በተደጋጋሚ የምንሰማው ቃል ‹‹አከራይ እና ተከራይ›› የሚል ቃል ነው፡፡ ጎበዝ አሁን ችግር እየተፈጠረ ያለው በደላሎች ምክንያት ነው፡፡ እንዲያውም የቤት ኪራይ ያስወደዱብን ከአከራዮች ይልቅ ደላሎች ይመስሉኛል፡፡ ኧረ እንዲያውም እየሄዱ ‹‹ይሄ ቤት እኮ ይህን ያህል ይያዛል፤ ለምንድነው በዚህን ያህል ብቻ ያከራያችሁት?›› ይላሉ አሉ፡፡ አያደርጉም አይባልም፡፡ ዓለም እንዲህ ናት፤ የአንዱ እንጀራ በአንዱ መቸገር ላይ ነው የሚገኝ፡፡ እኔ ግን ከብሩ በላይ ያስቸገረኝ ውሸታቸው ነው፡፡
ከሰሞኑ ለአንድ ጓደኛዬ ቤት ፍለጋ ከላምበረት እስከ ዜሮ ሁለት ያሉ አካባቢዎችን ስንዟዟር ነበር፡፡ ዜሮ ሁለት ኪዳነ ምህረት ከሚባለው አካባቢ አንድ ሀቀኛ ደላላ አጋጥሞን ገርሞኝ ነበር፤ ምክንያቱም እኔ ደላላ ሲባል ሁሉም አጭበርባሪ ነበር ሚመስሉኝ፡፡ ከዚህ ሀቀኛ ደላላ ጋር ስንሄድ ግን ቤቱ ስላላተመቸን ትተነው ወጣን፡፡ ከሀቀኛው ደላላ ጋር ለሌላ ቀን ቀጠሮ ይዘን ስንለያይ አንድ አፈ ጮሌ ደላላ አጋጠመን!
ኧረ ስንት አይነት ሰው አለ ጎበዝ! ‹‹በቃ እንዲያውም ትተነዋል›› ማለት ነበር የቀረኝ፡፡ ‹‹አልተመቸንም›› እያልነው በግድ ለማስያዝ የሚያደርገው ጥረት አንዳንዴ ያስቀኛል፤ ባስ ሲልብኝም ያበሳጨኛል፡፡ ሰው እንዴት ከባለቤቶቹ በላይ ይሆናል? ለነገሩ እኔው ነኝ ጥፋተኛ! ሳይቸግረኝ ‹‹እኛ ቤቱንና የሰዎቹን ፀባይ እንጂ ዋጋውን አናይም›› አልኩት፡፡ ሀብታም አልመስልም?፡፡
በመጀመሪያ ይዞን ሲሄድ ‹‹ዘመናዊ መጸዳጃ ቤት፣ ዘመናዊ ሻወር፣ ዘመናዊ በር ዘመናዊ መስኮት….›› ኧረ እንዲያም ሰዎችንም ዘመናዊ ናቸው ሳይለን አይቀርም! ያው እንግዲህ የደላላ ባህሪ ነው ብለን ተከተልነው፡፡
ስንገባ እንኳንስ ዘመናዊ መጸዳጃና ሻወር አሮጌም የለውም፡፡ በእርግጥ ገና እየተሰራ ያለ ሻወር ይሁን መጸዳጃ ቤት አለ፡፡ እዚህ ላይ ነበር እንግዲህ እያረሩ መሳቅ የመጣው፡፡ ገና ምኑም ያልተጀመረ ሥራ በ15 ቀን ውስጥ ያልቃል ይለናል፡፡ እየሳቅን ሴትዮዋን ጠየቅናት እሷም እየሳቀች እስከ አንድ ወር ውስጥ ሊያልቅ ይችላል አለችን፡፡ ተገረሙ እንግዲህ! የቤቱ ባለቤት ከአንድ ወር ወዲህ እንደማያልቅ እየነገረችን እሱ ‹‹ምኑ ነው ይሄ አንድ ወር የሚወስደው?» ይላታል፡፡
እንዲህ እንዲህ እያልን ከደላላው ጋር ስንዞር ቆይተን አንድ ቤት አሳየን፡፡ ይህኛውን ቤት ወደድነው፤ ለመያዝም ወስነን ቁርጥ ያለውን ዋጋ ለመጠየቅ ባለቤቱን ጥራልን አልነው፡፡ ‹‹ከዚህ ዋጋ ንቅንቅ አይሉም፤ ነግረውኛል›› አለን፡፡ አሁን እንግዲህ እነርሱ ከቀነሱልን እሱ ምን አገባው? ለዋጋውም ባይሆን ለሁሉም ነገር መነጋገር አለብን ብለነው ጠራልን፡፡
ከሴትዮዋ ጋር መነጋገር ጀመርን። ደላላው ግን በመሃል ጣልቃ እየገባ አስቸገረን፡፡ ይህኔ በጣም ተበሳጨሁና ‹‹ቤቱን ብንይዘውም ባንይዘውም ሁለት መቶ ብር እሰጥሃለሁ፤ አሁን ዝም በል ከእሷ ጋር እናውራ›› አልኩት፡፡ መቼም ለዚያች 200 ብር ብሎ አይደል ያን ያህል የሚያግባባ? ከሴትዮዋ ጋር ተግባባን፤ እሱ ‹‹ንቅንቅ አይሉም›› ካለበት ዋጋም ትንሽ ንቅንቅ አሉልን፡፡
በነገራችን ላይ ወደ ኮተቤ አካባቢ ቤት መከራየት ለሚፈልግ ደላላ አያስፈልገውም፡፡ ከበሩ ላይ ‹‹የሚከራይ ቤት አለ›› የሚል ጽሑፍ ይለጠፋል፡፡ በቃ ጉዳዩ ከባለቤቶቹ ጋር ብቻ ያልቃል ማለት ነው፡፡
እንግዲህ የኪራይ ቤት ነገር ከተነሳ አይቀር የሚያወጡት ህግና ደንብ ነው የሚገርመኝ፡፡ በቃ በግቢው ውስጥ ከሚፈቀደው ነገር የሚከለከለው ነገር ይበልጣል፡፡ በዚያ ላይ የቤቱን ኪራይ ተነጋግረው ከጨረሱ በኋላ ሌላ ጣጣ ያመጣሉ፡፡ የበዕውቀቱ ሥዩም ቀልድ ትዝ አለኝ፡፡ አልጋ ይዞ ነው፡፡
ባለቤቷ መጥታ ‹‹ብርድ ልብስ ያስፈልግሃል?›› አዎ፤ ‹‹አሥር ብር ያስጨምራል››፤ አሁንም ትንሽ ቆይታ መጥታ ‹‹አንሶላስ ያስፈልግሃል?›› አዎ፤ ‹‹አሥር ብር ያስጨምርሃል፤ አሁንም ትንሽ ቆይታ መጥታ ‹‹ትራስ ያስፈልግሃል?›› ይህኔ ባስ ሲልበት ‹‹እንዴ! ሴትዮ አልጋ መስሎኝ የተከራየሁ!›› ብሎ ቆጣ ሲል ‹‹ቢሆንም ይለያያል፤ አልጋ በአንሶላ፣ አልጋ በትራስ እና አልጋ ብቻውን ይለያያል›› አለችው፡፡
በዕውቀቱ ሥዩም ለቀልድ ይጠቀመው እንጂ ነገሩስ በእውኑም እያጋጠመ ነው፡፡ የቤቱን ዋጋ ተነጋግረህ ከጨረስክ በኋላ ‹‹የመብራት ይህን ያህል ያስጨምራል፣ የኤሌክትሪክ ምድጃ ይህን ያህል ያስጨምራል፣ የውሃ የምናምን እየተባለ እንደገና የቤቱን ኪራይ የሚያክል ይጨመራል፡፡ እንግዲህ ቤት ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው ቤት የሚከራየው ለዝናብ መጠለያነት ብቻ አይደለም፡፡ ቤቱ መብራት፣ ውሃ፣ መጸዳጃ ቤት ከሌለው ታዲያ ምኑ ነበር ቤት?፡፡
የአከራዮችን ባህሪ በተመለከተ ደግሞ አንድ የታዘብኩትን ልንገራችሁ፡፡ ተከራዩ ፀባይ ካለው፣ ካላመሸ፣ ካልጠጣ፣ ጓደኛ የማያበዛ ከሆነ አከራዮችም ጥሩ እንደሚሆኑ ነበር አይደል የሚገመተው? አንዳንዶቹ ግን የሚበጠብጥ ተከራይ ነው የሚወድላቸው። ሰካራም ተከራይ ነው ልክ የሚያስገባቸው፡፡ አንድ የራሴ አንድ የጓደኛዬ ገጠመኝ ልንገራችሁ፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ካዛንቺስ የተከራየ አንድ ጓደኛዬ ነበር፡፡ ይሄ ጓደኛዬ ምንም አይነት ሱስ የሌለበት፣ ጓደኛም ይዞ የማይገባ ነው፡፡ በሥራ አጋጣሚ ግን አንዳንድ ቀን ያመሻል፤ ያመሻል የምላችሁ ምናልባት እስከ ምሽት 3 ሰዓት ነው፡፡
ይሄ ጓደኛዬ ቤት ሳይገባ 2 ሰዓት ከሆነ ውጭ አልጋ ተከራይቶ ነው የሚያድረው፡፡ እመኑኝ ሁለት ቀን ውጭ አድሯል፡፡ አስቡት እንግዲህ ይህንን ግፍ! ይሄ ልጅ ያን ያህል ጊዜ አብሯቸው ሲቆይ ከነገሩት ህግና ደንብ አንድም አልጣሰም፤ ግን ፀባይ ያለው ልጅ ነው ብለው አላመሰገኑትም፤ እንኳን ማመስገን ግዴታቸውንም አልተወጡም እንጂ!
የዚህን ተቃራኒ ደግሞ ልንገራችሁ፡፡ ይሄኛው እኔው የተከራየሁበት ግቢ ነው፡፡ ከውሃ አጠቃቀም ጀምሮ መውጣትና መግባት ሁሉ በጥንቃቄ ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ ከተከራዮች አንዱ ለቀቀ (በራሱ ይሁን አስለቅቀውት አላወቅኩም)፡፡ ያንን ቤት ሌላ ሰው ተከራየው፡፡ ይሄ ተከራይ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? እስከ ሌሊት 6 ሰዓት የሚያመሽ እልም ያለ ሰካራም! ማምሸቱም ብቻ ቢሆን እኮ ቀላል ነበር፤ አምሽቶና ሰክሮ ይገባና ግቢውን በአንድ እግሩ ያቆመዋል፡፡
አንድ ዕለት ከፍተኛ ክርክር ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ፡፡ ገና ማታ ነው እንዴ ብዬ ሰዓት ሳይ ሌሊት ነው፡፡ ያ ሰካራም ተከራይና ባለቤቱ የጦፈ ክርክር ላይ ናቸው፡፡ ባለቤቱ እየተለሳለሰና እየተለማመጠ ያወራል፤ ተከራዩ ግን በቁጣና በስድብ የተከራይን መብት ያብራራል፤ እንዲያውም የመብቱ ብዛት ለአገሪቱ ተከራይ ረቂቅ ህግና ደንብ የሚያረቅ ነው የሚመስል፡፡ ሲጨቃጨቁ ሴትዮዋም ወጣች፡፡ ያቺ እኛን ትገላምጥ የነበረች ሴትዮ ፀጥ አለች፡፡ እንግዲህ እንዲህ ከሆነ የአከራይ መድሃኒቱ ሰካራም ነው ማለት ነው፡፡
በተለያየ አጋጣሚ እንደምንሰማው ደግሞ ፍጹም ቤተሰብ ሆኖ የሚኖርም አለ፡፡ ተከራዩም አከራዩም ሥርዓት ጠብቀውና ተከባበረው የሚኖሩበት፡፡ እንዲህ ለመሆን ለአከራይም ለተከራይም ልቦና ይስጥልን!፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2011
በዋለልኝ አየለ