በመንደሩ አንቱታን ያተረፉ የመሰላል አከራይ አሉ። በሰፈሩ ውስጥ ያለው መሰላል አንድ ነው፤ እኚህ ሰው ጋር የሚገኝ መሰላል ብቻ። ሰፈሬው መሰላል በፈለገ ጊዜ ወዲህ አባት ይመጣና ይከራያል፤ እርሳቸውም ከመሰላል ኪራይ ገቢ ያገኛሉ። ግለሰቡ በዚህ ስራቸው አንቱታን ያተረፉ በመሆናቸው የሰፈሩ ልጆች ምን መሆን ትፈልጋላችሁ ሲባሉ የሚመልሱት “መሰላል ማከራየት” የሚል ሆኗል። በሰፈሩ የሚገኘው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንም ሲያስተምሩ ምሳሌ የሚያደርጉት መሰላልን ነው። ሂሳብ ለማስተማር መሰላል ምሳሌ ይሆናል፤ አካባቢ ሳይንስ ለማስተማር መሰላሉ ይነሳል፤ በሌሎች ትምህርቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ በመሰላል ብዙ ይመሰላል። ለሽምግልና የተቀመጡ የአካባቢው ሽማግሌዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ መሰላል ለሽምግል ናቸው ምክር ማሳመሪያ የሚጠቀሙበት ምሳሌ ከሆነ አመታት አልፈዋል። በመሰላሉ ጉዳይ ግን ማንም የተለየ ጥያቄ አንስቶ የማያውቅባቸው አመታት። አንድ ቀን የተለየ ነገር ሆነ።
አንድ ቀን ከተማሪዎች መካከል አንድ ተማሪ “መሰላሉ ለምን አንድ ሆነ ለምንስ ብዙ ማድረግ አንችልም” ሲል ሀሳብ አቀረበ። ያገኘው ምላሽ አስደንጋጭና ምክንያታዊ ያልሆነ ምላሽ ነበር። አንዳንዱ “ይህን ጥያቄ ያነሳኸው በአካባቢያችን የተከበሩትን የእከሌን ገበያ ልትዘጋ አስበህ ነው” ሲል ምላሽ ሲሰጠ፤ ሌላው “ራሱን ከአባቶች በላይ ስለሚቆጥር ነው፤ በአባቶች ስራ ላይ አዲስ ሃሳብ ይዞ የሚመጣው” ሲል አስተያየት ሰጠ። ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ “በዓለም ላይ ያለው መሰላል አንድ መሆኑን ሳያውቅ ቀርቶ ነው ሌላ መሰላል ስለመስራት ያሰበው። ብቸኛውም መሰላል እዚህ መንደር ብቻ ያለ ነው። እንዴት የማይታሰብ ነገር ያስባል።” ሲል ከሰሰ።
በዚህ መሃል የመሰላል አከራዩ በራሳቸው ዓለም ሄዱ። እንዴት መሰላሉን እንደሰሩ፤ እንዴት መሰላሉ የእርሳቸው ብቸኛ መብት ተደርጎ እንዲታይ እንዳደረጉ፤ እንዴት ለአመታት የእርሳቸው መሰላል ሊተካ የሚችል እንዳይደለ አድርገው ማስረጽ እንደቻሉ፤ ይህን ሁሉ ያደረጉት ራሳቸውን በማህበረሰቡ ውስጥ ልዩ ቦታ ለማሰጠት እንደሆነ አሰቡ። ቢሳካላቸውም ከሞቱም በኋላ በመሰላሉ ምክንያት የሚታወሱና ተቀናቃኝ የማይነሳባቸው ሆነው እንዲያልፉ ነው። አሁን የተፈጠረው ጠያቂ ልጅ ግን ከወዲሁ አሰጋቸው። ልጁ መጠየቅ ከጀመረ በቀላሉ መሰላሉ በሌላም ሰው ሊሰራ የሚችል መሆኑን በማሳየት ጉድ ሊያደርጋቸው ይችላል። እንደ እዚህ ዘመን በማህበራዊ ሚዲያ ጉትጓቶ የዘመኑ ተጽእኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመታየት እንደሚደረገው ጥረት፤ እኚህም አባታቸው በዘመናቸው እውቅና ሲሉ የቋጠሩት ቋጠሮ።
እንደተለመደው ጉድ ለአንድ ሰሞን ነውና ልጁን ሲቃወሙ የነበሩት አንድ ሰሞን ከግራ ከቀኝ ሲቃወሙት ቆዩና ሁሉም ጸጥ አሉ። ልጁ የተፈጠረው አዲስን ነገር የመቃወም፤ ቢገባንም ባይገባንም ከጥንት የመጣውን በሙሉ ትክክል አድርጎ የመቀበል አዝማሚያ ፋታ ሲል ሁለት ነገር አሰበ። አንድ የሰውዬውን መሰላል አወላልቆ መልሶ መስራት ወይንም አዲስ መሰላል ሰርቶ ማሳየት። ሁለተኛውን መንገድ መሄድን ዓላማ አደረገና አዲስ መሰላል ሰርቶ ወደ ገበያ ሊገባ አሰበ።
ቀናት ተቆጠሩና አንድ ቀን በአካባቢው ባለው ትልቅ ገበያ በተለያየ መጠን የተዘጋጀ መሰላል ለገበያ ቀረበ። ሰው ሁሉ እየፈራና እየተባ አዲሱን መሰላል መንካት ጀመረ። እየወሰደም መሞከር ጀመረ። በቅድሚያ ለአመታት ከአንድ መሰላል በስተቀር መሰላል የለም ብሎ ሲያስብ የነበረውን አስተሳሰቡ ጋር ተጋጨ። በመቀጠል ይህን አስተሳሰብ እንዲይዝ ካደረጉት ጋር ተጋጨ። ልጁ ዓላማ ብሎ የተነሰውን በተግባር አሳክቶም አሳየ። በሰፈሩ አዳዲስ ነገሮችን የማሰብ፤ ዓላማን የማሳካት፤ ዓላማን ለማሳካት ለሚገጥም መውጣት መውረድ ምሳሌም ሆነ፤ በዓላማ በስተቀር በምንም ሊሰራ የማይችለው ሁለተኛው መሰላል በሰፈሩ ተሰርቶ ወደ ስራ ገባ። የአገሬው ሰው አዲሱን መሰላል ከእጁ አድርጎ መጠቀም ሲጀምር ለአመታት አንድን ብቸኛ ተደርጎ የቀረበ መሰላል በኪራይ ለማግኘት ወረፋ ይጠብቅ የነበረበትን ዘመን አስታውሶ አዘነ።
ቀስ በቀስ የመሰላል ኪራይ እየቀረ፤ እያንዳንዱ ሰው የራሱን መሰላል መስራት የሚቻልበት ደረጃም ላይ ተደረሰ። መሰላል፤ መሰላል ይሆን ዘንድ የሚያስፈልገው እንጨትና ሚስማር ነውና። ከዚህ ቀደም ከዓላማ አንጻር በዚሁ አምድ ላይ ያቀረብነውን ጽሁፍ ማስተካከያ በማድረግ እንደሚከተለው አቅርበናል።
ዒላማ ይኑርህ!
ወደ መሰላል የወጣ ሰውና ለአደን የወጣ ሰው ይመሳሰላሉ። ለአደን የተሰማራ ሰው ዒላማውን አስተካክሎ አንዳች ድል ይዞ መመለስ ፈልጎ ወደ ጫካው ውስጥ ይገባል። ዒላማው በራሱ ዓላማ አይደለም፤ ዓላማው ዒላማው ሲሳካ የሚሳካው ነው። ዒላማውን በትክክል አድርጎ የሰነዘረ ዒላማውን መትቶ አውሬውን ቢጥለው ነገር ግን ባዶ እጁን ተመልሶ ወደ መጣበት ቢመለስ አንዳች ችግር እንዳለበት ይቆጠራል። ምክንያቱም ሕይወቱን አስይዞ የተሰለፈበት የዒላማ ፍልሚያው ዓላማ ገድሎ መመለስ አይደለምና። ወደ መሰላል የወጣም እንዲሁ ነው፤ በመሰላል ላይ ወጥቶ ሊደርስበት የሚገባው ጫፍ አለ፤ አንዳች ነገር ደርሶ የሚሰራበት ስፍራ።
በሕይወት ጉዞ ውስጥ ሰዎች ዒላማ የሚያደርጉት ብዙ ነገር አለ። ጎበዝ ተማሪዎች ዒላማ አድርገው የደረጃ ተማሪ ለመሆን ያጠናሉ። ካሱበት ደረጃ ተንሸራተው ሲገኙ አንዳች የጎደላቸው ነገር እንዳለ እስኪሰማቸው ድረስም ይደርሳሉ። አንድ ቀን በተማሪዎች የውጤት መቀበያ ቀን አንዱ ታዳጊ ተማሪ ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል። አንዳች ነገር እንደተፈጠረ እምባው በሁለቱም አቅጣጫ ይፈሳል፤ ምክንያቱ ደግሞ በአንድ ማርክ ተበልጦ ደረጃውን ማጣቱ ነበር። ዒላማ ያደረገው ነገር ነበርና ዒላማውን መምታት ባለመቻሉ የተፈጠረበት ሃዘን።
ከግለሰብ አልፎ የዒላማ ነገር በተቋማት ውስጥም ይሰራል። ተቋማት ግብ/ታርጌት አስቀምጠው እያንዳንዱ ሰራተኛ እንደ ግለሰብ፤ ከእያንዳንዱ የስራ ክፍል እንደ ክፍል፤ ከአጠቃላይ ድርጅቱ እንደ ድርጅት ዒላማ ይደረጋል። ዒላማውም ይሳካ ዘንድ የተለያዩ ተግባራትም ይከናውናሉ። ዒላማ በአግባቡ ታልሞ ውጤት ሲመጣ ደስታ ይሆናል። ዒላማ የተደረገው ነገር ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ ምክንያቱ ይገመገምና የማስተካከያ መንገድ ይቀየስለታል፤ በዚሁ መንገድ የዒላማ ጉዞ ይቀጥላል።
ዒላማ ማድረግን እንደ ባህል በአደጉት አገራት ዘንድ የተለመደ ነው። ጃፓኖች የማኔጅመንት ሳይንስ እንዲዳበር የአሰራር ማሻሻልን በየጊዜው በማድረግ ዒላማን መምታት የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረስ እንዲቻል ምሳሌ የሚሆኑ አሰራሮችን ለዓለም አስተዋውቀዋል። ዒላማን ትኩረት ያደረጉ በጥራት፣ በሰው ኃይል አስተዳደር፣ በንግድ አስተዳደር፣ በንብረት አያያዝ ወዘተ ውስጥ አሰራሮችን አስተዋውቀው ውጤታማም ሆነዋል።
አንባቢው አዲስ አመት በመጣ ቁጥር ዒላማን በማለም ልምድ ያለው ሊሆን ይችላል። አንዳንዱ ሰው የአዲስ አመት እቅድን በልኩ አቅዶ ተግብሮ ራሱን ገምግሞ የመሸለም ልማድም አለው። በሂደት ውስጥ ከዛሬ ነገን በስራ መቀየር። ዒላማ እዚህ ውስጥ ያለው ድርሻ ትልቅ ነው። ዒላማ የምናደርገው ነገር ግልጽ ነው። በቁጥርም፤ በስፋትም፤ በርዝመትም ወይንም በሆነ አንዳች መለኪያ አማካኝነት የሚለካ ስለሆነ። በመሰላል ላይ የወጣ ለምን በመሰላል ላይ እንደወጣ ካላወቀ ችግር ነው።
ዒላማ አድርጎ ቀኑን በሰዓት ከፋፍሎ የሚንቀሳቀስና እንዲሁ ቅርጽ በሌለው አካሄድ ቀኖቹን ተቀብሎ የሚሸኝ ተመሳሳይ ውጤት ሊኖራቸው አይችልም። ተማሪው፣ አርሶ አደሩ፣ ነጋዴው፣ ሰራተኛው ወዘተ በዒላማ ውስጥ ስራቸውን ያከናውኑ ዘንድ ይመከራል፤ በዚህ መንገድ የሚያከናውኑት ለውጤት ደርሰው ይታያል። ከፍ ያለው ጥያቄ ግን ዓላማ ነው፤ ከዒላማ የሚገዝፈው፤ የዒላማ ድምር ውጤት የሚገልጸው። በትውልዱ ውስጥ ቦታ የተነፈገ የሚመስለው በዒላማ ተሸፍኖ የሚኖረው፤ ዓላማ!
ዓላማ ይኑርህ!
ማርክ ትዋይን የተባለ አሜሪካዊ ፀሀፊ “በሕይወት ውስጥ ወሳኝ የሆኑት ሁለት ቀናት አንደኛው የተወለድክበት ሲሆን ሁለተኛው የሕይወትህን ዓላማ ያገኝበት ነው” ይላል። ዓላማ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ቦታ በሚገባ የሚያሳይ አባባል ነው።
የስድብ ጥሩ ባይኖረውም “ዓላማ ቢስ” የሚል ስድብ የሰዎችን ስሜት የመንካት አቅሙ ከፍተኛ ነው። ማንም ሰው ዓላማ ቢስ እንደሆነ ተደርጎ እንዲቆጠር አይፈልግም። በዘመናት መካከል አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የደረሰችበት ምእራፍ ላይ ለመድረስ ያለፉ በርካታ ስልጣኔዎችን አልፋለች። እያንዳንዱ ዘመን ይዞት የነበረው ስልጣኔ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ተጽፎ ከሚገኘው ባሻገር በእያንዳንዱ አካባቢ አሻራው ዛሬም ድረስ ይታያል። ኢትዮጵያውያን አንድ ሰው ዓላማ ብሎ የያዘውን ነገር ዳር በማድረስ ውስጥ የሚሰጡት ሙገሳ ወይንም አድናቆት የታሪካችን አካል ነው። ከዚህ አንጻር “ዓላማ ቢስ” የሚለው ቃል ለአንድ ኢትዮጵያዊ ስሜትን የሚጎዳ ቢሆን ሊገርመን አይችልም።
ቤተሰቦች ልጆቻቸው ትምህርትን በአግባቡ እንዲያጠኑ፤ በአግባቡ እንዲከታተሉ ሲመክሩ ትምህርትን እንደ ዓላማ አድርገው በማቅረብ ነው። ሴት ልጅ ከሆነች ደግሞ ከዓላማዋ ሳትዘናጋ ትምህርቷን ዓላማ አድርጋ እንድትማር ትመከራለች። ለሃላፊነት ብቁ ሳይሆን ወደ ጾታዊ ግንኙነት መሄድም እንዲሁ ከዓላማ መስመር መሳት ተደርጎም ይቀርባል። አባቶቻችን በመደበኛ ትምህርት ውስጥ ገብተው ሳይማሩ ከግል ሕይወት ተነስቶ እስከ አገር ድረስ በዓላማ ውስጥ የመኖርን አስፈላጊነትን ይገልጻሉ።
ባለንበት ዘመን ደግሞ ዓላማ የሚባለው ነገር ፈጽሞውኑ የጠፋ ነው ባንል እንኳን እየደበዘዘ የሄደበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ዓላማ እጅግ ጠቦ በየትም በኩል ተደርጐ ገንዘብ ላይ መድረስ የሚለው የሕይወት ዘይቤ የሰፋ ይመስላል። በስራ መንገድ ገንዘብ ላይ መድረስ የሚጠበቅ ቢሆንም ባልተገባ ስራ መድረስ እንዲሁም መነሻ ዓላማቸው ገንዘብ ባልሆኑ ዘርፎች እንደ ሃይማኖት፤ ፖለቲካ፤ ሕዝብ አስተዳደር ወዘተ ከብዙሃን ጋር በሚሰጥ አገልግሎት ውስጥም ታልፎ ገንዘብ ጋር መድረስን ግብ የሆነበት ዘመን ላይ መገኘት አሳዛኝ ነው። ዓላማ በገንዘብና በእውቅና ለመለካት የተሄደበት እርቀት ብዙ እንደሆነ በግልጽ የሚታይበት ወቅት።
መነሻችንን ዒላማ ያደረግነው በዒላማ ስሌት ዓላማ እየወደቀ ስላለ ነው። ገንዘብ የማግኘት ዒላማ ወይም ግብ ያለው ሰው በማንኛውም መንገድ አድርጎ ገንዘብ ጋር መድረስን ከሆነ የሚያስበው በመደበኛ ንግድ ገንዘብ ጋር ከመድረስ በኮንትሮባንድ መንገድ ላይ መሄድን ሊመርጥ ይችላል። በሙስና ገንዘብ ላይ መድረስን ዒላማ ያደረገ ሰው ካለበት አንድ ኃላፊነት ወደሚከተለው ሲያድግ ዒላማው በተጨማሪ ሃላፊነት ህዝብን ማገልገል መሆኑ ይቀርና ለበለጠ ሌብነት ልምምድ እያደረገ ይሰነብታል።
የዒላማ ሕይወት በዓላማ ውስጥ ሲሆን እጅግ ጠቃሚ መሆኑን የሚያስረዱ አያሌ የማኔጅመንት ሳይንስ ጽንሰ ሃሳቦች አሉ። እውነታው ግን ዓላማ የለሽ በመሆን ውስጥ የበቀሉት ዒላማዎች ትርጉማቸው ማትረፍ እየመሰሉ መክሰር፤ ማግኘት እየመሰለ ማጣት፤ መገኘት እየመሰለ መጥፋት ነው። ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ሊባል የሚችልባቸው ክስተቶች በየፌርማታው ከዓላማ አንጻር በዝቷል። ያል እጅ መንሻ ውጤት ማግኘት በማይታስብበት ዘመን ውስጥ ስንኖር በተለመደው መንገድ ወጥቶ የሚገባው ዓላማውን ለማሳካት በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆን አዋጭ እንዳልሆነ በማሰብ ተስፋው እየተሸረሸረ ሊሄድ ይችላል።
የዓላማ ሕይወት
ዓላማን ውስብስብ አድርጎ ከማቅረብ በቀላሉ “ሰዎችን ማእከል አድርገን ልንኖረው የተገባው ሕይወት” ብለን ልናየው እንችላለን። በምድር ላይ የምንኖረው ኑሮ በጊዜ ገደብ የተገደበ መሆኑ እሙን ነው። ሰው በመሆናችን በውስንነት ውስጥም እንኖራለን። በዚህ ሁኔታ ምድር ላይ ስንኖር ዓላማ ትልቁ ስንቃችን ነው፤ ልንኖር የተገባውን ሕይወት ላይ ያደረስነው ውሳኔም ነው።
እንደ ግለሰብ በውስጣችን ያለውን ተሰጥኦ ተጠቅመን ልንኖር የምንፈልገውን ሕይወት ለመኖር እውቀትን ማእከል አድርገን ስንመላለስ እርሱ ዓላማ ነው። የዓላማ ሕይወት ራስን ፈልጎ በማግኘት ለሌሎች የሚመነዘር ማድረግ ነው። አንድ ሰው በቁጥር አንድ ቢሆንም ለራሱ በቂውን ጊዜ ሰጥቶ ራሱን ፈልጎ ባገኘበት እርቀት ለብዙዎች የሚመነዘር ሊሆን ይችላል። የዓላማ ሕይወት ሰዎች ግራ ተጋብተው በሚኖሩበት ሁኔታ ውስጥ የተረጋጋን ሕይወት እንድንኖር የሚረዳ ነው። ራስን ፈልጎ ማግኘት በውጤቱም ለሌሎች መድረስ። ሮበርት ኤፍ. ኬኒዲ “የሕይወት ዓላማ ነገሮችን መልካም ለማድረግ በሆነ መንገድ የምናደርገው አስተዋጽኦ ነው” በማለት ዓላማን ከራስ አጥር ባሻገር መመልከት እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ሲሆን የውስጥ ጩኽት ምላሽ መስጠት፤ ከፈጣሪም ከተፈጥሮም ጋር ታርቆ የመኖር ሕይወት ይከተላል። ተልእኮ አድርጎ የሚወሰድን ነገር ዳር ማድረስ የሚያስችል ሕይወትም ይሆናል።
በመቃብራችን ላይ የሚገኙ ሰዎች ምን አድርገን እንዳለፍን ቢያውቁ ደስ ይለናል። የተጣላን አስታራቂ፣ ተስፋ ላጡ ተስፋን መመለስ፣ የተራቡትን የሚያበላ፣ በስራው ታታሪ ሆኖ ብዙ የስራ እድል የፈጠረ፣ ወይንስ ምን? ፒካሶ እንዲህ ይላሉ “የሕይወት ትርጉም ስጦታህን ማወቅ ነው።” የሕይወት ዓላማ ደግሞ ስጦታህን ለሌሎች መስጠት።
ዓላማ በተቻለው መጠን ራስን ማእከል ከማድረግ ወጥቶ ሌሎችን የሚያስብ ቢሆን እያንዳንዱ ርምጃ አስደሳች ይሆናል። አንድ ሰው ነግዶ ገንዘብ ማግኘት ቢፈልግ እንደ ዓላማ መያዝ ያለበት በሚሰራው የንግድ ስራ ሰዎችን የሚጠቅምበትን ነው። ለአርሶ አደሩ የሆነ እቃ አቅርቦ የአርሶ አደሩን የሆነን ችግር ፈቶ ገንዘብ ማግኘት ሲሆን ትርጉሙ እንዲሁ ነግዶ ገንዘብ ማግኘት ከሚል ዓላማ ይሻላል። ገንዘብ ማግኘት ዒላማ ሲሆን የሚሰራው ስራ የሚጨምረው እሴት ግን ዓላማ ነው።
የማይጠየቁ ብዙ ነገሮች በዙሪያችን አሉ። መጠየቅ ሲጀምሩ ወደ መልስ መድረስ ይቻላል። የዓላማ ሕይወትም ውጪውን ሳይፈሩ ወደ ውስጥ በመጠየቅ የሚኖር ሕይወት ነው። ይህን ሕይወት ብዙዎች አይኖሩትም፤ ጥቂቶች እንጂ!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015