ቅድመ -ታሪክ
በድህነት ስትንገዳገድ የቆየችው ጎጆ በአባወራው ድንገቴ ሞት ይበልጥ ተዳፈነች። ይህኔ መላው ቤተሰብ በችግር ተፈተነ። አባት ለቤቱ አባወራ ብቻ አልነበሩም። በላባቸው ወዝ በጉልበታቸው ድካም ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ኖረዋል። አሁን አርሶ የሚያበላ ሸምቶ የሚያጠግብ አባት የለም። ወይዘሮዋ በትካዜ እንደተዋጡ በላይ በላይ የተወለዱ ልጆቻቸውን አስተዋሉ። ሁሉም ለሆድ እንጂ ለሥራ አልደረሱም።
ኀዘኑ ጋብ ብሎ ለቀስተኛው ሲመለስ ከአዲስ አበባ የመጡ የሟች ታላቅ እህት ከወይዘሮዋ ጋር መከሩ። ከወንድማቸው ልጆች አንዱን ወስደው ማስተማር ይችሉ እንደሆን ጠየቁ። እናት ጥያቄያቸውን ለመቀበል አላንገራገሩም። ከልጆ ቻቸው መሀል የአራት ዓመቱን ሕፃን ሁሴን መሀመድን «አደራ» ብለው አስረከቡ።
ሁሴን ተወልዶ ያደገበትን ቀዬ ለቆ አዲስ አበባ ከተመ። ለጊዜው የዕድሜው ለጋነት ቤተሰቡን እንዲናፍቅ አስገደደው። ጥቂት ቆይቶ ግን ሁሉን ረስቶ ከአካባቢው ለመደ። የዘነበወርቅ ሰፈር ለእሱና ጓደኞቹ ምቹ የሚባል ነበር። ውሎ አድሮ ትምህርት ቤት ሲገባ ደግሞ ከሁሉ የሚግባባ ተጫዋች መሆን ጀመረ። ስምንተኛ ክፍል ሲደርስ ግን ይህ እውነት እንደ ጅማሬው አልዘለቀም። ለእሱና ለዕድሜ እኩዮቹ ፈታኝ የሚባል ሆነ።
ወቅቱ የደርግ መንግሥት ወጣቶችን እያፈሰ ውትድርና የሚልክበት ጊዜ ነበር። እንደወጡ መቅረት ብርቅ ባልነበረበት በዚያን ጊዜ ሁሴን ይህ እንዳይሆንበት ተጠነቀቀ። ጠዋት በወጣበት ማታ ሳይመለስ፤ ትናንት በታየበት ዛሬን ሳይከሰት ቀናትን በመደበቅ አሳለፈ። ይህ ድብብቆሽ ታፍሶ ከመሄድ፣ ተገዶ ከመቀጠር አዳነው። እንዲህ መሆኑ ግን አላማዬ ብሎ የያዘውን ትምህርት ሊያደናቅፍ ግድ ነበር።
ሁሴን በድብብቆሽ ያሳለፈው ቆይታ ብዙ ዋጋ አስከፈለው። ሳይማር የዘለለው የትምህርት ጊዜ ተጠራቅሞም ለፈተና እንዳይቀመጥ አገ ደው። አጋጣሚው ሰበብ ሆኖበት ትምህርቱን እስከወዲያኛው ያቋረጠው ወጣት ሰፈር ተቀምጦ መዋልን ለመደ። ዘመድ ቤት ተጠግቶ የሚኖረው የገጠር ልጅ በቀን ሥራ ከመዋል ሌላ ምርጫ አልነበረውም።
እንደዋዛ ትምህርቱን አቁሞ በቀን ሥራ መድከም የያዘው ሁሴን ለኪሱ በቂ ገንዘብ አገኘ። ይህ መሆኑ ደግሞ በራሱ እንዲያምን ምክንያት ሆነው። አሁንም ከአክስቱ ቤት እየኖረ መሆኑ ለቤት ኪራይ እንዳያስብ አድርጎታል። ከሥራ መልስ ያሻውን መንዝሮ የልቡን ፈቃድ ይፈጽማል። ያየውን ለይቶ ያማረውን ገዝቶ ይለብሳል።
አሁን ዘመን ተቀይሮ መንግሥት ተለውጧል። ዛሬ ላይ ሁሴንን በውትድርና ስም የሚያሳድደው የለም። በሰላም ወጥቶ በቸር መመለስ ልምዱ ሆኗል። ያም ሆኖ ግን ትምህርቱን የመቀጠል ሃሳብ የለውም። ሕይወት እንደ ትኖንቱ ቀጥሏል። ከዕለታት በአንዱ ቀን በአክስቱ ቤት አንዲት ለጋ ወጣት ድንገት ደረሰች።
ልጅት የአክስቱ ባል የቅርብ ዘመድ ስለመሆኗ ሰምቷል። እንግዳዋን አባወራው ከገጠር ያመጧት እያስተማሩ ለመርዳት አስበው ነው። ዓለምነሽ ቀልጣፋና ጎበዝ በመሆኗ ትምህርቷን ለመጀመር አልዘገየችም። ቀለም ስትቆጥር ውላ ስትመለስ ደግሞ በሥራው የሚያህላት የለም። ተፈላጊነቷ ከቤተሰብ አልፎ ለአካባቢው ሲተርፍ ተወዳጅነቷ ጨመረ። እሷ ጉልበቷን አትሰስትም በትምህርቷም አትቀልድም። ሁሌም ትማራለች፣ ሌት ተቀን ትደክማለች።
ሁሴንና ወጣቷ ተማሪ ከሌሎች በበለጠ
ተግባብተዋል። ሁለቱም የዘመድ ልጅነታቸውና የሰው አገር ሰውነታቸው ያቀራረባቸው ይመስላል። ባመቻቸው ጊዜ ቀረብ ብለው ይወያያሉ። ሰው በሌለ ጊዜም እየተቀላለዱ ይላፋሉ፣ይታገላሉ። ይህ ቅርበት ግን እያደር መልኩን ይቀይር ያዘ። ጓደኝነታቸው ወደ ፍቅር ተቀይሮም መነፋፈቅ፣ መተሳሰብ ጀመሩ።
በሁለቱም ልብ ውስጥ ያደረው መፈላለግ ፀሐይ የሞቀው እውነት መሆን ሲጀምር ምስጢራቸውን ከቤተሰቡ መደበቅ አልቻሉም። ሁለቱም እውነ ታውን ተናግረው በትዳር እንደሚፈላለጉ አሳወቁ። ዘመዶቻቸው በወጉ መርቀውም ጎጆ እንዲያወጧቸው ጠየቁ። ይህ እንደታወቀ አሳዳጊዎቻቸው ሁለቱን ልጆች በትዳር ለማጣመር ፈቀዱ። እንደ ወግና ልማዱም በሀገር ሽማግሌ ውል አፈራርመው በክብር መርቀው ዳሯቸው።
አሁን ሁሴንና ዓለምነሽ በአዲስ ጎጆ አዲስ ሕይወት ጀምረዋል። ትናንት ያለፉበትን መንገድ እያሰቡም ለትዳራቸው ደፋ ቀና ማለት ይዘዋል። የዘነበወርቅ «ገደል ግቡ» ሰፈር ለጥንዶቹ ኑሮ መልካም ሆነ። አብሮ መኖር የለመደው ሰፈርተኛ እንግዶቹን ሙሽሮች በወጉ ተቀብሎ አላመደ። ጥቂት ቆይቶ አዲሱ ጎጆ በልጅ ሲሳይ ተባረከ። የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ ከቁጥራቸው ተደምራ የቤታቸውን ዓለም በደስታ ሞላች።
ጊዜያት ሲቆጠሩ የቤቱ አቅም ሊፈተን ግድ ሆነ። ሁሴን በጉልበቱ ወዝ ከሚያመጣው ገንዘብ በቀር ሌላ ገቢ የለም። ይህ ብቻ ደግሞ ለቤት ኪራይና ለቤተሰቡ ፍላጎት አይዳረስም። ይህኔ ዓለምነሽ ከባሏ መከረች። በአካባቢው ካለው ጉልት የአቅሟን እያመጣች ብትነግድ እንደሚበጅ አሳመነችው። ሁሴን ሃሳቧን ከልቡ አምኖ አጸደቀላት።
ዓለምነሽ የጉልቱን ሥራ ስትጀምር በርካታ ደንበኞችን አፈራች። ሳቂታነቷ ከትህትና ተጣምሮም ገበያውን ሳበላት። በየቀኑ የያዘችውን ሸጣ ያሰበችውን ቋጥራ መመለስን ለመደች። ሁለት ተጨማሪ ሴት ልጆች ከተወለዱ በኋላ ደግሞ የቤቱ ፍላጎት ጨመረ። ልጆችን ማስተማሩ፣ በአግባቡ ማሳደጉና የቤት ኪራይ መክፈሉ ቀላል አልሆነም።
ወይዘሮዋ ማለዳ የወጣች ከፀሐይ ተቀምጣ ትውላለች። ያመጣችው እንዳይመለስ፣ የገዛችው እንዳይበላሽ ትጥራለች። አተርፋለሁ ያለችበት እንዳያከስራትም ከሁሉ ትግባባለች። ስትግባባ ደንበኞቿን አሳምናና ተለማምጣ ነው። ፈገግ ካላለች ገዢዎቿ አልፈዋት ይሄዳሉ። ካልተለማመጠች ለቤት ለጎጆዋ ቋጥራ አትገባም። አልፈው የሚሄዱትን እየጠራች፣ ቅር ላላቸው እየመረቀች ስለልጆቿ ታስባለች። ስለጎጆዋ ሙላት ታልማለች።
በብርድና ፀሐይ፣ ዝናብና ጎርፍ የእሷና የመስሎቿ አይቀሬ ውሎ ነው። በእዚህ መሀል ካላለፉ እንጀራ ቆርሶ መብላት የለም። እንዲያም ሆኖ አብዝተው የገዙት ሊያከስር፣ ይገኝበታል ያሉት ሊያጎድል ይችላል። እነሱ ግን ሁሌም ቢከፋቸው ሁሌም «ተመስገን » ማለትን ለምደዋል። አንድ ቀን ዓለምነሽ እንደዋዛ በስሟ የተመዘገበችው የኮንዶሚኒየም ዕጣ እንደወጣላት ሰማች። ይህን ባወቀች ጊዜም ደስታዋ ወደር አጣ።
ሁሴን አልፎ አልፎ በቀን ሥራው ውሎ ይገባል። ሥራው ግን እንደቀድሞው በቶሎ አይገኝም። እንዲህ በሆነ ጊዜ ቤቱ ተኝቶ የሚውልበት አጋጣሚ ይበዛል። ዓለምነሽ ጉልት ቆይታ ማታ በድካም ስትመለስ ሁሴንን ተኝቶ አልያም ተቀምጦ ታገኘዋለች። በእሷ ትከሻ የእሱ ተቀምጦ መብላት ደግሞ ሆዷን ማጎሽ ከጀመረ ከራርሟል። ሁሌም በአንድ እጅ ማጨብጨብ መስሎ የሚታያት ወይዘሮ ለልጆቿ ስትል መታገስ እንዳለባት አምናለች።
አሁን ልጆቻቸው እያደጉ ነው። ለእነሱ የትምህርት ወጪ፣ ለልብስና ለሌላም ፍላጎት የሚያስፈልግ ገንዘብ በእጥፍ ጨምሯል። ይህን ለመወጣት ደግሞ በአንድ ሰው ጉልበት ብቻ
የሚሞከር አልሆነም። ወይዘሮዋ ይህን ስታስብ በስሟ የደረሳትን ቤት ለብዙ ታቅደዋለች። ይህን እያቀደች በድካሟ ያጠራቀመቻትን ጥቂት ገንዘብ ታሰላለች። ሁሌም የዕለት ገቢዋን ጣል የምታደርገው ከፍራሻቸው ስር በመሆኑ በየቀኑ ሳታየው አታድርም።
አንድ ቀን ባለቤቷ ከተቀመጠው ገንዘብ ጥቂት ቀንሶ ስለማንሳቱ ደረሰችበት። ይህን ስታውቅ በእጅጉ ተበሳጨች። ለምን ሆነ? ስትልም ከባሏ ጋር ክፉ ደግ ተመላለሰች። የሆነውን ለማስረዳት የሞከረው አባወራ ሰሚ ጆሮ አላገኘም። ዓለምነሽ በእሷ ድካም እሱ እየተጠቀመ መሆኑ ከልቧ አሳዝኗት ቅያሜዋን በግልጽ አሳየችው። ይህ ከሆነ በኋላ ወይዘሮዋ በብስጭት ቤቱን ትታ ለሦስት ወራት ከወንድሟ ቤት ተቀመጠች። ሰላም ወርዶ በእርቅ ከተመለሰች በኋላ ግን የጎጇቸው ሰላም እንደፊቱ አልጠናም።
ሁሴን የባለቤቱን ከቤት ወጥቶ መመለስ በበጎ አልተረጎመውም። በሚስቱ ላይ የነበረው ዕምነት ተሸርሽሮ በጥርጣሬ ይቃኛት ይዟል። በወጣች በገባች ቁጥር ውስጡ የበቀለው የቅናት መንፈስ ሰላም እያሳጣ ያነጫንጨው ጀመር። ዓይኖቹ በክፉ እየሸኟት መቀበሉን ለመዱት። እንደፊቱ ቤት መዋሉን ትቶ መግቢያ መውጫዋን መከታተል ያዘ። የቀረቧትን ሁሉ እየገላመጠ «ተው» ብለው የመከሩትን እያመናጨቀ ቀናትን ቆጠረ። በቤቱ ሰላም ጠፋ፣ ጭቅጭቅ ነገሰ። ክፉ ቃላትና መጥፎ ንግግሮች ተለመዱ።
አባወራው የቀን ከሌት ክትትሉ ከአንድ ጫፍ እንዳደረሰው እርግጠኛ ሆኗል። አሁን በዓመታት ድካም ጎጆዋን ያቆመችበትን የጉልት ሥራ እያመነው አይደለም። ባለቤቱ «ከአንድ ሰው ጋር በፍቅር ወድቃለች» በሚል ጥርጣሬ ዕንቅልፍ ካጣ ሰንብቷል። እሷን ከወዳጅዋ ጋር እጅ ከፍንጅ ለመያዝም መባዘን ጀምሯል። ወጥመዱ ግን አልያዘም፤ ሙከራው እንዳሰበው አልተሳካም። ያም ሆኖ ከድርጊቱ አልታቀበም።
ይህን እያደረገ ባለበት አጋጣሚ ደግሞ ዓለምነሽ በስሟ የደረሳትን ኮንዶሚኒየም ቤት ለመሸጥ መፈለጓን አሳወቀችው። ባል ጉዳዩን ሲሰማ በ«አይደረግም» ስሜት ሞገታት። እሷም ብትሆን ከአቋሟ ውልፍት
እንደማትል ነገረችው። ለሽያጩ ደላሎች ተሯሯጡ ገዥዎች ቀረቡ። ቤቱ ዋጋ ተቆርጦለት ለድርድር ቀረበ።
አሁን የቤተሰቡ ሰላም ይበልጥ ተናግቷል። ልጆች በወላጆቻቸው ጠብና ቅያሜ መሸማቀቅ ከጀመሩ ቆይተዋል። መግባባት ጠፍቶ ጨኸት ለበረከተበት ጎጆ አስታራቂ ሽማግሌ አልተገኘም። መፍትሄ የሚሆን መላ አልተመታም። ጥንዶቹ እንደተኳረፉ፣ ልጆቹ እንደ ደነገጡ፣ ጎረቤት እንደተንሾካሾከ ቀናት ተቆጥረዋል።
አንድ ምሽት ደግሞ ዓለምነሽ ከጉልት ስትመለስ «እዚህ ቤት አላድርም» ስትል ወሰነች። ይህ ውሳኔዋ ጥቂት አልዘገየም። ቤቱን ትታ ለቀናት ከአካባቢው ራቀች። ተመልሳ ከመጣች በኋላ ግን ሁሴን ወጥታ መክረሟን እያሰበ ተብከነከነ። ሊሆን የሚችለውን እየገመተም በንዴት አረረ። ጭንቀት፣ ብሽቀትና ጥርጣሬ አቅሉን አሳጡት።
ሁሴን ከሚስቱ ጋር በቅናት ሰበብ መጋጨት ከጀመረ ወዲህ ማንንም አያምንም። በተለይ ዓለምነሽ ድንገት ልትደበድበው እንደምትችል እያሰበ ይጠራጠራል። ከቤቱ አልፎ የሚሰማው የሰዎች ድምጽም እንደረበሸው ይውላል። ድንገት ወጣ ሲል ከመንገዱ የሚያገጥመውን ወንድ በክፉ ዓይኑ ማየት ልማዱ ሆኗል። አትኩሮ ሲያየው መልሶ የሚመለከተው ካለ ደግሞ ይበልጥ ደሙ ይፈላል። ቤተሰቦቹ የሰውዬውን ማንነት እንዲነግሩት ያስፈራራቸዋል። በቂ ምላሽ ካላገኘም ቀኑን ሙሉ ጥርሱን እየነከሰ በሚስቱ ላይ ሲዝት ይውላል።
ሰኔ 4 ቀን 2003 ዓ.ም
ቀኑን ሙሉ በጉልት ንግድ የዋለችው ወይዘሮ በድካም ዝላለች። ቤቷ ለመግባት ስታስብ ውስጧ ቢከፋም ምርጫው አልነበራትም። የያዘችውን ሸካክፋና ለነገው ውሎዋ አመቻችታ ወደቤቷ አመራች። ጎጆዋ እንደተለመደው በጠብ ድባብ እንደተዋዛ አገኘችው። ልጆቿን ስታይ የምትጽናናው ወይዘሮ የምታየውን እውነት ለመርሳት እየሞከረች ስትጫወት አመሸች። ሁሴን ከልጆቿ ጋር ያመሸ ችበትን ፈገግታ ሲያስተውል ሳቅና ደስታዋ
አበሸቀው። ይህ ሁሉ የሚሆነው እሱን ለማናደድ እንደሆነ እያሰበም መሬት ሲቆረቁር አመሸ።
ምሽቱ ገፍቶ ሁሉም ወደ መኝታው ሲያመራ የአባወራው ዓይኖች ዕንቅልፍን እንደተራቡ ቆዩ። የቀን ውሎውን እያሰበ ራሱን ለማታለል ሞከረ። ዕንቅልፍ ይሉት ጉዳይ ከአካሉ ሊስማማለት አልቻለም። የቤቱ መብራት ከጠፋ ቆይቷል። ባለቤቱና ሦስቱ ልጆቹ በህልም ዓለም እንዳሉ እየተሰማው ነው። እሱ ግን የሚያስበውን ለመፈጸም ጊዜው መድረሱን አውቋል። ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከሰላሳ ሲሆን የሁሴን እግሮች ወደ አንድ አቅጣጫ ተራመዱ። የት እንደሚሄድ ጠንቅቆ ያውቀዋል።
ኮቴ አልባው እርምጃ ከአንድ ጥግ እንዳደረሰው እጆቹ የተሸሸገውን ፍለጋ መራኮት ያዙ። ከመኝታው ስር የፈለጉትን ምስጢር አላጡትም። በጨርቅ የተጠቀለለውን ገጀራ አንስተው ለአዕምሮው አቀበሉት። ገጀራው ለክፉ ቀን በሚል ለራሱ መጠበቂያ ያስቀመጠው ነበር። ሁሴን ጊዜ ማባከን አልፈለገም። አመቻችቶ የያዘውን ገጀራ እንዳጠበቀ ሚስቱ ወዳለችበት መኝታ አመራ።
ግርግዳውን ዳብሶ መብራቱን እንዳበራ ባለቤቱን አተኩሮ ተመለከታት። ቀን የዋለችበት ድካም በእንቅልፍ አሸንፎ «ዧ» ብላ ተኝታለች። ከወለሉ የተኙትን ልጆች መላልሶ ተመለከታቸው። እነሱም ልክ እንደሷ በእንቅልፍ ዓለም ወድቀዋል። ሁሴን ገጀራውን እንደያዘ ወደባለቤቱ አናት ቀረበ። የሰነዘረውን አልመለሰውም። ሁለት ጊዜ ደጋግሞ አሳረፈባት። ጭንቅ ይዟት መንፈራገጥ ስትጀምር ከመሳቢያው የተቀመጠውን የሽንኩርት ቢላዋ አስታወሰ። ስለቱን አንገቷ ላይ ለማሳረፍ ጊዜ አላጠፋም።
ድምጽ ሰምታ ድንገት የባነነችውን የመጀመሪያ ልጁን ሲመለከት ቢላዋውን አንስቶ የቀኝ አንገቱን መገዝገዝ ጀመረ። ልጅቷ እየሆነ ባለው ነገር ብርክ እንደያዛት አባቷ ወገብ ላይ ተጠመጠመች። ራሱን ስቶ በጀርባው እንደወደቀ ቤቱ በእናት አባቷ ደም መታጠቡን አስተዋለች። ውድቅቱ በልጆቹ የ«ድረሱልን» ጨኸት ተደበላለቀ። የዘነበወርቅ «ገደል ግቡ» ሰፈር በሕፃናቱ እሪታ ታወከ።
የፖሊስ ምርመራ
አስቸኳይ የስልክ ጥሪ የደረሰው ፖሊስ ከስፍራው ተገኝቶ ባልና ሚስቱን በአምቡላንስ ሆስፒታል አድርሶ ምስክሮችን ለይቷል። ወይዘሮ ዓለምነሽ ከሆስፒታል ስትደርስ እስትንፋሷ ቢኖርም በደረሰባት የከፋ ጉዳት ሕይወቷን ማትረፍ አልተቻለም። ሁሴን የተለየ ጥበቃ እየተደረገለት ህክምናውን እንዲያጠናቅቅ ተደረገ። ራሱን አውቆ ማገገም ሲጀምርም የሆነውን ሁሉ አምኖ ቃሉን ለፖሊስ ሰጠ።
ልጆቹ አባታቸው በየቀኑ እናታቸው ላይ ይዝትባት እንደነበር ተናግረው ቃላቸውን ሰጡ። ወዳጅ ጎረቤቱም የቀድሞ ሰላማዊ ትዳራቸውን አስታውሶ የወንጀሉ መነሻ ቅናት የወለደው ጥርጣሬ መሆኑን መሰከረ። በዋና ሳጅን ግርማ በቀለ መሪነት የተከፈተው የፖሊስ መዝገብ ቁጥር 813/2003 መረጃዎችን ከማስረጃዎች ሰንዶ ጉዳዩን ለክስ ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቀቀ።
ውሳኔ
በጭካኔ ሰው በመግደል ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት የቀረበው ሁሴን መሀመድን ለመዳኘት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱ በ1996 ዓ.ም በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ 593/1/ሀ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል ሁሴን መሀመድን ለክስ አቅርቦ ጥፋተኝነቱን አረጋግጧል። ግለሰቡ በትዳር አጋሩ ላይ የፈጸመውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትን መሠረት በማድረግም ኅዳር 2 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ለእሱ ይገባዋል ለሌሎችም ያስተምራል ያለውን የሞት ፍርድ ወስኗል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2011
በ መልካምስራ አፈወርቅ