ስሟ አረጋሽ ዘሪሁን ይባላል። ከወላጆቿ ቤት ትዳር ይዛ እንደወጣች ነው ያረገዘቺው። እርግዝናው አስባበትና ፈልጋው ነው የመጣው። የአብራኳ ክፋይ የሆነ የራሷ ልጅ እንዲኖራት ትመኛለች። እናም ትዳር የመሰረተችበት የመጀመርያ ምክንያቷም ልጅ መውለድን ስለምታስብ ነው። ተከታታይ የወሊድ ክትትል ለማድረግ በመጀመሪያ የሄደችበት ቦታ ካዛንቺስ ጤና ጣቢያ ነበር። እናት ልትሆን በመሆኑ ደስተዋ ከመጥን ያለፈ ነበር። ክትትሉን ለመጀመር የሚያስችለው ቅድመ ምርመራ ሲደረግላት ሁሉ ሁለመናዋ ጥርስ በጥርስ ሆኗል። በደሟ ውስጥ የኤች አይቪ/ኤድስ ቫይረስ እንዳለ ሲነገራት ግን ዙርያ ገባው ጨለማ ሆነባት። መሬት ተከፍታ እንድትውጣት ሁሉ ተመኝታ እንደነበር ታስታውሳለች።
‹‹በፍፁም እውነታውን ልቀበል አልቻልኩም። ምክንያቱም ባለቤቴ ሹፌር ቢሆንም መስክ የሚያስወጣ ሥራ የለውም። በቤተሰቡ ላይ ማግጦ እንዲህ ዓይነት ችግር ያመጣልም ተብሎ አይታማም። ሆኖም ለብዙ ጊዜ እንዴት መጣና ማን አመጣው እየተባባልን ተፋጥጠን ቆይተናል። አንዳችን አንዳችንን ብንጠረጥርና ሺህ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ብንወያይም ቫይረሱ በማናችን ሳቢያ እንደመጣ ማወቅ አልቻልንም።›› የምትለው ባለታሪካችን፤ ቆይቶ የሰፈር ልጆች ተሰባስበው የሚያግዙት አንድ ወጣት እንደነበረ ትዝ እንዳላት ትናገራለች።
ይህ ወጣት ነፍሱን ይማረውና ለእናቱ አንድ ነው። በተኛበት አልጋ ላይ የሚያደርጉለት እንክብካቤና ድጋፍ ይሄን ሰብኣዊነት ታሳቢ ያደረገ ነበር። ሆኖም በፍፁም የደም ንክኪ እንዳልነበራቸው እርግጠኛ በመሆኗ ወጣቱን መጠራጠሯን አቆመች። ዜናው ሲነገራቸው መሬት ላይ ተንበርክካ ፀጉሯን እየነጨች የጀመረቺውን ለቅሶ ለዓመታት አላቋረጠቺውም። የአርባ ቀን ዕድሏን በፀጋ መቀበል አቅቷትም ሌት ተቀን ትንሰቀሰቅ ነበር። አሸዋ ላይ ተንበርክካ ስታነባ ኖራለችም። በእጅጉም በሕይወት በመኖሯ ተስፋ ቆርጣለች።የካዛንቺስ ጤና ጣቢያ የምክር አገልግሎት ባለሙያዎች በቀላሉ ሊያረጋጓት እንኳን አልቻሉም ነበር። በዚህ የተነሳ በሪፈር ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እስከመላክም ደርሳለች።
‹‹ሆስፒታሉ በፊናው ንጋት በተሰኘና አሁን የት እንዳለ የማላውቀው ፕሮጀክት ውስጥ እንድታቀፍ አደረገኝ። ይሄኔ ሲዲ ፎሬ 900 በመሆኑ መድሃኒት አላስጀመሩኝም። ፈጥኖ መድሃት የሚጀምረው ሲዲ ፎሩ 500 የሆነ ነው። የባለቤቴ የሲዲ ፎር መጠን እዚህ መካከል በመሆኑ መድሃኒት የጀመረው ቀድሞኝ ነው። ቆየት ብዬም እኔ ሲዲ ፎሬ 900 ቢሆንም በማርገዜ ምክንያት መድሃኒት ተጀመረልኝ።›› የምትለው አረጋሽ፤ በንጋት ፕሮጀክት አማካኝነት እርሷን ጨምሮ 50 ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው እናቶችን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሰባተኛ ፎቅ ላይ ልጆቻቸውን እንዲወልዱ እንደተደረጉ ታስታውሳለች።
‹‹በየጊዜው አንድ ፌስታል ሙሉ ኪኒን ተሸክሞ መግባት ይሰለቻል። በየቀኑ እስከ 10 ፍሬ የሚደርሰውን መድሃኒት መቃሙም መፈጠርን ያስጠላል። ልጄ በፈሳሽ መልክ የምትወስደው መድሃኒት በራሱ ራሱን የቻለ ራስ ምታት ሆኖብኝ ቆይቷል። ልጄ መድሃኒቱን ከወሰደች በኋላ ከ30 ደቂቃ በፊት ካስመለሳት የግድ ተደግሞ ይሰጣታል። በየጊዜው ለፈጣሪዬ እያለቀስኩ ነበር። መድሃኒቱ ዳግመኛ የመሰጠቱ ጉዳይ በእጅጉ ያማርረኝ ነበር። በየጊዜው በምሬት ወደ ፈጣሪዬ አልቅሻለሁ።›› ትላለች ትናንትን በትዝታ ስታስታውሰው።
ትቀጥልናም ‹‹ያኔ ዘመኑ ጨለማ ነበር። ያኔ የመድሃኒት እጥረት ነበር። በመሆኑም ለረጅም ጊዜ በሲዲፎር መጠን ነበር ተገድበን የቆየነው። ከሦስት መቶ እያለ ነው 500 የገባው። ያኔ እኔ ከ800 እስከ 1ሺህ ይደርስ ነበር ሲዲ ፎሬ። በማርገዜ ነው እኔ ሲዲ ፎሬ 900 እያለ መድሃኒት ልጀምር የቻልኩት ።አሁን ላይ ማንኛውም ቫይረሱ በደሙ ያለበት ሰው መድሃኒት የሚጀምርበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። የደረስንበትን ጊዜ የብርሃን ዘመን ካሰኘኝም እንዱ ይሄ ሁኔታ ነው።›› ትላለች።
ሐኪም ያላትን በመተግበሯ ውጤታማ እንደሆነች፤ ለዚህ ያበቃትም በአግባቡና በሰዓቱ መድሃኒት መውሰዷ መሆኑን ትናገራለች። ቤት ያፈራውን መብላት መጠጣት ሌላው ነው። በእርግዝና ሰዓት ዋናውን የፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት መውሰዷ፣ ልጇ ከተወለደች በኋላ ጡት እያጠባች የምትወስደውን መድሃኒት እስከ ስድስት ወር ድረስ በአግባቡ መከታተሏ ብዙ ነገሯን እንደቀየረውም ታስረዳለች።
ለልጇ በርካታ እንክብካቤዎችን አድርጋለች። እስከስድስት ወር በጡት ከስድስት ወር በኋላምደግሞ በምግብ እየተንከባከበቻት ቆይታለች። ከዚያ ጎን ለጎን በፈሳሽ መልክ መድኃኒቱን እንድትወስድም አድርጋታለች። መድሀኒቱ ከዘጠነኛ ወር በኋላ የተቋረጠ ሲሆን፤ የመጀመርያ ምርመራ እንድታደርግ አደረገቻት። በዚህም በወቅቱ የሰማችው ነገርም የሚያስደስት ሆነላት። ልጇ በተደረገው ምርመራ ነፃ ነሽ ተባለችላት። ከዓመት ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ ደግሞ ነጻ ማረጋገጫ ምርመራ እንድታደርግ ወደ ሀኪም ቤት ወስዳት አሁንም ነፃ እንደሆነች ተነገራት። የዚህን ጊዜ እልል ነበር ያለቺው። ይህ ደስታ ግን እስከመጨረሻው የዘለቀ አልሆነላትም። ሁለተኛ ልጇን ባላሰበቺው ሁኔታ አርግዛ ነበርና በቀደመቺው ልጇ ልክ ልትታደጋት አልቻለቺም።
‹‹ ሁለተኛ ልጄን ማርገዜን ያወቅኩት ለሌላ ምርመራ በሄድኩበት አጋጣሚ ነው። መዘናጋቴ ራሴን ቢያስወቅሰኝም የመጀመርያዋን ባዳንኩበት አግባብ ላድናት ሞክሬ ነበር። ሙከራውን ለመተግበር ብዙ ጥረት ሳደርግም ቆይቻለሁ። በእርግጥ ቀድሜ በአልትራ ሳወንድ ስላልታየሁ የምወልደው ወንድ ይሁን ሴት አላወቅኩም። ቢሆንም ዘር ለማብዛት እግዚአብሄር የሠጠኝን ለመቀበል ተስፋ አድርጌ ሳይሆን ድንገት ሳይታሰብ ያረገዝኳት አሁንም ሴት ነበረች። ሂደቱ አድካሚ በመሆኑ ምንም ያህል ልጠነቀቅ ብሞክርም የቱ ጋር ስህተት እንደፈፀምኩ አላውቅም። ዘጠኝ ወር ደርሶ ሴት ልጅ ወለድኩ። ስትመረመር ቫይረሱ በደሟ ተገኘባት። የጤና ባለሙያዎች ከዚህ በኋላም ልጄን ከቫይረሱ ነፃ የሚያደርጋት መፍትሄ እንዳለ በሚያውቁት ልክ ምክራቸውን ለግሰውኛል። ሆኖም ሜሪ ነፃ ልትሆንልኝ አልቻለችም።›› የምትለው አረጋሽ፤ በምግብና በተለያየ መንገድ ብሎም እሷ በማታውቀው መድሃኒት ስለምትንከባከባት እንኳን ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ያለ ምንም ጉዳት የደረሰባት አትመስልም። ቆንጆና ድንቡሽቡሽ ያለች ነች።
‹‹ ከመጀመርያው ጀምሮ እስከ እዚህ ድረስ መዘናጋቴ እራሴን የልጄ ገዳይ አድርጌ እንድቆጥር አደረገኝ። ደግሞም ቫይረሱ በደምሽ ውስጥ አለ ብሎ የመንገር ድፍረት አሳጣኝ። እንዴት ልንገራት?›› እያለች ራሷን በሰቀቀን ውስጥ የከተተቺው አረጋሽ፤ ለእንደእርሷ አይነት ሰዎች ምክር አላት። ይህም በማንኛውም ጊዜ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራ የየቀኑ ሥራችን መሆን አለበት። ምክንያቱም ራሳችን ባንድንም ለምንወልዳቸው ልጆች እንድንደርስላቸው እንሆናለን ትላለች። እውነት ነው መመርመር ከብዙ ነገር ይጠብቃልና ምክሯ ተግባራዊ ይሁን በማለት ሀሳባችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 13 ቀን 2015 ዓ.ም