በጎ ፍቃደኝነት ከበጎ ህሊና የሚመነጭ የተቀደሰ ተግባር ነው:: ከራስ አልፎ ለሌሎች የመሆንን ፤አሳቢነትን አካፋይነትን አቋዳሽነትን፤ ተባባሪነትን ፤እኔ ብቻ አለማለትን ፤ተጋግዞና ተደጋግፎ መኖርን የሚገልፅ ከፍ ያለ ስብዕና መገለጫ ነው::
በጎነት ለራስ ጤንነት የሚሰጥ ፤ በፈጣሪ ዘንድም ውድ ዋጋ ያለው ነው::በጎነት በማግኘትና ማጣት ስሌት የማይለካ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሌሎች ያለምን ክፍያ የሚደረግ ተግባር ነው:: የአፍ ወይም የቃል ምስጋናን እንኳን የማይጠብቅ ወይም ይሄን እንኳን ለማግኘት ታስቦ የማይደረግ ነው::በጎ ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎች በሕይወታቸው አእምሯዊ እርካታን የሚያገኙ፤ጤናሞችና ደስተኞች መሆናቸውን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
ኢኮኖሚስቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ጠበብቶች በፊናቸው እንዲህ መሰሉ በጎ ፈቃደኝነት ለአንድ ሀገርና ለእዛ ሀገር ሕዝብ ዕድገትና ሕይወት መሻሻል በተናጠልም ሆነ በጋራ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ይናገራሉ። ለተደጋገፉና ለተባበሩ እጆች ለውጥ ቀላል ነው::በጎ ፈቃደኝነትም የህብረተሰብን አኗኗርን ሊያሻሽሉና ሊለውጡ እንዲሁም ሃገርን ሊያሳድጉ የሚችሉ ተግባራትን፤ በራስ ተነሳሽነት፤ ተጨማሪ ክፍያ ወይም ምንዳ ሳይጠየቅበት የሚከወን ተግባር ነው::
ኢትዮጵያና በጎ ፈቃደኝነት ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ትውውቅና ትስስር አላቸው፡ለ ኢትዮጵያውያን የመረዳዳት፣ የተቸገረን የመደገፍ፣ የታመመን የመጎብኘት ልምድ አላቸው፡ይህ የእርስ በርስ መደጋገፍ ለዘመናት አብሮ የኖረ እና ዛሬም ድረስ የዘለቀ ነው::
እዚህ ጋር ለአብነት ትላንትና በአንድ ዳቦ ቤት ያየሁትን ላካፍላችሁ ።አንድ ታዳጊ የሚፈልገውን ዳቦ ለመግዛት አንድ ብር ጎደለው ።አንዱ ምስኪን እናት ለእኔ ዘጠኝ ዳቦ ስጠኝና ለእሱ አንድ ብሩን ሞልተህ የሚፈልገውን ስጠው አሉ።
ይሄን ለራሳቸው ሳይኖራቸው ሌላውን ለመደገፍ ወይም ካላቸው ለማካፈል የፈለጉን በጎ እናት ተግባር የሰሙ አንድ አባት በፊናቸው ‹‹ለእሱም ለእሳቸውም የሚፈልጉትን ስጣቸው››ብለው ለዳቦ ሻጩ 50 ብር ሰጥተው ወጡ። ከዚህ የበለጠ የኢትዮጵያዊያኖችን እርስ በእርስ መደጋገፍ መሰረት ያደረገና በማግኘትና ማጣት ስሌት የማይለካ በጎነት የሚያሳይ ምሳሌ የለም።
በአሁን ወቅትም ሚሊየኖች ባላቸው እውቀትና ሃብት በመላካምነትና በበጎ ፍቃድ ስራዎች ተሳታፊ በመሆን በርካቶችን እየደረሱ ናቸው::መንግስት ይህንን በጎ ተግባር ዕውቀቱ፣ ልምዱና ፍላጎቱ ያላቸውን ሰዎች ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንዲገናኝ በማድረግ ተግባሩን በማስተባበር ወሳኙን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል::
ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃደኞች ቀን በኢትዮጵያ ካሳለፍነው ህዳር 26/2015 ጀምሮ ‹‹በጎ ፈቃደኝነት ለአብሮነት›› በሚል መሪ ቃል በብሔራዊ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል።የበአሉ መከበርም በሕዝቡ ዘንድ ለዘመናት የቆውን የበጎ ፈቃደኝነት አስተሳሰብ ከፍ ለማድረግ አቅም የሚፈጥር ነው::
የበጎ ህሊና ባለቤቶችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የእርስ በርስ የመተዋወቂያ መድረክ በመፍጠር ልምድና ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ ያስችላል።መልካም ተግባሩ ይበልጥ እንዲጎለብትና በርካታ ቅን ልቦናዎች እንዲፈጠሩም ያደርጋል።
ሀገራዊ አንድነትን፤ ሀገራዊ ትስስርና ፍቅርን የሰነቀው የክብረ በአሉ መሪ ቃልም እርስ በእርስ የመተሳሰብ፤ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህልን ማጎልበት ከፍ ሲልም እንደ ሀገር አንድ ሆነን የቆምንበትን የአብሮነት ገመዳችንን የበለጠ ለማጠናከር የሚያግዝ ነው::
በዓሉ በተከበረበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ እና ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት አዋጅ በረቂቅ ደረጃ መዘጋጀቱ ታውቋል:: አገልግሎትን ለማሳለጥ የሚያስችል ሶፍት ዌር ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ መዋሉ ይፋ ሆኗል:: አሁን ወቅትም ፖሊሲውና አዋጁ በተለያየ ደረጃና ቦታ ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል::
ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ እና ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት አዋጅ እውን መሆንም ከበጎ ህሊና የሚመነጭ የተቀደሰ ተግባር ይበልጥ ለማጎልበት ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው:: በጎ ፈቃደኞች ተጠያቂነትን ታሳቢ አድርገው የበለጠ ተግባራቸውን እንዲከውኑ ያግዛሉ።በተግባሩ ዙሪያ የትኛውም ዓይነት ጥርጣሬና ቅሬታ በውስጣችን እንዳይፈጠር ይረዳል።ግልፅነትን ለማስፈንም ጥሩ መደላድል ይሆናል።
በተለይ ወጣቶች በሰላም ግንባታ፣ በማህበረሰብ ልማት፣ በአካበቢ ጥበቃና በብዙ መስኮች በባለቤትነት ስሜት በመንቀሳቀስ ሀገራዊ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ያስችላል።በዚሁ ተግባር ዙርያ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ እንዲያጠናክሩና እንዲቀጥሉበት ያግዛል::
ተግባራቸው በወቅት እንዳይወሰን በተለይም በበጋና ክረምት ብቻ እንዳይወሰን፤ በድንበር እንዳይገደብ የማድረግም ኃይል ይኖረዋል። ሥራው በራሱ የክረምት ወይም የአንድ ወቅት የዘመቻ ሥራ ሆኖ ከሚከናወንበት አሰራርም እንዲላቀቅ የጎላ ሚና ይኖረዋል።
በአጠቃላይ የፖሊሲና አዋጅ መዘጋጀት ወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል በተግባሩ ላይ ያለውን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገር በተጨማሪ በሕዝቡ ዘንድ ለሀገር ዋልታና ማገር የሚሆን የተጠናከረ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲኖር ከፍተና አቅምን የሚፈጥር ነው::
በወጣቶች የተዘጋጀው ሶፍት ዌርም መልካም ተግባሩን ከማሳለጥም ባለፈ ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው::የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንቅስቃሴ አንድ ወጥ በሆነ፤በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እንዲቀጥል ዘርፈ ብዙ ዕድሎችን ይፈጥራል።በውጭም በሀገር ውስጥ የሚገኙ በጎ ሰዎችን ቁጥር ያበራክታል።
ተግባሩ በዳበረ የመረጃ ቋት ተሳልጦ መሰራቱ በጎ ፈቃደኝነት ከባህላዊ ወይም ከዘልማድ ተላቆ ወደ ዘመናዊና የሰለጠነ አሰራር ደረጃ እንዲሸጋገር ያደርጋል:: ለበጎ ፈቃደኝነት የዋለን ጊዜና ገንዘብ፤ተግባሩ እንደ ሀገር እያደረገ ያለውን አስተዋጾኦ በቀላሉ ለመረዳት ያስችላል። በተለይ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን አስተዋጾኦ በቁጥር መናገር የሚቻልበት ግልፅ ስርዓት ይዘረጋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215