ፈረንጆች አሁን ያለንበትን 21ኛውን ክፍለ ዘመን የስልጣኔ ጥግ ይሉታል … አንዳንዶች ደግሞ የዓለም ፍጻሜ ዋዜማ ያደርጉታል:: ሁለቱም እሳቤ አሁን ያለችውን ዥንጉርጉር ዓለም ይገልጻታል ብዬ አስባለሁ:: የእኔና የእናንተ አሁናዊ መልክ እንኳን ከዚህ የዘመን እድፍ ጋር የተለወሰ ነው:: ዘመን የበረከቱን ያክል የሚነጥቀን ብዙ ነገር አለው:: ጊዜ የእድሉን ያክል የሚቀማንና የሚወስድብን ብዙ ማንነት አለው::
ስልጣኔ ጌጥ ብቻ አይደለም፤ ነውርም፣ ኩነኔም ነው:: አረማመድ ካላወቅን፣ አያያዝ ካልቻልን ራሳችንን፣ ታሪካችንን ሊበርዝ የሚችል በርካታ ስውር ገጽ አለው:: የ21ኛው ክፍለ ዘመን እሳቤ በፈጠረውና ግሎባላይዜሽን በሚል ትስስር የተፈበረከው ዓለምን ወደ አንድ መንደር የማምጣት እሳቤ በረከቱ እንዳለ ሆኖ እኛን ከራሳችንና ሌላውንም ከራሱ ነጥቆታል ብዬ አስባለሁ:: አለምን አንድ ቦታ ላይ የማየት አባዜ በፈጠረው የስልጣኔ ልክፍት ምክንያት ተያይዞ በመጣው የዘመን አብዮት ተጽዕኖ ስር የወደቀ በርካታ ማንነት አለ::
ሰው ከዘመን ሲልቅ እንጂ ዘመን ከሰውነት ሲልቅ ውበት የለውም:: ዘመን ከሰውነት ሲልቅ የሚነጥቀን ብዙ ነገር አለው:: ዛሬ ላይ በስልጣኔ ስም ያጣናቸውና እያጣናቸው ያሉ ታሪኮቻችንና ማንነቶቻችን በዘመን መበለጣችን የፈጠረው ጣጣ ነው:: አንዳንዶች ዘመንን በልጠው፣ ከጊዜ ቀድመው ራሳቸውን ሳያስነኩ፣ ታሪካቸውን ሳያጎድሉ በኩራት ይኖራሉ:: ሰው በዘመን ሲበለጥና ዘመንን ሲበልጥ አንድ አይነት አይደለም::
የጠፉ ማንነቶች፣ የተበረዙ ታሪኮች በዘመን የመበለጣችን ምልክቶች ናቸው:: ሰው በጊዜ ሲበለጥ ምንም ነው… የዘመን ባሪያ፣ የጊዜ ሎሌ ከመሆን ያለፈ ጥቅም አይሰጥም:: ይሄ ዘመን ራሳችንን በንቃት የምንጠብቅበት ዘመን ነው:: ሁሉም ስልጣኔ ሊባርከን ወደ እኛ አልመጣም:: የዓለም ስርዐት ሰጥቶ የመቀበል መርህ ነው:: አንድ ስልጣኔ ወደ እኛ ሲመጣ የሆነ ነገራችንን ሊወስድብን ነው:: በጥንቃቄና በማስተዋል ዘመኑን መዋጀት ይኖርብናል::
የምንጠቀማቸው ስማርት ስልኮች፣ የምናያቸው ፊልሞች፣ የምንጫወታቸው ጌሞች የሚሰጡን ተዝናኖት እንዳለ ሆኖ ከጊዜ አኳያ የሚቀሙን ብዙ ነገሮች አሉ:: ጊዜን በንቃትና በብልጠት መቅደም አለብን:: ብዙ ጊዜያችንን ስልካችን ላይ ስናሳልፍ በጊዜ እየተበለጥን ነው:: ብዙ ጊዜያችንን ፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ መገልገያዎች ላይ ስናጠፋ በጊዜ እየተሸነፍን ነው::
ጊዜን የምናሸንፈው የሰጠንን በረከት በእውቀትና በምክንያታዊነት ስንጠቀመው ነው:: ለበጎ ነገር ስንገለገልበት ነው:: ዘመን የሰጠንን በረከት እንዴት፣ ለምን፣ መቼና የት እንደምንጠቀመው ካላወቅን እየጠፋን ነው:: ሰው ራሱን ካጣ ምንም ነው:: በህይወት ውስጥ እንዳናጣው ልንታገልለት የሚገባን አንድ እውነት ራሳችን ነው:: ራሳችንን ያጣን ቀን ሁሉም ነገራችን ይቆማል::
ሰጥቶ የመቀበል መርህ በሚገባ ካልተረዳንው አደገኛ መርህ ነው:: ስልጣኔ ምናችንን እንደሚወስድብን አናውቅም:: አንድ ቀን፣ ድንገት ራሳችንን አንሰንና ጎድለን እናገኘዋለን:: ‹‹ውሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው›› እንደሚባለው፣ እያዝናና እያጫወተ ልናስተካክለው ወደማንችለው የህይወት ቀውስ ይከተናል:: ስልጣኔ ህይወትን በብዙ መንገድ ያቀልልናል:: በዚያው ልክ የሰውን ልጅ ከህይወት ሙላት የማጉደል አቅምም አለው:: ምናችንን እንደሚወስድብን አናውቅም::
ካልነቃን ህልማችንን ሊወስድብን ይችላል:: አስተዋይ ካልሆንን ታሪካችንን፣ ማንነታችንን፣ ባህልና ወጋችንን አንድም ሳይቀር ሊበርዝብን ይችላል:: ዘመን የሰጠን የሆነ ነገር ላይ ብዙ ጊዜያችንን ስናሳልፍ ህልማችንን እያጣን፣ እቅዳችንን እየሳትን ነው ማለት ነው:: ልንሰራው የሚገባንን እንዳንሰራ ጊዜያችንን በመሻማት ከእቅዳችን እንድንዘገይ በማድረግ ወደ ኋላ ያስቀረናል::
ሁሉም ነገር ስርዐት አለው:: ሁሉም ነገር ልክና እውነት የሚሆነው በስርዐት ውስጥ ሲከወን ነው:: ጊዜ የሰጠንን በረከት በአግባቡ መጠቀም ከህይወት ሙላት እንዳንጎድል ያደርገናል የሚለው የዚህ ጽሁፍ ትልቁ መልዕክቴ ነው:: ህይወት ዘልማድ አይደለችም፤ እቅድና ተልዕኮ ናት:: በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ውስጥ የምናደርገው ነገርና የምንሆነው መሆን የህይወታችንን የወደፊት እጣ ፈንታ ይወስነዋል::
በእቅድና በመላ መኖር የዘመናዊነት አንዱ መገለጫ ከመሆኑም በተጨማሪ ለህይወት እሴት የሚጨምር ልምድ ነው እላለሁ:: ከተፈጥሮ መጉደል መሸነፍ ነው:: በዙሪያችን ያሉ ማናቸውም ነገሮች ከተፈጥሮ እንዳያጎድሉን እድል ልንሰጣቸው አይገባም:: በአሁኑ ወቅት ለወጣቱ አደገኛ ከሆኑ ሱሶች ውስጥ አንዱ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ነው::
እንዴት መጠቀም እንዳለብን ብቻ ሳይሆን ምን እየተጠቀምን እንደሆነ ካላወቅንም አደጋ ውስጥ ነን:: አጠቃቀማችን ጊዜያችንን ይወስነዋል:: ምን እየተጠቀምን እንደሆነ ማወቃችን ደግሞ ማንነታችንን ይታደገዋል:: እንዴትና ምን እየተጠቀምን እንደሆነ በማወቅ ጊዜያችንን ከመባከን፣ ራሳችንንም ከመጥፋት ልንታደገው እንችላለን::
በዘመን ስጦታ ከራሳችንና ከታሪካችን ከእውነትና ከተፈጥሮ ጎድለን ሌላ ሆነን እየኖርን ያለንበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው:: ሀገር፣ ትውልድና ማህበረሰብ መልካቸው እስኪጠፋን ድረስ ከማንነታችን ጎድለን እየኖርን ነው:: ባህል፣ ታሪክ ስልጣኔ ውሀ ሳያነሱ ዘመን አመጣሽ በሆነው አውሮፓዊ ስልጣኔ እየተወሰድን ‹‹ማን ናችሁ?›› ስንባል ማንነታችን እየጠፋን የተቸገርንበት ወቅት ላይ እንገኛለን::
እኔና እናንተ በዚህ ዘመን ለሚፈበረኩ ማናቸውም የውሸት ፈጠራዎች የተጽዕኖ ማረፊያ ነን:: ራሳችንን ከዘመን እድፍና ከስልጣኔ ነውር መጠበቅ አለብን:: ራሳችንን መከላከል ካልቻልንና የሰማንውና ያየነው ሁሉ ልክ እንደሆነ የምንቀበል ከሆነ የሌሎች መጠቀሚያ ከመሆን ባለፈ ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን የምናመጣው ትርፍ የለም:: ከሁሉም በፊት የስልጣኔን ትርጉምና ምንነት ማወቅ ይኖርብናል:: ስልጣኔ ራስን ከመውደድና ከመንከባከብ የሚጀምር ነው::
ስልጣኔ ራስን መተው፣ ራስን መርሳት፣ ማንነትን መቀየር አይደለም:: ስልጣኔ ትላንትን መናቅና የኋላን መተው አይደለም:: ስልጣኔ አስተሳሰብን መቀየር ነው:: ስልጣኔ መሰረትና መረጃ ከሌለው የህይወት ልማድ ተላቆ ወደ ላቀ እውነት መሸጋገር ነው:: አርነት የሚያወጣን እውነትና እውቀት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም:: በእውቀት መኖር ደግሞ የዚህ ዘመን አንዱ የስልጣኔ መገለጫ ነው:: ያየነውን ሁሉ ማመን፣ የሰማነውን ሁሉ እንዳለ መቀበል ሳይሆን እውነቱ የቱ ጋ እንዳለ መመርመር ያስፈልጋል::
ይህ ዘመን ዓለም በእውቀት በስልጣኔ እንዲሁም በውሸትና በማስመሰል ጥግ የደረሰችበት ዘመን ነው:: በስልካችን እንኳን ብዙ ውሸቶችን የመቀበልና ብዙ ውሸቶችን የመላክ እድል አለን:: ዘመኑ ዘመናዊ ውሸቶች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመነ ፍዳ ልንለው እንችላለን:: እውነቱ ውሸት፣ ውሸቱ ደግሞ እውነት የሆነበት ግራ የሚያጋባ ስልጣኔ ላይ ነን:: እንደወጣት እንደ አንድ ምርጥ ዜጋ የሰጡንን ሁሉ መቀበል ሳይሆን ‹‹ለምን?›› ብለን መጠየቅ ይኖርብናል::
እስከዛሬ እውነት የሚመስሉ፣ ለእውነት የቀረቡ ፍጹም ውሸቶችን ስንሰማ ኖረናል:: እኛም የፈጠርናቸው ሆኑ በሌሎች የተፈጠሩ ውሸቶች በማህበረሰቡ ላይ ይሄ ነው የማይባል ጥቁር ጠባሳዎችን አሳርፈው አልፈዋል:: ዘመናዊነታችንን ከእውነት እንጀምር:: ስልጣኔን ሀገርን ከመውደድና ሀገርን ከመጠበቅ እንጀምር:: ውሸት እውቀት አይጠይቅም፤ማንም ሊያደርገው የሚችል ነገር ነው::
የላቀው እውቀት በእውነት መኖርና በእውነት ሌሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ነው:: ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ እውነት ትሻለች:: በምንጠቀመው ማህበራዊ ሚዲያ ከቻልን ህዝብ የሚጠቅም፣ ትውልድ የሚቀርጽ አስተማሪ መልዕክት እንጻፍ..እናብብ:: ካልቻልን ደግሞ ዝም እንበል:: ዝምታ ውበት ነው:: ከክፉዎች ጋር አለመተባበርና የክፉዎችን ሀሳብ አለማስተጋባትም አንዱ የዘመናዊነት መገለጫ ነው::
እጆቻችንንና ኮምፒዩተሮቻችንን ለክፋት አንጠቀም:: እስከዛሬ ድረስ በኮምፒዩተር የታገዙ በርካታ ዘመናዊ ውሸቶችን ሰምተናል:: እነዚህ ውሸቶች እኛ ዘንድ ደርሰው የፈጠሩት ማህበራዊ ቀውስ አለ:: ራስን በእውቀትና በጥበብ በማነጽ ለሀገር ባለውለታ መሆን ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል:: እውቀት በምክንያት እንጂ በወሬ አይመራም…እውነት በተግባር እንጂ በይሆናል አይወሰንም::
ወሬኞች ስራቸው ማውራት ብቻ ነው… ሌላ ነገር ስለማይችሉ የተሻለ ነገር መፍጠር አይሆንላቸውም:: እኛ ደግሞ በእውነትና በእውቀት የውሸታሞችን ሴራ ተረት ማድረግ ይጠበቅብናል:: ስልጣኔ የሰው ልጅ የእውቀትና የማስተዋል ውጤት ነው:: የሰው ልጅ እውቀቱን ላልተፈለገ አገልግሎት ሲጠቀምበት ግን ስልጣኔ ስይጥንና ይሆናል::
ዘመኑ የስልጣኔና የስይጥንና ነው:: በርካታ የተሳሳቱና ሀገር አፍራሽ የሆኑ መልዕክቶች የሚነገሩበት:: ስልጣኔው ተራቅቆ በኮምፒዩተሩ ቁልፍ ማንም ቤቱ ሆኖ የፈለገውን የሚጽፍበት፣ የፈለገውን የሚዋሽበት ጊዜ ነው:: ሀገራችን በምክንያት የሚኖር፣ ስለሀገሩ የሚቆረቆር፣ እውነትን፣ እውቀትንና በጎነትን የተላበሰ ትውልድ ትሻለች:: እነዚህ የዘመናዊነት ጸዳሎች የዚህ ትውልድ መገለጫዎች ሊሆኑ ይገባል:: ሌላው ሁሉ የሚጥለን ነው:: ሌላው ሁሉ የሚያጎሳቁለንና ከክብራችን ዝቅ የሚያደርግ ነው::
ስልጣኔና ስይጥንና፣ እውነትና ማስመሰል የአሁኗ አለም አሁናዊ ስቃዮች ሆነው በየቤታችን አሉ:: አንዳንዱ የዘመኑን ጥሩ ነገር ተጠቅሞ ሀገር ይለውጣል፤ አንዳንዱ ደግሞ ስልጣኔውን ባልተፈለገ መንገድ በመጠቀም በውሸት ወሬ የግል አጀንዳውን ያራምዳል:: ማህበረሰባችን የወሬን አደገኝነት ሲገልጽ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› ይላል:: ወሬ ምን ያክል አደገኛ እንደሆነ ይህን አባባል መገንዘብ በቂ ነው::
እኛ ኢትዮጵያውያን ለወሬ ብርቅ አይደለንም:: ለበርካታ ዘመን በወሬና በአሉባልታ ፍቅራችንን፣ አንድነታችንን አጥተን እናውቃለን:: በውሸትና በማጭበርበር አብሮነታችንን፣ ኢትዮጵያዊነታችንን ተነጥቀን እናውቃለን:: ለዚህም እኮ ነው ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› ብለን የተቀኘንው::
አሁንም ከውሸትና ከአሉባልታ አልወጣንም:: የሚጠቅመን ወሬ ሳይሆን ስራ፣ አሉባልታ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ነው:: እንደ ዜጋ፣ እንደወጣት የጊዜ አጠቃቀማችንን ማስተካከል አለብን:: በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለን አቋም ሊስተካከል ይገባል:: ጥሩ ነገር ምንና የት እንደተቀመጠ በመረዳት ሀገራችን አሁን ካለችበት ፈተና እንድትወጣ ማገዝ ይጠበቅብናል::
ወጣትነታችን ለሀገር የምንሰራበት፣ ህልማችንን የምናሳካበት እንጂ የማንም መጠቀሚያ የምሆንበት አይደለም:: በወጣትነታችን ውስጥ ሀገራችንን እንፈልጋት:: ስልጣኔ ለሀገር ከመስራት፣ ለሀገር ከማሰብ፣ ለሀገር ከመሞት የሚጀምር ነው:: ለሀገር ስንሰራ ለራሳችንና ከእኛ በኋላ ለሚመጣውም ትውልድ እየሰራን ነው:: ስልጣኔያችንን ከሀገር እንጀምር:: ሀገር በመውደድ፣ የራስን እውነት ከመቀበል እንጀምር::
ባህልና ታሪክን በማክበር ወደምንፈልገው የስልጣኔ ጥግ መሄድ እንችላለን:: በጊዜ ከመበለጥ ይልቅ ጊዜን በመብለጥ ከፍ ማለት እንችላለን:: የዚህ ዘመን አብዛኛው ስልጣኔ ከራስ ሽሽት ነው:: ሀገርና ህዝብ፣ ታሪክና ባህል የሚለይ ነው:: ከወግ ባህል የሚጣረስ ነው:: እውነተኛ ስልጣኔ ደግሞ በትላንት እውነት ውስጥ ዛሬን መፈለግ እንጂ ትላንትን ትቶ ወደ ነገ መሄድ አይደለም:: የኋለኛው ከሌለ የፊተኛው የለም። እውነተኛ ስልጣኔ በራስ እውነት ውስጥ መኖር … በትላንት ዳና የዛሬን አብራክ መፈለግ ነው::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2015