በ2012 ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አሰራርና ያሉበትን ሁኔታ ተመልክቶ የዘርፉን ፖሊሲ አሻሽሎ አጽድቋል። ፖሊሲው በዋናነት መሰረት ያደረገውም ከህትመትና ከብሮድካስት ሚዲያው በሻገር ከዚህ ቀደም በመገናኛ ብዙኃን ሕጎች ላይ ያልነበሩትን በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሰራጨውን የኦንላይን ሚዲያንና እና የማህበራዊ ሚዲያን እንደ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ በማካተት ተጠያቂነት እንዲኖራቸው በማድረግ ነው::
ይል መልካም ነገር ነው:: ምክንያቱም ዛሬ ላይ እንደ አገር ስናየው ከመደበኛዎቹ መገናኛ ብዚኃን በላይ ማህበራዊ ሚዲያው የህብረተሰቡን ቀልብ በመሳቡ በሚያሰራጨው መረጃም ነገሮችን ከቁጥጥር ውጪ ሲያደርጋቸው ይታያል:: በተለይም ግጭቶችን ከማፋፋም አኳያ ጉልህ ሚና ነበረው:: እናም ይህንን እልባት ለመስጠት በፖሊሲው ላይ የኢትዮጵያ ሚዲያ ምን ዓይነት መልክ ሊኖረው ይገባል፤ አቅጣጫው ወዴት መሄድ አለበት፣ የመንግሥት ድጋፍ ምን ድረስ ሊሆን ይገባል፤ እና መሰል ነገሮችን አካትቶ በአዋጅ መልክ እንዲወጣ ሆኗል:: ይህ ደግሞ በርካታ ችግሮችን የፈታና መፍትሄ የቸረ እንደነበር በጥቂቱም ቢሆን ታይቷል:: እስከመጨረሻው ዘልቋል ወይ ከተባለ ግን ጥያቄ አለበት:: ምክንያቱም ዛሬም ላይ ብዙ ሚዲያዎች ይህንን አጸያፊ ተግባራቸውን ሲከውኑ ይስተዋላልና::
በአዲሱ አዋጅ ብሮድካስት ሚዲያዎች በይዘታቸው እስከ 80 ከመቶ የሚሆነው አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ያስገድዳል:: ይሁን እንጂ የሰሞንኛ ወሬያችንን ብቻ ስናነሳ የውጪው የእግር ኳስ ጉዳይ በስፋት ይዞታል:: መዝናናትና መልካም ነገሮችን በሕዝብ ልቦና ላይ መፍጠር መልካም ቢሆንም ጉዳያችን እርሱ ብቻ ነው ወይ? ሲባል ግን መልሱ አይደለም ነው:: ከዚያ የሚቀድሙ ብዙ ልናሳያቸው የሚገቡን ነገሮች አሉ:: ለምሳሌ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ግጭት ለማስቆም የተደረሰው ስምምነት ጋር ተያይዞ ምን ምን አይነት ለውጦች እየመጡ ነው፤ ምንስ ይቀራል፤ ማን ምን ማድረግ አለበት የሚለው ጉዳይ በስፋት ልንዘግበው የሚገባ ነበር:: ሆኖም በዚህ ዙሪያ በጣም ጥቂት ሥራዎች ብቻ ይስተዋላሉ::
የውጪ ሚዲያዎችም ቢሆኑ ይህንን የሰላም ሂደት ችላ ብለውታል:: ምክንያቱም ይህ ለእነርሱ ጉዳያቸው አይደለም:: ለእነርሱ ዘገባና የገቢ ምንጭ የሚሆነው ግጭት ብቻ ነው:: በዚህ ዘገባቸው ደግሞ ከዚህ በፊት የነበሩትን ብቻ ማንሳት ይቻላል:: የየቀኑ ዜና መክፈቻቸው ኢትዮጵያ ነበረች:: ለብዙዎች የመሰብሰቢያ አጀንዳ እስከመሆንም ደርሳለች:: ዛሬስ ከተባለ ጸጥ ረጭ ብሏል:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ የፈረሰውን እየገነባች ወደፊት እየተራመደች ነው:: በስንዴውም በግዙፎቹ ፕሮጀክቶቿም እየላቀች ነው:: ታዲያ ይህ ለእነርሱ ምን ገቢ ያመጣል፤ እንዴትስ ጉዳያቸው ይሆናል?
አሁን ጉዳዩ መሆን ያለበት የአገር ውስጥ ሚዲያው ነው:: ምክንያቱም ትርፉ የአገር ጉዳይ እንጂ ሌላ አይደለም:: ውጪው ጭምር እንዲደነቅና ዝም እንዳይል ማድረግ ያለበት እርሱ ብቻ ነው:: አሁን አገሪቱ ካለችበት ችግር የሚያላቅቀውን ድጋፍ ማስገኘት የሚችለው መሬት ላይ ያለውን እውነታ ሲያስረዳ ብቻ ነው:: ስምምነቱ ያመጣውን ለውጥና ወደፊት ለመሄድ ምን እንደሚያስፈልግ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት አለበት:: የኢትዮጵያን የለውጥ ምዕራፍ ዘግቦ ይህቺ ናት ኢትዮጵያ ሊል ይገባል:: የዚያን ጊዜ ውጪ ላይ ያለው ማህበረሰብ ሚዲያውን መከተል ይጀምራል:: ይሄኔ የውጪው ሚዲያም ቢሆን ምርጫ ስለማይኖረው ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገሮችን መዘገቡ ይጀምራል::
ለዚህ ደግሞ እንደአገር ጥሩ ነገሮች ተፈጥረዋል:: አንደኛው ለአገር እድገትና ግንባታ የሚጫወተውን ሚና ከፍ ለማድረግ የሙያውን ነጻነት መጠበቅና በመርህ መመራት እንዲችል መንገዶች ተከፍተውለታል:: ይሁንና አሁንም ከህዝብ ይልቅ ቡድኖችን ማዕከል ማድረጋቸው ለሙያው ዕድገት መቀጨጭ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ነው:: እና ምን ይሁን ከተባለ ሰሞኑን የተሰማው ዜና አስደሳች ነገርን ይዞ ብቅ ያለ ይመስላል:: ይህም መገናኛ ብዙኃን ከሰላም ስምምነቱ ጋር የተያያዙ ዘገባዎችን በምን መልኩ መሥራት እንዳለባቸው የሚጠቁም መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑ ተሰምቷል::
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን እንዳስታወቀው በሰላም ስምምነቱ ከተጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ ስምምነቱን ከሚረብሹ ዘገባዎች መታቀብ የሚለው ይገኝበታል። እንዲሁም የሰላም ስምምነቱን ተከትለው የሚወጡ ዘገባዎችም በመልካም እይታና በሚገባቸው ልክ መዘገብ አለባቸው ይላል:: የሰላም ሀሳቦች በምን መልኩ መሰራት እንዳለባቸው የሚጠቁም፣ ለተቋማቱ አቅም የሚፈጥርና እንደ ማጣቀሻ ሊጠቀሙበት የሚችል መመሪያም ተዘጋጅቷልና ከዚህ በኋላ ሁሉም መገናኛ ብዙኃን ከሰላም ስምምነቱ ጋር የተያያዙ ዘገባዎችን ሲሰሩ ሀሰተኛና የጥላቻ ንግግሮችን የያዘ አይሆንም:: ምክንያቱም መመሪያው በሰላም ስምምነቱ የተቀመጠውን ግዴታ መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው።
መመሪያውን መነሻ በማድረግም ባለስልጣኑ ሁሉም መገናኛ ብዙኃን የሚኖራቸውን የሞራል፣ የሙያና ሕጋዊ ግዴታዎችን አክበረው እንዲሠሩ በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል:: የማስተካከልና ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመጡም ያስችላል:: ከምንም በላይ ሁሉም መገናኛ ብዙኃን የሰላም ግንባታ ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ያግዛል:: ምክንያቱም የሰላም ጉዳይ የሕዘብ ጉዳይ ነው:: መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ሁሉ ነገራቸው ሕዝባዊ ነው::
እናም በሰላም መረጋገጥ ላይ መገናኛ ብዙኃን የሚኖራቸው ሚና የማይተካ ሊሆን ይገባል:: ለዚህ ደግሞ ከሙያዊ ሥነምግባርና ከሞራልም ጭምር የሚመነጭ ሥራም ሊሰሩ ይገባል:: የመገናኛ ብዙኃን ሚና የሰላም ስምምነቱ ተሳክቶ ወደ ልማት ለመግባትና ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲያገግሙ ማገዝ ነው:: እናም መገናኛ ብዙኃን የሰላም ስምምነቱ ወደ መሬት ወርዶ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በኃላፊነት መንቀሳቀስ አለባቸው:: ስምምነቱን ከአውዱ ውጪ ባለመተርጎምና አገሪቱ ላይ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀየር የሚያግዝ ሥራ ላይ ማተኮር ያስፈልጋቸዋል::
እያንዳንዱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም የተጎዱት እንዲበረቱና የማኅበረሰቡ የእርስ በእርስ መስተጋብር እንዲጠናከር በማድረግ የሰላም ስምምነቱ ከግብ እንዲደርስ አዎንታዊ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል:: በዚህ ደግሞ ነገ ተስፋ የምናደርጋትን ኢትዮጵያ በሩቅ ሳይሆን በቅርብ እንድናያት እንሆናለን:: በተለያዩ ጊዜያት ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎችን እንዳታስተናግድም እናግዛታለን::
እስከዛሬ በነበረው ነገር ተሳስተናልም ብዙ ተፈትነናልም:: እናም በዚህ ይብቃ ማለት መጀመር የአሁን ሥራችን መሆን አለበት:: ይህን ጫና ለመቀልበስም መንግስትና መገናኛ ብዙኃን የጋራ መግባባት ፈጥረው ሊሰሩ ይገባል:: ለሀገራዊ አንድነት ከእነርሱ በላይ ማንም ስለሌለም የመገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ከሚመለከታቸው አካላት በመቀበል ለህብረተሰቡ ማድረስም ያስፈልጋል::
ክብረ ነገስት
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2015