ቅን ልቦች በድቅድቅ ጨለማ እንደ አጥቢያ ኮከብ ያበራሉ፣ ብርሃናቸውም ለብዙኃኑ የሕይወት ስንቅ ነው። በጭላንጭሎቻቸው መንገድ ስተው ለሚያማትሩ መንገድ፣ ጎንበስ ላሉት ምርኩዝ፣ ለተቸገሩት እርዳትና ለመልካም ነገር ሁሉ አብነት ሆነው ይታያሉ፡፡ቅን ልቦች በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው ፊትና ኋላ ቀኝና ግራቸውን በንቃት ይመለከታሉ፣ አንድም የምድሪቱን ሌላ ጊዜ ደግሞ የሰማዩን በማሰብ። ብቻ ጥሩ አልም የነገን ማን ያውቃል?
ለቅን ልቦች በሕይወት ውጤታማ መሆን ማለት ቁስ መሰብሰብ አይደለም። በእነርሱ ዘንድ ከቁስ ባሻገር የሀሳብ ልዕልናና ጥሩ የሕሊና እርካታ ወደር የሌለው ደስታ ምንጭ ነው። ቅን ልቦች እርዳታ በሚሹ ሰዎች ጫማ ውስጥ ቆመው መራመድ ይችላሉ፤ መልካም ለመሆን አዋቂ ወይም ጠቢብ ባለፀጋ ወይም ታዋቂ መሆን አይጠበቅባቸውም፣ ቀና ልብና በጎ ሕሊና መታደልን እንጂ። እኛ አወቅን ዘመንን ብለን ጉርብትናን፣ መረዳዳትን፣ መተሳሰብና የመቻቻል ባህላችን ገፍተን የኢትዮጵያዊነት መገለጫችንን አውልቀን ልንጥለው ስንታገል “ አይ መዘመንማ እንዲህ አይደለም ወግ ልማዳችን፣ ሰብአዊነታችን ዘመን የማይሽረው የኢትዮጵ ያዊነታችን አብነት አድርገን በአብሮነት ተጋግዘን መኖር ነው እንጂ” ብለው በተግባር ያሳዩናል።
“ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ነብር ዥንጉርጉ ርነቱን አይተውም” እንዲሉ ይህ ሁሉ ለእኛ የቆየ ወግና ልማዳችን ነው ብንል ማጋነን አይሆንብንም።ሰው በዘር በሐይማኖት ፤ በጎሳና በቋንቋ አጥር ታጥሮ በሚኖርበት በዚህ ዘመን ከሰብአዊነት አልፎ ለተጠማ ውሻ መራራትና ማሰብ አጀብ የሚያሰኝ በጎ ተግባር ነው።
ይህን ጉዳይ ለማንሳት ያነሳሳኝ ትዝብት ነገሩ እንዲህ ነው፣ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በአራዳ ክፍለ ከተማ አራት ኪሎ ወረዳ ዘጠኝ በተለምዶ ባሻ ወልዴ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ለብዙ ዓመታት በቀበሌ ቤት በጉርብትና ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ቦታው ለልማት ተፈልጎ ወደ ሌላ ሰፈር ተዘዋወሩ። ይህ አጋጣሚ እዛው ሰፈር የሚኖሩ ውሾች ከባለቤቶቻቸው አለያያቸው። ባለቤት አልባ የሆኑት ውሾች ለከፋ ችግር ተጋለጡ፣ ታዛ አጥተው ጠዋትና ማታ ቁሩን ረፈድ ሲልም የፀሐይ ሐሩሩና የውሀ ጥሙ ተፈራርቆባቸው የተኮማተረ ጨርቅ መስለዋል። ታዲያ ይህንን ችግሮቻቸው አይተው በዝምታ ለማለፍ ያልመረጡት አባወራና እማ ወራ ችግሮቻቸው በጥቂቱም ቢሆን ለማቃለል አንድ በጎ ሀሳብ አመጡ። እሱም ትንሽ የውሀ መሙያ ጉድጓድ በኮንክሪት ማዘጋጀትና በየቀኑ ውሀ በመሙላት ቢያንስ ጥማቸውን ለመቁረጥ ቆርጠው ተነሱ። እንዳሰቡትም ሲሚንቶ ከበጎ ፈቃደኛ አግኝተው ለውሾቹ ውሃ መጠጫ አሰሩ። ይህን በጎ ተግባር እውን ያደረጉት ሰዎች አቶ ብርሀኑ ለማ እና ባለቤታቸው ወይዘሮ ዘሪቱ ተማም ይባላሉ። ሁለቱ ባለትዳሮች የቀበሌ ቤቶቹ ፈርሰው በዚሁ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ወክማ ወደሚባለው ሰፈር ከመግባታቸው በፊት ባሻ ወልዴ ሰፈር ከ45 ዓመታት በላይ ኖረዋል ።መተዳደሪያቸውም በድሮው ሰፈራቸው መንገድ ጠረዝ ሸራ ወጥረው ሸቀጣ ሸቀጥ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የጀበና ቡና በመሸጥ ነው።
ባለትዳሮቹ ጠንካራ ሰራተኞች ናቸው። ከእሁድ በስተቀር ሁሌም ስራ ቦታቸው ላይ ስለማይጠፉ ባለቤት አልባ የሆኑት ውሾች ውሀ ሲጠማቸው ያስቸግሯቸዋል። አንዳንዴም እቃ ያበላሹባቸዋል፡፡ታዲያ ይህንን ችግር በርህራሔ የተመለከቱት አባወራና እማወራ <<ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ>> አንድም የውሾቹን መጠማትና መንከራተት በአዘኔታ ነበር ያዩት። በሌላ ጎኑ ደግሞ ከጤናቸው አንፃር ውሻ በተፈጥሮው ውሀ ሲጠማው የሚያስከትልበትን የጤና እክል እንዲሁም በሕብረተሰቡ ላይ የሚያመጣው መዘዝ የከፋ መሆኑን በመገንዘብ የውሀ ጉድጓድ አበጅተው እለት ከእለት ውሀ ተሸክመው እያመጡ ማጠጣትን ስራዬ ብለው ተያያዙት። በዚህ መልካም ተግባራቸው የተማረኩ የአካባቢው አንዳንድ ሰዎችም ውሀ እያመጡ ይሞሉላቸዋል፣ የአቶ ብርሀኑም የክትባት ጊዜያቸውን ጠብቀው ማስከተባቸውም ሌላኛው በጎ ምግባራቸው ነው፡፡እንስሳቱና አእዋፋቱም ተነጋግረው ቀጠሮ የያዙ ይመስል ሰዓታቸውን ጠብቀው በውሀ ጥም እንደ ቁርበት የተኮራመተውን ጉረሮቸው ለማረስረስ ዘወትር ወደ ገንዳው ይሄዳሉ።
ለመስጠትም መሰጠት ያስፈልጋልና ቀና አመ ለካከትና አርቆ አሳቢዎች ስንሆን መሠናክሎቻችንና ችግሮቻችን ለመልካም ሀሳባችን አጥር ሊሆኑብን አይችሉም።ይልቁንም መወጣጫ መሠላሎቻችንና የጥንካሬዎቻችን ምንጭ ይሆናሉ እንጂ። አንዳንዴ በጎ አሣቢ ስንሆን እራሰችንን ብቻ አይደለም የምንገነባው ቤተሰቦቻችን፣ ጎረቤቶቻችን ከፍ ሲልም የሀገርን ምሦሦ ነው የምንተክለው ።ከላይ ያየነው መልካም ምግባር ትንሽ ነገር መስሎ ሊታየን ይችላል፣ ነገር ግን የሚያመጣው በጎ ተፅዕኖ የጎላ ነው ።እንዲሁ አርቀን ብናስብ እንስሳት ገፀ በረከቶቻችን እንደሆኑ ይታወቀናል፣ አዳም የሚያስፈልገውን ሁሉም ነገር ተሟልቶለት በመጨረሻ ሲፈጠር አንዱ ስልጣን የተሰጠው እንስሳት ላይ መሆኑን ስንረዳ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳላቸው ለማወቅ አያዳግትም፡፡እኛም ዛሬ እንስሳቱ፣ እፅዋቱ፣በአጠቃላይ ስነ ፍጥረታት ሁሉ የሕይወታችን ግማሽ አካል ናቸው፣ እውነት ለመናገር ግን ተፈጥሮን ማግባባትና ተላምዶ እንደመኖር የሚያስደስት ነገር የለም፣ ምክንያቱ ደግሞ ብንጠብቃቸው ብንከባከባቸው ይበልጥ ተጠቃሚዎቹ እኛው ነን።ያው መልካምነት መልሶ ሚከፍለው ለራስ ነው ይባል የለ? ለዚህም ደግሞ ከላይ ያየናቸው ባለታሪኮቻችን ትክክለኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ልጅአለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 12 ቀን 2015 ዓ.ም