ጃሬድ ዳይመንድ /Jared Diamond/ ይባላሉ። ስመጥር አሜሪካዊ ፕሮፌሰር ናቸው። ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸውና የተፈጥሮ ሃብትን የሚመለከቱ መፅሃፍትን በመፃፍ ይታወቃሉ። ‹‹Collapse–: How Societies Choose to Fail or Succeed›› በሚል ያሳተሙት መጽሐፋቸው ደግሞ ከሁሉ ልቆ ይጠቀስላቸዋል።
ፕሮፌሰሩ እኤአ በ2005 ባሳተሙት በዚህ መፅህፍ ‹‹የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን በተገቢው መንገድ የማይዙና ጥቅም ላይ የማያውሉ ሕዝቦች ላልታሰበ ስርአተ ምህዳራዊ አጥፍቶ የመጥፋት አደጋ ይጋለጣሉ›› በማለት ተፈጥሮን መንከባከብና በአግባቡ መጠቀም የሕልውና ጉዳይ ስለመሆኑ በአፅእኖት አስገንዝበዋል። የሰው ልጆችም ከተፈጥሮ ጋር መታረቅና ጥበቃ ማድረግ ግድ እንደሚላቸው አመላክተዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰሩን ሁሉ የተለያዩ ምሁራንና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች የተለያዩ ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን ተመርኩዘው የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር መታረቅ እንዳለበት በተደጋጋሚ ቢወተውቱም ሰሚ ጆሮ ያገኙ ግን አይመስልም። የሰው ልጅ ተፈጥሮን እየተንከባከበ ለማቆየት ዳተኝነቱን ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡
የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ጋር በገጠሙት ጦርነት አለማችን ለመኖሪያነት የነበራትን ምቹነት እያጣች ትገኛለች። ሰዎች በተለያየ መንገድ ተፈጥሮን እያራቆቱ መሄዳቸው እየዋለ ሲያድር በየፈርጁ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል። ቀውሱም ድሃም ሆኑ ሃብታም የሚባሉ አገራትን ሳይለይ የጥፋት በትሩን ሁሉም ላይ እያሳረፈ ይገኛል፡፡
በሰው ልጅ ኑሮን ለማዘመን በካይ የአኗኗር ዘይቤን በመከተሉ ሳቢያ የምድራችን የሙቀት መጠን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው። በየቦታው ድርቅ እየታየ ነው። ሚሊየኖች በድርቅ ምክንያት በረሃብ እና ቸነፈር እየተገረፋ ናቸው። ግግር በረዶዎቻቸው እየቀለጡ ናቸው፡፡
የውቅያኖሶች መጠን ጨምሯል። በርካታ እንስሳት ከምድረ ገፅ እየጠፉ ናቸው። የተለያዩ ከተሞች በተደጋጋሚ ጎርፍ እየተጥለቀለቁ ናቸው። ወንዞች፣ ሀይቆች እና ግድቦች ደርቀዋል። በደለል ተሞልተዋል። ከዕለት ተዕለት እየጨመረ በመጣው የሙቀት መጨመር ምክንያት በአንዳንድ ሥፍራዎች ወደ በረሃነት እየተቀየሩ ነው።
በሌላ በኩል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ከፍተኛ የዝናብ መጠን አጋጥሟቸዋል። የተለያዩ ከተሞች በከፍተኛ ሙቀት እየተቃጠሉ ናቸው። ጥቅጥቅ ደኖች በእሳት ነበልባል ተበልተዋል። ወንዞች ደርቀው ወደ ሜዳነት ሲቀየሩም ለመመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡
እርግጥ በአየር ንብረት ለውጡ እሳት የበላቸውም ሆነ ቀጣዩ ቀውስ የሚያሰጋቸው የተለያዩ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራትና አጀንዳው ብሎም የፖሊሲያቸው አካል አድርገው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። ሁሉም በየፊናቸው የዓለም ስጋት ለሆነው ችግር መፍትሔ የሚለውም እየከወኑም ናቸው፡፡
በተለይ እኤአ በ2015 በተካሄደው የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አገራት የዓለም ሙቀት መጠን ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺዬስ በላይ እንዳይሆን ለመገደብ በጋራ ለመትጋት ‹‹ተስማምተናል›› በሚል ተጨባብጠዋል።
በዚሁ ጉባዔም ለካርቦን ልቀቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የበለጸጉ አገራት በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን መቋቋሚያ በዓመት እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። እያደጉ ላሉ አገራትም ከካርቦን የፀዳ አረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን በማድረግ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ከስምምነት ተደርሷል።
ይሁንና ድጋፉን ለማድረግ ቃል የገቡት አገራት በቃላቸው ሊገኙ እንዳልቻሉ በተለያየ መልኩ ሲገለጽ ቆይቷል። መንግሥታት ቃል የገቡትን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ተጠያቂ የሚያደርጋቸው አስገዳጅ አካል ያለም አይመስልም። አገራቱ የገቡትን ቃል ለመተግበር በመዘግየታቸው ዓለማችን ከፍተኛ አደጋ እየተጋፈጠች ትገኛለች።
‹‹የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከተፈለገ ከሁሉም በላይ ያለ ደን ልማት አይታሰብም›› የሚሉ የዘርፉ ምሁራንም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመቀነስ ረገድ የደን ሽፋኑን በከፍተኛ መጠን ማሳደግ ግድ እንደሚል ደጋግመው በመናገር ላይ ተ ጠምደዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ላለው ተፅዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናት። ጊዜ እየቆጠረ የሚከሰተው ድርቅ የሚያሳድረውን ጫናም ሆነ የአየር ንብረት ለውጡን የሚቋቋም አቅም የላትም። መጠነኛ የከባቢ አየር ለውጥን መቋቋም የማትችለው ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀርፃ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ዓመታት አልፈዋል፡፡
አገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል የምታደርገው ግብ ግብ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር የተዛመደ ነው። የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ዝቅተኛ የካርበን ልቀት መጠን እንዲኖር የሚያደርግ አብዮት ነው።
ደኖች ለአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ የካርበን ልቀትን ለመምጠጥ፣ ለብዝሀ ሕይወት ጥበቃ፣ ለመሬት ምርታማነትና ለሰው ልጅ ጤንነት፣ ለማኅበራዊ ኢኮኖሚው ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው። ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ዕድገቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል የምታደርገው ግብ ግብ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር የተዛመደ እንደመሆኑም በተለይ ለደን ልማት የሰጠችው ትኩረት ትልቅ ራዕይን ያነገበ ነው። እንደ አገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከካርቦን ልቀት ለመታደግ ለተያዘው ዓለም አቀፍ ትግል ግብ ስኬትም ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት 25 ቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የራሷን አስተዋጾኦ ከማበርከቷም በተጨማሪ እንደ አገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከካርቦን ልቀት ለመታደግ ለተያዘው ዓለም አቀፍ ጥረትም ጉልህ ፋይዳ እያበረከተች ትገኛለች። አገሪቱ ህዝቦቻችን በማስተባበር የዓለምን ችግር ለመፍታት የራሷን ድርሻ እየተወጣች በመሆኗ ሊያስመሰግናትና እውቅና ሊያሰጣት የግድ ይላል።
በእርግጥ ከቀናት በፊት በዩናይትድ እስቴትስ በተካሄደ ስነ ሰርአት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ለአለማችን ችግር ላበረከተችው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እውቅና ተሰጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄን አስመልክቶ ላሳዩት አመራር ‘የአፍሪካ የላቀ አመራር’ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። እውቅናውን በቦታው በመገኘት ተቀብለዋል፡፡
እውቅና ለኢትዮጵያ ትልቅ ክብርና ማበረታቻ ቢሆንም የአገሪቱን ትጋት ይበልጥ ፍሬ እንዲያፈራ ግን ከእውቅናም ባለፈ ገንዘብን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ሊደረግላት ይገባል። ይህ ደግሞ አገሪቱ እስከ እአአ 2030 ሃያ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተጨፈጨፈ ደንን መልሳ ለማልማት እየሰራች ላለችው ስራ ስኬት የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው ፡፡
በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ምእራባውያን አገራት እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገራት ጋር በቅርበት መስራት የግድ ይላቸዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሯ ችግሩን ለመከላከል እያደረገች ያለችውን ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ በማስተዋወቅ ረገድ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረትና በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 10 ቀን 2015 ዓ.ም