቻቸው ለዓመታት ጨለማ ውስጥ ነበር የሚያድሩት። በጨለማ መኖራቸውን ያስተዋሉ በጎ ሰው ታዲያ በብዙ ርቀት ከእሳቸው ጠልፈው እንዲያስገቡ ፈቅደውላቸው ነው የኤሌክትሪክ ገመድ አስገብተው ብርሃን ያዩት። የእግር መንገድ እንኳን የሌለው አስፋልት ውስጥ የገባው የ38 ዓመቷ የወይዘሮ ብርሃኔ የጣሊያን ሰፈሩ ቤት የሚገኘበት ቀበሌ 04/05 ነው።
ይሄ ቀበሌ በወረዳ ሁለት ውስጥ ይገኛል። በመሆኑም ቀበሌውም ሆነ ወረዳው የወይዘሮዋን ቤት አሳምረው ያውቁታል። የቤት ቁጥር 605 ብሎክ ዘጠኝ በሚል መዝግበውትም ይገኛል። ቤታቸው በቀጠና አምስትም እንዲሁ ዕውቅና ያገኘበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን ወይዘሮ ብርሃኔ እንደሚሉት፤ ግድግዳና ጣሪያው በአላፊ አግዳሚ መኪኖች ሲገነጠል፤ በዚሁ ምክንያት እንቅልፍ አጥተው ዘብ ቆመው ሲያድሩ ያገባኛል ብሎ ተከራክሮላቸው አያውቅም። በዚህም የወይዘሮ ብርሃኔ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ቀንም ሆነ ማታ ዕጣ ክፍሉ በመኪና መገንጠል ፤ በድንጋይ ውርወራ መነረት ነው ሥራው::
‹‹አሁን በቀደም ዕለት የቄራ መኪና ጣሪያውን ገንጥሎብኝ ነው የሄደው:: ማታ ወይራና ከሰል ይዤ ስመጣ ነው ያየሁት። ከትላንት በስቲያ ደግሞ አንድ ከባድ መኪና እንዲሁ ግድግዳውን ገንጥሎት ያሠራሁበት ሁኔታ አለ።” ይላሉ ወይዘሮ ብርሃኔ ሁኔታውን በምሬት እየተንገፈገፉ ሲገልፁት። ቀጥለውም ”አብዛኞቹ፣ እንደውም ሁሉም መኪኖች ቤታቸውን በዚህ መልኩ አጓጉል ካደረጉ በኋላ በፍጥነት እንደሚያልፉ በታከተ ስሜት ያወሳሉ:: የገነጠሉት አጥር ይሁን ቤት ቁብ ስለማይሰጣቸው ዞር ብለው እንኳን አያዩትም:: እንደ ነፋስ ሽው እያሉ ነው የሚያልፉት :: ሲገነጥሉት አይተን የአካባቢው ሰው ወይም እኔ ስንናገር አሽከርካሪዎቹ ቆም ብለው እንኳን አያዳምጡንም›› በማለት የዕለት ተዕለት ገጠመኛቸውን በምሬት ይገልፁታል::
በጥበቃ ሥራ የተሠማሩት ባለቤታቸው በየወሩ ከሚያገኝዋት ሦስት ሺህ ብር ላይ ለቤት ወጪ ብለው የሚሰጧቸውን አንዴ ጣሪያውን፣ ሌላ ጊዜ ግድግዳውን እያሉ ለዚሁ ቤት ጥገና ነው የሚያውሉት:: በብዛት አንዳንድ ለነፍስ ያሉ አናጢዎች በነፃ ይጠግኑላቸዋል:: ሰፈርተኛው መልሶ ለሚገነጠለው ባታሠሪው ይሻላል ይላቸዋል:: ወይዘሮ ብርሃኔ በቤታቸው ዕጣ ፈንታ ከንፈሩን የሚመጣው ጎረቤት ብዙ እንደሆነም ይናገራሉ። እሳቸውም እንደለመዱትና ሁሉም ትዕይንት ምንም እንደማይመስላቸው ያወሳሉ። ግን ደግሞ በሁኔታው ቆሽታቸው እርር ድብን ማለቱ እንደማይቀር ፤ በዚሁ ምክንያትም በሚደርስባቸው ብስጭትም በአሁኑ ወቅት ለኃይለኛ ጨጓራ በሽታ መዳረጋቸውን ያስታውሳሉ::
የቤታቸው ስጋት የቆርቆሮ፣ግድግዳና ጣሪያ በመገንጠል ብቻ የሚያልቅ አለመሆኑ ወይዘሮ ብርሃኔን ዘወትር ያሳስባቸዋል:: ቆርቆሮና አጥሩ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡ በተለይም ሦስቱም ልጆቻቸው ለመኪና አደጋና ለድንጋይ ውርወራ የተጋለጡ እንደሆነ ያወሳሉ:: ‹‹ ምንም ደሃ ብሆንና እንደዚህ ዓይነቱ ለኑሮ ምቹ ያልሆነ ቤት ብኖርም ልጆቼን በጥርሴ ይዤ ነው ያሳደኳቸው›› የሚሉት ወይዘሮ ብርሃኔ፤ ብዙ መከራና ስቃይ እያዩ ያሉትም እነሱኑ ለማሳደግ ብለው እንደሆነ በአፅንዖት ይናገራሉ::
እነሱ ባይኖሩ እንደዚያ ባለ ቤት ውስጥ በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ መኖርን አይመርጡም ነበርም:: ግን ‹‹ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች›› እንዲሉት ሆነና ነገሩ ሁሉ ነገር ተደፍቶባቸው ኑሮውን እየኖሩት ይገኛሉ:: ደስተኛ ባይሆኑም ‹‹ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል›› ዓይነት ሆኖም ለልጆቻቸው ደስታን ለመፍጠር እየተጉ ነው:: ልጆቼን አሳድጋለሁ ብለው በማሰብ ሌት ተቀን መልፋታቸውንም አላቆሙም:: ነገር ግን እሳቸው ለልጆቻቸው ይሄን ያህል ዋጋ በመክፈል ይኑሩ እንጂ ልጆቻቸው በዕለት ተዕለት ኑሯቸው በፍፁም አልተመቻቸውም:: ለበርካታ አደጋ የተጋለጡም ናቸው:: እንደውም ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው ስላሉበት ጉዳይ ሲናገሩ እንባ ይተናነቃቸዋል:: ከዚያም አልፎ ከንግግራቸው ቀድሞ መውረድ ይጀምራል:: እናም ወይዘሮ ብርሃኔ የ14 ዓመቱና የሰባተኛ ክፍል ተማሪው ልጃቸው እግዚአብሔር ረድቶት ከሞት ይትረፍ እንጂ ደጋግሞ የመኪና አደጋ ሰለባ ሆኖ እንደነበርም ያስታውሳሉ:: ሁለት ጊዜ ገፍትረው ጥለውት በመጡበት ፍጥነት በመሄዳቸው እራሳቸው ናቸው ያሳከሙት::
ከዚህ አገገመና ተረፈ ብለው ሲሉ ለሦስተኛ ጊዜ አንድ መኪና ገጭቶት እየበረረ ሄደ:: እንደ ዕድል በሥፍራው የነበሩ የሰፈር ልጆች ገጭቶ ጥሎት እየበረረ መሄዱ በአጅጉ አስቆጭቷቸውም ሌላ መኪና በመለመን አሳድደው ያዙት:: ታርጋውን የያዙም ነበሩ:: በዚህ መልኩ ባደረጉት ርብርብም እንዲያሳክመው አደረጉ:: ፊኛውን ስለመታው ፊኛው ክፉኛ ተጎድቶ ነበር:: በዚያ ላይ ሲገጨው እንጨት ይዞ ሲጫወት ስለነበር እንጨቱ በመኪና ሲመታ ነጥሮ ወግቶት ከፍተኛ ጉዳት አድርሶበታል:: በዚህ የተነሳ ልጃቸው ብዙ ጊዜ ታመመ::
ትምህርቱን በሥርዓት መከታተል ባለመቻሉም ዘንድሮ ሰባተኛ ክፍልን ደግሞ እየተማረ ይገኛል:: በእርግጥ በአደጋው ብቻ ሳይሆን በቤቱም ምክንያት ነው ሰባተኛ ክፍልን ሊደግም የቻለው:: ቤቱ ጠባብ በመሆኑ ቁጭ ብሎ የሚያጠናበት ቦታ የለውም:: የሚያስጠናውም የለም:: እሳቸውም ቢሆኑ የቀለም ትምህርት ባለመማ ራቸው አያስጠኑትም:: ባለቤታቸውም እንዲሁ ::
ቤቱ ልጆች የሚያጠኑበት ቀርቶ የሚያድሩበት እንኳን አይደለም የሚሉት ወይዘሮ ብርሃኔ፤ ማታ ማታ ሁልጊዜ ራታቸውን ካበሏቸው በኋላ ለአዳር በአካባቢው ያሉ ዘመዶቻቸው ጋር እንደሚልኳቸውም ገልፀውልናል:: እሳቸውና ባለቤታቸውም ቢሆኑ የአንድ ዓመት ከሦስት ወር ሕፃን ልጃቸውን ይዘው ተራ በተራ እየተጠባበቁ ነው የሚተኙት:: ምክንያቱም ይህ ካልሆነ መኪናው በላያቸው ላይ ወጥቶ ቤታቸውን ደምስሶ እነርሱንም ያጠፋቸዋል:: ስለዚህም ከመሞት መሰንበትን አስቀድመው በተራ ይተኛሉ:: የቤቱ ጥበትም ቢሆን ተራ በተራ እንጂ በጋራ የሚያስተኛቸው አይደለም:: እናም ወይዘሮ ብርሃኔ እንደሚሉት ዘወትር ምግብ የሚበላውም ሆነ ቡና የሚጠጣው አልጋ ላይ ተቀምጦ ነው:: አልጋ ቢባል ደግሞ እዛው ከቤቱ ቆርቆሮ ጋር እንደ አልጋ ተመሳስሎ የተመታ እንጨት እንጂ የዕውነት አልጋ አይደለም:: ልጆቹን እራት እያበሉ ዘመድ ቤት እንዲያድሩ የሚልኩትም ለዚሁም ሲሉ ነው::
ወይዘሮ ብርሃኔ ቆርቆሮ በቆርቆሮ በሆነው የቀበሌ ቤታቸው የሚያዩት አበሳ በዚህ ብቻ አያበቃም:: ራሳቸውን ከስጋቱ ለመታደግ ከባለቤታቸው ጋር እየተጠባበቁ ተራ በተራ ቢተኙም እንቅልፋቸው እንዲህ በቀላሉ አይመጣም:: ምክንያቱም በአካባቢው በርካታ መጠጥ ቤቶች አሉ:: ከጎናቸው ደግሞ ሙዚቃ ቤት ይገኛል:: ባለ ሙዚቃ ቤቱ 24 ሰዓት ሙዚቃ ያስጮሃል:: ከዚሁ አጠገብ ያለው ሥጋ ቤት ጋርም ድራፍት ይሸጣል:: ከእሱ ጎንም እንዲሁ መሸታ ቤት ነው የሚገኘው:: ጩኸቱና ጫጫታው የጉድ ነው::
አረቄና ድራፍት ቤት ያሉት ተጠቃሚዎች ሲሰክሩ ጠርሙስና ድንጋይ ይወራወራሉ:: የሚወረወረው ድንጋይ የሚያርፈው ደግሞ እሳቸው ጣሪያ ላይ ነው:: አንዳንዴም እነሱ ላይ አርፎ ለጉዳት የሚዳረጉበት አጋጣሚ አለ:: በተጨማሪም ቤቱ ፊት ለፊቱ አፉን የከፈተ ትልቅ የቱቦ ገንዳ ስለሚገኝ በአካባቢው የሚኖሩና መፀዳጃ ቤት የሌላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ማልደው ሰገራቸውን በባልዲ እየሞሉና እያመጡ ይደፉበታል:: ከጎናቸውም ሌላ ቱቦ አለ:: ይሄም ቱቦ ለተመሳሳይ ተግባር ይውላል:: በዚህ ሽታም ወይዘሮ ብርሃኔና ቤተሰባቸው ተደጋጋሚ የጤና ችግር እያጋጠማቸው ነው የሚኖሩት::
አሁን በቅርቡ የአንድ ዓመት ከሦስት ወሩ ልጃቸው በሳንባ ምች ተይዟል ተብሎ ሆስፒታል ለሆስፒታል እየተመላለሱ ይገኛሉ:: ለሳንባው ሽታ እንዳያገኘው በጣም ጥንቃቄ አድርጊለት፤ ምግብም በቤት ውስጥ አታብስይ ቢባሉም አማራጭ በማጣታቸው የሐኪሙን ትዕዛዝ ሊተገብሩት አልቻሉም:: እንደመፍትሔ የወሰዱት ተለዋጭ ቤት እንዲሰጣቸው ቀበሌ መመላለስን ነው:: ለቀበሌው‹‹ቤቱ ለልጆቹ ጤና ጠንቅ ነውና ተለዋጭ ይሰጣቸው›› ተብሎ ከጤና ጣቢያና ከሚመለከተው ሌላ አካል የተሰጣቸውን ማስረጃና ማመልከቻ አስገብተዋል:: ሆኖም እሳቸው ያሉበትም ቤት ሆኖ ‹‹አንቺ ቤት ይዘሽ ቤት ትጠይቂያለሽ መጠለያ እንኳን የሌለው አለ›› የሚል ምላሽ ነው የተሰጣቸው::
ይሄንኑ ለኃላፊው ለመንገር በተደጋጋሚ ቢሄዱም ሊያገኙት ያልቻሉት ወይዘሮ ብርሃኔ፤ ዓይናቸው እንባ እንዳቆረዘዘ ‹‹ልጆቼ አንድ ቤት ተሰብስበው መኝታ አግኝተው የሚያርፉበትን ቀን እናፍቃለሁ›› ይላሉ:: ያለባቸው ችግር ጊዜ የሚሰጥ አይደለም:: ማስረጃ ካላቸው ደግሞ መፍትሔ መስጠቱ አስፈላጊ ነው:: እናም ቀበሌው የችግራቸውን ክብደት ተመልክቶ መፍትሔ ቢቸራቸው ሲል መልካም እንደሆነ በመጠቆም ለዛሬ የያዝነውን አበቃን::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215