በቅድሚያ፤-
ጥንታውያኑ ግሪካውያን ፈላስፎች የአደባባይ እሰጥ አገባ ሙግታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ “በመጀመሪያ በቃሉ ትርጉም እንስማማ” ይሉ እንደ ነበር በብዙ ድርሳናት ውስጥ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። ይህንን መልካም መርህ ለጽሑፋችን ግብዓትነት ብንጠቀምበት መልካም መስሎ ስለታየን የብዕረ መንገዳችንን ጉዞ የምንጀምረው በርዕሳችን ውስጥ ለተጠቀሱት “ወርቅ” እና “ደበሰ” ለሚሉት ሁለት ጽንሰ ሃሳቦች ተገቢውን የማብራሪያ መደላድል በማኖር ይሆናል።
የወርቅ ወግ፤-
“ወርቅ” የተሸከመው እሴትና ምሥጢረ ሃሳብ ከዕለት ተዕለቱ ምልከታችንና ከአዘቦት ቀን የተለምዶ ወጋችንና ከጌጥነቱ በእጅጉ የላቀና የመጠቀ ነው። ወርቅ ማጌጫና መዋቢያ ብቻም አይደለም። ወርቅ የሀብት፣ የስኬት፣ የክብር፣ የገዢነት፣ የቅንጦት፣ የዝና፣ የመልካም ባህርይ፣ የጉብዝናና የብርታት ወዘተ. ወካይም ጭምር ነው።
በወርቅ ዙሪያ የተንዠረገጉት እነዚህን መሰል ሽሽግ ትርጉሞች በተለምዶ በምናውቃቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ሃይማኖታዊ የማሕበረሰብ ተቋም ውስጥ ተሰግስገው ያሉና እንደ አእማድ የሚቆጠሩ እሴቶች ጭምር ናቸው። ወርቅ የገዢነትን ክብር ይወክላል ስንል የፖለቲካዊውን ባህርይ ማጣቀሳችን ነው። የነገሥታት በትረ ሥልጣን የሚወከለው፣ ዘውዳቸውም የሚንቆጠቆጠው በወርቅ ነው።
ሰብአ ሰገል ለሕጻኑ ክርስቶስ ካመጡለት ስጦታዎች መካከል አንዱ የስጦታ ዓይነት ወርቅ መሆኑ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የታወቀ ነው። “ስለምን ወርቅ አመጡለት?” ተብሎ ሲጠየቅ “የክርስቶስን የሉዓላዊነት ሥልጣነ መንግሥት ስለሚወክል ነው” በማለት የሃይማኖቱ መምህራን ማብራሪያውን ይሰጣሉ።
የአንድ አገር ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ መፈርጠሙ የሚረጋገጠው አገረ መንግሥቱ ባለው የወርቅ ሀብት ክምችት መጠን መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ምስክርነት ይሰጣሉ። ይህ እውነታ የወርቅን፣ የኢኮኖሚውንና የፖለቲካውን ጠንካራ ትሥሥር በሚገባ የሚያመለክት ነው። የመሠረታዊ ሸቀጦች ውድነት የሚገለጸውስ “ልክ እንደ ወርቅ ዋጋው ሰማይ ደርሷል” እየተባለም አይደለም።
በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ ለአሸናፊዎች የሚበረከተው የወርቅ ዋንጫ ወይንም ሜዳሊያ መሆኑስ እርግጥ አይደል። ለጦር ሜዳ ጀግኖችና በተለያዩ ዘርፎች አገራዊ ስኬት ባስመዘገቡ አርአያ ግለሰቦች ደረት ላይ በክብር የሚቀመጠው ሽልማትና ማድነቂያው ኒሻንስ “የወርቅ” የሚል ቅጽል ታክሎበትም አይደል። እነዚህና ሌሎች በርካታ መሰል ሽልማቶች ከማሕበራዊው ዘርፍ ጋር በሚገባ የሚጠቆሙ ናቸው። በባህርይው ሸጋ የሆነ ሰው ሲሞካሽስ “አመሉ ወርቅ ነው” እየተባለ መሆኑስ መች ይጠፋናል።
የወርቅ መገለጫ ቀለማት ብዙዎቻችን እንደምናስበው ቢጫው ብቻ ሳይሆን በርከት ያሉ ናቸው። ነጭ፣ ቀይ፣ ሮዝ፣ አረንጓዴ፣ ሰማያዊ ወዘተ. እየተባሉ ልክ እንደ ቀስተ ደመና በበርካታ ሕብረ ቀለማት እንዲሚታወቁ የዘርፉ ተመራማሪዎች በየጥናታቸው ማረጋገጫውን ሰጥተዋል። የወርቅ ደረጃ የሚመደበውም ካራት በተባለ መስፈርት እየተለካ 10፣ 14፣ 18፣ 24 ወዘተ. በሚሉ ቁጥሮች ውክልና መሆኑም ይታወቃል። በአጭሩ ወርቅ ከይዘቱ በተጨማሪ የያዘው ምሥጢራዊ ፍች ልክ እንደ ማዕድን ሥፍራዎቹ እጅግ የጠለቀና የረቀቀ እንደሆነ አስታውሶ ማለፍ ይቻላል።
ወደ አገራዊ ሥነ ቃሎቻችንና ትውፊቶቻችን መለስ ስንልም በብሂሎቻችን፣ በተረታ ተረቶችም ሆነ በፈሊጣዊ አጠቃቀሞቻችን ውስጥ ወርቅ ተደጋግሞ መነሳቱ የተለመደ ነው። ለማሳያነትም፡- “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ፣ ወርቅን በሚዛን እህልን በላዳን፣ ወርቅ ላበደረ ጠጠር፣ የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አይደለም፣ ወርቅ በእሳት ይፈተናል፣ ወርቅና ጨዋ አስታራቂ ነው፣ ወርቅ የያዘ ሳጥን በወርቅ አይለበጥም ወዘተ.” በሚሉት ምሳሌያዊ አነጋገሮች የሚተላለፉት መልእክቶች ምን ያህል የገዘፉ እንደሆኑ መመርመር ይቻላል። ወርቄ፣ ወርቅነሽ፣ ወርቅአየሁ፣ ወርቁ ወዘተ. የሚሉት የተለመዱት የግለሰቦች ስያሜዎችም ምን ለማለት ተፈልጎ ስሙ እንደተሰጣቸው አንባቢያን ሊገምቱ ይችላሉ።
ሌላው በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከወርቅ ጋር ተዳብሎ የተጠቀሰው እንግዳ መሰል ቃል “ደበሰ” የሚለው ነው። ወርቅ ይደብሳል ሲባል፣ ይወይባል፣ ይጠቁራል፣ ይቆሽሻል፣ ተፈጥሯዊ ውበቱንና ቀለሙን ያጣል፣ ያድፋል፣ ይነብዛል ማለት ነው። ስለዚህ በሁሉም የአዳምና የሔዋን (የአደምና የሐዋ) ዝርያዎች መካከል የማሕበራዊውን መስተጋብር ዋጋ ከፍ የሚያደርገው ይኼው የወርቅ ሀብት መጠን ነው።
በአገራት መካከል ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና ማሕበራዊ ሱታፌውን የሚያደምቀው፣ የሚያስከብረውና የሚያቆነጀው “ወርቅ” ይሉት ትንግርተኛ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል። የወርቅ ሀብት በአግባቡ ካልተያዘ በስተቀር መወየቡ፣ መበላሸቱ፣ መልክና ውበቱ መጠየሙ፣ በእድፍ መቆሸሹና በመጨረሻም ተገቢውን ዋጋ ማጣቱ አይቀሬና የግድ ነው። ወርቅ በእሳት ሲፈተን ያምር ካልሆነ በስተቀር ቀልጦ ያለመጥፋቱም የዚህ የከበረ ማዕድን ሌላው መገለጫ ነው።
በወርቅ ተምሳሌትነት የአገራችንን ገመና እንፈትሽ፤-
ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ በልዩ በረከትነት ከፈጣሪ የተቸረች በወርቅ የምትመሰል ድንቅ አገር ነች። ይህንን እውነታ ለመሞገት መሞከር ከቶውንም ቢሆን ያዳግት ይመስለናል። እንሟገት እንኳን ቢባል ግጭቱ የሚፋፋመው ከታሪክ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት እውነታዎችና ከተፈጥሯዊ የማሕበረሰባችን የአገነባብ ሥሪት ጋር መሆኑ አይቀሬ ነው።
ጉዳዩ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” ከሚለው አገራዊ ብሂል በእጅጉ የራቀ መሆኑን ማስታወሱ አግባብ ይሆናል። ትምክህት ተደርጎም ሊቆጠር አይገባም። ይህቺ ምድር በተፈጥሮ ሀብት፣ በብሔረሰቦቿ ጥበብና እውቀት፣ በአሥራ ሦስት ወራት ተስማሚ የአየር ንብረቷ፣ በታሪክና በባህሏ እንደምን የበረከት ፀጋ እንደተጎናጸፈች በንጹሕ አእምሮ ለሚያስብ ዜጋ ይጠፋዋል ተብሎ አይገመትም። በብብቷ ውስጥ አቅፋ የያዘቻቸው ብሔረሰቦቿም ልክ እንደ ወርቅ የከበረ ማንነት ያላቸውና የስብጥራቸው መገለጫ “ቀለማትም” እጅግ የተዋቡና የደመቁ ናቸው።
እውነታውን ቀድመንና ተቻኩለን ከመጻረራችን አስቀድሞ ሁላችንም ልንጠይቅ የሚገባው መሠረታዊ ጥያቄ እነዚህን የመሰሉ በወርቅ ባህርያት የሚመሰሉ አገራዊ እሴቶቻችንና ፀጋዎቻችን ስለምን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበሱ፣ እየወየቡ፣ እየጠቆሩና እየከፉ ሊሄዱ ቻሉ? ቆም ብለንና ሰክነን ልንነጋገርባቸው ጊዜው አጀንዳ አድርጎ ያቀበለን ዋና ጉዳይ ይመስለናል።
ዛሬ እያስተዋልናቸው ያሉት በርካታና ቅጥ አምባሩ የጠፋባቸው አገራዊ ችግሮቻችን ስለምን እንደ ክፉ ባዕዳን ወራሪዎች አስገብረው ሊገዙን እንደቻሉ ደፈርና ጫን ብለን ልንመክርባቸው ይገባል እንጂ “ጉዳዬ አይደሉም” ብለን ገሸሽ በማድረግ ብንርቃቸው የሚያዋጣ አይሆንም።
ለምሳሌ፡- “በዚህች መሰሏ የገነት ተምሳሌት ምድር” ላይ እየኖርን ስለምን በርሃብ ለመቀጣት በራሳችን ላይ ፈረድን? ስለምን ወደ ለምለሙ ምድራችን የስንዴ ርዳታ እንዲጎርፍ በራችንን ወለል አድርገን ከፈትን? እኮ ስለምን ያለ ግል ምርጫችንና ፍላጎታችን ለተገኘንበት ብሔር፣ ቋንቋና ባህል እያዳላን መገዳደልን ምርጫችን አደረግን? ልብ ተቀልብ፣ ሩሕ ለሩሕ እየተናበብን ወደ ጋራ መፍትሔ መቃረብ እስካልቻልን ድረስ እኛ ብናልፍም ታሪክ መትረፉ ስለማይቀር ውጤቱ ትዝብትና ማንነታችንን ጥቀርሻ አልብሶ ከማለፍ ውጭ አንዳች ፋይዳ አይኖረውም።
በታሪካችን ውስጥ ዘመን አምካኝ ሆነው ሲያሸማቅቁንና አንገት ሲያስደፉን የኖሩትን የደበሱና የበለዙ አገራዊ ታሪኮቻችንን በሙሉ ከመዘርዘር ታቅበንና ለጊዜ ጊዜ በመስጠት አቆይተናቸው ወደ ሰሞንኛው መሪር ሀዘናችንና ቀልባችንን ወዳስቆጣው ጉዳይ ውሱን ጥቁምታ እናድርግ።
በአዲስ አበባ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የአንድን ክልል ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ምክንያት አድርገው የተነሱት ሰሞንኞቹ ሁከቶችና ረብሻዎች ሥር መሠረታቸው ቢጠና በርግጡ ምክንያቱ ከላይኞቹ ባለሥልጣናትና ከታችኞቹ እንደሚነገረን ነው ወይንስ ሌላ ድብቅ አጀንዳ ይኖረዋል?
ይህ በአዲስ አበባ የተጫረው የእሳት ወላፈንስ በዚሁ በመዲናችን ብቻ ተወስኖ ስለመቅረቱ ምን ዋስትና ይኖራል? የችግሮቻችንን ሰበቦች ደፍረን ማፍረጥ እስካልቻልን ድረስ እየተደፋፈርን እርስ በእርስ ለመጠፋፋት ስለምንበረታታ ልባችንን ሰፋ አድርገንና የስሜታችንን ግለት አቀዝቅዘን መመካከሩ ውዴታ ብቻም ሳይሆን ግዴታም ጭምር ይመስለናል።
አገሪቱ እንደ ወርቀ ዘቦ ተጎናጽፋ ለዘመናት ያኖረችን የእርስ በእርስ የመከባበር እሴት ዛሬ ዛሬ እየተሸረሸረ ለመተማመን እስከማንችል ድረስ “ብሔራዊ የጥርጣሬ ባህል” ወደ መሆን ደረጃ ሊፋፋ የቻለው ምን ይሉት ማዳበሪያ ቢቀላቀልበት ነው? ይህን መሰሉ “ወርቃማ” እሴት እንዲደብስ ምክንያቱስ ምንና ማን ነው? ማንስ ነበር?።
በአንድ የእውቀት ማዕድ ላይ የተቀመጡ ልጆቻችን እርስ በእርስ የጎሪጥ እየተያዩ ውለው እንዲገቡስ ምክንያት የሆነው ክፉ ነቀርሳ በርግጡ ተለይቶ ይታወቃል ወይንስ እንደ ገበያ ውስጥ ሌባ ሰራቂውና ተሰራቂው “ሌባ ሌባ!” እየተባባሉ እንደሚሯሯጡት ዓይነት ይሆንን? በሰላም የወጡት ልጆቻችን በማያውቁት ጉዳይ በደም አበላ ተጠምቀው ሲመጡ ማየት ለወላጆች ምን ያህል ቅስም ሰባሪ እንደሆነ አጥፊዎቹም ሆኑ ተሟጋቾቹ አልተረዱትም ይሆን?።
ቋንቋና ባህላችንን ከልብ የምንወዳቸውና የምናከብራቸው ሁለቱንም ስለተወለድንባቸው እንጂ በደም ውርስ የተገኙ ፀጋዎች ስለሆኑ አይደለም። ቋንቋን ማወቅ ያስከብራል እንጂ የመለያያ ምክንያት ሆኖ ከቶውንም “ሰይፍ አያማዝዝም”። የክልል ሰንደቅ ዓላማም ቢሆን የአንድ ውሱን ክልል የፖለቲካ ምልክት እንዲሆን በአንድ ወቅት የፖለቲካ ተዋናዮች ፍላጎት የተፈጠረ አርማ እንጂ ከዘመናት አስቀድሞ “እንዳይለወጥና እንዳይሻሻል በውግዘት ማህተም ፀድቆ” የተላለፈ ውርስ አይደለም።
መዝሙሩም ቢሆን ለተወሰነ የሥልጣን ዘመን የተገደበ እንጂ እስከ ዕለተ ምጽአት የሚኖር “የሃይማኖት ቀኖና” አይደለም። እናስ በእነዚህ እውነታዎች ስንመዝነው የሰሞኑ ረብሻ መንስዔ በርግጡ ውሃ መቋጠር የሚችል ጉልበት ነበረውን? ደግሞስ ይኖረዋልን? የደረሰውን የንብረትና የሥነ ልቦና ጉዳትና ስብራትስ የመጠገን ብርታት አለው። አገራችንንስ ባልተፈለገ ሌላ መከራ ውስጥ ብትወድቅ የሚጠቀመው ማነው?።
ዛሬ ፖለቲካውን በመዘወር የአገር ናላ የሚያዞሩት አብዛኞቹ ፖለቲከኞችና “እሳት አራጋቢ አክቲቪስቶች” ያለምንም ይሉኝታ የተማሩት በውጭ አገራት ቋንቋ ጭምር እንጂ (ብዙውን ጊዜያቸውን ያጠፉት በባዕድ ቋንቋ በመማር መሆኑ ሳይዘነጋ) “የእናት አባቴ ውርስ” በሚሏቸው የአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዳልሆነ ጫን ብለን ማስረገጥ ያለብን ይመስለናል። የትኛውንም ቋንቋ መማር ክብርም ጌጥም ቢሆንም።
ይህ ጸሐፊ አፍ የፈታበትን ቋንቋ እና በአንድ የተለየ ቋንቋ ተናጋሪ ማሕበረሰብ መካከል በመኖር የለመደውን ሌላ ተጨማሪ ቋንቋ በማወቁ አትርፎበታል እንጂ አንድም ጉዳት አላጋጠመውም፤ አልከሰረምም። እየተደነቃቀፈም ቢሆን በውጭ አገራት ቋንቋ መማሩም በእጅጉ ጠቅሞት አንቱ አሰኘው እንጂ ሰብእናውን አላንኳሰሰም። እናስ ልጆቻችንን ባልገባቸውና ባልተረዱት ጉዳይ “የፖለቲካ ማስተሰረያ ጦስ” እንዲሆኑ የተፈረደባቸው ስለምንድን ነው? የታወኩትና የሥነ ልቦና ቀውስ እየደረሰባቸው ያሉት ልጆቻችን ብቻ ሳይሆኑ እኛ ወላጆች ጭምር ስለመሆናችን ያልገባቸው አካላት ይኖሩ ይሆን?።
አንዱን ስንቋጥር ሌላው አገራዊ ጉዳያችን እየተተረተረ፣ አንዱን ቀዳዳ ስንደፍን ሌላኛው እያንጠባጠበ፣ ያኛውን ችግር ስናጠራ ሌላኛው ጉዳይ እየተበጠበጠ መኖሩ ለድህነታችን ጉልበት ይሆን ካልሆነ በስተቀር አንዳች እርባና ስለማይኖረው ቆም ብለን በስክነት ብናስብበት አይከፋም።
በወርቅ መስለን የኖርንባቸውና ያኗኗሩን እሴቶቻችንንና ዛሬ ከእጃችን ወድቀው ለመከራ የዳረጉንን ፀጋዎቻችንን ቆም ብለን መፈተሽ ጊዜው የሚጠይቀው የመፍትሔ መንገድ ስለሆነ ሰከን እና ትንፋሻችንን ሰብስበን አድርገን በመወቃቀስ ሳይሆን በመከባበር፣ በመፈራት ሳይሆን በመቀራረብ፣ በመተቻቸት ሳይሆን በመደማመጥ ልንመካከር ግድ ይሏል።
“አሌፍ፡- ወርቁ እንዴት ደበሰ? ጥሩው ወርቅስ እንዴት ተለወጠ? ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ [ልጆቻችን] የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቆጠሩ?” (ሰቆቃወ ኤርሚያስ ምዕ. 4፡1-2)። በማለት እንዳነባው የቅዱስ መጽሐፉ ነብየ እግዚሃር ኢትዮጵያም ዛሬ “ወርቃማ የሆኑት እሴቶቿ ደብሰው ስለተበላሹባት” መንታ መንታ የምታነባ ይመስለናል።
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በተጻፉ ጥቂት የግጥም ስንኞች ሃሳባችንን እንጠቅልል።
“ትናንት መሠረት ነው ዛሬ የቆመበት፣-
ዛሬም መሠረት ነው ነገ የሚያርፍበት።
የዛሬው ውሳኔ ሚዛን ነው ለነገው፣
ዛሬ ያልከበደ ነገ መቅለሉ ነው።
ዛሬ እንደሠፈሩት ቢተርፈም ቢጎድልም፣
ነገ ይሠፈራል ታሪክ ፍርዱ አይቀርም።
ከባዱ ውሳኔ ትልቅ ኃላፊነት፣
የነገው ቅርጸ-መልክ የሚታነጽበት።
ነገ ዛሬ ሲሆን ዛሬም ትናንትና፣
የዛሬ ቁራኛ ግልጽ ድንቁርና።”
(ምንጭ፡- “ሕያው ድምፆች” ከቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የግጥም ስብስብ ተመጥኖ የተወሰደ።) ሰላም ይሁን።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015