የእንግሊዝ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በመሆን ለታዳጊ ሴቶች እግር ኳስ አሰልጣኞች የክህሎት ማሻሻያ ስልጠና ሰጠ። መሰል ስልጠናዎችን በቀጣይ ለማጠናከር መታሰቡም ተገልጿል።
ይህ የሴቶች እግር ኳስን ማሳደግ ዓላማው ያደረገ የአሰልጣኞች ስልጠና ለሶስት ቀናት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ የታዳጊ ሴቶች የእግር ኳስ አሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ክህሎት እንዳገኙበት ተጠቁሟል። ስልጠናው ለ25 ሴት አሰልጣኞች እንዲሁም ሴቶችን በማሰልጠን ላይ የሚገኙ ወንድ አሰልጣኞች እንደተሰጠም ታውቋል። በስልጠናው ተካፋይ የሆኑትም ከአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ከአጎራባች ከተሞች የተውጣጡ አሰልጣኞች ሲሆኑ፤ በተግባር ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ እየሰሩ የሚገኙ መሆናቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቁሟል።
የእንግሊዝ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ‹‹ግሬት ፉትቦል›› በመባል ከሚታወቀው ፕሮጀክት እና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያካሄደው ይህ ስልጠና፤ ሴት ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች እግር ኳስ እንዲጫወቱና የሴት ቡድን አሰልጣኞችንም በክህሎት በማብቃት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው። ለሶስት ቀናት የተካሄደውን ስልጠናም በኦውን ሳውዝጌት እና የእግር ኳስ ለሰው ልጆች መስራች ቤሊ ቲዮንግኮ አማካኝነት ተሰጥቷል። የሁለት ቀናት ስልጠናው በክፍል ውስጥ ከተሰጠ በኋላም የመጨረሻውና ሶስተኛው ዕለት የ ስልጠና መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በተግባር ተደግፎ ተጠናቋል።
ስልጠናውን ተከትሎ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ኤምባሲው መሰል ስልጠናዎችን በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል። የእንግሊዝ ኤምባሲ ተወካይ ሉሲ ጎርደን፤ ውድድሩ የሴቶችን አቅም ለማጎልበት የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹ ሲሆን እንደ እግር ኳስ ያሉ ስፖርቶችን መጫወት ለታዳጊዎች ያለውን አስፈላጊነት አስረድተዋል። ለአካላዊ ጥንካሬ እና አዲስ ነገርን እንዲማሩም ይረዳቸዋል ሲሉም አክለዋል። ሴቶችም መሰል አጋጣሚዎችን ማግኘት እንዲሁም ተነሳሽነቱም ሊፈጠርባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። በመሆኑም ስልጠናው አሁን ላይ ከአዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን፤ የሴቶች ስፖርት በመላው አገሪቷ መስፋፋት ስላለበት በቀጣይ ስልጠናው ተደራሽነቱን የሚያጠናክር ይሆናል ተብሏል።
ስልጠናውን ከሰጡት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት ኦውን ሳውዝጌት በበኩላቸው፤ ስልጠናው ቀጣይነት ያለው እንደሚሆንና በቀጣይም በአጭርና በረጅም የጊዜ የመስጠት ዕቅድ እንዳላቸው ጠቁሟል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይም የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተከናውኗል። በውድድሩም ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 18 የሚሆናቸው ታዳጊ ሴቶች የተካፈሉ ሲሆን፤ ውድድሩም በአራት ቡድኖች መካከል ነው የተካሄደው። ቡድኖቹ የተመረጡትም በስልጠና ላይ የተካፈሉት ባለሙያዎች ከሚያሰለጥኗቸው መካከል ሲሆኑ ለውድድሩም በጎ ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩ መሆናቸው ታውቋል። ይኸውም የውድድር ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ሴቶች እድሎች ቢመቻቹላቸው ከወንዶቹ በተሻለ ስፖርቱን ማሳደግ እንደሚችሉም ማሳያ እንደሚሆን ተገልጿል። ፌዴሬሽኑም ሴቶች ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደመሆኑ በቀጣይም ከኤምባሲው ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ በሴቶች እግር ኳስ ላይ እየሰሩ ለሚገኙ ባለሙያዎች ስልጠናውን መስጠት እንደሚቀጥል ተነግሯል።
ስፖርት ለሰው ልጆች የሚል መጠሪያ ያለው ፕሮጀክት ማዕከል አድርጎ እየሰራ የሚገኘው እግር ኳስን ብቻ ሳይሆን እንደ አጠቃላይ ማህበረሰብን የመለወጥ አላማም በማንገብ መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ከአሰልጣኞቹ መካከል አንዷ የሆነችው ቤሊ ቲዮንግኮ ናት። ስፖርት በሰዎች መካከል ጤናማ ግንኙነትን የሚፈጥር በመሆኑ የሴቶች እና የታዳጊዎች ተሳትፎ ከፍተኛ ሊሆን ይገባዋል ብላለች። ስፖርት ሴቶችን በማነቃቃት ከፍተኛ ሚና ያለው ከመሆኑም ባለፈ የወደፊት ሕይወታቸውንም የተቃና እንዲሆን እንደሚያግዝም ጠቁማለች።
ስልጠናውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በመገኘት ያስጀመሩ ሲሆን፤ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጋር በመሰል ስልጠናዎች ላይ በጋራ በመሆን እንደሚሰሩ መግለጻቸውንም ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015