ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ሳምንቱ ያለፈው በትምህርት ነበር እንዳላችሁ እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም ጎበዝ ተማሪ ሳምንቱን የሚያሳልፈው በትምህርትና በጥናት ብቻ ነው። እናንተ ደግሞ ጎበዝ ተማሪ እንደሆናችሁ አምናለሁ። ልጆችዬ ዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት የእናንተ ጉዳይ ቢሆንም አንብበው የሚያደርጉት ግን ወላጆቻችሁ ናቸው። ስለዚህም የዛሬው አምዳችን ተረኛ አንባቢ ወላጆቻችሁ ይሆናሉ። በእርግጥ እናንተም ብታነቡት ይጠቅማችኋል። ያው አድራጊው እናንተ ስላልሆናችሁ ለቤተሰብ ይሰጥ አልኩ እንጂ።
ጉዳዩ ምን መሰላችሁ? የልጆች መጻሕፍት ዝግጅትን ይመለከታል። ስለዚህም ወላጆቻችሁ ይህንን ካነበቡ በኋላ ለእናንተ በሚገባ መልኩ ያስረዷችኋል። ከቤት ውጪ መጻሕፍትን ስታነቡ እንዴት አይነት መጻሕፍት ለእናንተ እንደሚመጥኑ ያስረዳችኋልና ነው። ቀደም ሲል በነበረው የልጆች አስተዳደግ ባህላችን ውስጥ ልጆች መጻሕፍትን እንዲረዱ ለማድረግ የመረዳት አቅማቸውን በማየት በተረት መልክ በማስደገፍ በቃል እየነገሩ ያስጠኗቸው ነበር። አሁን ደግሞ ዘመን እየተለወጠና ቴክኖሎጂ እያደገ ሲመጣ በቃል ይነገሩ የነበሩት ወደ ጽሁፍ ተለውጠው በህትመት መውጣት ጀመሩ። እነዚህ የህጻናት መጻህፍት ግን በተለያየ ጊዜ ትችት ሲቀርብባቸው ይስተዋላል።
ደራሲ ጌታቸው በለጠ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሀሳቦችን ሰጥተውናል። ለህፃናት የሚጻፉ መጻህፍት ምን መምሰል እንዳለባቸውም ከራሳቸው አንጻር በመነሳትም ነግረውናል። መጻሕፍቱ ስእላዊ እና በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ መሆን አለባቸው። በህጻናት የስነ-ልቦና ልክ ሊጻፉ ይገባል፤ በማህበረሰባቸውና በሚኖሩበት አካባቢ አውድ ልክ እንዲረዱት ተደርጎ ይዘቱ መቅረብ አለበት። ይሁን እንጂ አሁን አሁን ገበያ ላይ የሚውሉ የህጻናት መጻህፍት ሁሉንም የእድሜ ክልል በአንድ ላይ ያጠቃለሉና ለየትኛው እድሜ ታስቦ እንደተጻፈ በግልጽ የሚያስቀምጡ አይደሉም ይላሉ።
አቶ ጌታቸው፤ የህጻናት መጻህፍት ስንጽፍ በእድሜ መከፋፈል አለብን፤ ልጅ በሚለው እሳቤ ብቻ ሁሉንም ጠቅልለን አንድ አይነት ይዘት ያላቸው መጻህፍት መጻፍ የለብንም። ልጆች እድሜያቸው ብቻ ሳይሆን የሚማሩት የክፍል ደረጃም ይለያያል። ስለዚህም የመረዳት አቅማቸውም በዛው ልክ ልዩ ነው። እናም የሚያዩት፣ የሚሰሙት እንዲሁም የሚያነቡት ነገር በእድሜያቸውና በክፍል ደረጃው መወሰን አለበት ባይ ናቸው።
ለኢትዮጵያ ህጻናት ከዓለም አቀፍ ማህበራት የምንጠይቀው ገንቢ ንጥረ ነገሮችን የያዙ ምግቦች እርዳታ ብቻ አይደለም የውጭ ድርጅቶች መጥተው ራሳቸው በፈለጉት ቅኝት የህጻናት መጻሕፍትን እናሳትማለን እያሉ የተለያዩ መጻሕፍትን ያሳትማሉ። ይህ ግን ትክክል አይደለም። ልጆችን ለሌላ አገር ባህል አሳልፎ እንደመስጠትም ነው። መጻሕፍቱ ከኛ አገር የአኗኗር ዘይቤ ሆነ አስተዳደግ ጋር አይቆራኝም። ስለዚህም በባህላቸውና በአኗኗራቸው የሚጻፉ መጽሐፍት ያስፈልጓቸዋልና መንግስትም ሆነ ማህበረሰቡ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያስረዳሉ።
ቴክኖሎጂው እጅግ በመዘመኑ የተነሳ ልጆች እድሜያቸውን የሚመጥኑና በልካቸው የተጻፉ መጻህፍትን እንደልብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። ወደ ኢንተርኔቱ ዓለም እጅጉን እየሳባቸው ነው። ይህ ደግሞ ህጻናት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እድሜያቸውን የማይመጥኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንዲመለከቱና ከዛም አለፍ ሲል ያዩትን ወደ መተግበር እንዲገቡ አድርጓቸዋል። በዚህም ልጆቻችን ከእጃችን እንዲያመልጡ እየሆነ ነው። እናም አገራዊ የሆነ ማንነታቸውን የሚያሳይና የሚመጥናቸው መጻሕፍት ተዘጋጅቶ ካልቀረበላቸው መመለስ አይቻልም ይላሉ።
አሁን ልጆች የማህበራዊ ሚዲያዎችን በማየት ተጠምደዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ምንም ሳይሆን በይዘትም ሆነ በቋንቋ የሚመጥን መጻሕፍት ተዘጋጅቶላቸው አለመቅረቡ ነው። ስለሆነም መንግስት የህትመት ዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል። ደረጃቸውን የጠበቁና ይዘታቸው ለህጻናት የሚመጥኑ መጻህፍትን በብዛት ገበያ ላይ እንዲገኝም በራሳችን ቋንቋና ባህል ላይ የተመሰረቱ የህጻናት መጻህፍት የሚያዘጋጁ ደራሲያንን ማበረታታት ያስፈልጋል።
ልጆች በተስተካከለና ቀና በሆነ መንገድ ጥሩ ስነምግባር ይዘው እንዲያድጉ ወላጆች ትልቁን ሚና ይጫወታሉ። ስለሆነም ልጆች የሚጠቅማቸውንና የሚጎዳቸውን ነገር ለይተው ማወቅ ስለማይችሉ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚጠቅመውን መርጦ የመስጠት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። በተለይም የሚያነቧቸውን የልጆች መፃህፍት ገዝተው ሲሰጡ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ይመክራሉ። መጻህፍትን ከመግዛታቸው በፊት የሚገዟቸው መጻህፍት ለየትኛው የእድሜ ክልል የተጻፈ ነው የሚለውን ማጤን ይኖርባቸዋልም ብለዋል።
የትኛውንም ጽሁፍ ህጻናት ከማንበባቸው በፊት ወላጆች ሊያነቡትና ለልጄ ይመጥነዋል ወይስ አይመጥነውም፤ ካለበት የእድሜ መጠን ጋር የሚሄድ ጽሁፍ ነው አይደለም የሚለውን መለየትም አለባቸው። ልጆች ከእድሜያቸው በላይ የሆኑ የልጆች መጻህፍትን ማንበብ የለባቸውም። በዚያው ልክ ከእድሜያቸውና ከብስለታቸው መጠን የሚያንስ ይዘት ያላቸውን መጸሐፍትም እንዲሁ። ምክንያቱም ከሚያነቡት መጽሃፍ ይዘት በላይ ብስለት ካላቸው ሊሰላቹና መጻህፍት ላይ ፍላጎት ሊያጡ ይችላሉ። በተመሳሳይ የመጽሃፉ ይዘት ከብስለታቸው በላይ ከሆነም በቀላሉ መረዳት ስለማይችሉ ይጨነቃሉ። እናም ሁሉም ነገር በሚገባቸውና በሚመጥናቸው ልክ በደረጃቸው የተሰራ ሊሆንላቸው እንደሚገባም ያስገነዝባሉ። ምክራቸውን ተግባራዊ አድርጉት በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን በሚቀጥለው ጊዜ በሌላ ጉዳይ እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን እሁድ ታህሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም