ማዋዣና መንደርደሪያ፤
ሰሞኑን በሀገር ፍቅር ቴአትር የተገኘሁት እግር ጥሎኝ እንጂ ለትዕይንተ ጥበባቱ ድግስ ታዳሚ ሆኜ አልነበረም:: በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር የተጻፈ አንድ “የትብብር መጠየቂያ” ደብዳቤ ለማድረስ በተገኘሁበት በዚያ አጋጣሚ እጅግ ብዙ ጉዳዮችን ለመታዘብ ችያለሁ:: ቅጥረ ግቢው ውስጥ ዘልቄ እንደገባሁ አንዳች ሀሴት ይሉት መግነጢስ ሲያነዝረኝና ሲወረኝ ታውቆኛል::
በልጅነት፣ በወጣትነትና በጉልማሳነት የዕድሜዬ እርከኖች ጉዞ የቤቴን ያህል የማውቀው ያ ዘመን ጠገብ ግቢ “መታደስ” ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ “ሥር ነቀል” ለውጥ ተደርጎበትና ተውቦ ማየት ስሜትን በደስታ ያረሰርሳል:: ከዓመታት በፊት በቴአትር ቤቱ መድረክ ላይ በቀረቡት ውሱን ቴአትሮች ላይ የዚህ ጋዜጣ እህት በነበረችው ተወዳጇ “ነፍሰ ሄር” የዛሬይቱ ጋዜጣ ላይ ያቀረብኳቸው ሂሳዊ ጽሑፎች እየታወሱኝም በትዝታ መንጎዴ አልቀረም::
የብርሃኑ ዘርይሁን “ባልቻ አባነፍሶ”፣ በተፈሪ ዓለሙ የተተረጎመው “አሉ”፣ የፍስሐ በላይ ይማም “የወፍ ጎጆ”፣ በመስፍን ዓለማየሁ ተተርጉሞ አርቲስት ደበበ እሸቱ የትወና ጥበቡን አሟጦ ችሎታውን ያስመሰከረበት “የቬኒሱ ነጋዴ” በዕድሜ ዘመኔ ሁሉ በፍቅር እንደታወሱኝ ይኖራሉ:: እነዚህ ድንቅ የጥበብ ውጤቶች በድጋሚ ለመድረክ መቅረብ ቢችሉ ተሽቀዳድሜ ለትኬት ግዢው ሰልፉን ለመምራት አልቦዝንም ነበር::
የዕድሜዬን ሦስት አራተኛ ያህል አውቀዋለሁ የምለው ያ ግቢ ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበር ታሪኩና የትዝታው ክብር ሳይነካ ይመሳሰልብኝ የነበረው “እርጅና ተጫጭኗቸውና ጥርሳቸው በሙሉ ረግፎ በድዳቸው ፈገግ በማለት ዘመናቸውን እንደሚታዘቡ አንድ የከበሩ አዛውንት” ነበር:: ያለፈውን ዝርዝር የድክመት ገመና እንዲህና እንደዚያ ነበር በማለት ዛሬ ላይ ቆሞ መተረኩ እጅግም ስለማያንጽ ጥቁምታውን ብቻ ለአንባቢያን ፈንጥቆ ማለፉ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም::
ያ ተዘንግቶ የኖረው “የማዕደ ጥበባት” ቅጥረ ግቢ ቀን ወጥቶለት ተለውጦና አምሮ መመልከት በእጅጉ ደስ ያሰኛል:: በዚያ እግር በጣለኝ እለት ባለሙያዎቹም ሆኑ የሥራ ኃላፊዎቹ “ተፍ ተፍ” ሲሉ ያስተዋልኳቸው ፊታቸውን አኮስትረው ሳይሆን በፈገግታ እየተፍለቀለቁ ነበር:: የቤተ ተውኔቱ ሁለቱ ታሪካዊ አዳራሾች (ትልቁና ትንሹ)፣ ቢሮዎቹና መሰል መገልገያዎቹ በሙሉ የይዘት ተሐድሶ ተደርጎላቸዋል::
በተለይም “መለኪያ” ይጋጭበት የነበረውና ለረጅም ዘመን ቴአትር ቤቱን ሲያስወቅስና ሲያስተች የነበረው “ክበብ ተብዬ” ከፊት ለፊት ዞር ብሎ ወደ ጀርባ መዞሩ ሌላው አስመስጋኝ ተግባር ነው:: በውጫዊ ይዘቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥበብ ዝግጅቶቹም ላይ ተሐድሶው ነፍስ ዘርቶ አዳዲስ ዝግጅቶችን እንደምንመለከት ተስፋ አደርጋለሁ::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዚህ አንጋፋ ቴአትር ቤት ትኩረት ሰጥቶ ትርጉም ያለው “የቅርጽ ተሐድሶ” ሥራ በመሥራቱ ምሥጋናችንን ብንቸረው ተገቢ ይመስለናል:: ብዕረ መንገዴን ሳልጠቅሰው የማላልፈውን አንድ ሌላ ተያያዥ ጉዳይ ላስታውስ:: ወግ ባለው ሁኔታ አምሮና ሰምሮ የተሞሸረው የአዲስ አበባ ባሕልና ቴአትር አዳራሽ ዕጣ ፈንታስ ምን ሊሆን ነው? የጥበብ ቤትነቱ ተለውጦ የፖለቲካ ሸንጎ መሰብሰቢያ ብቻ ሆኖ መቅረቱ ይሆንን?።
የከተማችን አስተዳደር ተገቢውን መልስ ሰጥቶ እህህ! እያሰኘ እንደ ሻህላ በቁጭት ሆድ ሆዳቸውን ለሚበላቸው የቤተ ጥበቡ ባለሙያዎችና ለሰፊው የከተማው አፍቃሬ ጥበብ ነዋሪዎች ቁርጡን ቢያሳውቅ አይከፋም:: የማዘጋጃ ቤቱ የቴአትር አዳራሽ የታደሰው ለጥበብ ሥራ ወይንስ ለሌላ ዓላማ? ሳይድበሰበስ ቢገለጽልን አዲስ አበባም ከሐሜት ትድናለች እኛም ከትዝብትና ከጉርምርምታ አደብ ገዝተን አርፈን እንቀመጣለን::
“የሀገር ፍቅር”፡- ዝክረ ታሪክ፤
“የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገር ፍቅር ማኅበር” የተመሠረተው ሐምሌ 11 ቀን 1927 ዓ.ም ነበር:: ዕድሜውን እናስላ ካልን 88 ዓመቱን ደፍኗል:: “ይህ የፍቅርና የአንድነት ጉባኤ” እንዲመሠረት ምክንያት የሆነው በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረው የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ነበር:: ገና ከጅምሩ የማኅበሩ አባላት የወራሪውን ሠራዊት ይቃወሙ የነበረው በስብከት፣ በግጥም፣ በዜማ፣ በፉከራና በቀረርቶ እንደነበር በታሪኩ መዘክር ውስጥ በዝርዝር ተመልክቷል::
እነዚህን መሰል የቅስቀሳ ሥራዎች ይከወኑ የነበረው በወቅቱ ዝነኛ በነበሩት ባለቅኔዎች፣ ደራስያን፣ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች፣ የመንግሥት ሹማምንትና በተመረጡና አንደበተ ርቱዕ በነበሩ ዲስኩረኞች አማካይነት ነበር:: ሕዝቡ ጉልበቱ ሳይላላ አንድነቱን ጠብቆ ሊወረው የመጣውን ጠላት እንዲመክትና ራሱን እንዲያዘጋጅ ይዥጎደጎዱ የነበሩት የንግግርና የጽሑፍ መልዕክቶች፣ ግጥሞችና ፉከራዎች በእጅጉ የሚያስገርሙና ወኔን በማኮስተር የሚያጀግኑ እንደነበሩ ታሪክ ምስክርነቱን ይሰጣል::
ከብዙዎቹ የወቅቱ ተጠቃሽ ባለታሪኮች መካከል፤ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ተሰማ እሸቴ፣ አበበ ወልዴ፣ መላኩ በጎሰው፣ ሣህሌ ፀዳሉ፣ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ ተስፋ ገ/ሥላሴ፣ ሀጂ በዳሶ፣ ተመስገን ገብሬ፣ ደምስ ወ/አማኑኤል ወዘተ. የመሳሰሉት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ:: ከእነዚህ የሀገር ባለውለታና የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች መካከል በወቅቱ ለቅስቀሳ የዋሉ ጥቂት የግጥም ስንኞችን እየመዘዝን እንደሚከተለው እናስታውሳለን:: ዮፍታሔ ንጉሤ በ1927 ዓ.ም ካስነበቧቸው ግጥሞች መካከል አንዱና ተደጋግሞ የሚታወሰው ይህ ግጥም ሳይደበዝዝ በብዙዎች ዘንድ እንደተጠቀሰ እነሆ ዛሬን ደርሷል::
“አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣
ጎበናን ከሸዋ አሉላን ከትግሬ፣
ስመኝ አድሬያለሁ ትናንትና ዛሬ፣
አሉላን ለጥይት ጎበናን ለጭሬ::
አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ የእምቧይ ካብ::”
በኋለኛው ዘመን በደራሲነታቸውና በጋዜጠኝነታቸው የሚታወቁት ወልደ ጊዮርጊስ ወ/ዮሐንስም በዚያው ዓመት ለሕዝብ ያሰራጩት ግጥም እንዲህ ይነበባል::
ደሙ እየተረጨ አጥንቱ እስኪፈለጥ፣
ሰው ላገሩ ቢሞት ምንም አይቆጠቁጥ::
የሀገርን ፍቅር አጥብቀን ስናይ፣
ሰው ላገሩ ቢሞት ቁምነገር ነው ወይ?
ጠላት በዋናው ላይ ትርፍ አገኛለሁ ሲል፣
እኛስ ከዋናችን ስለምን እናጉድል::
ተጋዳይ፣ ተጋዳይ፣ ተጋዳይ አርበኛ፣
እንዴት ያመልጥሃል ያገርህ ደመኛ::”
በሥዕል ጥበባቸው ከፍተኛ አድናቆት የተቸራቸው ሠዓሊ አገኘሁ እንግዳም በዚያው በ1927 ዓ.ም ከተቀኟቸው ግጥሞች መካከል አንዱ ይህ ነበር::
ይህ የመጣ ጠላት ሳይደርስ ከጠረፍ፣
ተነሱ እንነሳ ደማችን ይፍሰስ::
ይሂድ ይቀላቀል ከዓባይ ጋር ይውረድ፣
ነፃነት ያጣ ሕዝብ አይባልም ወንድ::”
እነዚህን የመሳሰሉ ግጥሞች በጋዜጣ፣በበራሪ ወረቀቶችና በመጻሕፍት እየታተሙና እየተሠራጩ ለሕዝቡና ለሠራዊቱ ይበተኑ ነበር::
በጠንካራ መሠረት ላይ የተመሠረተውና ወደ ዘጠኝ አሠርት ዕድሜ እየተጠጋ ያለው የሀገር ፍቅር ቴአትር ሀገራዊ አደራውን እንደጠበቀ ከትውልድ ትውልድ ተሸጋግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል:: ይህ አንጋፋ የጥበብ ቤት ቢቻልና ቢሆንለት በተደራጀና በተጠና መርሐ ግብር የዛሬ ኑባሬ (አኗኗራችንንና ዐውዳዊውን ውሎ አምሽቷችንን) ከትናንቱ ታሪክና ተሞክሮ ጋር በማስተሳሰር “በታደሰው መድረክ” ላይ ዝግጅቱን ቢያቀርብልን ኅላዌነቱን አክብሮና አድምቆ ማሰንበት ለመቻሉ አያጠራጥርም::
ያለበለዚያ አካልቦ በሚያካልበው በዚህ በእኛ ዘመን አረጋግተውንና አስክነውን ወደ ቀልባችንና ወደ ሩሐችን እንድንመለስ መግራት ብቻም ሳይሆን ዳግም እንዳንስትም ወደሚያስጠነቅቁን የጥበብ ሥራዎች እስካላተኮርን ድረስ ዮፍታሔ ንጉሤ እንደተቀኙት “ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ” መሆኑ አይቀሬ ይሆናል:: በእድሳት የተሞሸረው ታሪካዊው የሀገር ፍቅር ቴአትር ይህን አደራ ተሸክሞ እንደተለመደው ትውልዳዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተስፋ እናደርጋለን::
ጭጋግ ያጠላበት ሀገራዊ ፍቅር፤
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለራሷ ለሀገሪቱም ሆነ ለዜጎች ዕንቆቅልሽ ለመሆን ዳር ዳር ወደሚባል ደረጃ እየተደረሰ መሆኑን በብዙ ውሎ አምሽቷችን እያስተዋልን ነው:: በዓለም ታሪክ (ተመዝግቦም ይሁን ወይንም በአሉ ተባባሉ ቅብብሎሽ) በአደባባይና በፀሐይ ፊት ሀገሩን በክህደትና በእብሪት እያንኳሰሰ “ገሃንም ትግባ፣ ትበጣጠስ፣ ትፈራርስ ወዘተ.” እያለ ክፉ የተመኘና ክፉ የሚመኝ ትውልድ ከእኛ ውጭ መኖር ስላለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም:: እንደሚመስለን ግን ይህን መሰሉ “ሠይጣናዊ ምኞት” ክፉና እርኩስ መንፈስ የሚያቀብለው የተረገመ ሃሳብ ካልሆነ በስተቀር ከጤናማ አዕምሮ የሚወጣ አይመስለንም::
ስለ ትልቋ ኢትዮጵያ ከመመስከር ይልቅ ስለ ራስ ጎጥና ብሔር ብቻ የተለየ ክብር መስጠት፣ በገናና ታሪክ ከመኩራት ይልቅ በተናጠል ማንነት ላይ ተንጠልጥሎ ዥዋዥዌ መጫወት የዘመናችን ፋሽን ከሆነ ሰነባብቷል:: በፍልስፍናው ጎራ “ሥነ ኑባሬ” የሚባል የመሟገቻ ሃሳብ በዘርፉ ባለሙያዎች የተለመደ የእንካ ሰላንትያ መፋለሚያ ርዕስ ነው:: የሥነ ኑባሬ ፍልስፍና በአብዛኛው በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን ነው:: አንዱ በአካል ወይንም በማንነት ላይ ሲሆን ሁለተኛው በምንነት ላይ አጽንኦት ይሰጣል:: ስለዚህም “አካል” የኅላዌ መገለጫ ብቻ ሳይሆን የአካል መሠረትም ጭምር ነው::
አካል በራሱ ግዘፍ የነሳ ተፈጥሮ ነው:: ያ አካል ካላሰበ፣ በምክንያታዊነት ካልተመራ፣ ለነፍሱና ለሚገዳደረው የእውነትና የኅሊና ሙግት ምላሽ ለመስጠት ዳተኛ ከሆነ ወይንም ቅርብ ማደር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ሩቅ ከማሰብ ከተፋታ ውጤቱ የቁም ድንዛዜ ብቻ ሳይሆን ያ አካል ተብዬ ሰብዕና ትርጉም እንደጠፋበት ለማረጋገጥ አይከብድም::
“የሰው አካል” ማገናዘብ፣ ማሰብና ማሰላሰል፣ ከተሳነውና ለእውነት፣ ለፍትሕና ለበጎነት መጨከንን ችላ ማለት ከጀመረ “ሰው መባል ብቻ” ከተራ ቁስነት በምንም ሊሻል አይችልም:: በተለይም ጤነኛ አቋምና ሰብዕና ያለው ዘረ አዳም አዕምሮውንና ጊዜውን ለነፍሱና ለጉርሱ ብቻ መድቦ ከኖረ ምንትስ ከምንላቸው ፍጡራን በምንም ሊሻል አይችልም:: ይህ ፍልስፍና ትንሽ ረቀቅና ጠነን ስለሚል አቅልሎ ለማስረዳት ፈታኝ መሆኑ አይቀርም:: “መሆን ወይንም አለመሆን” የሚለው ሙግት የሚታወሰው እዚህ ላይ ነው::
ወደ ዋናው ጉዳያችን እንመለስና የሀገር ፍቅር መገለጫዎች እነዚህና እነዚያ ብቻ ናቸው ብሎ ለመበየን ይሞከር ካልሆነ በስተቀር ድምዳሜ የሚሰጥበት ጉዳይ አይደለም:: የሀገር ፍቅር ተዘርቶ፣ እየተኮተኮተና እየታረመ የሚፋፋ ስሜት እንጂ እንደ ወፍ ዘራሽ ፍሬ በተገኘው ቦታ ላይ የሚበቅል ተክል አይደለም:: የዘሩ መደብ የልጅነት ዕድሜ ነው:: በቀዳሚነት “መደቡ” መለስለስ የሚጀምረው በቤተሰብ ጓዳ ውስጥ ነው::
“ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ፣ ቤተሰብ ለብዙ ሰብዓዊ ሥሪቶቻችንና የባህርይ ቀረጻ ዋናው ምንጭ ነው:: ይህ ከፍተኛ ኃላፊነት የወደቀበት የቤተሰብ ተቋም ችግር ኖሮበት ኃላፊነቱን ካልተወጣ ወይንም ምንጩ በተለያዩ ችግሮች የተበከለ ከሆነ ጨቅላ ዕድሜን በሀገር ፍቅር ለማነጽ ቀርቶ ራሱ ቤተሰቡ የችግሮች መፈልፈያ መሆኑ አይቀሬ ይሆናል:: የሀገሬ ቤተሰብ ይህንን ወሳኝ ጉዳይ ልብ ሊል ይገባል::
ከቤተሰብ ከፍ ሲል ማኅበረሰቡም ለሀገር ፍቅር ስሜት መዳበርና መጎልበት ድርሻው የላቀ ነው:: ጉርብትናው፣ የቤተዘመድ ቅርርቡና ተዛምዶው፣ የአካባቢው ልዩ ልዩ ተቋማት (ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ዘርፎች) ሚናቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ከፍ ሲልም የኅብረተሰብ ድርሻ (የትምህርት ሥርዓቱ፣ ፖለቲካው፣ ኪነ ጥበቡ፣ ሚዲያውና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቋማትና ክስተቶች) የዜጎች የሀገር ፍቅር ስሜት ወይ እንዲጎለበት አለያም እንዲጨነግፍ የሚያበረክቱት አሉታዊም ሆኑ አወንታዊ ተጽዕኖዎች ከሚገመተው በላይ የበረቱ ናቸው:: በዚህም ጉዳይ ላይ ልብ ገዝተን ልብ ልንል ይገባል::
በተለይም ቤተሰብ ውስጥ የተዘራው ዘር በትምህርት ቤት ውስጥ ሥር ካልሰደደ፣ ሥር የያዘው ዘርም በአትኩሮት ማኅበራዊና መንግሥታዊ ድጋፍ ካልተደረገለት በስተቀር “የሀገር ፍቅር” የምንለው ፀጋ ለመጠውለግ ፈጣን፣ ለመወየብም ቅርብ ነው:: እናስ ዛሬ በስፋት ሀገርን መውደድ የምንለው ስሜት ጭጋግ አጥልቶበት “ምን ግዴ” ትውልድ ሊፈጠር የቻለው በምን ምክንያት ነው? ከትልቅነት ይልቅ ማነስን፣ ሰፋ ያለ አመለካከትን በመጠየፍ መጥበብን ምርጫ አድርጎ የአስተሳሰብና የአመለካከት ድንክነት እንዲንሰራፋ ምክንያት የሆነው ሀገራዊ ችግራችን ምንጩ የተበላሸው የትና በምን ዓይነት አረም ተጠቅቶ ይሆን?
ከትልቅ ሀገርና ባለሀገርነት ይልቅ “እኔን ራሴን እና የእኔን” ብቻ አስቀድሙልኝ ማለትን ምልዑ በኩለሄ ምርጫችን አድርገን ነገሮችን ሁሉ በራሳችን ክበብ ውስጥ ለማሽከርከር ያስመኘንና ያስጨከነን ምን ይሉት አዚም ነው? የጥቂቶች ፍላጎትና የውስን ፖለቲካዊ ርዕዮት ተጽዕኖ ምክንያት ሆኖ ከሆነም ቆም ብሎ ማሰቡ፣ ሳይዘናጉ ግራ ቀኝ አስተውሎ መራመዱ ስለሚሻል “ጆሮ ያለው ይስማ፣ ልቦና ያለው ያስብ” የአዋጃችን መደምደሚያ መልዕክት ነው:: ያለበለዚያ ግን በመነሻችን ላይ እንደተንደረደርንበት ተዘንግቶ እንደኖረው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ይዞታ “ታሪክና ትዝታ በመሸከም” ነበርን ብቻ እየተረክን እንዳናልፍ ሀገራዊ መነቃቃትና ተሐድሶ ያስፈልግ ይመስለናል:: ሰላም ይሁን::
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215