ለዚህም ይመስላል የዘንድሮ የጸረ ሙስና ቀን ‹‹ሙስናን መታገል በተግባ›› በሚል መሪ ቃል መከበሩ።በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ስር የሰደደውን ሙስና ለመዋጋት ቀን ከማክበር እና በመድረክ ከማውገዝ የዘለለ የተግባር እርምጃ ይሻል መባሉ።
በየትኛውም ሁኔታ የመንግስት አገልግሎት የሚፈልጉ ዜጎች በየአገልግሎት መስጫው እጅ መንሻ ይጠየቃሉ።ይህ አሰራር ነውር መሆኑ ቀርቶ ህጋዊ የሚመስልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለመንግስታዊ ስራ በመንግስት ተቋም የተቀመጠ ሰራተኛ ለሚሰጠው መንግስታዊ አገልግሎት በግልፅ ገንዘብ መጠየቅና ያለ ፍርሃት መቀበል ከተለመደ ውሎ አድሯል፡፡
‹ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሁት ኖሮ› እንዳለቸው እናት ችግሩ በዚህ ደረጃ የአገር ህልውና ስጋት ከመሆኑ በፊት ተገቢውን ትኩረት ቢሰጠው ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ እንደማይደርስ ብዙዎች ይስማማሉ። ‹‹ሌቦቻችን›› እስኪጎረምሱና ጥርስ እስኪያወጡ ከመጠበቅ ሌብነትን ሲጀምሩ የሚቆነጥጥ አሰራር መዘርጋት ያስፈልግ እንደነበርም እንዲሁ።
‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› እንዲሉ አበው፤ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙ ኃይሎች ችግሩ የከፋ ገጽታ እንዲኖረው አድርገውታል። አገር ባለቤት የሌላት ያህል ስርቆት አንገት የማያስደፋ የአደባባይ ተግባር ሆኖ ታይቷል።
በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በሚባል ደረጃ ዜጎች መብቶቻችውን በእጅ መንሻ የሚያገኝበት ሁኔታ አስገዳጅ ሆኗል። በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንደ ሞኝነት /አላዋቂነት/ የሚታይበት የአዕምሮ ውቅርም እየተፈጠረ ይገኛል።
በፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኩል በተደጋጋሚ የሃብት ማስመዝገብ ቢደረግም ይህም ምዝገባ ለሙስና ተጋላጭ ከሆኑት አካላት ይልቅ ምንም የሌለው የበታች ሠራተኛ ላይ ያተኮረ ከመሆኑ በላይ፤ በበላይ አመራሩ ረገድ ለመመዝገብ ዳተኝነት ቢኖርም የተመዘገበውም ሃብት ይፋ አለመደረጉ ሕብረተሰቡ የተደበቀ ሃብት እንዳይጠቁም ማነቆ ሆኖበታል።
በመንግስት በኩል ችግሩን ለመከላከል የተጀመረው ጥረት አገሪቱን አጋጥሟት ከነበረው የጸጥታ ችግር አንጻር በታሰበው መንገድ መሄድ ባይቻልም አሁን ላይ ሌባን ሌባ ብሎ መጥራት መጀመሩ፤ከዛም ባለፈ ብሄራዊ የጸረ-ሙስና ኮሚቴ በማቋቋም ችግሩን በዘመቻ ለመዋጋት እየሄደበት ያለው መንገድ የሚበረታታ ነው።
ይህንን ተከትሎ በወንጀሉ ተጠርጥረው ሆነ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ሙሰኞች ለህግ እየቀረቡ ያለበት ሁኔታ የሚያበረታታ ቢሆንም ሙስና በአገሪቱ ካለበት ደረጃ አንጻር ገና ብዙ መስራት የሚጠይቅ እንደሚሆን ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
ከሙስና የፀዳች አገር ለመፍጠር የግዴታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረብ ባይጠበቅ ባቸውም፤ የእሳቸውን ጥሪ ተከትሎ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የጸረ ሙስና ክልላዊ ኮሚቴ በሟቋቋም ወደ ሥራ መግባታቸው ጥሩ ጅምር ነው።
ታዲያ ይህ ጅምር ፍፃሜው ያምር ዘንድ ከለመድነው የጸረ ሙስና ያዝ ለቀቅ አሰራር ወጥተን ችግሩን አምርረን የምንዋጋበትንም ቁርጠኝነት መላበስ ይጠበቅብናል። በተለይም መላው ህዝባችን ከሙስና የጸዳች አገር የመፍጠሩ እውነታ የምንመኛትን የበለጸገች አገር ለመፍጠር ወሳኝ አቅም በመሆኑ በዘመቻው የሚኖረውን ተሳትፎ ማሳደግ ይጠበቅበታል።
ሌቦችን ከማጋለጥና ለፍርድ ከማቅረብ በተጓዳኝ ሙስናን የሚያበራታቱና ለችግሩ አቅም የሚፈጥሩ ማህበረሰባዊ ልምዶችንና አባባሎችን በመጠየፍ፤ ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገሉ ምስጉኖችን ማመስገን የሚያስችል አዲስ ሥርዓት መፍጠር፤ በዚህም የነገ ተመስጋኞችን ዛሬ ላይ መፍጠር የሚያስችል ዘር መዝራት ይጠበቅብናል፡፡
ይህን ለማድረግ ደግሞ የተወሰኑ ቡድኖች፣ ግለሰቦች፣ ተቋማት ወይንም የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻቸውን የሚወጡት ኃላፊነት አለመሆኑን በአግባቡ መረዳት ይገባል።ይልቁንም ሙስናን ለመዋጋት የተጀመረው ዘመቻ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ በየፊናው አገራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 13 ቀን 2015 ዓ.ም