ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት በእጅጉ ከሚፈተኑባቸው ችግሮች መካከል ሙስና ወይም ሌብነት አንዱና ዋነኛው ነው። በመላው ዓለም ማለት በሚቻል ደረጃ መጠኑ ቢለያይም ችግሩ በእጅጉ ተንሰራፍቶ ይገኛል ፤ለሀገራትንም የዕድገታቸው ነቀርሳ ሆኖ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል ፡፡
ችግሩ በተለይም ባላደጉ እና እያደጉ ባሉ ሀገራት በስፋት የሚስተዋል ሲሆን የሀገራቱ ሕዝቦችን የመልማት ተስፋ ከማቀጨጭ አንስቶ በድህነታቸው ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለም በየዓመቱ በሙስና እስከ አራት ትርሊዮን ዶላር ይመዘበራል።አፍሪካም በየዓመቱ 50 ቢሊዮን ዶላር በሙስና ምክንያት እንደምታጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እኤአ በ2021 ያስጠናው ጥናት ያመለክታል።
ሀገራችን ቢሆን የችግሩ ሰለባ መሆን ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ በተለይም በመሬት ነክና አገልግሎት ዘርፎች ሙስና ጎልቶ ይስተዋላል። እንደ ግሎበል ፋይናንሽያል ኢንተግሬት ጥናት ከሆነ ሀገሪቱ እኤአ ከ2000 እስከ 2011 ብቻ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሙስና አጥታለች።
የሀገራችን ባህላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ሌብነትን የሚጠየፉ ፤ እንደ ነውር የሚቆጥሩ ቢሆንም ችግሩ ግን ስር ሰድዶ የሀገር ደህንነት ስጋት የሚሆንበት ደረጃ ስለመድረሱን አምርረው የሚናገሩ እየበዙ ነው ።
‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል፡፡›› እና የመሳሰሉት ሙስናን/ሌብነትን የሚያበረታቱ፤ ለሙስና አስተሳሰብ መሠረት የሆኑ አባባሎች በተለይም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ችግሩ ከመጠን በላይ እንዲንሰራፋ የራሱን አስተዋጽዖ አበርክቷል።
ችግሩ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ አብዛኛውን የሀገሪቱን ዜጋ እያስመረረ ያለ፤አገልግሎቶችን በእጅ መንሻ ካልሆነ በስተቀር ማግኘት እስከማይቻልበት ደረጃ እንዲደርስ ያደረሰ ነው ። ይህ እጅግ አስፋሪ የሆነ ትውልድ አጥፊ ድርጊት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረና እየረቀቀ ሄዷል።
በቅርቡም መንግሥት ሙስና/ሌብነት የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው ብሎ በመለየት ይህን አደባባይ የሞላ ወንጀል ለመከላከል ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። የፀረ ሙስና ትግሉ ውጤታማ እንዲሆንም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ችግሩ በእርግማን ብቻ ሊጠፋ እንደማይችል በመገንዘብ መላው ሕዝብ የፀረ ሙስና ትግሉ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባ ፤ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነትና ዝግጁነት እንደሚያስፈልግም አመልክቷል።
ከጸረ-ሙስና ዘመቻው ማግስትም መንግሥት ይህን የብሔራዊ የደህንነት አደጋ ለመከላከል በሌብነት የተጠረጠሩ ከከፍተኛ የመንግሥት ባስልጣናት እስከ ታች የሥራ ኃላፊዎች ድረስ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያደረገ ስለመሆኑ እያየንም፤ እየሰማንም እንገኛለን፡፡
“ግርግር ለሌባ ያመቻል”እንዲሉ፤ ይህንኑ የፀረ ሙስና ትግል ዘመቻ ለመግታት በሚመስል መልኩ በተለያዩ የሀገሪቱ ስፍራዎች የፀጥታ ችግር በመፍጠር የመንግሥትን ትኩረት ለማስቀየር መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ እያስተዋልን ነው፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የማይጠበቁና ድንገታዊ ግጭቶችን በመፍጠር የመንግሥትን ትኩረት ከሙስና ትግሉ ይልቅ ግጭቶችን በመፍታት እንዲወጠር የማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።ይህም በሌብነት የተገኘ ሀብትን በማሸሽ ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ ይታመናል፡፡
በሌላ በኩል በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በሰላም ስምምነት መጠናቀቁ ደስታ ያልፈጠረባቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጨምሮ ሀገሪቱ ከግጭትና ጦርነት ተላቃ ፊቷን ወደ ልማት በማዞር ስኬታማ እንዳትሆን የሚሹ ኃይላት በተመሳሳይ መንገድ ስለጥፋት ሰልፍ የማሳመራቸው እውነታ የሚጠበቅ ነው።
ሀገሪቱ ከለውጡ ማግስት ያለመችው ብልጽግና እውን እንዳይሆን፤ከዚህ ይልቅ በተራዘመ ጦርነትና ግጭት እንዲሁም በሙስናና ሌብነት የተራቆተችና የደቀቀ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር እንድትሆን ረጅም መንገድ ከመሄድ አይመለሱም ።
ይህንንም ምኞታቸውን እውን ለማድረግ የጥፋት ኃይሎችን ከመፍጠርና ከመደገፍ አይመለሱም ፤ለዚህም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ የወለጋ ዞኖች በታጣቁ ኃይሎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
ይህ አጠቃላይ የሆነውን የመንግሥት የልማትና ይህን ተከትሎ የመጣውን የጸረ-ሙስና ትግል ለማሰናከል እየተደረገ ያለ የሞት ሽረት ትግል ለመቀልበስ የመላው ሕዝባችን የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ፡፡
ሕዝቡ ከእያንዳንዱ የሁከትና የብጥብጥ አጀንዳ በስተጀርባ ያለውን እውነታ በሚገባ ተረድቶ ብዙ ዋጋ የከፈለለትን ለውጥ በማስቀጠል የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር የተጀመረው ትግል ስኬታማ እንዲሆን ከፍ ባለ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 12 ቀን 2015 ዓ.ም