ኢትዮጵያ መልኳ ምንድን ነው? ብየ ልጠይቃችሁ ወደድኩኝ። በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ብዙም ውሃ ላይቋጥር ይችላል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቀለል ያሉ ነገሮችን መልሶ መላልሶ መጠየቅና ማጠያየቅ ክፋት የለውም። ምናልባትም ቀላል በሚመስሉ ነገሮች ውስጥ የገዘፉ፤ የተስተካከሉ በሚመስሉ ነገሮች ውስጥ የተዛነፉ፤ የጨዋ ልኬት በምንላቸው ውስጥ ቅጥ ያጣ ቅሌት፣ በማወቅ ውስጥም አለማወቅን ያሳያሉና። እኔም ኢትዮጵያ መልኳ ምንድን ነው? ብዬ ስጠይቃችሁ እነዚህን ታሳቢ ማድረጉ ጠቃሚ ይመስለኛል።
የአገር መልኳ ሰሪዎቿን ይመስላል። ወዳጄ ልቤ! ኢትዮጵያ መልክ አላት፤ ለዚያውም ፍንትው ብሎ የሚታይ። አንተ ደግሞ መልክህ በኢትዮጵያ ውስጥ ይገለፃል። ኢትዮጵያ ስትደስት መልክህ ፈገግታ ነው፤ እርሷ ሲከፋት የአንተ መልክና ውበት የወረዛ ነው፤ የኢትዮጵያ መገለጫ መልክና ውበቷ እኛ ልጆቿ ነን። አንተ ማለት ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ ማለት አንተ ነህ። ይህን ነገር መልሰህ መላልሰህ ስትጠይቅ ነገሩ ይገባህና፤ እውነት ኢትዮጵያ መልኳ ምን ይሆን ብለህ ራስህን መጠየቅ አይቀሬ ነው።
ግሪካዊ ፈላስፋ ሶቅራጥስ ‹‹እራስዎን ይወቁ እና መላውን ዓለም ያውቃሉ›› ሲል ሁሉን ነገር ለማወቅ መጀመሪያ ሰው ራሱን፤ አገሩን እና ወገኑን በሚገባ ማወቅ እንዳለበት በአንክሮ ይናገራል። ሰው አካባቢውን ለማወቅ መጀመሪያ ግራ ቀኝ ያሉትን ጎረቤቶቹን ማወቅ ይጠበቅታል። እኔም ስለነገሮች በዝርዝር ከመግባቴ በፊት ሌሎች እንዴት ይገልጹናል የሚለውን ለማወቅ እና ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንዴት እንደምትገለጽ በጥቂቱ ለማሳወቅ መሞኮር ተገቢ ይመስለኛል።
ዊኪፒዲያ ገና በመግቢያው ገጽ ኢትዮጵያ ማለት ይላል፤ ‹‹በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት አገር ናት። በአፍሪካ ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች ብቸኛም አገር ነች። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ዕድሜያቸው ከአንድ ምዕተ-ዓመት የሚያንስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ-ነገሥታት እና ንግሥተ- ነግሥታት የተመራች አገርም ናት። የሠለሞናዊው ሥርወ- መንግሥት የአመጣጡን ዘር እስከ አስረኛው ዓመተ-ዓለም ድረስ ይቆጥራል።
”ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የኖረባት ቦታ እንደሆነች ብዙ የሳይንሳዊ መረጃ ተግኝቷል። በበርሊን ጉባኤ በኩል የአውሮፓ ሃያላት አገሮች አፍሪካን ሲከፋፍሏት፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃለች። የሊግ ኦፍ ኔሽንስ (League of Nations) አባል ከነበሩት ሦስት የአፍሪካ አገሮች አንዷ ነበረች። ከኢጣልያን ወረራ ጊዜ በኋላም የተባበሩት መንግሥታት መሥራቾች አንዷ አገር ናት።
” ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ የአፍሪካ አገራት ነፃነታቸውን ሲያገኙ፣ ሰንደቅ-ዓላማቸውን በኢትዮጵያ ቀለሞች ማለትም በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ላይ ነው የመሠረቱት። አዲስ አበባ ደግሞ ለየተለያዩ በአፍሪካ ላይ ያተኮሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ሆነች›› ሲል ከዕድሜ ጠገቦቹ አገራት ቀዳሚ፤ ከታሪክ ድርሳናትም በዋና ምንጭነት የምትጠቀስ፤ በጀግንነት ምዕራፍ ደግሞ ነጮችን አንበርክካ የጥቁር ህዝቦችን ገድል ከፍ ያደረገች እጹብ አገር ስለመሆኗ ይመሰክራል።
የኢትዮጵያ ማለት መልክ ብዙ፤ የውሃ ልኳ የተመጠነ ግን ደግሞ ከፍ ያለ ማንነቷ ያልተበረዘች ማለት ነው። ታዲያ የዚህ ሁሉ ኢትዮጵያ መልኳና ክብሯ ልጆቿ ናቸው። ኢትዮጵያ የምትገለጠው አሁን ባሉ ዜጎቿ እንጂ ባለፈ ታሪክ ላይ ብቻ ቆማ የምትቆዝም አገር መሆን የለባትም። የትናንት አባቶች በደም በአጥንታቸው ኢትዮጵያን መልከ ሸጋ አድርገው አቆይተዋል።
አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ ቡሩሹን ከቀለሙ ነክሮ የሚያኖራት ኢትዮጵያ ጥንት ከነበረችው በብዙ እጥፍ ያማረች፣ ያሸበረቀች፣ በባህልና ትውፊቷ የተከበረች፤ ለልመና ሳይሆን ክብሯን ለማስጠበቅ የምታትር መሆን አለባት። የኢትዮጵያ መልክ መገለጫው ግጭት፣ አለመግባባት፣ ጦርነት፣ ርሃብና ድህነት ሆኖ መቀጠል የለበትም።
ይህ ትውልድ ዕዳ አለበት። የኢትዮጵያ ቀለም መቀየር፤ የኢትዮጵያን አንድነት ማጉላት፤ የኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች መኩሪያና መታፈሪያ ሆና የኖረችና በዚሁ የምትቀጥል መሆኗ ማረጋገጥ የትውልዶች አደራ ጭምር የተጣለበት ትውልድ ነው።
ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፤ ኢትዮጵያዊ መልክ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነት፤ ኢትዮጵያዊ ዘረመል፣ የኢትዮጵያዊነት እሳቤ በሁሉም አቅጣጫ ነው መታየት ያለበት። አመራሩ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ተላብሶ የህዝቡን መብት አክብሮ መሥራት አለመስራቱን ራሱን መፈተሸ አለበት።
ይህ ትውልድ ውብ የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር፤ ለመጪው ትውልድ ማኖር ይጠበቅበታል። አገር በነበር ብቻ አትጠራም፤ ነገን ታሳቢ በማድረግ ጭምር እንጂ። አገር ባለፉት መሪዎችና ትውልዶች ታሪክ ብቻ ስትዘከር አትኖርም፤ አሁንም መራር ትግል በማድረግ ለመጪው ትውልድ ደማቅ አሻራ በማኖር እንጂ። አገር በትናንት መልኳ ብቻ አትገለፅም፤ ነገዋን በሚሰሩ ጥበበኞችና ብርቱዎች ትጋት እንጂ።
በአንድ ወቅት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘለግ ባለው ፅሁፉ ‹‹ኢትዮጵያ አብዛኛው ህዝብ በድህነት እየማቀቀ ጥቂቶች የሚበለፅጉበት አገር ሆናለች። የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ እየተጣሱ›› ሲል በዘመነ ኢህአዴግ የነበረውን ግፍ ለመተንተን የጠቆመበት ቃል አንዳች ነገር ያስታውሰኛል።
ብዙ ጊዜ በተለያዩ ደረጃዎች ወደ መንበረ ስልጣን የሚመጡ አመራሮች የኢትዮጵያን መልክ ካለማወቃቸው የተነሳ፤ የጠላትን ጭቆና አሽቀንጥሮ የጣለን ህዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት ያሳዝኑታል። ካለው የሚያካፍልን ማህበረሰብ አራቁተውት ተመፅዋች ሊያደርጉት ይዳዳቸዋል።
ኢትዮጵያ ከግለሰቦችና ከአንዳንድ ቡድኖች ግልፈተኝነት የተሞላበት እሳቤ በጣም የላቀች አገር መሆኗን ባለመረዳታችን ከወርቅ ማማ ላይ ጎትተን አረንቋ ውስጥ ልንከታት የሚዳዳን ብዙዎች ነን። አለቀላት፤ አከተመላት ስትባል እንደ ዓደይ አበባ ፈክታ፤ እንደ ጥዋት ጀንበር ደምቃ ብቅ የምትል ል ዩ ሙሽራ ና ት።
ኢትዮጵያ አሸናፊነት፣ ኢትዮጵያዊነት መመካከርና ታጋሽነት፣ ኢትዮጵያዊነት ሠላምና አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት ችግር ወደ ድል መቀየር ነው። ኢትዮጵያ ሁሉንም ነገር ችላ ለሁሉም የምትሆን አገር ናት። እኛ የአገራችን መልክ የምንሠራ መሆናችን ከአሁኑ ተገንዝበን በህይወት ዘመናችን ሁሉ የሚጠበቅብን ማድረግ ይገባል።
የአገር መልኳ መገለጫዋ እኛ ዜጎቿ ነን። በመሆኑም አገራችን ተልቃ የምታተልቀን፤ ገዝፋ የምታገዝፈንና በዓለም ዓደባባይ በልጽጋ የምታኮራን ትሆን ዘንድም የሁላችንም ጥረት፣ ፅናትና ትጋት ይጠይቃል።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015