ያለፉት ሰማንያ ዓመታት ለእማማ ሁሉአገርሽ ተሰማ በጎና ምቹ አልነበሩም። በእነዚህ ጊዜያት አብዛኛው የሕይወት መንገድ ጎርባጣና ሻካራማ ነበር። ወይዘሮዋ ያለፈውን በትዝታ መልሰው ሲያወጉት ከልብ ይከፋቸዋል፣ ያዝናሉ፣ ይተክዛሉ። እንደዋዛ ሰማንያ ዓመታት ነጉደዋል። እንደቀልድ ስምንት አስርት አመታት አልፈዋል። የእሳቸው የሳቅ ደስታ ዘመን ግን በጣም ጥቂቱ ነበር።
ዛሬ ሁሉአገርሽ ድፍን ሰማንያ ዓመት ሞልቷቸዋል። እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ዕድሜያቸው ከአካላቸው ሲናበብ ስልሳዎቹን የተሻገሩ አይመስልም። ገጽታቸው የነቃ፣ አካላቸው የጠበቀ ነው። ቁመናቸው የዕድሜ ጥላ ያንዣበበት አይመስልም። ዛሬም ለመኖር ይታገላሉ፣ ለሕይወት ይሮጣሉ።
ስምንት አስርት ዓመታት ወደኋላ
የልጅ ልጃቸውን አብዝተው የሚወዱት መነኩሴዋ አያት ህጻኗን ከእሳቸው መለየት አይሹም። በየሄዱበት አዝለዋት ይዞራሉ። እሳቸው ልጆቻቸውን በልፋት ድካም አሳድገዋል። ዛሬ ሁሉም ራሱን ችሎ የራሱን ሕይወት ይመራል፣ እማሆይ ጉልበታቸው እየደከመ ትከሻቸው እየተፈተነ ነው። እንዲያም ሆኖ ለልጅ ልጃቸው የሚሆን አቅም አላጡም። ህጻኗን በየሄዱበት ከትከሻቸው አዝለዋት ይጓዛሉ።
የእሳቸውን ልፋትና ድካም ከልጅ ልጃቸው ፍቅር አጣምረው የሚያዩ ዘመዶች ታዲያ ሁሌም ይገረማሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለእሷ የሚመጥን ስም እንዲያወጡላት ይጠይቃሉ። አያት ሀሳባቸውን አልናቁም። ለልጅ ልጃቸው ስም መረጡ፣ አማረጡ። ዘወትር ከትከሻቸው አዝለው በየቦታው የሚያዞራትን ህጻን ‹‹ሁሉአገርሽ›› ሲሉ ጠሯት።
ሁሉአገርሽ ከአያታቸው ትከሻ ታዝለው ብዙ ቦታን አይተዋል። ደጀሰላም ገዳሙን፣ አገር መንደሩን፣ ቀዬ ገበያውን ጎብኝተዋል። ይህ አጋጣሚ ለሁኔታው ፈቅዷልና ሁሉ አገራቸው ቢባል አያስደንቅም። ስማቸው በሌሎች ተወዷል። ትርጓሜው በሁሉም ጸድቋል።
በአያታቸው እጅ ያደጉት ሁሉአገርሽ ከትከሻቸው ወርደው መራመድ እንደያዙ የሕይወትን ግዴታ ‹ ሀ..› ብለው ጀመሩት። ልጅነታቸው እንደ እኩዮቻቸው ነበር። እናት አባታቸው ቤት ካፈራው፣ ሁሉ አይነፍጓቸውም። ከቀዬው እየቦረቁ፣ ከባልንጀሮቻቸው እየተጫወቱ አድገዋል።
ከአካባቢው ጥቂት የሚባሉት በያዙት ዕውቀት ስማቸው ይጠራል። እሳቸው ግን ትምህርትን የማግኘት ዕድል አልነበራቸውም። እንደሴት ልጅ ወግ ከእናታቸው ጉያ ሳይርቁ ቤተሰቡን በጉልበት አግዘዋል። የታዘዙትን ከውነዋል።
ኮረዳነት
አሁን ሁሉአገርሽ ከልጅነት ዕድሜ አይደሉም። ህጻንነታቸው አልፎ፣ ሩጫ ዝላዩን ትተዋል። እንደበፊቱ ቀና ብለው አይሄዱም። ሲያናግሯቸው ያፍራሉ። ለእርምጃ ጉዟቸው ይጠነቀቃሉ። በእሳቸው ዕድሜ ያሉ እኩዮቻቸው ዕጣ ፈንታ ባል ማግባት ትዳር መያዝ ነው። ሁሉአገርሽም ቢሆኑ ለዓይን የሚስቡ ልጃገረድ ሆነዋል። አስራ አምስተኛ ዓመታቸውን ከያዙ ጀምሮ ‹‹ልጃችሁን አጋቡን፣ ዳሩልን ›› የሚሉ በዝተዋል።
እናት አባት ለጋብቻ የሚመጡ ጥያቄዎቹን አልገፉም። ልጃቸው ባል አግብታ፣ ትዳር ይዛ ወግ ማዕረግ ብታይ ይወዳሉ። ቆይቶ ጋብቻውን ከጠየቁት መሀል ለአንደኛው ልባቸው አጋደለ። ቀልባቸው ለፈቀደው ሰው ሁሉአገርሽን ሊድሩ ተስማሙ።
ሁሉአገርሽ በአስራ አምስተኛ ዓመታቸው በወላጆቻቸው ይሁንታ በሰርግ ተዳሩ። የልጅነት፣ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ ተረሳ። ዝላይ ፈንጠዝያው ቀረ። ሁሉም አለፈና ወይዘሮ ተባሉ። ‹‹ሙሽሪት ልመጂ›› የተባለላቸው ወጣት የእናት አባታቸውን ቤት ትተው ባላቸውን ተከተሉ። አዲሱ ጎጆ በአዲስ ሙሽሮች ድምጽ ሞቀ፣ ደመቀ። አዲስ ሕይወት ቀጠለ።
ትዳር እንደጀመሩ የመንግስት ሰራተኛው ባለቤታቸው ለስራ ከአካባቢው ሊርቁ ሆነ። ትዳር ነውና ሁሉአገርሽ ከእሳቸው መነጠል አልቻሉም። ባለቤታቸውን ተከትለው ወደ አሰብ አቀኑ።
በወለጋ መስመር ጅባትና ሜጫ ‹‹ጨሊያ›› የተወለዱት ወይዘሮ ዕድገታቸው ከአካባቢው የራቀ አይደለም። ከስፍራው ወጥተው ባያውቁም ባላቸውን ለመከተል ዓይን አላሹም። ‹‹ጨርቄን ማቄን›› ሳይሉ አብረዋቸው ተጓዙ።
አገራቸው ላይ እናት አባታቸውን ትተዋል። ‹‹የራሴ›› የሚሉት ሀብት ንብረትም አላቸው። ይህ ሁሉ ግን ከባላቸው አልነጠላቸውም። አሰብ ገብተው ትዳራቸውን ቀጠሉ። አሰብ ላይ ሁሉም ሮጦ ተግባብቶ ያድራል። ማነህ ? ከየት ነህ ? ምንድነህ ? ይሉት ጉዳይ የለም። ሁሉም በግሉ ሰርቶ በጋራ ይበላል። ልዩነት አይታወቅም፡ እንደቤተሰብ ቋንቋው አንድ ነው። በፍቅር ተዋዶ፣ ተከባብሮ ይኖራል።
ባለቤታቸው በአሰብ ነዳጅ ማጣሪያ ድርጅት ይሰራሉ። እሳቸውን ጨምሮ በርካቶች የድርጅቱ ነዳጅ ማጣሪያ ላይ ሕይወታቸው ተወስኗል። ሁሉአገርሽ ለቤት ለኑሯቸው የባላቸውን እጅ አልጠበቁም። ሌሊቱን እንጀራ እየጋገሩ ሲነጋ ለሽያጭ ያስረክባሉ።
ጊዜው በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ነው። የዛኔ እንዳሁኑ ሕዝብ አልበዛም። ኑሮ አልተወደደም። እንዲያም ሆኖ ራስን ለማሸነፍ ሌት ተቀን መልፋት ግድ ነው። ሁሉአገርሽ ለእሳቸው፣ ለባለቤታቸውና ለልጆቻቸው መኖር እየታገሉ ነው። ሙቀት እያጋያቸው፣ በጉልበታቸው ድካም በላባቸው ወዝ ያድራሉ።
ጥቂት አይሏቸው ዓመታት በአሰብ ሕይወትና ኑሮ ተገፉ። በእነዚህ ግዜያት ልጆች ተወልደው አደጉ። ጊዜዎች ነጎዱ፣ ዕድሜ ጨመረ። ከጊዜያት በኋላ የንጉሱ ወንበር በስልጣን ነቅናቂዎች ተገርስሶ ወደቀ። በመላው አገሪቱ ለውጥ መጣ፣ ኑሮ ተለወጠ።
አብዮትና ፖለቲካ ይሉት ጦስ የብዙዎችን ቤት አንኳኳ። የነበረው ባልነበረው ጥግ ሲጓዝ እንደነ ሁሉአገርሽ ያሉ ሰርቶ አዳሪዎች ኑሯቸው ተንገጫገጨ። ሁኔታዎች ተረጋግተው ቦታቸውን እስኪይዙ ጥቂት ቸገራቸው። ቆይቶ ግን ሕይወት እንደቀድሞው ቀጠለ። ዓመታትን በስፍራው የገፉት ቤተሰቦች የአቅማቸውን እየሰሩ እስከ 1983 ዓ.ም ዘለቁ። ከዚህ ዓመት በኋላ ግን ሁሉም ነገር ተቀየረ። አዲስ የመንግስት ለውጥ መጣ። ስልጣን በሌሎች ሀይሎች በተተካ ጊዜ ሰራዊቱ ተበተነ፣ ይሄኔ በየስፍራው ያለ ነዋሪ ስለደህንነቱ ዋስትና አጣ። ስደት፣ መፈናቀል፣ ስራአጥነት በረከተ።
የአሰብ ነዳጅ ማጣሪያና በውስጡ ያሉ በርካታ ሰራተኞች ከዚህ ችግር አልዳኑም። በሌሎች የሆነው ሁሉ በእነሱም ደረሰ። አብዛኞቹ የነበሩበትን ለቀው ወደ መሀል አገር ተሰደዱ። ጥቂት የማይባሉት ቤት ንብረታቸውን ትተው ተፈናቀሉ። ህጻናት ሴቶችና አረጋውያን፣ ጉዳትና እንግልት አገኛቸው።
ጥቁር እንግዳ
ወይዘሮ ሁሉአገርሽና ቤተሰቦቻቸው የአሰብን ምድር ለቀው ወጥተዋል። አሁን በአገሪቱ አዲስ ለውጥ ሆኗል። አብዛኞች በያዙት ለመቀጠል፣ በትናንቱ ለመኖር ተቸግረዋል። ሁሉም ሕይወቱን ለማትረፍ ይበጃል ያለውን እያደረገ ነው። አቅም ያለው አገሩን ትቶ ወጥቷል። ስደት ብርቅ አልሆነም። ችግር እግር በእግር ተከትሎ የብዙዎችን ማንነት መፈተን ይዟል።
ሁሉአገርሽ አዲስ አበባ ደርሰዋል። ብቻቸውን አይደሉም። ከእሳቸው ጋር ልጆችና ባለቤታቸው አሉ። አሁን ‹‹ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ›› ይሉት ስሜት በውስጣቸው ነግሷል። በእጃቸው እዚህ ግባ የሚባል ጥሪት የለም። ድንገቴው ለውጥ ብዙ ነገራቸውን ቀይሯል።
ከእጅ ባጡ፣ በነጡ ጊዜ ከዘመድ መጠጋት፣ እንግዳ መሆን ያሳቅቃል። ሌላውን ለመጠየቅ፣ ለመጠያየቁ ያወጡት፣ ይመነዝሩት ሲኖር፣ ደስ ይላል። ባዶ እጅ ደርሶ ያስጨንቃል፣ ያሳፍራል። ሁሉአገርሽና ቤተሰቦቻቸው ምርጫ አላገኙም። ተፈናቅለው አዲስ አበባ ከመጡ ጀምሮ ማረፊያቸው ከዘመድ ቤት ሆኗል።
ያረፉት ከባለቤታቸው እህቶች ዘንድ ነው። እነሱ የራሳችን ይሉት ቤትና መጠጊያ አላገኙም። ቀን አልፎ ችግር እስኪርቅ እንዲህ ሊሆኑ ግድ ብሏል። ሁሉአገርሽ ግን ተጨንቀዋል። ካደጉበት አገር የራሳቸው ቤትና ንብረት ነበራቸው። እሱን ትተውት ከራቁ ዓመታት አልፈዋል። ይህን ሲያስቡ ወላጆቻቸው ትውስ ይሏቸዋል። እስከዛሬ ተመላልሰው ጠይቀዋል። አሁን ግን ሁለቱም በሕይወት የሉም። ውስጣቸው ባዶነት እየተሰማው ነው። ትናንት ለሌሎች ይተርፍ የነበረው እጃቸው ዛሬ ለእርዳታ ተዘርግቷል። አሁን የሚያዙበት ዕልፍኝ እንዳሻቸው የሚቆርሱበት ማጀት የላቸውም። እንዲህ መሆኑ አስከፍቷቸዋል።
ጥቂት ጊዚያት ቆይቶ ወይዘሮዋ ራሳቸውን ለመቻል መሮጥ ያዙ። በወቅቱ ለሌሎች መሰሎቻቸው የሆነውን እርዳታ አላገኙም። በተፈናቃይ ስም የጠየቁት የቀበሌ ቤትም አልተሳካም። መቀመጥ አልፈለጉም። ጉልት ለመሸጥ ጥቂት ነገሮች ይዘው ከመንገድ ተቀመጡ። በውሏቸው ያገኙትን ቋጥረው ቤት መመለስ ልምዳቸው ሆነ።
ውሎ አድሮ መላው ቤተሰብ የአዲስ አበባን ሕይወት ለመደው። ባለቤታቸው እያረጁ ነው። ወይዘሮዋ ባላቸው የጡረታ አበል እንዳላቸው ሰምተዋል። ሽማግሌው ግን ለአንድም ቀን አሳይተው፣ ሰጥተዋቸው አያውቁም። ልጆቻቸው ቢደርሱም ሊያግዙ ሊደግፏቸው አይፈቅዱም። ዘወትር ለየራሳቸው ኑሮ ይሮጣሉ።
ከዓመታት በፊት በሴት ልጃቸው እጅ የነበረን የንግድ ሱቅ ተከራይተው ነበር። በእሱ ጥቂት እየሰሩም ቀን ገፍተዋል። ቆይቶ ግን ‹‹ቦታው ይፈለጋል›› በሚል ሰበብ መተዳደሪያቸው ተነጠቀ። ይህ ከሆነ ወዲህ ቤት ከመዋል ያለፈ መላ አላገኙም።
ሁሉአገርሽና አዛውንቱ ባለቤታቸው ዛሬም በአንድነት ይኖራሉ። አባወራው በህመም ምክንያት ከአልጋ ከዋሉ ቆይቷል። መነሳት፣ መንቀሳቀስ ተስኗቸዋል። እሳቸውን የማገዝ የማኖር ጫናው ከአዛውንቷ ሁሉአገርሽ እጅ አላለፈም። ህመምተኛውን በደከመ አቅማቸው እያነሱ ያገላብጧቸዋል፣ ያገኙትን እያቀመሱ መድኃኒታቸውን እየሰጡ ያስተኟቸዋል።
ዛሬ አብሮ አደጎቹ ባልና ሚስት ከአባወራው እናት አባት በተላለፈ የቀበሌ ቤት ይኖራሉ። ከአጠገባቸው የሰውዬው የቅርብ ዘመዶችና እህቶቻቸው አሉ። የእነሱ መኖር ግን ለሁሉአገርሽ ኑሮ የጠቀመ አይመሰልም። ሰላማቸውን ካጡ ቆይቷል።
የእሳቸው ውስጠት በገለልተኝነት ስሜት ተይዟል። ሁሌም ብቸኛ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ሁሉም የሚናገሩትን የሚያምኗቸው፣ የሚሉትን የሚቀበሏቸው አልመስል ካላቸው ሰንብቷል። አንዳንዴ ባለቤታቸው ጭምር ከዘመዶቻቸው አብረው ይናገሯቸዋል። ያስከፏቸዋል። ይህ እውነት ‹‹ብቸኛ ነኝ›› ለሚሉት ሴት ልዩ ትርጉም አለው።
በዕድሜ ብዛት መፍረስ የጀመረው ቤታቸው ክረምቱን ዝናብና ጎርፍ ያስገባል። እንዲህ መሆኑ ወይዘሮዋን ጤና አሳጥቷል። በድካም እየተንገላቱ የሚያቀኑትን ጎጆ የሚጎበኘው የለም። ወዲህ ችግሩ፣ እልፍ ሲልም እጅ ማጠሩ ሲያሳስባቸው ይውላል።
የሰባቶች እናት
ወይዘሮዋ ዕድሜያቸው እየገፋ አቅማቸው እየደከመ ነው። ማንም ግን ‹‹እናቴ፣ እረፊ፣ እንጡርሽ፣ እንደግፍሽ›› አይላቸውም። ባለቤታቸው ከሌላ እናት የወለዷቸው ልጆች አሉ። አንዳንዴ አባታቸውን ያስባሉ፣ ይጠይቃሉ። ሁሉአገርሽ ግን ከሰባቱ ልጆቻቸው አንዳች የሚያገኙት የለም።
ይህን ባሰቡ ጊዜ ከልብ ይከፋሉ። ዕንባቸው በአንገታቸው ይወርዳል። በዕድሜያቸው ማምሻ አብረዋቸው የኖሩ አጋራቸውን መተው፣ መራቅ አይሹም። ሁሌም ጉዳት ህመማቸው ይሰማቸዋል። መቼም ቢሆን ችግራቸው የእሳቸውም ችግር ሆኖ ይዘልቃል።
ዛሬ ለጎደለው ኑሯቸው ከጎናቸው የሚቆም ልጅ የለም። ሰባት ልጆችን ወልደው፣ አሳድገዋል። አንዳቸውም ግን ‹‹እናታችን የት ነሽ ?› ብለዋቸው አያውቁም። እሱንም ቢሆን ‹‹ተመስገን›› ብለው ትተውታል። አንዳንዴ ግን ከባለቤታቸው ዘመዶች የሚደርስባቸው በደል ከአቅም በላይ ሲሆን ውስጣቸው ይነካል። እነሱ ቤት ለዋሉት ሽማግሌ ባይሆኑም ለእሳቸው ሲሆን ይበረታሉ። እንዲህ መሆኑ ጠዋት ማታ እጅ ለሚያጥራቸው፣ ጓዳቸው በችግር ለሚፈተነው ሴት ኑሮን አክብዷል።
በግቢው ያሉ ነዋሪዎችም ውስጣቸውን አላዩላቸውም። ሁሌም እንደሚሉት በእነሱም ዘንድ ፊት ተነስተዋል። እንዲያም ሆኖ ቂም ለመያዝ፣ ክፋት ለማሰብ ተዘጋጅተው አያውቁም። ለማይረዷቸው ልጆችና ዘወትር ለሚያስቀይሟቸው ሁሉ ውስጣቸው ይቅር ባይነትን ለምዷል።
ዛሬ ሁሉአገርሽ በማምሻ ዕድሜያቸው ላጠረ እጃቸው የፈጠነ ዕድል አላገኙም። እስከዛሬ ጾም ውሎ ላለማደር የአቅማቸውን ሞክረዋል፤ ያገኙትን ሰርተዋል። ዛሬ ግን እንደትናትናው አይደሉም። ተስፋ መቁረጥ ከችግር ተዳምሮ ሲያስከፋ፣ አንገት ሲያስደፋቸው ይውላል።
ችግርን በምስጋና
በቅርቡ ውስጣቸውን የተረዱ አንዳንድ የወረዳ አመራሮች ከግቢው ደርሰው ቤታቸውን አንኳኩ። በአካባቢው ከሚገኝ የምገባ ማዕከል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በጠየቋቸው ጊዜ አላንገራገሩም። ጠያቂዎቹ የርሀባቸው ማስታገሻ፣ የችግራቸው መላ መሆናቸውን አመኑ። ውለው አላደሩም። በየቀኑ አንድ እንጀራ በወጥ እየተቀበሉ ለራሳቸውና ለህመምተኛው አባወራ ሆድ ደረሱ። በሆነው፣ በተደረገው ሁሉ ደስ አላቸው። በዚህ ዕድሜ ተቸግረው እጅ ቢያጥራቸውም አብልቶ ላሳደራቸው ፈጣሪ የተለመደውን ቃል አይነፍጉም። ዘወትር ‹‹ተመስገን›› ይላሉ። ‹‹ተመስገን››
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015