የዓለም ተወዳጁን ዋንጫ ለመውሰድ ሰማያዊዎቹ ከውሃ ሰማያዊ ለባሾቹ (ላ አልቢሲለስቴ) ጋር ተፋጠዋል። ከ88ሺ በላይ ደጋፊዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሉሴል ስታዲየም ደግሞ የላቀውን ብሄራዊ ቡድን ለመሸለም የተዘጋጀው ፍልሚያ አስተናጋጅ ሆኗል። ከእግር ኳስ ውድድርነቱ ባለፈ በርካታ ድራማዊ ክስተቶችን ሲያስተናግድ የቆየው የኳታሩ ዓለም ዋንጫ፤ የአምናዋን ቻምፒዮን ፈረንሳይን ዳግም ያነግሳል ወይስ የ30 ዓመታት የዋንጫ ድርቅ የመታትን አርጀንቲናን በድል ያረሰርሳል የሚለው ዛሬ የዓለም ህዝብ በጉጉት የሚጠብቀው ጉዳይ ነው።
ሚሊዮኖች በአካል ተገኝተው፣ ቢሊዮኖች ደግሞ በቴሌቪዥን መስኮቶች የሚከታተሉት የዓለም ዋንጫ በኳታር ምድር ከእግር ኳስም በላይ ሆኖ 28 ቀናትን ቆይቷል። ምሽት በሚካሄደው የፈረንሳይ እና የአርጀንቲና የፍጻሜ ጨዋታም፤ ተናፋቂው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ለቀጣይ አራት ዓመታት በቀጠሮ ይሰናበታል። የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋ የአዘጋጅነቱን ሚና ለመካከለኛው ምስራቅ ከበርቴዋ ኳታር ሲሰጥ በበርካቶች ዘንድ ስጋት ቢሰርጽም ትንሿ አገር ግን የምንጊዜም ደማቁንና ታሪካዊውን ዓለም ዋንጫ በስኬት አስተናግዳ እንግዶቿን ዛሬ በደማቅ ስነስርአት ትሸኛለች።
22ኛው የዓለም ዋንጫም በምርጥ ደራሲ እንደተጻፈ ታሪክ በአስገራሚና የማይጠበቁ ክስተቶች ተሞልቶ ተገባዷል። ድንቅ ፉክክር፣ አሳዛኝ ተሸናፊዎች፣ አስገራሚ ቡድኖች፣ ለአገራቸው ኩራት የሆኑ ተጫዋቾች፣ ምርጥ የአጨዋወት ስልት ቆማሪ አሰልጣኞች፣ ስልጡን ደጋፊዎች፣ ውድድሩን አድማቂ የጥበብ ሰዎች፣… በዓለም ዋንጫው ታይተዋል። በምዕራባውያኑ እና በአረቡ ዓለም ለዘመናት የዘለቀውን ስንጥቃት የደፈነው ይህ ውድድር፤ ፖለቲካዊና ሌሎች ጉዳዮችም በስፋት ተንጸባርቀውበታል።
ይህ የዓለም ዋንጫ ሞሮኮ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካን ለግማሽ ፍጻሜ ያደረሰችበት፣ ለዋንጫ ተጠባቂዎቹ ቡድኖች (ብራዚል፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል እና ቤልጂየም) በጊዜ የተሰናበቱበት፣ በፖለቲካው ባላንጣ የሆኑትን አሜሪካ እና ኢራንን ያገናኘ ጃፓን አውሮፓውያኑን አገራት አሸንፋ የምድቡ ቁንጮ የሆነችበት፣ ዛሬ ለፍጻሜ የምትጫወተው አርጀንቲና በሳዑዲ አረቢያ የተሸነፈችበት፣ አስተናጋጇ ኳታር በሜዳዋ አንድም ጨዋታ ባለማሸነፍ አስገራሚ ታሪክ የጻፈችበት፣ ረጃጅም ተጨማሪ ደቂቃዎች የታዩበት፣ ጥቂት ቀይ ካርዶች የተመዘዙበት፣ ከብጥብጥና ከረብሻ የጸዳ ጨዋ ድጋፍ የታየበት፣ … ድንቅ ፉክክር ዛሬ ይቋጫል።
የዚህ ታሪካዊ ዋንጫ መደምደሚያ ሁለተኛ ተከታታይ ድል ለማግኘት የቋመጠችውን አውሮፓዊቷን ፈረንሳይ፤ ጀግናዋን በክብር ለመሸኘት ካቀደችው ደቡብ አሜሪካዊቷ አገር አርጀንቲና ጋር አገናኝቷል። ለዕለቱ ተጠባቂ ክስተት የደረሱት ሁለቱ አገራትም ዓለም ዋንጫን ሁለት ሁለት ጊዜ በማንሳት ተመሳሳይ ታሪክ ይጋራሉ። ፈረንሳይ እአአ በ1998 የመጀመሪያውን ድሏን ስታስመዘግብ በ2018ቱ የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ደግሞ ሁለተኛውን ድሏን አጣጥማለች። አርጀንቲና በበኩሏ ዓለም ዋንጫን የሳመችው እአአ በ1978 እና 1986 ነበር።
ፈረንሳይ ከ60 ዓመታት በኋላ ጣሊያን እና ብራዚል በተከታታይ የዓለም ዋንጫዎች በማሸነፍ ስኬታማ የሆኑበትን ታሪክ ለመጋራት ከኳታር የተሻለ እድል የላትም። አርጀንቲና በበኩሏ ወርቃማ ተጫዋቿን ሊዮኔል ሜሲ ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ የሚሳተፍበትን የዓለም ዋንጫ መድረክ በስኬት እንዲታጀብ የማትፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። በምድባቸው አንድ አንድ ሽንፈትን ብቻ ቀምሰው ለፍጻሜ የበቁት ሁለቱ ቡድኖች በአንድ ክለብ በሚጫወቱ ጀግኖቻቸው ታሪካቸውን ለማሳመር በሉሴል ስታዲየም ይፋለማሉ።
በዓለም ዋንጫው አምስት ግቦችን በማስቆጠር በእኩል ደረጃ የተቀመጡት አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ሊቅ ሊዮኔል ሜሲ እና ወጣቱ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን የቀኝ እጅ ኬሊያን ምባፔ ለታላቁ ክብር ተፋጠዋል። እንደ ቡድን አሸናፊ የሚሆነውን አስቀድሞ ለመገመት አዳጋች እንደመሆኑ፤ ሁለቱ የዓለም ምርጥ ተጫዋቾች ደግሞ አንዳቸው ለሌላኛቸው ራስ ምታት መሆናቸው አያጠራጥርም። በየትኛውም ሁኔታ ልዩነት በመፍጠር የተካነው ሜሲ አንቱ በተሰኘበት የእግር ኳስ ህይወቱ ያላሳካው ብቸኛ ነገር ዓለም ዋንጫ እንደመሆኑ በዛሬው ጨዋታ ለማሸነፍ ይሰለፋል። ፈጣኑና የተከላካዮች ጭንቀት የሆነው ምባፔም የአገሩን ክብር ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ ይገባል።
ውድ የተባለውን የዓለም ዋንጫ ባሰናዳችው ኳታር የዓለም ቁጥር አንዱን የእግር ኳስ ቡድን ምሽት ላይ ይለያል። አሸናፊውም የዓለም ውዱን ዋንጫ ሲያነሳ 42 ሚሊየን ዶላርም ይበረከትለታል። ሁለተኛ የሚሆነው ቡድን 30 ሚሊየን፣ ከሞሮኮና ክሮሺያ አሸናፊ የሚሆነው 27 ሚሊየን እንዲሁም ተሸናፊው 25 ሚሊየን ዶላር ወደ ካዝናቸው ያስገባሉ። ከሁሉ በላይ ግን የአሸናፊነት ጽዋዋን የምትጎነጨው የታሪካዊው ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ አገር ኳታር ትሆናለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ታህሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም