ብዙዎች የስኬትን ትርጉም በራሳቸው መስፈርት ለክተው ያስቀምጡታል። አንዳንዶች ደግሞ የወል ትርጉም ሰጥተውት በዚያ መለኪያ ስኬታማ ሰዎችን ይበይኑበታል፤ አድናቆትና ከመስጠት ባሻገር ስኬታማውን ሰው አሊያም ተቋም እንደ በጎ ምሳሌና አርአያ ይመለከቱታል። ሁለቱም አካሄዶች መስፈርቱን ባወጡት አካላት እይታ ትክክል ቢሆኑም፣ አብዛኛውን ጊዜ ስኬት የሚመዘነው ብዙሃኑ በሚስማማበት መለኪያ እንደሆነ ይታመናል።
ስኬት እንዲያው በቀላሉ የሚደረስበት ሳይሆን ከራስ አልፎ ለብዙሃን ብርሃን መሆን፤ ለመድረስ ዋጋና ጥረትን የሚያስከፍል መንገድን በትጋትና በትእግስት የመጓዝ ወኔን፤ እየወደቁ መነሳትን፣ ከስህተት መማርን፣ ታናናሾችን ማድመጥና ሁሌም ለመማር ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል፤ ዳገት ቁልቁለት የበዛበት ጭምርም ነው። መጨረሻው ግን ሃሴትን የሚያላብስ፣ በብዙዎች ምሳሌ የመሆን ሞገስን የሚያጎናፅፍ ሙሉ የመሆን ፀጋ ነው።
የዝግጅት ክፍላችን ሁሌም በዛሬው እለት በስኬት አምዱ ላይ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ሌሎችም አገርንና ማህበረሰብን በሚጠቅም መስክ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አካላትን እየጋበዘ ስኬት የተጎናጸፉበትን መንገድ ቀጣይ ጉዟቸውን ያመላክታል። ከልምዳቸው እየጨለፈ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለሌሎች ትምህርት እንደሚሆን ይጋብዛል።
በዛሬው እለትም አንድ እንግዳ ይዞላችሁ ቀርቧል። እንደ ከዚህ ቀደሙ በስኬት መለኪያ መነፅራችን ውስጥ ከገቡት መካከልም ኤልሳቤጥና ታደለ የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ህብረት የሽርክና ማህበር አንዱ ነው። ማህበሩ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ እንዲሁም በፕላስቲክ ምርት ተሰማርቶ በጊዜ ሂደት ውጤታማ እየሆነ መጥቷል።
ማህበሩ ከቆዳ የተሠሩ የህጻናትና የአዋቂ ጫማዎችን እንዲሁም ቦርሳዎችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል። ከቆዳ በተጨማሪም ፕላስቲክ ጫማዎችን በማምረት ለገበያ እያቀረበ የሚገኘው ይህ ማህበር ከተቋቋመ ከአስር ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በአሁኑ ወቅት እያመረታቸው ያሉ የቆዳ ጫማዎችና ቦርሳዎች በተለይም በእጅ የሚሠሩ ክፍት የቆዳ ጫማዎች ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያም ተፈላጊም ናቸው።
የማህበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ሽፈራሁ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ነው። ጫማ ወደ ማምረት ሥራ የገቡበትን አጋጣሚ፣ ዛሬ ላይ ለመድረስ ያሳለፉትን ውጣ ውረድ እንዲሁም ያለፉባቸውን መንገዶች አጫውተውናል። ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ከቤተሰብ ተለይተው ለመኖር አስገዳጅ ሁኔታ የገጠማቸው አቶ ታደለ፣ ሕይወትን ለማሸነፍ ሲሉ ሥራ ሳይመርጡ በትጋት ሰርተዋል።
የልጅነት ዕድሜያቸውን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች አሳልፈዋል፤ ካለፉባቸው የሙያ ዘርፎች መካከል ለጫማ ሥራ አድልተዋል። አብዛኞቹ አጋጣሚዎቻቸውም ወደ ጫማ ሥራ ይገፋቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ። ያገኙትን ሁሉ ሠርተው ማለፍ ቢችሉም የጫማ ሥራ ሙያን ግን እስካሁን ሳይተው ዛሬም ድረስ ይዘውት ቆይተዋል። ይህን ስራ መተዳደሪያቸው ከማድረግ ባለፈም ሙያውን ለሌሎች በማስተማር ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል።
‹‹በወቅቱ ወደ ዘርፉ እንድገባ ያደረገኝ ለሙያው የነበረኝ ፍላጎትና ድፍረት ነው›› የሚሉት አቶ ታደለ፤ አንበሳ ጫማ ፋብሪካ ተቀጥረው ይሠሩ ነበር። በፋብሪካው በቆዩበት ጊዜም ለሙያው የነበራቸው ቅርበት የተሻለ በመሆኑ ብዙ እውቀት ቀስመዋል። በቆይታቸው የጫማ ሥራ ሙያን ጥንቅቅ አድርገው ባያውቁም በለቀቁ ጊዜ ግን የጫማ ሥራን በግላቸው ለመሥራት እንዲዘጋጁ ረድቷቸዋል። በወቅቱም የጫማ ጥገና እና የልክ ጫማ ሥራን ነበር የጀመሩት።
ለሙያው ያላቸውን ፍላጎትና በጥቂቱም ቢሆን በአንበሳ ጫማ ፋብሪካ የቀሰሙትን ልምድ ተጠቅመው ወደ ሥራው ለመግባት ጊዜ ያልፈጁት አቶ ታደለ፤ ሥራውን ወደ ክልል ቢወስዱት አዋጭ እንደሆነ አመኑ። ጉዟቸውን ሀዋሳና ሻሸመኔ በማድረግ በሁለቱም ከተሞች የጫማ ጥገናና የልክ ሥራ (የሰዎችን እግር ለክተው) ሠርተዋል። በየዕለቱ በሚያደርጉት ጥረትም ከጫማ ሥራ ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቁ ረዳቸው። የራሳቸውን ሙያ ከማሻሻል አልፈው ለሌሎች ማስተማር ጀመሩ።
ሙያቸውን ለሌሎች በማስተማርም ከነበራቸው ልምድ ጋር ቴክኖሎጂው በእጅጉ ያገዛቸው እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ታደለ፤ የእውቀት ሽግግሩን የጀመሩትም በሀዋሳና በሻሸመኔ ከተማ ነበር። ወደ አዲስ አበባ በተመለሱ ጊዜም ብሩህ ተስፋ ከተባለ የውጭ ድርጅት ጋር በጋራ የሠሩ ሲሆን፤ ድርጅቱ የጎዳና ልጆችን ከየጥጋ ጥጉ ሰብስቦ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጥንም ነበር። በወቅቱ በጋራ ለመሥራት ሲወስኑ ከሚከፈላቸው ደመወዝ ይልቅ ድርጅቱ ይዞት የመጣው ሃሳብ እጅጉን አስደስቷቸዋል።
‹‹ብሩህ ተስፋ የተባለው የውጭ ድርጅት ጎዳና ላይ የወደቁ በርካታ ወጣቶችን አንስቶ የተሻሉና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ አድርጓል። እኔም የዚህ በጎ ተግባር አካል ብሆን በብዙ አተርፋለሁ በማለት ነው የተቀላቀልኩት›› የሚሉት አቶ ታደለ፤ በወቅቱም ከጎዳና የተሰባሰቡት ወጣቶች እንደየፍላጎታቸው የተለያየ ሙያ ይማሩ እንደነበር ይናገራሉ። የጫማ ሥራ ሙያን ለመማር የፈቀዱትንም በነበራቸው ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት አስተምረው በርካቶችን ባለሙያ ማድረግ ችለዋል።
በጊዜው 1800 የሚደርሱ ወጣቶች የጫማ ሥራ ሙያን ከአቶ ታደለ እጅ ተምረዋል። አብዛኛዎቹም ወደ ስራ የገቡ ሲሆን አንበሳና ጥቁር አባይ ጫማ ፋብሪካን ጨምሮ በተለያዩ ፋብሪካዎች ተቀጥረው እየሠሩ የሚገኙ አሉ። ተቀጥረው ከሚሰሩት ባለፈም በግላቸው አምራች የሆኑ ስለመኖራቸው ምስክር እንደሆኑ ገልጸው በዚህም እጅጉን ደስተኛ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
በጫማ ፋብሪካ ተቀጥሮ ከመሥራት ጀምሮ የተቀደዱ ጫማዎችን መጠገን፣ ጫማ ለክቶ በመሥራትና ሙያውን ለበርካቶች ሲያስተምሩ የቆዩት አቶ ታደለ፤ በአሁኑ ወቅት ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ኤልሳቤጥ ፍቅሬ ጋር በመሆን የተለያዩ የቆዳና የፕላስቲክ ውጤቶችን እያመረቱ ይገኛሉ። ‹‹ከትናንት ተነስተን ዛሬ ላይ ለመድረሳችን ምክንያቱ የባለቤቴ ጥንካሬ ነው›› የሚሉት አቶ ታደለ፤ ወደ ማምረት ከመግባታቸው አስቀድሞ ባለቤታቸው በምርት ሂደት እንከን የገጠማቸውን ጫማዎች ከተለያዩ ጫማ አምራቾች በመረከብ ያለመሰልቸት ተዘዋውረው ይሸጡ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በአንድ አጋጣሚ መንግሥት ባመቻቸው ዕድል ተደራጅተው ሁለት በሁለት የሆነ ቦታ ያገኙት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ፤ ትጉህና ታታሪ በመሆናቸው በዛችው ቦታ ጫማ ይሰፉ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ቦታውን በቆርቆሮ በመከለል አንድ ሲንጀር የስፌት መኪና ገዝተው ወደ ሥራው የገቡት አቶ ታደለ፤ የጫማ ሥራ ሙያን ለባለቤታቸው ቀደም ብለው ያስተማሯቸው በመሆኑ ወደ ሥራው ለመግባት ብዙም አልተቸገሩም። ወይዘሮ ኤልሳቤጥ፤ የተማሩትን የጫማ ሥራ በተግባር በማሳየት እርሳቸው ሲሰፉ አቶ ታደለ ደግሞ የውጭውን ሥራ (ዕቃ የማቅረብ) ይሠሩ ነበር።
ቀስ በቀስ የጀመሩት ጫማ የማምረት ሥራ አሁን ከመንግሥት ባገኙት የማምረቻ ቦታ ላይ በስፋትና በአይነት እያመረቱ ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያም ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። ሲጀምሩ አንድ ሲንጀር መኪና የነበራቸው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 12 መስፊያ ማሽኖች፣ የተለያዩ መላጫ ማሽኖች፣ ሶል ማጣበቂያ ማሽኖች፣ ቤዛ ማሽንና ሌሎችንም በማፍራት አንድ ጫማ ፋብሪካ ሊኖረው የሚገባውን ማሽኖች በማሟላት ምርቶቻቸውን በጥራት እያመረቱ ይገኛሉ።
ከምርቶቻቸው መካከልም የህጻናትና የአዋቂ የቆዳ ጫማዎችና ፕላስቲክ ጫማዎች ይገኙበታል። ፕላስቲክ ጫማዎቻቸውን የሚያመርቱት መልሰው ጥቅም ላይ በሚውሉ የተጣሉ ፕላስቲካ ጫማዎች በመሆኑ ለየት ያደርጋቸዋል። አገልግሎታቸውን ያጠናቀቁና በየአካባቢው ተጥለው የሚገኙ ፕላስቲክ ጫማዎችን በኪሎ ገዝተው መልሶ ጥቅም ላይ መዋል እንዲችል ሲያደርጉም ጫማዎቹ ጸድተውና ተፈጭተው አዳዲስ ፕላስቲክ ጫማዎች የመሆን ዕድል አላቸው። ይህም ጫማዎቹ አካባቢን እንዳይበክሉ ከማድረግ ባለፈ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ አስችሏል፤ ያገለገሉ የፕላስቲክ ጫማዎች ሰብስበው ለሚያመጡ ሰዎችም የገቢ ምንጭ እንዲፈጠርላቸው አግዟል።
የሚያመርቷቸው ጫማዎችና ቦርሳዎችም ቆዳ በቆዳ የሆኑና በተሻለ ጥራት የሚመረቱ ስለመሆናቸው ያነሱት አቶ ታደለ፤ በተለይም ክፍት የቆዳ ጫማዎቹን ከአገር ውስጥ ባለፈ ወደ ቻይና፣ ሱዳን፣ ኬንያና ታንዛንያ እንደሚልኩ ተናግረዋል። ድርጅቱ ጫማዎቹን ወደ እነዚህ አገሮች የሚልከው በቀጥታ ሳይሆን በወኪሎች አማካኝነት ነው። በአገር ውስጥ ደግሞ በተለያዩ ክልሎች በተለይም በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል በስፋት ይፈለጋሉ።
በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ሱቅ ይዘው የሚሸጡ ደንበኞች አሏቸው። የቆዳ ጫማዎቹ በእጅ የመሥራት ሂደትን የሚከተሉ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ታደለ፤ ምርቶቻቸው የሚፈለጉትም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ። የሚጠቀሙት ሶልም ምቾት ያላቸውና ቡሽ በመሆናቸው ተመራጭነታቸውን ከፍ አድርጎታል።
“በአሁኑ ወቅት ቡሽ ሶል ለማምረት አስፈላጊ የሆነውን ጥሬ ዕቃ ማግኘት አልተቻለም” የሚሉት አቶ ታደለ፣ ያም ሆኖ በአገር ውስጥ የሚገኝ ጥሬ ዕቃን በመጠቀም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት ሥራ እየሠሩ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህም እንደ ከተማ ሞዴል በመሆን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የዕውቅና ሰርተፍኬት አግኝተው ተሸላሚ ሆነዋል።
ሶልን በአገር ውስጥ ምርት ተክተው ከመሥራታቸው በተጨማሪ አገልግሎታቸው ያበቃላቸውን ፕላስቲክ ጫማዎችን በኪሎ ገዝተው አጽድተውና የተለያዩ ኬሚካሎችን ተጠቅመው በከፍተኛ ሙቀት በማቅለጥ በተለያዩ ሞልዶች ውስጥ እያስገበ በሁለት የተለያዩ ቀለማት ጫማዎችን እያመረቱ ናቸው። እነዚህ ጫማዎችም በአብዛኛው ወደ ክልል የሚላኩ ሲሆን በተለይም በሰሜኑ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚዘወተሩ ጫማዎች እንደሆኑም ነግረውናል።
የሶልና የፒፒሲ ወይም የፕላስቲክ ጫማ ፋብሪካው በቀን 3600 ጫማ ወይም ሶሎችን የማምረት አቅም እንዳለው አቶ ታደለ ይናገራሉ። 28 ሠራተኞችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ይችላል። ሁለት ቀለም ያላቸው ፕላስቲክ ጫማዎችን ያመርታል።
የቆዳ ምርት የሆኑት ጫማዎች አብዛኛው ሥራ በእጅ የሚከናወን በመሆኑም በቀን ከ70 እስከ 90 የሚደርስ የሰው ኃይል ይፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ገበያው የተቀዛቀዘ በመሆኑ እስከ 20 ሠራተኞች ይሳተፋሉ። በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች የሚዘወተረው ፕላስቲክ ጫማ እንደመሆኑ ይመረታል። በተለይም በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በስፋት የሚፈለጉ ቢሆንም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲዚህ ግን በአካባቢው በነበረው ጦርነት ምክንያት ገበያው መቀዛቀዙን ገልጸዋል። አስቀድመው ከላኳቸው ጫማዎች ገንዘብ መቀበል እንዳልቻሉና በርካታ ቁጥር ያላቸው ጫማዎችም ወደ አካባቢው ገበያ መላክ እንዳልቻሉ ነው ያስታወሱት።
በአገሪቱ ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳት ማድረሱን አንስተው በድርጅታቸውም ተመሳሳይ ኪሳራ አስከትሎባቸው ማለፉን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አሁን በመጣው ሰላም ትልቅ ተስፋ መሰነቃቸውን አልሸሸጉም። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘላቂ ከሆነ ምርቶቻቸውን እንደቀደመው ለማምረትና ወደ ገበያው ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015