በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ልዑክ ወደ አሜሪካ አቅንቶ የአፍሪካ- አሜሪካ ጉባኤ ተሳትፎ ተመልሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከተለያዩ የአሜሪካ መሪዎች እና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር መወያየታቸውም ይታወቃል፡ ፡ በጉባኤው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አሜሪካ በአፍሪካ የተለያዩ ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሰራች እንዳለችም በጉባኤው መጥቀሳቸው ተገልጿል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ያሳለፈቻቸው ፈተናዎች ጠንከር ያሉ መሆናቸውን ለአገር ውስጡም ሆነ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ መግለጹ ለቀባሪው የማርዳት ያህል የሚቆጠር ነው፡፡ በአገር ውስጥ መንግስት ተገዶ የገባበት የህልውና ዘመቻው በዋናነት ተጠቃሽ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ሲያሳርፉት የነበረውን ጫና ቀላል እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡
ይሁንና በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎችም ከየአቅጣጫው ሲያሳድሩ የነበረው ጫና የኢትዮጵያን አንገት ማስደፋት አልቻለም፤ ይልቁኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በየጊዜው ቀርበው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ‹‹የቀረው ይቅር እንጂ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፌ አልሰጥም፤ በኢትዮጵያ ክብርና ጥቅም ከመጣችሁ አንገቴ ይቀላል እንጂ አይደረግም፡፡›› ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡ መንግስት ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የያዛቸው ጽኑ አቋሞች ለዛሬው ወሳኝ ማንነቱ ትልቁን ሚና ተጫውቷል ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተደማጭነት እና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚመጥን ስራ እየሰራች መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለዚህ አንዱ ማሳያ በአፍሪካ – አሜሪካ ጉባኤ ተሳትፎ ላይ የታዩ ሒደቶች ማሳያዎች ናቸው፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተደማጭነቷ ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡ አገሪቱ ታሪካዊ ኃላፊነትን የሚመጥን ስራ እየሰራች ስለመሆኗም ተገልጿል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቀድሞዎቹን ዲፕሎማቶች አነጋግረናል፡፡
አምባሳደር መስፍን ቸርነት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ናቸው፤ እርሳቸው እንደሚሉት ፤ አገር ውስጥ በተፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት በዲፕሎማሲው ዘርፍ አንዳንድ አጋሮቻችን ጋር የተለየ ሐሳብ በማራመዳቸው ምክንያት የዲፕሎማሲ ግንኙነታችን በመጠኑም ቢሆን ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ ነገር ግን የመቀዛቀዙ ዋናው መሰረቱ የአገሪቱን ሉዓላዊ የግዛት አንድነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መንግስት የያዛቸው ግልጽ አቋሞች ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁንም ሆነ አስቀድሞም ቢሆን መንግስት ይፈታሉ ብሎ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች አሉ፡፡
ችግሩ ሊፈታ የሚችለው በሰላምና በድርድር እንደሚሆን ከዛ ውጭ ደግሞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ባስከበረ መልኩ መሆን አለበት። ችግሩ በአፍሪካ መድረክ የአፍሪካ ኅብረት ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ማለትም የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መንገድ በመፍታት አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት በሚለው አቅጣጫ መሰረት ነበር፡፡
ስለዚህ ይላሉ አምባሳደር መስፍን፣ ይህንን በጥብቅ ዲሲፒሊንና በጸና አቋም መንግስት ሲያራምድ ቆይቷል፡ ፡ ይኸው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በተመለከተ ወደ ሰላማዊ ድርድር መሔድ እንዳለብንና የአፍሪካ ኅብረትም ሰፋ ያለ እምነትና አቋም አራምዶ ወደ ስራ መገባቱ የሚታወቅ መሆኑን ይናገራሉ፡ ፡ ስለዚህ መንግስትም ሰላማዊ ስምምነቱን ይፈልግና ያምን ስለነበር የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እንዲሁም ሉዓላዊነት ያከበረ ፣በዘላቂነት ግጭትን የሚያስወግድ የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲሆን ይፈልግ ስለነበር በዚህ አቅጣጫ ችግሩን መፍታት መቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡
አምባሳደር መስፍን እንደሚሉት፤ ይህን ተከትሎ አሁን ያለው እንድምታ ኢትዮጵያ ያራመደችው የአገሪቱን ጥቅም የሚያስከብር፣ ወዳጅን የሚያበዛ ከሁሉ በላይ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ያከበረ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ይሄ አቋም ከመጀመሪያውም ጀምሮ ትክክለኛ ነበር፡፡ ቆይቶም ይህን ሐሳብ የሚቀበሉና የሚደግፉ አካሎች የኢትዮጵያ አቋም ትክክል ስለመሆኑ እየተረዱት መጥተዋል፡፡ ስለዚህ ይህ የሚያሳየው መጀመሪያም ቢሆን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የተቀመጠው አቅጣጫ ትክክለኛ መሰረት መሆንን ነው፡፡
የቀድሞ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፣ ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራትን ቦታ መልሳ ለመያዝ ተደማጭነቷ ከፍ እንዲል ለማድረግ የሚቻለው በዲፕሎማሲ እና በወታዳራዊ ኃይል ጠንካራ ሆና በመገኘት ነው፡፡ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በምግብ ዋስትና ራሷን ለመቻል የጀመረችው ጥረት ተጠቃሽ ነው። የምንከበረውም በምንም ጊዜ ወታዳራዊ ኃይል ሲኖረን ነው፤ አገሮች እኛን ያወቁት በአጼ ምኒልክ ጊዜ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ነው፡፡ ከዛ በፊት ኢምባሲ የለንም፡፡ አድዋን ስናሸንፍ ግን ጣሊያን ማንነታችንን አወቀች፤ ቀጥሎም እንግሊዝ ከዛ ደግሞ ፈረንሳዮች አወቁን፡፡ እነዚህ አገራት እኛን በአግባቡ ያወቁትና ኢምባሲዎችን የመሰረቱት ከአድዋ ጦርነት በኋላ ነው ፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ እንደሚሉት፤ ከዛ በፊት የነበረው ቆንስላ ነው፡፡ ስለዚህም ወደ ኤምባሲ ደረጃ የመጣነው ስናሸንፍ ነው፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት በጣም ትልቅ ሆነን የነበረው ሱማሊያን ካሸነፍን በኋላ ነው፡፡ የቅርቡንም ስንመለከት የኤርትራን ጦርነት በማሸነፋችን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንድንሆን ያስቻለን እንደነበር ይታወቃል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ግን ተደማጭነት የመጣው ዲፕሎማሲያችን ላይ ስላጠናከርን ብቻ ነው ብዬ አላምንም የሚሉት አምባሳደር ጥሩነህ፣ ወታደራዊ ኃይላችንና ጡንቻችንን ስላሳየን ጭምር ነው ብለዋል፡፡ ለዛ ያበቃን አሸናፊነታችን ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹እኛን ሊያጠቁን ፈለጉ፤ ሊገዙንም ሊያዙንም ፈለጉ፡ ፡ ነገር ግን እኛ አሸናፊ ሆነን ወጣን፡፡ እነርሱ ደግሞ ምንም ጊዜ የሚሄዱት ከአሸናፊዎች ጋር ነው፡፡ ስለዚህም ወደእኛ ተመልሰዋል፡፡ አገራችን ዝም ብላ የምትሸነፍ አይደለችም፤ ያለእርሷ ደግሞ ሌሎቹን የአፍሪካ አገራትን መያዝ አይችሉም፡፡ ስለዚህም ያለኢትዮጵያ ውጤት እንደሌለው ተረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ማጣት ስለማይፈልጉም ማጥላላቱን ወደጎን ትተው በሰላምና በመከባበር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መቅረቡን መርጠዋል፡ ፡›› ይላሉ፡፡
በእርግጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይሏ አገሪቱን ባለማስደፈር በኩል ትልቁን ሚና ተጫውቷል፤ ከዚህ ጎን ለጎን አትዮጵያ ‹‹ስንዴ ልመና ይብቃኝ›› በሚል በምግብ ራስን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ራሷን ለመመገብ ቆርጣ እንደተነሳች የሚያሳይ ስራ እየታየ ነው፡፡ ይህም አቋሟ እና የሕዝቡም በአንድነት መነሳሳት እንዲሁም ከመሪው ጋር ማበር በራሱ ለኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ተደማጭ መሆን ትልቁን ሚና የተጫወተ ነው። እነዚህ ዋና ነጥቦች አገራችንን ወደፊት የሚያስፈነጥሯት ሆነው ተገኝተዋል፡፡ እነርሱም ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ መክተት አዋጭ አለመሆኑን እንዲረዱ አድርጓል ብለዋል፡፡
አምባሳደር መስፍን በበኩላቸው፤ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም አቅጣጫ መሰረት የተሰራው ስራ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከብራል ፡፡ አገሪቱን ወደ ተሻለ ከፍታ ይመልሳል፡፡ አንዳንድ አገሮች ተመልሰው የኢትዮጵያን አቋም እንዲያዩና አብረው እንዲሰሩ ያስገደደ አቋም ላይ ለመድረስ ችለዋል። ይህም ትልቅ ውጤታማ የሆነ ስራ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከተቀዛቀዘው የዲፕሎማሲ ግንኙነት አልፈን የአገሪቱን ጥቅም ወደሚያስከብር ወደ ከፍተኛ ደረጃ መምጣት መቻሉን አምባሳደር መስፍን ይናገራሉ። ይህም አብረው ሊሰሩ የሚችሉ አጋሮቻችን እንዲሁም የአፍሪካ ወንድሞቻችንን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ ማኅብረሰብ ጋር ጠንካራ ትስስር እንድንፈጥር ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለውም ውጤት የዲፕሎማሲን ውጤታማነት አመላካች ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ነው፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ ሔደው የጠበቃቸው አክብሮት በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጋር ኳስ ማየታቸው ኳስ ማየት ብቻ ሳይሆን ከዛ ያለፈ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ በራሱ የሚያሳየን ወደቀደመው ነገራችን እየመጣን ስለመሆናችን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ-አሜሪካ በነበረው ጉባኤ ገንዘብ ለመስጠት የተገባው ቃል በራሱ የአሸናፊነታችን ማሳያ ነው፤ ፕሬዚዳንቱን ብቻ ማነጋገራችን ሳይሆን ከሴኩዩሪቲ ኃላፊ ጋር መነጋገራችን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ለብቻችን መነጋገራችን፣ የአይ.ኤም.ኤፍ እና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጋር መነጋገራችን ሁሉ የሚያሳየው አገሪቱ ወደከፍታ እየተመለሰች መሆኑን ነው ይላሉ፡፡
እንደ አገር ተደማጭ ከመሆን የሚገኝ ትርፍ መኖሩን አምባሳደር ጥሩነህ ጠቅሰው፤ ተደማጭ ካልሆንን አገር አንባልም ብለዋል፤ ከ20 ዓመት በፊት ከአፍሪካ አገራት ከመጨረሻዎቹ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነበር፤ አሁን ከሰሃራ በታች አገሮች ከመጀመሪያዎቹ ሁለት አገራት ቀጥለን ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህን ያመጣው አንዱ ተደማጭነት ነው ፡፡ ከተደማጭነታችን ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ፖሊሲያችንም አለ፤ ሌሎችም በርካታ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ነገር ግን ተደማጭነቱ ከፍተኛ እርዳታ፣ ከፍተኛ የንግድ ግንኙነትም ማስከተሉን አስረድተዋል፡፡
ተደማጭነት ሊያመጣልን የሚችለው በተለይ በሚመጡት አስርና ሃያ ዓመታት የዓለምን ኢኮኖሚ ሊያንቀሳቅስ የሚችሉት አፍሪካውያውን ናቸው የሚል መላ ምት አለ፤ ምክንያቱም አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ሕዝቧ ወጣት፣ ስራ ፈጣሪ እንዲሁም ሰራተኛ ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ወርቅ፣ አልማዝ እንዲሁም ሌሎች ማዕድናት ሁሉ ያለው አፍሪካ ውስጥ ነውና ይህ በራሱ እኛን ጨምሮ ሌሎቹንም የአፍሪካ አገራት የሚጠቅም ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ ፡፡
ሌላው ከዓለም እስካሁን ሳይታረስ የቆየ ወይም ሊታረስ ከሚችል መሬት 60 በመቶ ያለው በአፍሪካ ነው፡ ፡ ስለዚህ የምግብን ችግር መፍታት የሚቻለው አፍሪካን በማልማት እንዲሁም አፍሪካን በማሳደግ፣ በአፍሪካ ያለውን የእርሻ መሬት በመጠቀም ነው ወደሚለው ይወስደናል፡፡ አፍሪካን ካልያዙ ደግሞ ገበያም የማግኘት እድላቸው የተመናመነ ይሆናል፡፡ ጥሬ እቃም እናጣለን ብለው ይሰጋሉ፡፡ ስለዚህ አሜሪካም ሆነች ሌሎቹ አፍሪካን መያዝ አለብን ወደሚለው እሳቤ ያመጣቸው መሆኑ የሰሞኑን የአፍሪካ አሜሪካ ጉባኤ እንደሚያስረዳ አምባሳደር ጥሩነህ ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሜሪካና ቻይና ወደ አፍሪካ የማራቶን ሩጫ የጀመሩት ለዚህ ነው፤ አገራቱ ወደ አፍሪካ እየሮጡ ያሉት መንግስተ ሰማይ ለመግባት ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም ነው፡፡ ያንን ለማድረግ ደግሞ ጠንካራ የሆኑ እንደነኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮችን መያዝ አለባቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ምዕራባውያኑም ሆኑ እስያውያን እየፈለጉ ያሉት ሰሜን አፍሪካን ሳይሆን ጥሬ ሀብት ያለው፣ ሰውም በብዛት ያለው ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ነው፡፡ እነዚህን ለመያዝ ደግሞ መያዝ የሚፈልጉት ግብጽን ሳይሆን ኢትዮጵያን ነው፡፡ አሁን ያለው ድምዳሜያቸው ኢትዮጵያን ካልያዝን ተሰሚነት የለንም የሚል ነው፡፡
በመጀመሪያም ቢሆን ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተደማጭ ሊያደርጓት የሚችሉ መሰረታዊ ሁኔታዎች ያሏት አገር ናት ይላሉ አምባሳደር መስፍን ፡፡ ኢትዮጵያ እንደምትታወቀው የአፍሪካ አንድነት መስራች የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ናት፡፡ የብዙ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማት ተቋማት ማዕከል ናት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛው የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ናት፡፡ በዓለም ፖለቲካ ውስጥ የመልከአምድር አቀማመጧ ለብዙ አገሮች ለአፍሪካ ወንድሞቻችን ጨምሮ ለእስያ ብሎም ለአውሮፓ አገሮች ስትራቴጂክ ጠቀሜታዋ የጎላ ነው ሲሉ ያስረዳሉ ፡፡
እንደ አምባሳደር መስፍን ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ባስቀመጠቻቸው ፖሊሲዎች በዓለም ፖለቲካ መድረክ ላይ የምታራምዳቸው አቋሞች አሉ፡፡ በየጊዜው የምንከተላቸው ፖሊሲዎች ብቻ ሳይሆኑ የኣለም ሰላም ጉዳይ፣ የዓለም የአየር ንብረት አጠባበቅ ፣ በሽብርተኝነት እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ትግል ታካሂዳለች፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደምረው ኢትዮጵያ ተደማጭነት እንዲኖራት አድርገዋታል፡፡ በሰላም ማስከበር ከታየ ደግሞ ከአፍሪካ ጀምሮ በተለያየ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭት ባለባቸው አገሮች ሰራዊቷን አዝምታ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የበኩሏን በመወጣት የምትታወቅ አገር ናት፡፡ እነዚህ የፖለቲካ፣ የሰላም እና ደህንነት ስራዎች በአጠቃላይ ተደማምረው ሲታዩ ኢትዮጵያን ተደማጭ እያደረጋት ይገኛል፡፡
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ አቋሟ የሚንሸራተት አለመሆኗን እያሳየች የመጣች አገር ሆናለች፡፡ እንደአገር ሲታይ ጠንካራ ፖሊሲ ያላት፣ ጠንካራ አቋም የምታራምድ፣ በዓለም ሰላም ሆነ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ወደኋላ የማትል ጸንታ የምትቆም አገር መሆኗ ተደማጭ እንድትሆን እያደረጋት መሆኑን ነው አምባሳደር መስፍን የገለጹት፡፡ ከዚህ ባሻገር አፍሪካውያን በተቸገሩ ጊዜ የአፍሪካውያንን ድምጽ ይዛ የምትወጣ አገር መሆኗ ሁሉ ተደማምሮ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን የተደማጭነት ደረጃ ከፍ ሊያደርግ የቻለ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረት በአቋሟ ጸንታ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ወደዓለም አቀፍ መድረክ መሄዷ እንድታተርፍ ያስቻላት ነው ፤ ኢትዮጵያን ብዙ ትብብር የምትፈልግ እንዲሁም በቢዝነስና ኢንቨስትመንት ላይ ትልቅ ሀብት የምትፈልግ አገር ናት ፡፡ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ ብዙ ቴክኖሎጂም ወደአገራችን እንዲገባ እንፈልጋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዘው ከጉባኤው ጎን ለጎን የተካሄዱ ትልልቅ ስምምነቶች መኖራቸውን ያስታወሱት አምባሳደር መስፈን ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀማጭነታቸውን አሜሪካ ያደረጉ ታላላቅ ባለሀብቶች በብዛት ወደ ኢትዮጵያ ያተኮሩበትና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይና ከልዑካቸው ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው የሚያበረታታ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ገብተው በማዕድን፣ በአይሲቲና በመሳሰሉት ላይ ለመስራት የፈለጉበትን ሁኔታ ሲታይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ አንድንረዳ ያደርጋል። ይህንን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል ፡፡
የኢትዮጵያን ተደማጭነት ይበልጥ ለማስቀጠል ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ ዋናው ጉዳይ ነው ፡፡ ሀገራዊ ሰላም ብቅ ጥልቅ የሚል እንዳይሆንና መንግስትም ከዚህ በበለጠ ጠንካራ እንዲሆን ሁሉም የየበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አምባሳደር ጥሩነህ ገልጸዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ጠንካራ ኢኮኖሚና ጠንካራ የጦር ኃይል ሊኖር ይገባል ሲሉ ተናግረው፤ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ የምትሄድ ከሆነ ድሮ ከነበረው የተሻለ ደረጃ ላይ መገኘት ትችላለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 11 ቀን 2015 ዓ.ም