ኢትዮጵያ ምርቶቿን ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና ገበያ ማስገባት እንድትችል የቻይና መንግሥት የሰጠውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም በትኩረት እንደሚሰራ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በቅርቡ አስታውቋል። እድሉ ኢትዮጵያ 1 ሺ 644 የሚደርሱ የተለያዩ ምርቶችን ከቀረጥና ኮታ ነጻ ወደ ቻይና ገበያ ማስገባት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁሟል።
የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያ ምርቶች የቀረጥና ኮታ ነጻ እድል ሰጥቶ እንደነበር ያስታወሰው ሚኒስቴሩ፣ አሁን ደግሞ እድሉ ያካተታቸውን ምርቶች የሚጠቁም ዝርዝር ያካተተ ይፋዊ ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል። ሚኒስቴሩ ይህን ተከትሎም ‹‹ በእጃችን ላይ ያሉ ምርቶችን በመላክና ተመርተው መላክ ያለባቸውን ምርቶችም እንዲመረቱ በማድረግ የተገኘውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚሰራ ›› አስገንዝቧል።
ከቀረጥና ኮታ ነጻ እድሉ ጋር በተያያዘ ያነጋግርናቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና፤ ቀረጥ አንድ ዕቃ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ በታሪፉ መሰረት የሚፈጸም ክፍያ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በተመሳሳይ ከቀረጥ ነጻ ሲባል ደግሞ ምንም አይነት ክፍያ የሌለው መሆኑን ይገልጻሉ። ቻይና የፈቀደችው ከቀረጥና ከኮታ ነጻ ገበያ ከዚህ ቀደም 20 ለሚደርሱ የአፍሪካ አገራት የተፈቀደ መሆኑን ያስታወሱት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ያኔ ኢትዮጵያ እንዳልነበረችበት ተናግረዋል፤ ኢትዮጵያ የዚሁ ከቀረጥ ነጻ የገበያ ዕድል ተጠቃሚ እንድትሆን የተፈቀደላት በቅርቡ በሁለተኛ ዙር እንደሆነ ነው ያመለከቱት።
ኢትዮጵያ ምርቶቿን ከቀረጥና ኮታ ነጻ ወደ ቻይና ገበያ ማስገባት እንድትችል መፈቀዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አቶ ክቡር ይጠቁማሉ። እንደ እርዳታ የሚታይና ቻይና ከአፍሪካ ብሎም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያስችልም ተናግረዋል። ይህን ተከትሎም ወደ ቻይና የሚገባው የምርት መጠን ቁጥሩ ከፍ እያለ ይመጣል ተብሎ እንደሚገመትም ጠቅሰው፣ እድሉ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉ ይጠቁማሉ።
ያልተሸጡ የኢትዮጵያ ምርቶች ካሉ ወደ ቻይና ገበያ የሚገቡበት ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፣ በተመሳሳይ አዲስና ተጨማሪ ምርቶች ማምረት ካስፈለገም እንዲመረቱና ምርትና ምርታማነትን እንዲያድግ ለማድረግ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው ያስታወቁት።
እሳቸው እንዳሉት፤ ቻይና ከዚህ ቀደም 20 ለሚደርሱ የአፍሪካ አገራት በሰጠችው ከቀረጥ ነጻ ገበያ ዘጠኝ ሺህ የሚደርሱ የምርት አይነቶች ወደ ሀገሯ ገበያ እንዲገቡ ፈቅዳለች። ኢትዮጵያም ይህን ዕድል ማግኘቷ ከቡና በተጨማሪ ከዚህ በፊት ያልተመረቱና ወደ ውጭ ገበያ ያልተላኩ ምርቶችን የማምረትና የመላክ ዕድል እንደታገኝ ያስችላል።
በዋጋ ተመጣጣኝ ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ በርካታ የምርት አይነቶች ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና ገበያ እንዲገቡ ዕድል ይሰጣል። በተመሳሳይ ለውጭ ገበያ ቀርበው የማያውቁና ያልተመረቱ ምርቶችን በአዲስ መልክ ለማምረት ተነሳሽነትን ይፈጥራል።
በዚህ ከቀረጥ ነጻ ገበያ ውስጥ ዋናዎቹ ተዋንያን መንግሥትና የንግዱ ማህበረሰብ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ክቡር፣ ይህ ዕድል በተለይ ለኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ ጥሩ አጋጣሚን እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነትም ተናግረዋል።
መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እንደሚፈልገው ሁሉ ማህበረሰቡም ምርቱን አውጥቶ መሸጥ ይፈልጋል ሲሉ ገልጸው፣ ስለዚህ በአገር ውስጥ ያለው ምርት ወደ ውጭ ገበያ ወጥቶ መሸጥ እንዲችል ምርትና ምርታማነትን በስፋት ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባሉ። ከምርታማነት በተጨማሪም በጥራት አምርቶ ተወዳዳሪ በመሆን አገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል ያግዛታል ሲሉ ያብራራሉ።
ሌላው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ሞላ አለማየሁ ይህን ከቀረጥና ኮታ ነጻ እድል አስመልክተው ያነሱት ሃሳብም አቶ ክቡር ገና የጠቀሱትን ሃሳብ ያጠናክራል።
ቻይና አሁን የፈቀደችው ከቀረጥ ነጻ ገበያ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል። የገበያ ፍላጎት በሌለበት ማምረት እንደማይቻል፣ የገበያ ፍላጎት ሲኖር ደግሞ በስፋት ማምረት እንደሚቻል አብራርተው፣ የአገሪቱ አምራቾች በዋጋም ሆነ በጥራት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ባለመሆናቸው ከቀረጥ ነጻ ገበያ መፈቀዱ ይጠቅማቸዋል ይላሉ። ለገበያው ሊያወጡ የሚጠበቅባቸውን ወጪ በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንስላቸውም ይናገራሉ። ይህም ማለት ቀረጥ ተቀርጦባቸው ምርቶቻቸውን ወደ ቻይና ገበያ በሚያስገቡ አገራት ዋጋ የመሸጥ ዕድል ማግኘት ማለት ነው ሲሉ ገልጸው፣ በዚህም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል ነው ያመላከቱት።
ዶክተር ሞላ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከዚህ እድል በሚገባ ለመጠቀም ተወዳዳሪነቷን ከፍ ማድረግ ይጠበቅባታል። ጠቀሜታውን ዘላቂ ለማድረግም በአገሪቱ ያሉ አምራቾች ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
አምራቾቹን ፋይናንስን ከማቅረብ ጀምሮ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል በማቅረብና ከልምድ ልውውጥ አንጻር በተለይም መንግሥት ሊደግፋቸው ይገባል ሲሉ ገልጸው፣ ከመንግሥት በተጨማሪም አምራቾችም የውስጥ አደረጃጀታቸውን አጠናክረው ተወዳዳሪ በመሆን ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ገበያ መላክ አለባቸው። ተወዳዳሪ መሆን ሲችሉም ቀረጥ ኖረም አልኖረ የሚያሳስባቸው ችግር አይኖርም። ቀረጥ እያለም ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ ሲሉ ያብራራሉ።
ቀረጥ ለመክፈል ያወጡት የነበረውን ገንዘብ በምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ ማዋል እንዳለባቸውም ዶክተር ሞላ አስታውቀው፤ በአቅም፣ በፋይናንስና አጠቃላይ በቴክኒክ ራሳቸውን እንዲያደራጁ ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላሉ።
ዶክተር ሞላ ስጋታቸውንም አያይዘው ገልጸዋል። ከቀረጥ ነጻ በሆነው አግዋ ምርቶቻቸውን ለአሜሪካ ገበያ እንዲያቀርቡ ከተፈቀደላቸው ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 38 አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረች አስታውሰው፣ በዚህም የተለያዩ ምርቶችን ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደነበረች ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ከገበያው በመታገዷ በርካታ አምራቾች ሥራቸውን እንዲያቆሙ መገደዳቸውን ገልጸው፣ አገሪቷም የውጭ ምንዛሪ እንድታጣና የሥራ ዕድል እንዲቀንስ መሆኑን አንድ ችግር እንደሆነ ይናገራሉ።
ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ከቀረጥና ኮታ ነጻ ገበያ እድል አለ ብለው ለ10 እና 20 ዓመታት በዘርፉ ለውጥ ማምጣትና ተወዳዳሪ መሆን ካልቻሉ ቻይና የሆነ ጊዜ ላይ ከቀረጥ ነጻ ገበያውን ልክ እንደ አሜሪካ ሰርዣለሁ ብትል የአግዋ ገበያ አይነት ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ነው ያስረዱት።
አቶ ክቡር ገናም ይህን የሚያጠናክር ሀሳብ ነው የሰጡት። ቻይና የፈቀደችው ከቀረጥ ነጻ ገበያ አሜሪካኖች በአግዋ የሚያደርጉት አይነት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህ ውሳኔም የቻይና ውሳኔ እንደሆነና በተመሳሳይ ምርቱ ከአፍሪካ ወደ ቻይና ሲሄድ ነው እንጂ፤ ከቻይና ወደ አፍሪካ ሲመጣ የታክስ ቅነሳ ይደረጋል የሚል ስምምነት አለመኖሩን አስታውቀዋል።
ቻይና ለኢትዮጵያ የፈቀደችው ከቀረጥ ነጻ ገበያ ከአግዋ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አመልክተው፣ ከቀረጥ ነጻ የገበያ ዕድሉ በፈቃደኝነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የተሰጠ በመሆኑ ዋስትናው የሚረጋገጥበት መንገድ አይኖርም ይላሉ። በስምምነት ላይ ሳይሆን በፍላጎት ብቻ የተመሰረተ ነውና፤ ዕድሉን የሰጠው አካል ነገ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት አቶ ክቡር፣ ይህን እድል ወደ ህግና ስምምነት መለወጥ እንደሚያስፈልግም ነው ያመለከቱት። ወደ ህግና ስምምነት ከተለወጠም ዋስትና ሊሆን የሚችል የተሻለ ማረጋገጫ ሊኖር እንደሚችል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አምራቾች በዋጋም ሆነ በምርት ጥራት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠር እንዳለባቸው ያብራሩት ዶክተር ሞላ፤ ቀረጡ መነሳቱ የውጭ ገበያ ፍላጎትን በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ይገልጻሉ። የውጭ ገበያ ፍላጎት ከአገር ውስጥ ገበያ ፍላጎት በበለጠና በተሻለ ዋጋ የሚቀርብበት ነው። ከውጭ ገበያ የሚገኘው ገቢም የጥቅም ድርሻው ቢለያይም አገሪቷን ጨምሮ በዘርፉ የሚገኙ ተዋናዮችን በሙሉ ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉ አብራርተዋል።
ከመጨረሻው አምራች ጀምሮ ለውጭ ገበያ እስከሚያቀርበው አቅራቢ ድረስ ያሉ አካላት እያንዳንዳቸው የጥቅም ድርሻ ይኖራቸዋል ያሉት ዶክተር ሞላ፣ ለዚህም እያንዳንዳቸው ጥራት ያለውና የተሻለ ምርት ለማቅረብ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ ያስገነዝባሉ። ምክንያቱም ቀረጥ ተነሳ ማለት የጥራት መመዘኛዎቹ ተነሱ ማለት አይደለም በማለት ያብራሩት ዶክተር ሞላ፤ ከቀረጥ ነጻ የተፈቀደውን ዕድል ለመጠቀም አምራቾች በዋጋም ሆነ በጥራት ተወዳዳሪ ለመሆን በትጋት መሥራት የግድ እንደሚላቸው አመላክተዋል። በተለይም የቻይና ገበያ የሚፈልገውን የጥራት ደረጃ ለማሟላት በእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ተዋናይ የበኩሉን መወጣትና ብዙ መሥራት እንዳለበት ነው ያስረዱት።
ከፖሊሲና ከስትራቴጂ ጋር በተያያዘም አቅጣጫ በማሳየት ጭምር መንግሥት በዘርፉ ሰፊ ሥራ መሥራት እንዳለበት ጠቁመው፤ አምራቹን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለበት ይጠቁማሉ። ለአብነትም የጥቅም ግጭት ቢፈጠር እንኳ በመንግሥት በኩል እንዴት መፈታት እንዳለበት የተመቻቸ ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል ነው የሚሉት።
በተለይም በቅንጅት በመሥራት ገበያው የሚፈልገውን ምርት በጥራት በማቅረብ ዕድሉን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ያላሰለሰ ጥረት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል። ያ ካልሆነ ግን ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚ ናት የሚል ስም ብቻ እንደሚተርፋት ያስገነዝባሉ።
እንደ ዶክተር ሞላ ማብራሪያ፤ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅና ተወዳዳሪ ለመሆን ፋይናንስ ትልቅ ድርሻ አለው። በአገሪቱ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ካላቸው የፋይናንስ አቅም የተነሳ ለግብርናው ዘርፍ የተመቻቸ የብድር አገልግሎት አይሰጡም፤ ጥራት ያለው ምርት ለማምረትና ተወዳዳሪ ለመሆን አርሶ አደሩን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል።
እርግጥ ነው የግብርናው ዘርፍ በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ በመሆኑ በዝናብ እጥረትም ሆነ በዝናብ ብዛት ስጋት አለበት። የፋይናንስ ተቋማት ቢሰጉም መንግሥት ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ሊሠራበት ይገባል። የፋይናንስ ተቋማቱም አብዛኛው ህዝብ አርሶ አደር እንደመሆኑ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እሱ ላይ እምነት አሳድሮ መሥራትና ክትትልና ድጋፍ በማድረግ አርሶ አደሩ ምርቱን ለውጭ ገበያ በጥራት ማቅረብ እንዲችል መሥራት ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ ወደ ቻይና በምትልካቸው የምርት አይነቶች ብዛትና ጥራት ተወዳዳሪ በመሆን የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባት አቶ ክቡር ያስገነዝባሉ፤ በተለይም ቻይና በዓለም ላይ እያደጉ ካሉ አገራት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘች መሆኗን ጠቅሰው፣ ወደፊት የሚኖረው የገበያ ዕድል እጅግ ሰፊ መሆኑን ከግምት በማስገባት በርትቶና ጠንክሮ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና ገበያ እንዲገቡ ከተፈቀደላቸው ምርቶች መካከል እንደ በግ፣ ፍየል እና ግመል ያሉ የቁም እንስሳት እንዲሁም ስጋ እና የስጋ ውጤቶችና የተፈጥሮ ውሃ ይገኙበታል። እንደ ባቄላ እና ቦሎቄ ያሉትን ጨምሮ ጥራጥሬዎች፣ ሰሊጥ፣ ስንዴ (የስንዴ ዱቄት እንዲሁም ዱረም ስንዴን ጨምሮ)፣ በቆሎ እና አጃም ከቀረጥ ነጻ ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ተመላክቷል። ስኳር ድንች፣ አቮካዶ፣ ብርቱካን ሀባብ፣ የወይን ፍሬ እና ሌሎች ፍራፍሬዎችም ከቀረጥ ነጻ ፍቃድ ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ።
ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በእጅ የተሰሩ አልባሳት እንዲሁም ከእንጨት እና ከቀርከሃ የተሰሩ የቤት እና የቢሮ መገልገያዎች ጭምር ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና ገበያ ማስገባት እንድትችል ተፈቅዷል።
ቻይና ለኢትዮጵያ የፈቀደችው ከቀረጥ ነጻ የገበያ እድል በቻይና በኩል የተሰጠ ስለመሆኑ ሚኒስቴሩ የገለጸ ሲሆን፣ ከቀረጥ ነጻ ገበያው በኢትዮጵያ ላይ ምንም አይነት ግዴታን የማይጥል እንደሆነም አስታውቋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ የተሰለፈችው ቻይና፤ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ቡና በመቀበል 33ኛ ደረጃ ነበረች። በአሁኑ ወቅት ግን የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ቀዳሚ ከሆኑት ሀገራት ተርታ በመሰለፍ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደ ስምንተኛ ደረጃ መጥታለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 12 ቀን 2015 ዓ.ም