ይህ፣ ዛሬ በድንገት ለንባብ የበቃው ሀሳብ ከዚህ በፊት ”ፍልስፍና ማለት” በሚል ርእስ ይፃፍበት ዘንድ ተረግዞ የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም ያለ ጊዜው አይሆንምና ዛሬ ያ ሃሳብ በሚከተለው መልኩ ለንባብ ሊቀርብ ችሏልና ”እነሆ በረከት …” እንላለን።
እንደሚታወቀው፣ ብዙ ጊዜ በየዋህያን ዘንድ “ፍልስፍና ማለት”ን ከመጠየቅ ጋር ብቻ አያይዞ፤ ከመመለስ ጋር እንኳን ሳይገናኝ መጠየቅ ብቻም ሆኖ ምእተ አመታትን ዘልቆ፣ እዚህ እኛ ዘንድ ደርሷል። ”ልክ ነው”፣ ”ልክ አይደለም . . .” የሚለውን እየወረድን የምናየው ሆኖ፤ ሁሉም ግን በራሱ፣ ለየ እራሱ የሚለውን ለራሱ ሊይዘው ይገባልና ማንም ቢሆን ከጫና ሊያመልጥ የግድ ይሆናል። ጉዳዩን መሬት ለማሲያዝ ግን መነሻችንን እራሳችንን፤ ሌጋሲዎቻችንንም ፈላስፎቻችንን አድርገን ፈር እንያዝ። (እዚህ ላይ፣ ጉዳዩ “ፍልስፍና ማለት”ን ለመመለስ ከሞከረው፣ ከመጀመሪያው ፈላስፋ Thales (Raymond Geuss በበኩሉ Oedipus ነው ይላል) ጀምሮ የትኩረት ነጥብ ሲሆን፤ ወደ ፊት ስለመዝለቁም ጥርጥር የሌለ መሆኑን፤ ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው ምክንያት አለም እንደ ወንዝ መሆኗና የሰማው ሲሄድ ያልሰማው መምጣቱ መሆኑን በመሰረታዊነት ልንይዘው ይገባል።)
የፍልስፍናን ፋይዳ ምን ያህል እናውቀዋለን? ካወቅነውስ አሳውቀናል? ነው ወይስ ዛሬም ድረስ “ፍልስፍና ማለት መጠየቅ ማለት ነው” እያልን ከሰው ልጅ የእለት ተእለት ሕይወት አርቀነዋል? ፈላስፋውንስ ቢሆን።?
ሲጀመር፣ ፈላስፋው እኮ ሀሳቡን ገለፀ፤ ይሆናል፣ ይበጃል . . . ያለውን እንካችሁ አለ እንጂ አነሳሱ ልፈላሰፍ የሚል (ብሎ) አይደለም። የፈላስፋነቱን ማእረግ ያገኘው ስራውን ከሰራው በኋላና በሚመለከታቸው ተመዝኖ ነው ባለ ስራው ”ፈላስፋ” የሚባለውን ካባ የሚደርበውና የፈላስፋነቱን ደብር የሚቆጣጠረው። ፀጋዬ እኮ ከስራው በኋላ እንጂ ከስራው በፊት አይደለም ማህበራዊ አንቱታውን በእጁ ያስገባው። ገብረህይወት ባይከዳኝ፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ በአሉ ግርማ፣ ከበደ ሚካኤል . . . ሁሉ እኮ እውቅናቸውን ያገኙትና ማህበረሰባዊ ከበሬታን የተቆጣጠሩት ስራዎቻቸውን መሬት ካወረዱና ፍሬያቸው ከተቀመሰ በኋላ ነው። ዘርአያእቆብ እኮ ሲፈላሰፍ ”ፍልስፍና” የሚለው ቃሉም አልነበረም። እሱ ሲያከናውን የነበረው የነፍሱን ጥሪ ነበር። ማርክስም ለተጠየቀው ሲመልስ ”እኔ ማርክስ እንጂ ማርክሲስት አይደለሁም” ነበር ያለው።
ዛሬም እንጉርጉሯችን “ፍልስፍና ማለት መጠየቅ ማለት ነው” ከሆነ፣ የፍሬሽ አፍ መፍቻ ቦታው የቱ ጋ ነው? ነው ወይስ ዘርዓያዕቆብ ስላነሳቸው ብርቱ ጉዳዮች ጠየቀ እንጂ አላብራራም፤ አልተነተነም፤ አልተነበየም፤ እውነቱን አላመለከተም፤ መሆን ያለበትን ከሌለበት አልለየም ወዘተ (ለ)ማለት ነው? ነፍሳቸውን ይማረውና አማረ ማሞ እንዳሉት ጉዳዩ – ያወያያል፤ ያነጋግራል፤ ያመራምራል።
“ፍልስፍና በጥቅሉ የተጻፉትንና በቃል ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉትን የጋርዮሽ የማህበረሰብ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች፣ ወጎች፣ ልማዶች፣ እደ-ጥበቦች፣ የእውቀት ዘርፎቻችንና አስተሳሰቦችን፤ በጠባቡ አተያይ ደግሞ በግለሰብ ፈላስፎች በአንድ ዘመን ተሰርተው በጽሁፍ የተላለፉትን ስራዎች በጥቅል የሚመለከት ነው፡፡” የሚለው ብያኔ በብዙዎች ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ሌሎች ብያኔዎችን በዚሁ ጽሑፍ ሂደት በእግረ መንገድ ተነካክተዋል።
ወደ ጉዳያችን ስንገባ (ሳንገባም ቢሆን) ከጥንቱ፣ ከግዕዝ ስልጣኔያችን (የዓባይንም አክለን) በመጀመር ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር፤ “መጀመሪያ ቃል ነበረ(ር?)” ተብሏልና እኛም “መጀመሪያ ግዕዝ ነበረ” ብንል “አልነበረም” የሚለን ስለማይኖር ማለት ነው። ከጊዜና ገጽ አኳያ ግን ከፍልስፍናና ፈላስፎቻችን እንጀምር።
ስለ”የኢትዮጵያ የፍልስፍና አባት ዘርዓያዕቆብ” ከመናገራችን አስቀድሞም ይሁን ቀድሞ፤ “የኢትዮጵያ የሥነጽሁፍ ታሪክ በአጼ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግስት (1434-68)” ከሚል ነገራ በፊትም ሆነ በኋላ፤ ስለተለያዩ የፍልስፍና መጻሕፍት ከመናገራችን ሁሉ በፊትም ሆነ በኋላ፤ ስለ”ያሬዳዊ ዜማ” ከመተንተናችን በፊትም ሆነ በኋላ፤ ስለ”የዶርዜ ጥበብ” እና “ባህላዊ አልባሳቶቻችን” ከመደስኮራችን አስቀድሞ፤ የአክሱም ሀውልት ላይ ያሉትን ፈርጦች ማየታችንን ከማሳየታችን በፊት፤ ወይም በኩራት ከመናገራችን በፊት “ስለምን”አቸውን አጠይቀናል?
“በሎሬቱ አማካኝነት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጨረቃ ላይ ወጥቷል” ስንል “በየትኛው የአሳሳል ፍልስፍና መሰረትነት?” የሚል ጥያቄ ቢኖር መልሱ ምን እንደሚሆን/ማይሆን ማን/ምን ያውቃል? የ”ትልልቅ ዐይን”ን ጥበባዊ መሰረት፣ ፍልስፍናዊ ክዋኔ ምንነት ለመግለፅ ከመሞከራችን በፊትም ይሁን ከሞከርን በኋላ “ኢትዮጵያ የ’ትልልቅ ዐይኖች’ አሳሳል ጥበብ ባለቤት” ፍልስፍናችን የቱ ጋ እንኳን እንዳለ ሳንናገር፤ በ”አብስትራክት” የተተበተብን የተበላሹ አብስትራክቶች ሆነናል/አልሆንንም – ምርጫው የግል ሆኖ። (የሀበሻ ቢራ አርማን እንጥቀስ ካልተባለ በቀር።)
“ወግና ስርዓት፣ ነውርና ክብር ስለክፋትና ደግነት፣ ጥሩነትና መጥፎነት፣ እንዲሁም ስለሥነምግባር ጽንሰ ሃሳቦች ትክክለኝነትና ስህተትነት ምንነት፣ መስፈርትና አስፈላጊነት የመሳሰሉትን ሃሳቦች የሚያጠና ዓቢይ የፍልስፍና ዘውግ (ወይም ፆታ) ምን ይባላል?”ን ከመጠየቃችንም ሆነ አለመጠየቃችን፤ “ሥነ-ምግባር (Ethics)” “ነው” ወይም “አይደለም” ብለን ከመመለሳችንም ሆነ መመለስ ካለመቻላችን በፊት “ፍልስፍና ማለት” ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አይገባንም/ይገባናል የሚለው እራሱ መመለስ አለበት/የለበትም ላይ ልንግባባ እየተገባም ይሁን እያልተገባ ይህን ሳናደርግ ዛሬ ድረስ መዝለቃችን ስህተተኞች መሆን/አለመሆናችን ላይ እራሱ እራሱን የቻለ (የመግባባያ ሰነድ የማያስፈልገው) መስማማት ወይም አለመስማማትን ይጠይቃልና እዳው ገብስ የሆነ ይመስል ልናቀ’ለው አይገባም።
ይህ “ፍልስፍና ማለት መጠየቅ ነው” አተያይ መረዳትን ሁሉ እስኪከልል ድረስ ስር ሰዷል (ይህ ደግሞ So obviously, attempting to sum it up in a few pithy blurbs is a fool’s errand. ይሉት አይነት ነውና ፋይዳው ከዜሮ በታች ነው)። በመሆኑም – ሥነግጥም ከግጥምነት ያለፈ ፋይዳ የለውም፤ ልቦለድም ሆነ ሌሎች የፈጠራ ስራዎችም እንደዛው። ባህላዊ እሴቶቻችንና ታሪኮቻችን የፍልስፍናዎቻችን መገለጫዎች መሆናቸውን ልብ እንዳንልና የውጪውን እንድንጎመዥ አድርጎናል።
የፈጠራ ሰዎችንና ስራዎቻቸውን ከተራው ሰው ለይተን ተገቢውን ስፍራ ሰጥተን “አንቱ” እንዳንል ጋርዶናል። በመሆኑም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በቃ ገጣሚ እንጂ ሌላ አይደለም፤ በ”እሳት”፣ ”ውኋ” እና ”ዋርካ” ላይ ያለው አመለካከት፣ በስራዎቹ ውስጥ ያሏቸው ስፍራዎችና ፋይዳቸው ለእኛ ምንም እንዲሆኑ አስተዋፅኦ አደረገ እንጂ ስራዎቹ የባለቅኔው ፍልስፍና ማራመጃዎች መሆናቸውን እንዳንለይ አድርጎናል – ”… መጠየቅ ነው” መባሉ። ይህም በበኩሉ ስለ’ነዚህ የፍልስፍና ማሄጃዎቹ እስካሁን እሱ ከነገረምን ውጪ ሌላ ተጨማሪ የሰማነው ነገር የለም፤ በታትኖ የሚያሳየን ሥነጽሑፋዊ ሂስም ሆነ ሀያሲ አላየንም፤ አላገኘንም። “ጃንሆይ ፍቅር እስከ መቃብርን ልቦለድ ነው ብለው ባይንቁት ኖሮ የደረሰባቸው አይደርስባቸውን ነበር።” የሚባለውንም ከዚሁ አኳያ መረዳት እየተነጋገርንበት ያለነውን ከማቅለል ባሻገር ጉዳት የለውም።
ለነገሩ፣ የሂስና ሃያሲያን መንደር ጭር ካለ ቆይቷል። እንደው ጭራሹኑ ባዳ እንዳይሆንብ አድርገውት ከነበሩት አንዱ ነፍሱን ይማረውና አብደላ እዝራ ነበር። አስፋው ዳምጤም ሰሚ አጥተው የተሰላቹ ይመስላሉ – ጠፍተዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በ”የጋን ውስጥ መብራት”ነታቸው ፀንተው ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ በማለት ቃለ መሀላ የፈፀሙ እስኪመስልባቸው ድረስ ትንፍሽ ሲሉ አይሰሙም። ታዲያ ሥነፅሁፍ ለፍልስፍና እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ እንዴት ይታወቅ? ይህ ብቻም አይደለም ስንትና ስንት ዋልጌ ብእሮች አገር ምድሩን ሲያጥለቀልቁት ሀይ ባይ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ ቦታው ለምን ባዶ ሆነ? እኛንስ ለምን ”ከፍልስፍናችን ማንነት ግብአተመሬት በፊት” በሚል ርእስ እንድንፅፍ አስገደደን???
“ሰው በሀገር ይወለዳል ይባላል። ግን ደግሞ ሀገርን የሚወልዱ ሰዎች አሉ።” እንደሚባለው ብዙ ሰዎች አሉ አገር የወለዱ፣ እየወለዱ ያሉና ወደ ፊትም የሚወልዱ። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሰዎች እስከነመኖራቸው እንኳን የሚታወቁት በጭንቅ፣ አገር እንደዚህ እንደ አሁኑ አይነት መከራ ውስጥ ስትገባና ዜጋው ሁሉ ወደ ላይ ሲያንጋጥጥ ነው። ለዚህ ደግሞ ፀጋዬ ገብረመድህንና ግጥሞቹን፣ ጥላሁን ገሠሠንና ዜማዎቹን፤ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ በላይ ዘለቀ፤ አቡነ ጴጥሮስ ወዘተ ድልና መስዋእትነታቸውን መጥቀሱ ብቻ በቂ ነው። አገርን ከአዘቅት ያወጡ፤ ማንነታቸውንም ካዘቅጥ ባወጧት አገር ላይ ያቆሙ … ሆነው አልፈዋል።
ዛሬ፣ አስቀድሞ ሎሬቱ ”ፍቅር ፈራን . . .” እንዳለው ሁሉ፣ እኛ እንደ ፍቅር የፈራነው ነገር የለም ለማለት የሌለውን ከሌለበት ፈልጎ እንደ ማምጣት ነው የሚቆጠረው። ዛሬ ፍቅር፣ እንደ ተስፋ . . . ሁሉ፣ ርቆ ተሰቅሎብናል፤ ወደ ላይ ዘልለን ያዝነው ስንል ጭራሽ ወደ ላይ ይወጣና እኛ የ’ሱ ድውያን አድርጎን እርፍ ይላል። ይህ በበኩሉ፣ የሚከባበሩት እንዳይከባበሩ፣ የማይፈራሩት እንዲፈራሩ፤ የማይጠላሉት እንዲጠላሉ . . . አደረገና እርፍ። እስኪ አሁን ማን ይሙት የሀይማኖት ተቋማት ካልተከበሩና ካልተከባበሩ ማን ሊከበርና ሊከባበር ነው??? ምእመን እርስ በርስ፤ እጅ ለ’ጅ ካለተያያዙ ማን . . .? ፀብ በእነሱ ያምራልን? በእነሱ ካማረስ በማንስ ሊያስጠላ ነው???
ዛሬ፣ ዋና ባለ ታሪኩ ሄኖክ የሆነው ሌላው ዓለም ከእጃችን እየነጠቀን ያለው ”መጽሐፈ ሄኖክ”፣ ልክ እንደ ግእዝና ሌሎች ሁሉ አገር በቀል እውቀታችን መሆኑን ማን ነው የሚያውቀው? ”ሀተታ ዘርዓያዕቆብ” የመካከለኛው ዘመን ፍልስፍና አባት ነው የሚለውን የምሁራን ጥናት ማን ነው ከልቡ የጣፈው? የተማሪውን፣ የወልደህይወትን ፍልስፍናዊ ውለታ ማን ነው ”አባ ከና” ያለው፤ ”ፍልስፍና ማለት መጠየቅ ማለት ነው” የሚለው ወገን እንኳን እነዚህን ሲጠይቅ አለመሰማቱ ምክንያቱ ምንድን ነው?? ይህ አለመጠየቅ፤ ከልብም አለመጣፍ ላለመከባበራችንስ አስተዋፅኦ የለውምን? ግዕዝስ ምን አጠፋ?
“የጥንታዊ ኢትዮጵያ(ዊያን) ፍልስፍና”፣ “የግዕዝ ቋንቋ/ሥነጽሑፍ” (“የሲግመንድ ፍሮይድ (Oedipus complex) ንድፈ ሃሳብ የተመሰረተበትን ታሪክ በጽሁፍ ይዘው ከተገኙት አምስት የዓለማችን ቋንቋዎች (ግሪክ፣ ላቲን፣ ሲራይክ፣ አረቢክ እና ግዕዝ) አንዱ (ሰምነር እንደደረሰበትና ፍቃዱ ቀነኒሳ እንደጠቀሰው) መሆን/አለመሆኑን እንኳን ሳንጠቁም፤ “የዓባይ ስልጣኔ” እያልን ከማወጃችን በፊት፤ “በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍና ታሪክ ውስጥ በመጀመሪያው ክፍል እንደተጻፈ የሚነገርለት የመጀመሪያው የፍልስፍና ስራ መጽሐፈ ፊሳልግዎስ (physiologus) ይባላል፡፡”
ከሚለው ማስታወቂያችን አስቀድመን፤ “ከአስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በተለየ መልኩ በርከት ያሉ የፍልስፍና ስራዎችን በመስራት በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ናት” እያልን ከማለታችንና መደምደሚያችንን ከማስቀደማችን አስቀድሞ፤ “ኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠሩ ሥነቃላዊ፤ ከዚያም የጽሁፍ ፍልስፍናዎች ባለቤት ናት፡፡” ወይም “ሀገራችን ኢትዮጵያ ገና ያልተጠኑ የበርካታ ጥንታዊ ሥነጽሑፎች ባለቤት ናት።” እያልን መሆኗን ከመናገራችን አስቀድሞ፤ “ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ስርግው ሃብተሥላሴ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፣ ሎሬት ፀጋዬ ወዘተ እንዳጠኑት/እንዳሉት” ከማለታችን አስቀድሞ፤ ባህር ተሻግረን “እነ ፕሮፌሰር ፓኦሎ ማራሲኒ፣ አሌሳንድሮ ባውዚ፣ ሪቻርድ ፓንክረስትና ክላውድ ሰምነር ወዘተ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ለዓለም እንዳስተዋወቁት” ሳንል፤ “አንጋረ ፈላስፋ፣ የስክንድር ሕይወትና አባባሎቹ፣ ሀተታ ዘርዓያዕቆብ እና ሀተታ ወልደ ህይወት” ወዘተርፈ እያልን ከመቁጠር፣ መቆጣጠርና መቋጠራችን አስቀድሞ ማድረግ ያለብንን አድርገናል/አላደረግንም የሚለው እራሱ ግዕዝ አፍ አውጥቶ “አይሲሲ” ላይ ቢከሰን ምክንያታዊ ነውና አይፈረድበትም።
የአዲስ አድማሱ አምደኛ ዘርዓያዕቆብን “የመካከለኛው ዘመን ፖስት ሞደርኒዝም አቀንቃኝ ነው” ሲለን ምን ማለቱ ነው? እየጠየቀን ነው? እየመለሰልን ነው? ምን እያለን ነው? ዘርዓያዕቆብን “የመካከለኛው ዘመን ፖስት ሞደርኒዝም አቀንቃኝ” ከሆነ ታዲያ ለምንድን ነው በአሁኑ ዘመን እንደ አሸን የፈሉት የፍልስፍና መጻሕፍት (በፍልስፍና የሚያላግጡትን “ፍልስምና”ዎች ጨምሮ) ነን በማለት አደባባይ ለይ የተዘረሩት ይሄንን እማይነግሩን? ወይም ሀሳቡን አስፋፍተው የማያስረዱን? እሱም ይቅር፤ ምእራባዊያኑ ላይ ብቻ ከማተኮርና እነሱኑ ብቻ ከማንቆለጳጰስ ልምን “ዘርዓያዕቆብን የመካከለኛው ዘመን ፖስት ሞደርኒዝም አቀንቃኝ” መሆኑን እንኳን ደግመው ደጋግመው ሲጠቅሱ አይታዩም? የሰምነር “ዘርዓያዕቆብ የመካከለኛው ዘመን የዓለም ፍልስፍና ፈር ቀዳጅ” ግኝትንስ ለምን ቦታ ይነፍጉታል?
“አንቀጽ 39 ሲፀድቅ ሲያጨበጭቡ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን አልነበሩም እንዴ ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው …” የሚልውን የባእዳን ትዝብትም ሆነ ጥያቄ መመለስ/አለመመለስ ከእራስን ማወቅ/አለማወቅ ጋር ይገናኛል/አይገናኝም የሚለውም ያው አማረ አስቀድመው እንዳሉት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም/ይችላልና ፖለቲካዊ መፍትሄን እንኳን ባይሆን (ቢሆንም አናውቅም)፤ በአንድ ወቅት በዚሁ ጋዜጣ ላይ የደከምንበትን የ”ሀገር ግንባታ”ና “ሀገረ መንግስት ምስረታ”ን ጉዳይ ልምሻ ከማሲያዙ በፊት ሳይንሳዊ መላን፣ ፍልስፍናዊ ማጠቃለያን ይሻል እንላለን።
ሌላው አማረ አስቀድመው እንዳሉት የሚሆነው በ”ጭብጨባ! የድንቁርናና የአንባገነንነት ሽፋን” ርእሱ ስር በድሉ ዋቅጂራ (ዶ/ር) “ህዝባዊ አጨብጫቢነት” የሚለው ጉዳይ ነው። “ፍልስፍና ማለት” ምን ማለት እንደሆነ ሊነገር ይገባል እያልን እንዳልነው (ያላልነውንም ጨምሮ) ሁሉ፤ “ሕዝባዊ አጨብጫቢነት” ማለት ምን ማለት እንደሆነም ይሁን ምን ማለት እንዳልሆነ ሊነገር ይገባል፤ በየትኛው የፍልስፍና ዘውግ ሊታሽ እንደሚያስፈልግም ሊጠቆም/ሊጠቀስ ግድ ይላል የሚለው ነውና ኳሷን ለሚመለከተው መለጋት ይሁን ማቀበል ባይታወቅም ከሁለት አንዱ እንዲሆን ተደርጓልና ሀላፊነት ወርዳል ማለት ይሄኔ ነው (ማለት ነው?)።
በመጨረሻም
ዘመኑ የሚጠየቀው ከማይጠየቀው፤ የማይደረገው ከሚደረገው፤ ተገቢው ከነውሩ፤ እውነቱ ከሀሰት . . . ድብልቅልቁ የወጣበት፤ ታናሽና ታላቁ ስፍራ የተለዋወጡበት፤ ፍልስፍናችን ሁሉ “ተበድለሃል…”፣ “ተፈልጠሃል”፣ “ተቆርጠሃል…” “ተገርፈሃል”፣ “ተጨቁነሃል” ወዘተ…. የሆነበት፤ የማይግባባው፣ ሊግባባ የሚይገባው የሚግባባበት (ለምሳሌ በአገር ማፍረስ ጉዳይ ማንም ሊግባባ የማይገባው ሆኖ ሳለ፣ አገር ለማፍረስ ተግባብቶ መስራት) ወዘተርፈ ሲሆን፤ መፍትሄውም ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት የሆነበት ቅጥ ያጣ የአላዋቂዎች ዘመን ነው። በመሆኑም ይህ ሁሉ ይቀር፣ ሥርአታት ወደ ተፈጥሯዊ ምንነትና ማንታቸው ይመለሱ፣ የሀይማኖት ተቋማት (በተራዛሚው ምእመናን) እርስ በርሳቸው ይከባበሩና በየእምነታቸው ቀኖና ይመሩ ዘንድ፤ አንዱ አንዱን መዝለፉን ያቆም ዘንድ የሁላችንም ምኞት ነው። ካልሆነ፣ ”የበላችው ያገሳታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንዳይሆንብን ያሰጋል። ከስጋቱ ነፃ ለመሆን ደግሞ ፍልስፍናችን ከነማንነቱ ግብአተመሬቱ መፈፀሙ በፊት መጠየቅንም፤ መመለስንም … እንልመድ። መጠየቅ ብቻ ለሕይወት መልስ እንደማይሰጠው ሁሉ፤ መመለስ ብቻም እንደዛው። የማንነት ፍልስፍናዎቻችንን ማወቅ፣ መገንዘብ፣ መጠቀም … እንዳለብን ሁሉ፤ የተግባቦት ክሂልም በእጅጉ ያስፈልገናል!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215