ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ሁለተኛ ዙር ፉክክር ሊቋጭ የሁለት ጨዋታ ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ባህርዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን በተቀራራቢ ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ፉክክር ያደመቁት ሊጉ የድሬዳዋ ቆይታ በምን መልኩ እንደሚጠናቀቅ በጉጉት ይጠበቃል። የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ እየተቀያየሩ ከሚመሩት ሦስቱ ክለቦች በተጨማሪ በወራጅ ቀጠናው ሲዳማ ቡና፣ ኢትዮ አሌትሪክ እና ለገጣፎ ለገዳዲ የሚያደርጉት ትግልም በሊጉ የድሬዳዋ ቆይታ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነው። የከፍተኛ ግብ አግቢነቱ ፉክክር በቶጎዋዊው የፈረሰኞቹ ግብ አምራች እስማኤል ኦሮ አጎሮ አስር ግቦች እየተመራ ቢገኝም፤ ጌታነህ ከበደ ከወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ አስር ግቦች አስቆጥሮ ፉክክሩን አጓጊ አድርጎታል። የባህርዳር ከተማው ፍጹም ዓለሙም በሰባት ግቦች የኮከብ ግብ አግቢነቱን ፉክክር በቅርብ ርቀት እየተከተለ ይገኛል።
በሊጉ እየተሳተፉ የሚገኙ ክለቦች ከውጤት ማጣት ጋር ተያይዞ የአሰልጣኞችን ስንብት ያስታወቁበት ያለፉት ሳምንታት አነጋጋሪ ጉዳዮች ነበሩት። አንዳንድ ክለቦች ለተጫዋቾች ደሞዝ መክፈል አለመቻልም ሊጉ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ያስተናገዳቸው አበይት ክስተቶች ናቸው። በኳታሩ የ2022 ዓለም ዋንጫ ምክንያት የሊጉ ያለፉ ጥቂት ሳምንታት ጨዋታዎች የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ማጣት ውስጥ ቢከርሙም ፉክክሩ ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል። የአሰልጣኝ ስንብት ካደረጉ ክለቦች መካከል ለገጣፎ ለገዳዲ በቅርብ የሚጠቀስ ነው። ለገጣፎ ለገዳዲ የቀድሞ አሰልጣኙን ወደ ምክትል አሰልጣኝነት በማውረድ አሸናፊ በቀለን በዋና አሰልጣኝነት ከቀናት በፊት እንደሾመ ይታወሳል።
የሊጉ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ባህርዳር ላይ ሲካሄዱ ከሱፐር ስፖርት ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ጋር በተያያዘ ትልቅ ትኩረት አግኝቶ የነበረው ቢሆንም በሁለተኛው ዙር የድሬዳዋ ቆይታው በዓለም ዋንጫ ምክንያት ሊቋረጥ ችሏል። ከተለመደው ሰኔ ወደ ህዳር ቀይሮ እየተካሄደ የሚገኘው ትልቁ የዓለም ዋንጫ በሌሎች አገራት ሊጎች ላይ የፈጠረው ተፅዖኖ ተመሳሳይ ባይሆንም በኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ላይም አርፏል። ቢያንስ ሊጉ ከቴሌቪዥን ስርጭት ጋር በተያያዘ ሽፋን ማግኘት ያልቻለ ሲሆን ይህም ከድሬዳዋ ውጪ ያለው ተመልካች በቅርበት እንዳይከታተለው ሆኗል።
ፕሪምየር ሊጉ የስያሜ መብቱን ከሸጠ፣ የሱፐር ስፖርት ቀጥታ ቴሌቪዥን ሽፋን ካገኘና በሼር ካምፓኒ መተዳደር ከጀመረ ወዲህ የአገር ውስጥ ተመልካች ትኩረትን መሳቡ እርግጥ ነው።
ዓለምአየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2015