ለሁለት ዓመታት የዘለቀው እና አገርና ህዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈለው የሰሜኑ ኢትዮጵያ ግጭት በቅርቡ በፕሪቶሪያ በተደረሰ የሰላም ስምምነት መነሻነት አሁን ላይ የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ታዲያ ዜጎች ከጦርነት አደጋ እፎይታን ያገኙበት ብቻ ሳይሆን፤ ለመኖር የሚያስፈልጓቸውን መሰረታዊ የሚባሉ የምግብ፣ የመድሃኒትና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀየያቸው የሚመለሱበትን ዕድልም ፈጥሯል፡፡ የፈረሱና አገልግሎት ያቋረጡ የውሃ፣ የመብራት፣ የጤና፣ የባንክ፣ የቴሌ፣ የመንገድና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችም በየደረጃው እየተጠገኑና እየተደራጁ ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
ይሄ ዜጎች ከመንግስታቸው ማግኘት የሚገባቸው አገልግሎቶች እንዲያገኙ የመደረጉ ሂደት መሳካት ታዲያ፣ ከመንግስት ያላሰለሰ ጥረት በኋላ በሰላም ስምምነቱ ላይ እንዲካተት መደረጉ አጋዥ ምክንያት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ቀደም ሲል ሲሰራ ከነበረው በተሻለ መልኩ የሚሰሩ ስራዎች ለውጤት መብቃታቸው፤ የሚላኩ ሰብዓዊ ድጋፎችም ለሚመለከታቸው ዜጎች መድረስ መቻላቸው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ መንግስት እንደ መንግስት የወሰደው ግንባር ቀደም ቁርጠኝነት ጉልህ ሚና ያለው ሲሆን፤ የመንግስትን ቁርጠኝነት ተከትሎም በርካታ አጋር አካላት ድጋፍ ወደማድረግ እንዲገቡ፤ በሕወሓት በኩልም በስምምነቱ የገባውን ቃል ወደመፈጸም እንዲያማትር አድርጎታል፡፡
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትም ሆነ በናይሮቢው የጦር አመራሮች የመግባቢያ ስምምነት መሰረት፤ ለምሳሌ፣ ሕወሓት ታጣቂዎቹን በማወያየት ትጥቅ ማስፈታት እና ወደ ተሃድሶ መስጫ ማዕከላት ማስገባት እንዳለበት በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይሄን መነሻ በማድረግም የማወያየት እና በየደረጃው ትጥቅ የማስፈታት እንዲሁም ወደ ተሃድሶ መስጫ ማዕከላት የማስገባት ስራዎችን ስለመጀመሩ ተነግሯል፡፡ ይሄ ደግሞ መንግስት ለጀመረው መልካም ተግባር እንደ አንድ አጋዥ ሂደት የሚወሰድ ሲሆን በሕወሓትም በኩል ለሰላም ስምምነቱ እውን መሆን ሲባል የተጣለበትን ኃላፊነት በፍጥነት መወጣት አንዳለበት የሚያመላክት ነው፡፡
ይሄ በመንግስትም ሆነ በሕወሓት በኩል የታየው አበረታች ተግባር ታዲያ ሰላም ወዳድ የሆነውን ሕዝብ እና ለኢትዮጵያ መልካም የሚመኙ ኃይሎችን ሁሉ ይበል ያሰኘ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ለኢትዮጵያውያን ሰላምን፣ ለኢትዮጵያም ብልጽግናና ዕድገትን የማይመኙ በውስጥም በውጪም ያሉ ሰላም ጠል ኃይሎችን በእጅጉ እንቅልፍ የነሳ፣ ይልቁንም ለሰላም ስምምነቱ እውን መሆን የሚከወኑ ተግባራትን በየምክንያቱ እንዳይሳኩ ለማደናቀፍና በሃሰት ብሮፖጋንዳ ለማጓተት የሚያስችሏቸውን ስትራቴጂዎች ነድፈው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ በተለያዩ ሁኔታዎች እየተገለጡ ናቸው፡፡
ሆኖም በጥቂት ሰላም ጠል ኃይሎች ሴራና አካሄድ የሚዝል የሰላም ክንድ፤ የሚታጠር የሰላም መንገድ፤ የሚዘጋም የሰላም በር አይኖርም፡፡ ለዚህም ነው መንግስትም ሆነ ሕወሓት ለሰላም ስምምነቱ እውን መሆን በየፊናቸው ከሚያከናውኗቸው ተግባራት በተጓዳኝ በሚሰሯቸው ስራዎች አካሄድና ውጤታማነት፣ እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎቻቸው ላይ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሆነው መወያየትን መርጠው ከሰሞኑ በኬንያ ናይሮቢ የተገናኙት፡፡ በዚህም ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን፤ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትም የሚበረታቱና ተጠናቅረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው ስለመሆኑም ነው መረጃዎች ያሳዩት፡፡
በዚህ ረገድ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በመልሶ ግንባታና በሌሎችም የተገለጡ የመንግስትን ቁርጠኝነትና ከፍ ያለ ስራ ያሳዩ እንደመሆኑ፤ ይሄው ተግባር በአጋር አካላት ጭምር ሊታገዝና የበለጠ በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች ተደራሽ እንዲሆን ማስቻል ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ በሕወሓት በኩል የተጀመረው ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ተሃድሶ ማዕከላት የማስገባቱ ተግባርም በአከባቢው ውጥረትን የማርገብና ለዜጎች የሰላም ፍላጎት እውን መሆን ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ እንደመሆኑ፤ ጅምሩ ወደ ላቀ ቁርጠኝነት ተሸጋግሮ የስምምነቱን ተግባራት በፍጥነት ሊተገብረው ያስፈልጋል፡፡
በዚህ መልኩ በመንግስትም ሆነ በሕወሓት በኩል የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያሳዩት ቁርጠኝነትና ጽናት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተለይም በመንገሰት በኩል ለተፈጻሚነቱ ያሳየው ትጋትና ቁርጠኝነት የሚበረታታ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የሰላም ኃይሎችን የሚያስደስትና በዛው ልክ ለሙሉ ድጋፍ የሚያነሳሳ፤ በተቃራኒው ሰላም ጠል ኃይሎችን ምኞት የሚያኮላሽ ነው፡፡ ሆኖም ለስምምነቱ ትግበራ መሳካት የተጀመረው አበረታች ሥራ በሁለቱ ወገኖች ጥረት ብቻ ከዳር የሚደርስ አለመሆኑን መገንዘብ፤ ይልቁንም የሁሉንም ሰላም ወዳድ አካላት ያልተቆራረጠ ድጋፍ የሚሻ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ሰላም ወዳድ ኃይል ለውጤታማነቱ ያላሰለሰ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/20215