መሰለች ጃናቶ የስምንተኛ ክፍል ሞዴል ፈተናን ለመፈተን በክፍል ውስጥ ተገኝታለች። ሆኖም ሞዴል ፈተናውን እየሰራች ባለችበት ቅጽበት የዓይኗ ብርሃን ድንገት ድርግም አለ። በጨለማ ውስጥ ተዋጠች።
ይህንን ሁኔታ እንኳን እሷ ጓደኞቿ አላመኑም። ትምህርት ቤት በራሷ ሄዳ በመሪ ስትመለስ ቤተሰቦቿ ተደናገሩ። ክፉኛም ደነገጡ። ያላቸው አማራጭ ሆስፒታል መውሰድ ነበረና የተለያየ ሆስፒታል ወስደው አስመረመሯት። ከአርባ ምንጭ አልፈውም በአገሪቱ ያሉትን ሆስፒታሎች አዳረሱ።
መሰለች ጃናቶ በድንገት አይኗ ሲጠፋ አመቱ 2005 ነበር። እሷም የ20 ዓመት ወጣት ነበረች። መሰለች ጎበዝ ተማሪ ነበረች። ደብል በመምታትም ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው በማለፍ ትታወቃለች። ሆኖም የአይን ብርሃን በድንገት መጨለም ተስፋዋን አብሮ አለጨለመው። ሕይወቷ ባልታሰበ መንገድ ተቀየረ።
‹‹የእኔ ብርሃን መጨለም ሕይወቴን አመሰቃቀለው። ግራ ገባኝ። የአይኔን ብርሃን ለመመለስ ተንከራተትኩ። ሆኖም የትኛውም ሆስፒታል ብርሃኔን ሊመልስልኝ አልቻለም›› ስትልም መፍትሄ ሳታገኝ ወደ ቤቷ መመለሷን ታወሳለች። ዓይነስውር በመሆኗ ትምህርቷ ተቋረጠ። ስትዘጋጅበት የከረመችው ክልላዊውን የስምንተኛ ክፍል ፈተናም መውሰድ አልቻለችም። ትምህርት ቤት መሄድ ቀረና መሰለች ውሎዋ ቤት ቁጭ ማለት ሆነ።
‹‹ጓደኞቿ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እኔ ዓይነስውር በመሆኔ ምክንያት እቤት ውስጥ በመዋሌ እያለቀስኩ ነበር ጊዜዬን የማሳልፈው። በጣምም አዝን ነበር›› የምትለው መሰለች ዓመታትን በዚህ ጨለማ ውስጥ መኖር በእጅጉ እንዳማረራትም አልሸሸገችንም። በሕይወት የመኖር ተስፋዋም ተሟጠጠ።
ችግር ሲመጣ እየደራረበ ነው እንደሚባለው መሰለች ብርሃኗን ባጣች ማግስት ሁለቱንም ወላጆቿን በተከታታይ በሞት ተነጠቀች። የምትይዘውን የምትጨብጠውን አጣች። ሰማይና ምድሩ ተደፋባት። በወቅቱ የነበራት ጭላጭ ተስፋም ከውስጧ ተኖ ሲጠፋ ተሰማት። በተደጋጋሚም ራሷን የማጥፋት ሙከራ አደረገች። ሆኖም አልተሳካላትም።
ሕይወት ቀጠለ። ለራሷ ብቻም ሳይሆን ለሁለት ወንድሞቿ መኖር እንዳለባት አመነች። ከሁለት ወንድሞቿ ጋር መኖሯን ቀጠለች። ሴት በመሆኗ የቤቱ ኃላፊነትም በእሷ ጫንቃ ላይ ወደቀ።
መሰለች ቀጥላለች። ‹‹ሕይወት እየመረረኝ ስለመጣ ዕድሌን አሁንም በእጅጉ ከማማረር አልዳንኩም። በዚህ ወቅትም አልቀስ ነበር። ሕይወቴን ለማጥፋት የማደርገውንም ሙከራ አላቆምኩም ነበር ›› ትላለች በወቅቱ ነበረውን ሁኔታ ስታስታውስ። በዚህ ጨለማ ሰዓት አብዝታ በአቅራቢያ ያለ ቤተክርስቲያን ትሄድ ነበር ለራሷም ፀሎት ትፀልያለች። ለእሷም ሰዎች ይፀልዩላት ነበር።
በዚህ ወቅት ነበር አቶ ዘለቀ ከፋሞን ያገኘቻቸው። ዕውነት ለመናገር ለፀሎት ቤተክርስቲያን መሄዴና ከሰው መገናኘቷ ወጣቷን መሰለች ጠቅሟታል። አቶ ዘለቀ የልዩ ፍላጎት ትምህርት መምህር ናቸው። ታዲያም ትምህርት ቤት ወስደው የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን ለመቀጠል ሊያስመዘግቧት ሞከሩ። ሆኖም ምዝገባው አልፎ ስለነበር ሳትመዘገብ ቀረች። ይሄ የሆነው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2019 ነበር።
በዓመቱ ማለትም በፈረንጆቹ 2020 መሰለች ቀድሞ ትማርበት የነበረው ጆርጊ ትምህርት ቤት ከስምንተኛ ክፍል ያቋረጠችውን ትምህርቷን ለመቀጠል ተመዘገበች። መሰለች ትምህርቷን የቀጠለችው የዓይን ብርሃኗን በማጣቷ አንብባ፤ተረድታና ጽፋ ፈተናውን መሥራት የሚያስችላትን የብሬል ትምህርት ጎን ለጎን በመማር ነበር። በዚህ ሁኔታ ተምሮ ፈተና መፈተኑ እጅግ ቢከብድም መሰለች ተያያዘችው።
‹‹የብሬል ትምህርት በአካታችነት ይሰጥበት የነበረው ሙዳላ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሳምንት ሁለት ቀን እየሄድኩ የብሬል ትምህርት አከታተል የነበረ መሆኑ የበለጠ አድካሚ ነበር›› ስትል ታወሳዋለች።
እሷ እንደምትለው ሆኖም የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ አበጀ አቺኮ በጥናትም በማበረታታትም ይረዷት ነበር። የልዩ ፍላጎት መምህርቷ ታገሰች በብሬል ልምምዱ ወቅት ከፍተኛ እገዛ አድርጋላታለች። እናም በዚሁ ዓመት የስምንተኛ ክፍል ፈተና ተፈተነች።ጥሩ ውጤትም ማምጣት ቻለች።
‹‹በፈተናው አጥጋቢ ውጤት ማምጣት የቻልኩትም ብሬል በመከታተሌና እነዚህ ሰዎች ያግዙኝ ስለነበረ ነው›› ብላናለች።የብሬል ትምህርት እንድትከታተል ያደረጋት WEEMA International የተባለ ድርጅት እንደሆነ የምታወሳው መሰለች ‹‹ድርጅቱ እየተመራሁ ትምህርት ቤት እሄድበት የነበረውን በትር(ዘንግ) ጨምሮ የድምፅ መቅጃ ሪከርደር፤ ለሪከርደሩ የሚውሉ ባትሪ ድንጋዮች፤ የብሬል ስቴንስሎች፤የብሬል ወረቀቶችን ድጋፍ አድርጎልኛል››የምትለው መሰለች ድርጅቱ እና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ያደርግላት የነበረው ድጋፍ ተስፋዋን ሁሉ እንደገና እንደመለሰላት ታወሳለች። በተለይ ድርጅቱ ትምህርት እንደጀመረች ከትምህርት ሰዓት ውጪ በተከታታይ በስነ ልቦና ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት እንድትወስድ ያደረግላት የነበረ መሆኑን ታስታውሳለች።
‹‹ይሄን አገልግሎት ማግኘቴ ከእንግዲህ ዋጋ የለኝም ብዬ በተደጋጋሚ ረሳሴን ለማጥፋት አደርጋቸው የነበሩት ሙከራዎች ትክክል እንዳልነበሩ ዞር ብዬ ወደ ውስጤ እንዳይ አድርጎኛል።በራሴ እንድተማመንና ብሬል ተምሬ ትምህርቴን መከታተል ብሎም እንደ ዓይናማነቴ ዘመን ሁሉ ጥሩ ውጤት ማምጣት እንደምችል የሚያደርግ ጥሩ ግንዛቤ ፈጥሮልኛል ››ትላለች መሰለች።እንድትበረታታና ተስፋ እንዲኖራትም አስችሏታል።
መሰለች ስምንተኛ ክፍል ፈተናን በአጥጋቢ ውጤት በማለፏ ሆዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆና ገባች። ሆዶ ትምህርት ቤት በፊት እንደምትማርበት ትምህርት ቤት ሁሉ የትምህርቱ ማህበረሰብ መምህራን ተማሪዎች ያበረታቷትና ድጋፍ ያደርጉላት ነበር። WEEMA International የተባለው ድርጅት ምክርና የትምህርት አጋዥ መሳሪያዎችና ቁሳቁስ ድጋፍ አልተለያትም። የሚያስፈልጋትን ሁሉ በማቅረብ ከጎኗ ነበር። በመሆኑም በትምህርት ቤቱ ከሚገኙ ከሁሉም የደረጃ ተማሪዎች አንዷ በመሆን ተሸለመች። ጥሩ ውጤት በማምጣትም ወደ 10ኛ ክፍል ተዛወረች።
‹‹አሁን ሕይወት ለኔ አጓጊ ሆናልኛለች። ትልቅ ደረጃ የመድረስና በትምህርቴ ፕሮፌሰር እስከመሆን የሚያስችል ተስፋ ሰንቂያለሁ››ትላለች መሰለች ሀሳቧን ስትቋጭ። እኛም ተስፋዋ ዕውን እንዲሆን የሁሉም ድጋፍ አይለያት በማለት ጽሑፋችንን ደመደምን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2015