የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የ2015 ዓ.ም የሰራተኞች ስፖርታዊ ውድድርና ጨዋታ ‹‹ስፖርት ለሁሉም›› በሚል መሪ ቃል በቢሮው የሰራተኞች መዝናኛና ጅምናዚየም ማዕከል ትናንት በድም ቀት ተጀምሯል።
ውድድሩን ያስጀመሩት የቢሮው አማካሪ አቶ በኃይሉ በቀለ፣ ሰራተኞች በተለያዩ ስፖርቶች ላይ በመሳተፍ እየተዝናኑ የሚያስመዘግቡት ውጤት መነቃቃትን እንዲፈጥርላቸው ተናግረዋል። ‹‹ውድድሩ የሰራተኞችን ግንኙነት ያጠናክራል›› ያሉት አቶ በኃይሉ በስፖርት የዳበረ ሰራተኛ ጤናውን ከመጠበቁ ባሻገር አገልግሎት አሰጣጡንም ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል።
የ2015 የሰራተኞች መዝናኛ ጨዋታ ተወዳዳሪዎችን እና ደጋፊዎችን ከማዝናናት ባለፈ ጤናማ ሲቪል ሰርቫንት ለመፍጠር እንደሚያስችል የገለፁት የማሕበረሰብ ስፖርት ማስፋፊያና ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር አቶ እንግዳወርቅ ዳንኤል በዘንድሮ ጨዋታ በጠረጴዛ ቴኒስ፣ በፑል፣ በከረንቡላ፣ በቼዝ፣ በዳርት፣ በዳማ እና በጆተኒ ጨዋታዎች በሰራተኞች መካከል ውድድር እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ውድድሮቹ በሁለቱም ጾታ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ እንግዳወርቅ፣ ተወዳዳሪዎች የወጣውን መርሃ ግብር በማየት በውድድሩ ቦታ እና ሰዓት እንዲገኙ አሳስበዋል። የ2015 ዓ.ም የሰራተኞች ጨዋታ ውድድር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ፐብሊክ ሰርቪስ የሰው ሀብት ልማት ቢሮ፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሚሳተፉ ሲሆን ከታሕሳስ 5 እስከ 25 2015 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2015