የደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ደርባን 21ኛውን የመላው አፍሪካ ካራቴ ቻምፒዮና በቅርቡ አካሂዳለች። በዚህ ውድድር ከተካፈሉት አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ብትሆንም፤ ወደ ውድድሩ ያቀናው ብሄራዊ ቡድን በገንዘብ እጦት ምክንያት በጊዜ ከውድድር እንደተሰናበተ ገልጿል። ቡድኑ ከደርባን መመለሻ የሚሆነውንም ወጪ በከተማዋ በሚኖረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እንደተሸፈነለት ቅሬታውን አቅርቧል።
ቡድኑን ይዘው ወደ ደርባን የተጓዙት ኢንስትራክተር ኑሩ መሃመድ፤ በአራት ተወዳዳሪና በአንድ አሰልጣኝ የተወከለው ቡድን በውድድሩ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችል እንደነበረ ይናገራሉ። የቡድኑ አባላት የተመረጡት የኢትዮጵያ ለሁሉም ክፍት የሆነ የካራቴ ውድድር ሲሆን፤ በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደ ውድድር አንድ የብር እና አራት የነሃስ ሜዳሊያዎችን አግኝቶ ነበር። ቡድኑ ለደቡብ አፍሪካው ውድድርም የ10 ቀናት ዝግጅት ካደረገ በኋላ ወደ ደርባን ማቅናቱን ያስታውሳሉ።
ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ወቅት የገንዘብ ችግር የገጠመው ቢሆንም በቡድን ውጤት ምርጥ ስድስት ውስጥ መግባት ችሎ ነበር። ወደ ደርባን ለሚያደርገው ጉዞው ትኬት እስከመቁረጥ በነበረው ሂደት የፋይናንስ ችግር ገጥሞት የነበረው ቡድን የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚዎች ከኪሳቸው ገንዘብ ወጪ በማድረግ ሲያግዙት ቆይተዋል። በጉዞው ዕለትም በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስር ዴኤታ የሽኝት መርሃ ግብር መዘጋጀቱ የቡድኑን የገንዘብ ችግር ይቀርፋል ተብሎ ቢታሰብም እንዳልተሳካ ተገልጿል። የቡድኑ አባላት ግን በውድድሩ ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው በማመናቸው ጉዞውን በራሳቸው ገንዘብ ለማድረግ እንደወሰኑ አሰልጣኙ ያብራራሉ።
በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ በኩል የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ቡድኑ ወደ ደርባን ካቀና በኋላም ሂደቱን ጨርሶ ወደዚያው የመጓዝ አማራጭ ተይዞም ነበር። በዚህም ኅዳር 21/2015 ዓ.ም ወደዚያው የተጓዘው ቡድን ከጆሃንስበርግ ወደ ደርባን ያለውን ረጅም መንገድ በመኪና በመጓዝ፣ አነስተኛ ሆቴል ፈልጎ በማረፍ እንዲሁም ስልክና ፓስፖርት በእዳ አስይዞ ትጥቅ እስከመግዛት የደረሰ መሰዋዕትነትን ለመክፈል መገደዱን ጠቁመዋል። የቡድኑ አባላት በውድድሩ የገጠማቸውን ችግሮች ታግሰው እስከ አራት ዙሮች በፉክክር ቢጓዙም በውድድሩ ለመቆየት ተጨማሪ መመዝገቢያ መክፈል የነበረበትን ገንዘብ ባለማግኘቱ ምክንያት መሰናበቱ የግድ እንደሆነ ገልጸዋል። ቡድኑ በእዳ የተያዙትን ንብረቶች ለማስመለስ እና ወደአገር ቤት ለመመለስ ደግሞ ሌላ ወጪ በማስፈለጉ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ከማስቸገር ውጭ አማራጭ አልነበረውም።
አገር በምትወከልበት በዚህ ውድድር ላይ ለመካፈል ፌዴሬሽኑ እንዲሁም ስራ አስፈጻሚው ብዙ ጥረቶችን አድርጓል። ነገር ግን ስፖርቶችን በበላይነት የሚመራው ሚኒስትር መስሪያ ቤት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ምክንያት በሰው አገር ላይ የቡድኑ አባላት መጉላላቱን ተናግረዋል። ያም ሆኖ የደርባን ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን ጥረት ኅዳር 27/2015 ዓ.ም የቡድኑ አባላት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለቡድኑ አቀባበል ቢያደርግላቸውም ችግሩ ለምን እንደተከሰተ እንዲሁም በስነልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ተወዳዳሪዎች ማብራሪያ የሚሰጥ አካል እንዳልነበረም አስረድተዋል። በመሆኑም በተመሳሳይ መንገድ በግለሰቦች ወጪ ስፖርተኞቹ ወደየመጡበት እንዲመለሱ መደረጉን አሰልጣኝ ኑሩ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ፤ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆቹ ዓመት የጃፓን መንግስት ዕውቅና ከሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን መሆኑን ይናገራሉ። በምስራቅ አፍሪካም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በስፖርቱ አምስት ሜዳሊያዎች የተመዘገበበት ዓመት መሆኑን በማስታወስ በደርባኑ ውድድር ላይም ውጤታማ ለመሆን ዝግጅት መደረጉን ያስረዳሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ድጎማ እጅግ አነስተኛ ከመሆኑም ባለፈ በዚህ ዓመት ምንም ዓይነት ገንዘብ ለፌዴሬሽኑ እንዳልተለቀቀ ይጠቁማሉ። የቡድኑ ዝግጅትም እሳቸውን ጨምሮ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከኪሳቸው ገንዘብ በማውጣት እንዲሁም ሆቴሎችን ትብብር በመጠየቅ ነበር የተከናወነው። ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ለሚመራው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስለውድድሩ አስታውቆ ድጋፍ እንደሚደረግለትም ቃል ተገብቶለት እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ይሁንና የጉዞው ወቅት ሲደርስ የተባለው ባለመሆኑ ፕሬዚዳንቱ በራሳቸው ገንዘብ የጉዞ ትኬት መቁረጣቸውን ጠቁመዋል። በቡድኑ አባላት ላይ የስነልቦና ጫና እንዳይደርስባቸው ስራ አስፈጻሚው የድጋፍ ሂደቱን በመቀጠል ወደ ደርባን ይዞ የመሄድ አማራጭ እንደያዘ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ነገር ግን ጥረቱ ስኬታማ ሊሆን እንዳልቻለ ያስረዳሉ። ቡድኑ ወደ አገር ከገባም በኋላ የተደረገላቸው ምንም ዓይነት ነገር የለም ሲሉም ወቀሳቸውን ያቀርባሉ።
በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ተጠይቀው ምላሽ የሰጡት በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ በቀለ፤ ፌዴሬሽኑ አስቀድሞ ክስ እንደነበረበት ያስታውሳሉ። ከብሄራዊ ቡድኑ ምርጫ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያቀረቡ አካላትን በማጣራት ላይ እንደነበሩ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ ይሁንና በውድድሩ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አሳውቀው መቅረታቸው አገርንም የሚያስቀጣ በመሆኑ የተጀመረው እንዲቀጥል እንደተነገረው ያስረዳሉ። ይሁንና ቡድኑ ሲመለስም ሪፖርት ማቅረብ ሲገባቸው እንዳላቀረቡ ተናግረዋል። ‹‹ከውድድሩ አስቀድሞም እቅዳቸውንና የውድድር ወቅቱን አላሳወቁም›› ያሉት አቶ ተስፋዬ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቡድኑ ከውድድር ሲመለስ ድጋፉን እንደሚያደርግ አሳውቆ ነበር ገልጸዋል። ‹‹አብዛኛዎቹ የስፖርት ማህበራት አስቀድሞ ከማሳወቅ ይልቅ በድንገት ቀርበው ድጋፍ ይጠይቃሉ። ይህ ደግሞ ከመንግስት የበጀት አሰራር ጋር ይጣረሳል›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ በቀጣይም በፌዴሬሽኑ የተጀመረውን አቤቱታ ለማየትና ጉዳዩም ላይ እልባት ለመስጠት ቀጠሮ መያዙን አስረድተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም