ልክ የዛሬ ሳምንት ነበር አስደንጋጩ ዜና የተሰማው። አብዛኞቹ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ግድግዳ ላይ የተለጠፈው አስደንጋጭ መርዶ ትልቅ ትንሹን በእንባ ያራጨ የአርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) ህልፈትን የሚገልፅ ነበር። ሰዎችን በህይወት እያሉ የማመስገን ልማዳችን ደካማ ቢሆንም በዛሬው የዝነኞች ገፅ አምዳችን ባጭሩ የተቀጨው ወጣት አርቲስት ላይ ለማተኮር ወደናል።
ደግና እኔን ብቻ ይድላኝን አያውቅም ይሉታል በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች፤ ጨዋታ አዋቂ ነውና እርሱ ባለበት ሳቅ አይታጣም። ለሰው እንስፍስፍ አንጀት ነው ያለው። በጥበብ ስራው በሚያገኘው ክፍያ ወዳጅ ዘመዶቹን ቀድሞ ያስታውሳል እንጂ ለራሱ ለማሰብ ይዘገይ ነበር። ይህ በህልፈተ ህይወቱ ብዙሃንን ያስደነገጠና ያስለቀሰው ወጣት ከያኒ የጥበብ ህይወቱ በጋሽ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) እጅ ነው የቀናለት።
ባባ ከአባቱ አቶ ብርሃኑ አምባውና ከእናቱ ወይዘሮ አባይነሽ ክብረት በአዲስ አበባ፣ በተለምዶ ተክለሃይማኖት ጅምናዚየም ተብሎ በሚጠራው ሠፈር በ1977 ዓ.ም ነው የተወለደው። አርቲስት ታሪኩ ውልደቱ ብቻ ሳይሆን የህይወቱ እልፍና ወሳኝ ክዋኔዎችም መቼታቸው አዲስ አበባ ላይ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በባልቻ አባነፍሶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረ:: በመቀጠል ወደ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ተክኖሎጂ ኢንስትቲዩት አቅንቶ በሌዘር ቴክኖሎጂ ዲፕሎማውን አግኝቷል። በወቅቱ በኢንስትቲዩቱ አስተማሪዎች እንዲሁም ተማሪዎች ተወዳጅ ነበር።
ታሪኩና ጥበብ
አበቦች የትያትር ክበብ የተሰኘው ስፍራ በታሪኩ የጥበብ ህይወት ላይ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። የጥበብ ህይወት ጉዞው ጅማሬም እዛው ነው። በክበቡ የተጀመረው የታሪኩ የጥበብ ጉዞ ትልቅ አጋዥም አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ናቸው። እሳቸው ጋር ደጅ ፀንቶ የጥበብን ጉዞ አብሯቸው ተጉዞ ያጎደለ የለምና ታሪኩ በተለያዩ ጊዜያት የፊልም እና የቲአትር ኮርሶችን መውሰዱ የዛሬው የጥበብ ሎሌ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። በአበቦች የቴአትር ክበብ ባይተዋር የተሰኘ ቴአትር ሰርቷል፣ በቀንዲል ቤተ ተውኔት በተለያዩ የጥበብ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍም የትወና አቅሙን አሳይቷል።
አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ በፀርሀ ፅዮን ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ የማገልገል እድልም ገጥሞት ያውቃል። በሰንበት ትምህርት ቤቱ ባገለገለበት ጊዜም የነፍስም የስጋም ስንቅ ሸምቷል። የትወና ጥበቡንም አበልፅጓል። ዋዜማ፣ መንገደኛው እና የይቅርታ ዘመን የተሠኙ የሙሉ ጊዜ መንፈሳዊ ፊልሞችንም በሰንበት ትምህርት ቤት ህይወቱ ውስጥ ሰርቶ ነበር።
ከአበቦች የቴአትር ክበብ የቴአትር ስራዎች በመቀጠል በዓለማዊ ፊልም ለመጀመርያ ጊዜ በዋና ገፀባህሪ የተሣተፈበትን ላውንደሪ ቦይ የተሠኘውን ፊልም አበረከተ። በላውንደሪ ቦይ የጀመረው የፊልም ከያኒነት ጉዞው ከስልሣ በላይ ፊልሞች ላይ በመተወን ለጥበብ እጅ የሰጠ መሆኑን ለማስመስከርም ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም።
ወጣት በ97፣ ማርትሬዛ፣ ይመችሽ-የአራዳ ልጅ 2፣ ሞኙ የአራዳ ልጅ 4፣ አንድ ሁለት፣ ብር፣ ወደው አይሰርቁ፣ ወፌ ቆመች፣ እንደ ቀልድ ወቶ አደር፣ አባት ሀገር፣ የሞግዚቷ ልጆች፣ ይዋጣልን፣ ዋሻው፣ ወሬ ነጋሪ እና ሌሎችም ፊልሞች ላይ በተመልካች ዘንድ አድናቆትና ተወዳጅነት ያተረፈለትን የትወና ብቃት ማሳየት ችሏል። አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ የጥበብ ህይወቱ በተለያዩ ሽልማቶች የደመቀም ነበር። ከነዚህ ውስጥ አዲስ ሚውዚክ አዋርድ እና በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ ሆኖ የተሸለመበት እና በጉማ አዋርድ ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል ለእጩነት እና ለሽልማት የበቃበት የሚጠቀሱ ስኬቶቹ ናቸው።
ታሪኩና የበጎ አድራጎት ተግባራት
ባባ በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ለመሳተፍ በጥበብ ሙያው እውቅናን እስኪያገኝ አልጠበቀም። እኩዮቹ ጥያቄያቸው ሌላ በነበረበት ወቅት የሱ ነፍስ የውስጥ ጥያቄ በጎነት ነበር። በዚህም በኢትዮጵያ ሚሊኒየም በ23 ዓመት እድሜው ላይ ሆኖ ለኢትዮጵያ የዐይን ባንክ እኔ ሳልፍ አይኖቼን ሌሎች ማየት የተሳናቸው ሰዎች ይዩባቸው ሲል ቃሉን ሰጥቷል። መልካሙ ታሪኩ በሰጠው ኑዛዜ መሠረትም ህይወቱ ካለፈ በኋላ ቤተሰቦቹ የገባውን ቃል ለዐይን ባንክ በመስጠት ቃሉን አክብረውለታል። ለዚህም ቤተሰባዊ ደግነት የኢትዮጵያ ዐይን ባንክ ምስጋናውን በህዝብ ፊት አቅርቧል።
አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ ለደግነቱ ገደብ የለውም፣ ሰው ሳይመርጥ የሚደግፍ ነበር። በአገራችን ጥሩ ተከፋይ ከሚባሉ የጥበብ ሰዎች ተርታ ይመደብ የነበረ ቢሆንም ከነብሱ ጋር የተጣበቀው ደግነት እና ፍፁም ቸርነት ለኔ ይድላኝ እንዳይል አድርጎት በክፍያ ያገኘውን ገንዘብ እንኳን በበጎነት ለአካባቢው ሰዎች እየለገሠ መኖሩን ህይወቱ ካለፈ በኋላ ብዙዎች ሲመሰክሩ ተሰምተዋል። በኖረባት ጥቂት ዘመንም በምርቃት እና በመልካም ምግባር አሳልፎ የግል ህይወቱን ለሌሎች የሠጠ ድንቅ ባህሪ የነበረው ወጣት ነበረ።
አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ በየእለት ውሎው በተገኘበት ቦታ ሁሉ ህፃን አዋቂ ሳይል በፍቅር እና በመረዳዳት ሲያሳልፍ ኖሯል። ለጓደኞቹ እና ለሰፈሩ ሰዎች ሁሉ በችግራቸው ቀድሞ በመድረስ ይታወቃል። በአካባቢው ከሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንደ CBCDO ሲደርታ እና ሰዋዊ በጎ አድራጎት ማህበር ወዘተ በበጎ ፍቃድ በመሣተፍ በነበረው እውቅና እንደ አምባሳደር በማገልገልም ይታወቃል። ለቤተመፅሃፍት ከ500 በላይ መፃህፍትን በማሠባሠብ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትንና አቅመ ደካሞችን በመደገፍም በጎ ተግባሮች ላይ በፊት አውራሪነት ተሣትፎ እንደነበረው በህይወት ታሪኩ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
የአርቲስቱን የህይወት ታሪክ ያነበበው አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ ‹‹አርቲስቱ በህይወት እያለ ከፍተኛ ተከፋይ ቢሆንም የኔ ይቅር ብሎ ለምስኪኖች ሲለግስ የነበረ፣ ከኔ ይልቅ እኛ ማለት የሚቀናው ባለ ቅን ልብ ነበር›› ሲል የታሪኩን ለጋስነት መስክራል።
በብሔራዊ ቴአትር ይህን የጥበብ ውድ ልጅ ህልፈተ ህይወት ተከትሎ ወዳጅ ዘመዶቹን በማሰባሰብ ለአስከሬኑ የጀግና ሽኝት ሥነ ስርዓት አዘጋጅቶለታል። በዚህም የኢትዮጵያ ዐይን ባንክ ተወካይ ሲስተር ሊያ ትካበው የአርቲስቱን ዐይኑን መለገሱን በሚመለከት ለታላቅ ወንድሙ አሸናፊ ብርሃኑ የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።
የሽኝት መርሀግብሩ መድረክ አጋፋሪ የነበረው አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ በበኩሉ በእንባ የተቆራረጠ መልእክቱን ሲያስተላልፍ ወጣቱን ከያኒ እንዲህ ሲል ገልፆታል ‹‹አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ ጅላጅል ምሁር አፍቃሪና ስራ ተብሎ የታዘዘውን ገፀ ባህሪ ሁሉ ወክሎ ብቻ ሳይሆን ሆኖ በብቃት የሚተውን ነው››።
‹‹ጥቂት የማይባሉ አርቲስቶች በምኞታቸው ማህደር ውስጥ ከታሪኩ ጋር አብሬ ብሰራ የሚል ፍላጎት ይገኛል፤ ትንሽ ትልቁን አክባሪ የወጣት አዛውንቱን ልብ በሳቅ በጨዋታ የሚያጠፋ የሁሉ ወዳጅ ነው›› ሲልም አርቲስት ታምሩ ተናግሯል።
በአስክሬን ሽኝት መርሀግብሩ ላይ የጥበብ አፍቃሪያን፣ የጥበብ ሰዎች፣ የአርቲስቱ ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም ጭምር ተገኝተዋል። ከኃላፊዎቹ መካከል አንዷ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ‹‹አርቲስቱ ከእድሜው የማይጠበቅ መልካም ነገርን ያደረገ በልጅነቱ ማስተዋል የቻለ ነው። ከዓመታት በፊት የዐይን ብሌኑን በመስጠትና በፊልሞቹ ለትውልድ የሚተርፍ ስራ በመስራቱ በህይወት ባሉ ሰዎች ዐይን ውስጥ ህያው ሆኖ ይኖራል›› በማለት ተናግረዋል። ዶክተር ሂሩት በንግግራቸው ‹‹በህፃንነት እድሜ አስቦ ዐይኑን ለማያውቃቸው ሰዎች መለገሱ የሰውነት ጥግነቱን ያሳያል›› ሲሉም አክለዋል።
‹‹ታሪኩ በፊልሞቹ ሰውነትን ከራስ በላይ ሰው መኖርን ሲሰብክና የሰው ልጅን ህፀፅ በማሳየት የዜግነት ግዴታውን የተወጣ ነው፣ በተሰጠው ጊዜ ከማንም በላይ እውቀቱንም አቅሙንም መጠቀም ችሏል፣ በዚህም በእኛና በልጆቻችን ልብ ውስጥ ይኖራል›› በማለትም ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል።
አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ስለ ታሪኩ ብርሃኑ ያሰፈረው ፅሁፍ የበለጠ ባባን ይገልፀዋል። ቴዲ እንዲህ ሲል ይጀምራል ‹‹ከዓመታት በፊት ነው፣ የሚቀጥለውን የጨዋታ ከቴዲ ጋር” ሾው እንግዳ ከአዘጋጆቼ ጋር ስንወያይ ለምን ታሪኩ ባባ አይሆንም እንደውም በቅርቡ ስለሚሞሸር በዛው ስለፍቅር ህይወቱም እናወራዋለን ብለን ወሰንን።
እንደሚሞሸር ስሰማ ሰርጉን ከፍ አድርገን በአምስት ኮከብ ሆቴሎቹንና አጋር ድርጅቶችን አስተባብረን እሱ ምንም ወጪ ሳያወጣ እንደግስለትና የሾው አካል እናድርገው ብለን ወሰንን። ታሪኩ በዚህ አጋጣሚ በትልቅ ሆቴል ውስጥ ያማረ ሰርግ እንዲያደርግ ስለምናግዘው…… ሁላችንም ባመጣነው ሀሳብ ተደስተናል። የፕሮግራሙ አዘጋጅ የሺነህ ይህን የምስራች ለታሪኩ የመንገሩን ኃላፊነት ተቀብሎ ታሪኩ ጋር ደወለለት። ታሪኩ ሀሳቡን ከየሺነህ ከሰማ በኋላ ሰፈሩ ተክለሀይማኖት እንዲመጣና እንዲወያዩ ቀጠረው። የሺነህ ይህንኑ ነግሮኝ እኔ ሆቴሎችን የማነጋገሩን ኃላፊነት ወስጄ እሱ ደግሞ ከታሪኩ ጋር የሰርጉን ዝርዝር ሁኔታ ሊነጋገሩ ወደታሪኩ አመራ። እኔ በተሰጠኝ ኃላፊነት አንድ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል አነጋግሬ ተስማምተን ትክክለኛውን የሰርጉን ቀን እንደማሳውቃቸው ተነጋግረን የየሺነህን መምጣት መጠበቅ ጀመርኩ። የሺነህ መጣ። ሲመጣ ግን ሲሄድ የነበረው ጉጉትና ፈገግታ ፊቱ ላይ አልነበረም። ”ምነው” አልኩት የሺነህን ”ሰፈሩ የቀጠረኝ አውቆ ነው” አለኝ። ”ልክ እንደተገናኘን እጄን ይዞ የሰፈሩን ሰዎች እና የተክለሀይማኖት ጀርባ አካባቢዎችን በሙሉ እያስጎበኘኝና ሰዎቹን በሙሉ በትህትና እያጎነበሠ ሠላምታ እየሠጠ ”አየህ የሺነህ አሁን እናንተ ባዘጋጃችሁት ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ እነዚህን ሁሉ ሰዎች የሚያስገባ ቦታ ይኖራል? እነሱስ በባህላቸው እንደለመዱት ድንኳን ጥለው በሬ አርደው ‹‹ሙሽራዬ ሙሽራ አበባ ይዘህ….በጊዜ ግባ›› ብለው መርቀው ሳይሸኙኝ ይዤ ሰመለስ ‘ሀይሎጋ’ ብለው ሳይቀበሉኝ…… በጓዳቸው በጣሉትና በጠመቁት ጠላና ጠጅ ሳይራጩ ….እዛ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ያልሆናችሁትን ሁኑ……እኔ ስደሰት እናንተ ተመልከቱ ብላቸው ደስ እሚላቸው ይመስልሀል? ስላሰባችሁልኝ አመሠግናለሁ። እኔን ግን የሚያስደስተኝ በሰፈሬ ውስጥ በድንኳን ብዳር ነው። ብሎ እንደመለሰው ነገረኝ።››
ምድር ላይ በቆየባቸው 38 ዓመታት ውስጥ ከስልሳ በሚልቁ የጥበብ ስራዎችን መስራት የቻለው አርቲስት ታሪኩ የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ ታኅሣሥ ሁለት ይህችን ምድር ተለይቷል። የአርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማግስቱ ሰኞ ታህሳስ ሶስት ተፈጽሟል።
በዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን እሁድ ታህሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም