‹‹ገንዘብ በ30 ፣ ልብ በ40 ›› ሲባል ደጋግመን እንሰማለን:: አንዳንዶች በወጣትነት እድሜያቸው የገንዘብ ባለቤት ይሆኑና ልጅነት ይዟቸው፣ማስተዋል አጥሯቸው ገንዘብ ያባክናሉ፤ በአንጻሩ እነዚህ በወጣትነታቸው በገንዘብ የተንበሸበሹ በጉልምስና እድሜያቸው ማስተዋሉን ያገኙና ገንዘብ ሲያጥራቸው ይስተዋላሉ:: እነዚህን ሁለት የህይወት ገጽታዎች የተመለከቱ ታዲያ ይህን አይነቱን ህይወት ‹‹ገንዘብ በ30፣ ልብ በ40›› በሚለው ብሂል ይገልጹታል::
ሰው በእድሜው እየተማረ የሚሄድ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን የማስተዋል መሳሪያ የሆነውን ልብ የሚያገኘው እድሜው እየጨመረና በሕይወት የጉዞ ውጣ ውረድ ሂደት ብዙ ነገሮችን እየተመለከተና እያወቀ ሲሄድ መሆኑ ይታመናል:: ገንዘባቸው ልባቸውን ቀድሞ መጥቶ ገንዘብን በጥሩ ልብ መምራት ሳይሆንላቸው ቀርቶ ‹‹ ምነው ያኔ ከገንዘቡ ጋር ልቡም ኖሮኝ ቢሆን?!›› እያሉ ለገንዘብ ቅርብ፣ ለልብ ሩቅ ሆነው ያሳለፉትን ዘመናቸውን በቁጭት የሚያስታውሱ ብዙዎች ናቸው::
ጥቂት ቢሆኑም ሀብትንም ብስለትንም በአንድ ጊዜ፣ ያውም በጠዋቱ፣ የሚጨብጡትና ይዘው የሚያቆዩ አስደናቂ ሰዎችም አሉ:: እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሕይወት ገና በጠዋቱ ብዙ ያስተማረቻቸው፣ የሕይወትን ትምህርትና ልምድ በማስተዋል የተገበሩ፣ ያላቸውን ለሌሎች በማካፈል በፅኑ የሚያምኑ እና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መሆን የሚችሉ አርዓያዎች ናቸው:: ገንዘባቸው ልባቸውን ሳይቀድም የሚመጣላቸውና ልባቸውን ለገንዘባቸው መምሪያና ማስተዳደሪያ በብቃት የመጠቀም ችሎታ ያላቸውም ናቸው:: እነዚህ ሰዎች ለገንዘብ ቅርብ የሆኑትን ያህል ለልብም ቅርብ ናቸው:: የዛሬው የ‹‹ስኬት›› አምድ ባለታሪክ የሆነው የ29 ዓመቱ ብሩክ አበራም ሀብትና ልብ በአንድ ላይ ተገናኝተው እውነተኛ ስኬትን ያጎናፀፉት ወጣት ነው::
ብሩክ አበራ የተወለደው በሲዳማ ክልል፣ በንሳ ወረዳ ነው:: አባቱ ልጆቻቸው ጠንካራና ስኬታማ እንዲሆኑላቸው ትልቅ ምኞት ስለነበራቸው ‹‹ልጆቼ የከተማ ባህርይ እንዳያዘናጋቸው›› ብለው እነብሩክን ትምህርት ቤት ያስገቧቸው ከሚኖሩበት ቦታ ትንሽ ራቅ ያለ ቀበሌ ውስጥ ነው:: ብሩክ አራተኛ ክፍል ሲደርስ ሃዋሳ ሐይቅ ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን ተከታትሏል:: በእርግጥ ብሩክ ዛሬ ላይ ሆኖ ነገሮችን መለስ ብሎ ሲያስታውስ አባቱ የመረጡት መንገድ ጠቅሞት ለስኬት አብቅቶታል::
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የመጀመሪያ ድግሪውን ይዞ በ2005 ዓ.ም ከቤተሰብ ባገኘው 40ሺ ብር መነሻ ካፒታል በተማረበት የሙያ መስክ ተሰማራ:: ‹‹ብሩክ አበራ ኮንስትራክሽን ድርጅት››ን በማቋቋም ከስኬት ትግል ጋር ጉዞውን ጀመረ:: አባቱ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ስለነበሩ ስለንግድ ስራ እየሰማ አድጓል:: ይህም እርሱም የራሱን ስራ እንዲጀምር መነሻ ሆኖ አግዞታል::
የግንባታ ጨረታዎችን በማሸነፍ ስራውን ቀጠለ:: ለስራዎቹ የፈረማቸውን ውሎች አክብሮ በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የአስተዳደር ሕንፃዎችንና ሌሎች ግንባታዎችን አጠናቅቆ በማስረከብ ምስጋናና ሽልማቶችን ማግኘት ችሏል:: ድርጅቱ ካከናወናቸው ግንባታዎች መካከል በሲዳማ ክልል፣ በስልጤ እና በጋሞ ዞኖች የሚገኙ የጤና፣ የትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው::
‹‹ብሩክ አበራ ኮንስትራክሽን ድርጅት›› በስራ ላይ ከተሰማራበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ 17 የግንባታ ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ አስረክቧል፤ በአሁኑ ወቅት በ240 ሚሊዮን ብር የሚገነባውን የሐዋሳ አዳሪ ትምህርት ቤትን (Boarding School) ጨምሮ ሁለት የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል:: ‹‹ጨረታ አሸንፈን የወሰድናቸውን ስራዎች በታማኝነትና ቃል በገባነው መሰረት አጠናቅቀን ማስረከባችን ስኬታማ አድርጎናል:: በአጠቃላይ የስኬታችን አንዱ ምክንያት በታማኝነት ማገልገላችን ነው›› በማለት ይገልፃል::
ብሩክ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ብቻ ተወስኖ መቅረት አልፈለገም:: ከዚህ ስራው የሚያገኘውን ትርፍ ወደ ሌላ ተጨማሪ ስራ ለማስፋት ወሰነ:: ከኮንስትራክሽን ስራው ያገኘውን ትርፍ ወደ ሌላ የንግድ ዘርፍ በማሸጋገር ከባንክ ጋር ትስስር ፈጥሮ በ2010 ዓ.ም በቡና ንግድ ላይ ተሰማርቶ መስራት ጀመረ:: ‹‹ዶና ኮፊ›› የተሰኘው የቡና ድርጅቱ በሲዳማ ክልል በአራት ወረዳዎች (አርቤጎና፣ በንሳ፣ ሆኮ እና ጭሪ ወረዳዎች) በቡና ልማትና ንግድ ላይ እየሰራ ነው:: ዘንድሮ ደግሞ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ላይ መሳተፍ ጀምሯል:: በቡና ምርት ታዋቂ ከሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የሲዳማ ክልል ለብሩክ የቡና ልማትና ንግድ ስራ ጥሩ እድል እንደሚፈጥርለት አያጠራጥርም::
ባለፈው ዓመት ከቡና ሽያጭ እስካሁን ድረስ ተገኝቶ የማያውቅ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያገኘችው ኢትዮጵያ፤ ዘንድሮም በቡና ኤክስፖርት ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅዳለች:: ለዚህ እቅድ መሳካት ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትጋትና ቅንጅት ያስፈልጋል:: በዚህ ረገድ የብሩክ ‹‹ዶና ኮፊ›› ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ብሩክ ይናገራል:: ‹‹በቻልነው መጠን በቂ የሆነና ጥራት ያለው ቡና አዘጋጅተን ኤክስፖርት በማድረግ ለሀገራችን ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማስገኘት ጠንክረን እየሰራን ነው›› ይላል::
ብሩክ አበራ ገና በ29 ዓመቱ የቢሊየነርነት ደጅ ላይ ደርሷል:: ከቤተሰብ ባገኘው 40ሺ ብር መነሻ ካፒታል የጀመረው ስራው ዛሬ ከ700 እስከ 800 ሚሊዮን ብር ካፒታል ላይ ደርሷል:: ‹‹ስኬት የሚገኘው በግል ጥረት ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ እርዳታም ጭምር ነው›› የሚለው ስኬታማው ወጣት ብሩክ አበራ፤ ለስኬት ለመብቃት የግል ጥረት ወሳኝና አስፈላጊ ነገር መሆኑን ይገልጻል፤ ጊዜና ትኩረትን ለስራ መስጠት እንደሚያስፈልግም በአፅንዖት ይናገራል::
ብሩክ በወጣትነቱ የገንዘብ ሀብታም መሆን የቻለ ሰው ብቻ አይደለም፤ገና በወጣትነቱ ልባምነትንም የታደለ ነው:: ልባም ለመባል ያበቃው ሀብት እንዲያፈራ ያስቻለው ትጉህ ሰራተኛነቱ ብቻ ሳይሆን ያለውን ሀብት ለሌሎች የማካፈል ባህርይው ነው:: ‹‹ትናንትናን አለመርሳት ያለህን ለሌሎች ለማካፈል ያግዛል›› የሚለው ብሩክ፣ ያለፈበትን የሕይወት ጉዞ አለመርሳቱ ሀብቱን ለሌሎች ለማካፈል እንዳስቻለው ይገልፃል:: ብሩክ በአሁኑ ወቅት በሲዳማ ክልል በሐዋሳ ከተማ፣ በቦሪቻ እና አርቤጎና ወረዳዎች ቢሮዎችን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን የሚያካትቱ ሦስት ትምህርት ቤቶችን በበጎ ፈቃደኝነት እያስገነባ ይገኛል::
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደና ያደገ አብዛኛው ሰው በድህነት ህይወት ውስጥ ያሳለፈ መሆኑን መዘንጋት የለብንም:: ያሳለፍነውን ጊዜ ብናስብ አብዛኞቻችን የተማርነው ጥራቱን ባልጠበቀ ትምህርት ቤት ውስጥ እንደሆነ እንገነዘባለን:: እኔ ሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል የተማርኩት ከጭቃ በተሰራ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው:: ይህን ሳስታውስ ለአሁኑና ለመጪው ትወልድ የተሻለ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ አስባለሁ›› በማለት ትናንት ያሳለፈው ሕይወቱ ለዛሬ የበጎ አድራጎት ስራው መነሻ እንደሆነለት ያስረዳል::
ብሩክ የክልሉ መንግሥት፣ ባለሀብቶች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ተግባር ላይ እንዲሳተፉና እንዲያግዙ ያቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ በመጀመሪያ ደረጃ የዋጋ ስሌት እያንዳንዳቸው ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚፈጁ (የግብዓት ዋጋ በየጊዜው ስለሚጨምር ዋጋው ሊጨምር እንደሚችል ይታሰባል) ሦስት ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ ነው:: የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ከተጀመረ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፤ የቦሪቻው ትምህርት ቤት ከአንድ ወር በኋላ፣ የአርቤጎናው ከሦስት ወራት በኋላ እና የሀዋሳው ደግሞ ከሁለት ወራት በኋላ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ::
‹‹በአንድ ክፍል ውስጥ 100 ተማሪዎች ሲማሩ እናያለን:: ሐዋሳ፣ አዲስ አበባ ወይም ሌሎች ትልልቅ ከተሞች ላይ ያለውን በመመልከት ብቻ ትምህርትና ጤና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ የተዳረሰ ሊመስለን ይችላል:: ወደ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ስንሄድ ግን ሽፋኑ በጣም ገና እንደሆነ እንታዘባለን::›› የሚለው ብሩክ፣ በብዙ ወረዳዎች ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እንደሌሉም ይናገራል::
ብሩክ ሲዳማ ውስጥ ካሉ 36 ወረዳዎች መካከል እኔ 12 ወረዳዎች ላይ ያለውን ሁኔታ እንደሚያውቅ ይገልጻል:: በአንድ ወቅት አርቤጎና ወረዳ ውስጥ አንድ ቀበሌ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች እንጨት አዋጥተው፣ አራት ክፍል ትምህርት ቤት ሰርተው ጣሪያ ማልበስ ሲቀራቸው ተመልክቶ ሁኔታቸው አንጀቱን ይበላዋል፤ 80 ቆርቆሮዎችን ገዝቶም ይሰጣቸዋል::
‹‹ትናንት የነበርክበትን ስታስብና ስታስተውል የምታደርገውን ነገር በጥልቅ የማካፈልና የመስጠት ስሜት ነው የምታደርገው:: እንዲህ ዓይነት ስራ የምትሰራው ከዚያ ላይ የምታገኘውን ትርፍ ታሳቢ በማድረግ አይደለም:: የክልሉ መንግሥት ባቀረበው ገለፃ ላይ ትምህርት ገና እንዳልተዳረሰና ጥራቱም ገና እንደሆነ ተመልክተናል:: እኔ ብቻ ሳልሆን በሲዳማ ክልል ውስጥ ያሉ ሌሎች ባለሀብቶችም በትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተሳተፉ ነው›› በማለት ባለሀብቶች በትምህርት ዘርፍ ስለሚያከናውኑት የበጎ ፈቃድ ስራዎችም ያስረዳል::
ያለውን ሀብት በማካፈል መርህ በፅኑ የሚያምነው ብሩክ፣ ‹‹ትናንት የነበርክበትንና መጪውን ትውልድ ካሰብክ ያለህን ማካፈል አይከብድህም:: ንግድና ሀብት ወሰን የለውም፤አያልቅም:: ባለቤቱ ግን ያልቃል:: ስለዚህ ባለሀብቶች ከማለቃቸውና ከማለፋቸው በፊት ሀብታቸውን ለሌሎች ማካፈል አለባቸው:: ሀብትን ማካፈል ለራስ ህሊና ሰላም ይሰጣል፤ሌላውን ሰው ይጠቅማል ሲል ያስገነዝባል:: ‹‹ካለው ነገር አካፍሎ ስራ የሚሰራ ሰው፣ ኅብረተሰቡን በተለይም መጪውን ትውልድ የሚጠቅም ትልቅ ስራ እየሰራ እንደሆነ መገንዘብ አለበት›› በማለት የገንዘብ ባለቤት የሆኑ ሰዎች ከገንዘቡ በተጨማሪ የልብ ባለቤትም እንዲሆኑ ይመክራል::
‹‹ስራችን በዚህ ብቻ አይቆምም:: ሀብትን አከማችቶ ለብቻ በመኖር ደስተኛ መሆን አይቻልም:: የመጣንበትን አለመርሳት እንዲሁም ያለንን እያካፈልን መስራትና መኖር ስላለብን በቀጣይ ጊዜያትም የኅብረተሰቡን ችግር ሊያቃልሉ የሚችሉ ሌሎች ስራዎችን እንሰራለን›› በማለት አሁን እየሰራቸው ካሉ ማኅበረሰብ ተኮር የመሰረተ ልማት ስራዎች በተጨማሪ በሌሎች ስራዎች ላይም የመሳተፍ በጎ እቅድ እንዳለው ይናገራል::
ብሩክ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ጉዞው ቀላል እንዳልነበር ያስረዳል። የአሁኑ ስኬቱ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎና ጫናዎችን ተቋቁሞ የተገኘ ድል ነው። ያሳለፋቸውን ጊዜያት ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስታውሳቸው የዛሬው ስኬቱ በቀላሉ እንዳልተገኘ ይገነዘባል። ለአብነት ያህል ስራ በጀመረ በሁለተኛው ዓመት በ2007 ዓ.ም በስራ መኪናዎች ላይ የደረሰውን ውድመት እንደአንድ ፈተና የሚስታውሰው ብሩክ፣ ‹‹ቢዝነስ ብዙ ፈተናዎች አሉት፤ሀብት መፍጠር ቀላል ነገር አይደለም:: በፈጣሪ እርዳታና በትጋታችን ፈተናዎቹን አልፈን አሁን ላለንበት ጥሩ ደረጃ ደርሰናል›› በማለት ይናገራል::
‹‹መስጠትና ማካፈል ከፈጣሪ የሚገኝ ስጦታም ጭምር ነው›› የሚለውና ሁሉንም የበጎ አድራጎት ስራዎቹን ዘርዝሮ ከመናገር ይልቅ ትህትናን የመረጠው ብሩክ አበራ፣ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነው:: ‹‹ለዛሬው ስኬቴ መሰረትና አርዓያ የሆኑኝን ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ›› ይላል::
ወጣቶች ገንዘብ ለመስራትና ሀብት ለማፍራት ቀጥተኛ ያልሆኑ መንገዶችን ከመከተል እንዲቆጠቡና መንግሥት ደግሞ ወጣቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ በጥናት ላይ የተመሰረተ የፋይናንስና ሌሎች ግብዓቶች ድጋፍ እንዲያደርግም ይመክራል:: የወጣቱን እውቀትና የመንግሥትን ፋይናንስ በማጣመር የተሻለ ውጤት ማግኘት እንደሚቻልም ነው ያመለከተው::
‹‹በወጣትነታችን በትጋትና በፍጥነት ሰርተን ሀገርን ለመጥቀም መረባረብ አለብን›› የሚለው ስኬታማው ወጣት ብሩክ አበራ፣ ሌሎች ትልልቅ እቅዶችም አሉት:: አርቤጎና ወረዳ ላይ በቀን 24ሺ ሊትር የሚያመርት የውሃ ፋብሪካ የመገንባት፣ የቡና ልማትና ንግድ ስራውን በማስፋት በብዛት በቀጥታ ለውጭ ገበያ የማቅረብ፣ በሐዋሳ ከተማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ ሪዞርት እንዲሁም በተሻለ ጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ የመኖሪያ አፓርታማ (G+10) የመገንባት፣ የስሚንቶ ፋብሪካ የማቋቋም እና በማዕድን ልማት ዘርፍ የመሰማራት እቅዶችን ለማሳካት እየሰራ ነው::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215