ሰሞኑን የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ መኖሩን ተከትሎ ዘውዴ መታፈሪያ፣ ተሰማ መንግስቴ እና ገብረየስ ገብረማሪያም በጊዜ ወደ ቤታቸው በመግባት እግር ኳስ ማየት በመጀመራቸው አብሮ ማምሸት ቀንሰዋል። ትናንትና ግን ጨዋታው ባለመኖሩ ተደዋውለው ተገናኙ። አመሻሽ ላይ ገብረየስ እንደልማዱ ቀድሞ በግሮሰሪው ተገኝቶ ያላበው ቢራ እየተጎነጨና እያጣጣመ ጠበቃቸው። ዘውዴም ብዙ ሳይቆይ በቦታው ተከሰተ። ተሰማ ግን ግማሽ ሰዓት አስጠብቋቸዋል።
ስለሰሞኑ እግር ኳስ ካወሩ በኋላ ፋይዳው ላይ መከራከር ጀመሩ። ዘውዴ እግር ኳስ አገራዊ ስሜትን ለማምጣት እና አንድነትን ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ዓለምን አንድ ለማድረግም ትልቅ መሳሪያ ነው ሲል፤ ገብረየስ ግን ዓለምን አንድ ማድረግ የማይታሰብ ነው፤ እንዳውም ከመዝናኛነት ያለፈ ፋይዳ የለውም ሲል ተከራከረ። ተሰማ ሁለቱንም ለማስማማት ሳይሆን የሚያምንበትን እንደሚናገር ገልፆ፤ ለመዝናናት እንደሚያገለግል ግን ደግሞ ዓለምን አንድ ለማድረግ ሳይሆን አገራዊ ስሜትን እና አንድነትን ለማምጣት ትልቅ መሳሪያ ነው የሚል እምነት እንዳለው ጠቆም አደረገ። አያይዞ ግን ሁልጊዜ ዘውዴ ስለአንድነት አብዝቶ መናገሩ ልዩነት መኖሩን እንዳያስረሳ ስጋት እንዳለበትም አብራራ።
ዘውዴ ‹‹እርግጥ ነው። ሰው ከሰው ይለያያል። ሰው ከሰው እንደየደረጃው አንድ የሚያደርገው ነገር ደግሞ ይበዛል። በዓለም ያለው ሰው በሙሉ ይበላል፤ ይጠጣል። ሳይበላ ሳይጠጣ የሚኖር የለም። ይህ የዓለም ህዝብን አንድ ያደርጋል። በተቃራኒው ደግሞ የዓለም ሕዝብን እያንዳንዱን ሰው የሚያለያይ ነገር አለው። ምክንያቱም የእያንዳንዱ ሰው የዓይን ብሌንም ሆነ የጣት አሻራ የተለያየ ነው። ሰዎች በቀለማቸው በመልካቸውም ሆነ በአስተሳሰባቸው የተለያዩ ናቸው። ይሔ ምንም ጥርጥር የለውም። ልዩነታችንን አንዱ ከሌላው ለመለየት በሚያስፈልግበት ጊዜ እንገልጸዋለን። በተረፈ ግን ዓለም እንደሚስማማው ሰዎች ሁሉ ነፃ እና እኩል ናቸው። ስለነፃነት እና እኩልነት ስናስብም ሆነ ስንናገር ሰዎች ሁሉ አንድ ናቸው በማለት እንስማማለን።›› አለ።
ተሰማ በዘውዴ ሃሳብ ፈገግ አለ፤ ‹‹አንተ ስለዓለም ሕዝብ እኩልነት፣ ነፃነት እና አንድነት ትናገራለህ። እኛ የአገርን አንድነት ለማምጣት ተራራ ሆኖብናል።›› አለ። ዘውዴ በበኩሉ ‹‹በጥባጭ ካለ በሰላም ለመኖር ችግር ማጋጠሙ የማይቀር ነው። ‹በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ውሀ ይጠጣል› ይባል አይደል? ስለአንድነት ደጋግመን የምንናገረው ወደን አይደለም። ወይም የራሳችን የምንለያይባቸው ነገሮች መኖራቸውን ዘንግተን አይደለም። ስለዓለም አንድ መሆን መግለፅ ብዙም ትርጉም ላይሰጠን፤ ወይም ዓለም አንድ መሆን አለበት ብለን ልንከራከርም ሆነ ላንከራከር እንችላለን። ነገር ግን ስለአገር አንድነት የምንለፈልፈው ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ እንጠብቃት ብለን ነው።
ነገር ግን ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ክፍተታችንን ተጠቅመው እንደ አይጥ ጉድጓድ ውስጥ እየተሸሎከለኩ ተግተው የሚሰሩ አሉ። ወደድንም ጠላንም፤ ባለማወቅም ሆነ እያወቅን ለማመን ብናመነታም ልዩነታችንን በማጉላት ላይ የሚሠሩ አሉ። ልዩነታችን መለያያችን ሳይሆን ውበታችን መሆኑን ማሳየት አለብን። እነሱ የሚያደፈርሱትን የኢትዮጵያ አንድነት ለማጽናት ስለኢትዮጵያ አንድነት ደጋግመን እንገልፃለን። ስለልዩነታችንማ እነርሱ በደንብ ደጋግመው በተለያየ መንገድ እየገለፁ ስለሚያስደነብሩን ስለልዩነታችን ደጋግሞ ማንሳት ተገቢ አይደለም። ልዩነታችን ውበት ጌጥ መሆኑን ግን ማሳየት ያስፈልጋል።
ነገሩ የኢትዮጵያ ምሁራኖችም ሆኑ አንዳንዴም የመንግስት ባለስልጣኖች ‹ሞኝ ለጠበቃው ሚስጥር ይሸሽጋል› እንደሚባለው ለአገር ጠበቃ ለሆነው ሕዝብ ሁሉን ነገር ግልፅ አድርገው በማሳወቅ የጋራ ዓላማ ይዞ አገር ከማቆም ይልቅ ሞኝ ችግሩን ለሚያቃልልለት ሰው እንደማይናገረው እና ችግር ላይ እንደሚወድቀው ሁሉ እነርሱም ስለኢትዮጵያ ጠላቶች በግልፅ በሚገባው ልክ ለሕዝብ ባለመናገራቸው ችግር ያጋጥማል።
ከ120 ሚሊየን ያላነሰ ሕዝብ ያላትን ለዛውም 70 በመቶ የሚሆነው መሥራት የሚችል ሕዝብ ያላትን ኢትዮጵያን፣ በባህል፣ በቋንቋ እና አንዳንዴም በዘር ሃረግ ሳይቀር ከጎረቤቶቿ ከኬንያም ሆነ ከሱዳን፣ ከኤርትራም ሆነ ከጅቡቲ፣ ከደቡብ ሱዳን ጋርም ሆነ ከሶማሌያ ጋር የምትተሳሰረውን ኢትዮጵያ፤ ምስራቅ አፍሪካን ጠቅልላ ነገ የዓለም ታላቅ አገር ሆና ልዕለ ሃያል እንዳትሆን አጥብቀው የሚሰሩ አይጠፉም።
በተጨማሪ ኢትዮጵያ የወደፊት ስጋታቸው ናት ሲባል የውሃ በረከትን የተጎናፀፈች ሕይወት የሆነውን ውሃ ለጎረቤቶቿ አሳልፋ የምትሰጥ ነች። ለጎረቤት አገራት በሙሉ ውሃዋን እያሳለፈች ትቸራለች። ይህ ለጋስነቷ ከአገራቱ ጋር ያስተሳስራታል። ለሱዳን አባይን፣ ለኤርትራ ተከዜን፣ ለኬንያ ቱርካናን፣ ለጅቡቲ አዋሽን መስጠቷ አገራቱ እንደእናታቸው እንዲያዩዋት ያስገድዳቸዋል። በሚደንቅ መልኩ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በብሔር እና በቋንቋ ከእነዚሁ አገራት ጋር ትተሳሰራለች። በተጨማሪ በታሪክ በቀኝ ባለመገዛት እና ለቀኝ ተገዢዎች ‹እምቢኝ› እንዲሉ ምሳሌ መሆኗ እና ወደፊትም በዚሁ መልኩ ሌሎቹንም ለተዘዋዋሪ ቀኝ ግዛት አንበረከክም እንዲሉ መንገድ ትከፍታለች ብለው የኢትዮጵያ መኖር እና ማደግ ያሳስባቸዋል።
‹‹ኢትዮጵያውያን ግን ዳሩ ሲሄድ መሃሉ ዳር እንደሚሆን ረስተን፤ ዳር ላለው ጥንቃቄ ካልተደረገ የመሃሉ ላይ እንከን እንደሚፈጠር ዘንግተን፤ ለመሃሉ የዳሩ ጥንካሬ ወሳኝነት እንዳለው በውል ሳናስብ፣ ዳር ላለው ምንም ሳንሠራ ኢትዮጵያዊነት እንደሚቀጥል እርግጠኛ ሆነናል። መሃል ያለው ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ፣ አማራ … ማንም ሆነ ማን ብቻውን ‹ኢትዮጵያ ነኝ› ቢልም ብቻውን ከሆነ አማራ ወይም ኦሮሞ እንጂ ኢትዮጵያን መሆን አይችልም። ይሔንን ዘንግተነዋል። በማለት ዘውዴ ረዥም ንግግሩን የበለጠ እየለጠጠ ለማስረዘም ሲሞክር ተሰማ አቋረጠው።
‹‹ለማለት የፈለግከው አልገባኝም። ምን ማለትህ ነው?›› ሲል ተሰማ ዘውዴን ጠየቀ። ዘውዴም በደፈናው ‹‹ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው›› ማለቴ ነው። አለው። ተሰማ የበለጠ ግራ ተጋባ። ገብረየስም የዘውዴ ንግግር ግልፅ የሆነለት አይመስልም። ገብረየስ በመጠኑ የተረዳው ኢትዮጵያን ለሁሉም የምትመች አገር እንድትሆን ምሁራን በሙያቸው ሰፊ ስራ ሊሰሩ ይገባል። በጥናትና ምርምሩ፣ ለችግሮች መፍትሄ በማመላከት እንጂ እነሱ የችግሩ አካል መሆን የለባቸውም። ችግር አባባሽ መሆን አይገባቸውም። አሁን አንዳንዱ ከመሀይም አስተሳሰብ የባሰ ሀሳበ ያለው ነው። ግን ድፍረት አይሁንብኝ እንጂ የስም ምሁራን አጋጥመውኛል። ዘውዴ ወደ ኋላ የተነገረው ግን በደንብ አልገባውም።
ዘውዴ በበኩሉ ‹‹በየዘመኑ በተለያየ መልኩ በደል ይኖራል። በነገስታቱ ጊዜ ባላባቶች ደሃው ላይ ሲጨክኑ ‹ደሃ የሚለብሰው እንጂ የሚከፍለው አያጣም› እያሉ በብዛት ያስገብሩ ነበር አሉ። ደሃ ቢጥርም ቢለፋም የሚከፍለውን ሲቆልሉበት ቅሬታ እየተሰማው ቢቆይም ፈርቶም ቢሆን ከመክፈል ወደኋላ አይልም ነበር። ‹ትናንት ጦሙን ያደረ ማን ነው?› ሲባል ‹እኔ ነኝ› ለሚል መልስ የሚሰጠው ‹ዛሬም ድገም ተብለሃል› ተብሎ ተመሳሳይ ችግር እንዲያጋጥመው ይደረግ ነበር አሉ። ዛሬም በኢትዮጵያ ያለው ተመሳሳይ ነው።
ኢትዮጵያውያን ዛሬም በደህነት ውስጥ እየማቀቅን ነው። ዳኛ ገንዘቡን ተቀማ እንደሚባለው፤ ለሌላው መትረፍ የሚችል ሕዝብ ለራሱ ሳይሆን ቀርቷል። በምሁራኖችም በመንግስትም በኩል ነገር ከልኩ ላያልፍ ቁምነገርን መልቀቃቸው ያስከፋል። በስሜት ወይም በይሉንታ ፈርቶ ሁሉን ከማሳወቅ መገታት ያሳዝናል። ትክክል ሊሆኑ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም ከጠላት ቀድሞ በመንቃት ምቀኛ አታሳጣኝ እያሉ፤ ምቀኛ የጠላውን የጎዳ መስሎት ተንኮል ሲሠራ ሳያስበው የሚመቀኘውን እንደሚጠቅመው ሁሉ ኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች መኖራቸውን በውል በማሳወቅ፤ አገር ለመጉዳት እየሰሩ ያሉትን በማጋለጥ የአገርን አንድነት ከማጠናከር ወደኋላ ማለት ሞኝነት ነው።
ራሳቸው አጥፍተው ሌላውን እንደጥፋተኛ አስመስለው የሚናገሩ ሃላፊዎች፤ በብዙ መልኩ ስለአገሪቱ ታሪክ ብቻ ሳይሆን አሁን ስላለው የዓለምም ሆነ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ስለኢትዮጵያውያን ስነ ልቦና፤ ወደፊት ለማደግ ስለሚቻልበት መንገድ ያለውን የመርፌ ቀዳዳ የሚያህል ዕድል መጠቀም ሲገባ ወደኋላ ማለት ‹ ማዕረገ ቢስ ራቱ ገሚስ › እንደሚባለው ይሆንባቸዋል።
ምክንያቱም ከሞት በኋላ የሚፃፍ ታሪክ እንዲኖረው ዕድሉን ያገኘ ሰው የተሰጠውን ዕድል በትክክል የማይጠቀም ከሆነ እንደውም በተሰጠው ዕድል ሳቢያ ችግር ያጋጥመዋል። መቼም ጆሮ አይሰጥምና በብዙ መልኩ ስለአንዳንዶች ጥሩውንም ሆነ መጥፎውን እየሰማን ነው። እናም የጊዜው ዕድለኞች ከተቀበሉን በተቻለን መጠን እንመክራለን። ካልሰሙን ግን ችግር ሊያስተምራቸው ስለሚችል እንተዋቸዋለን። ‹ደንቆሮ የሰማ ዕለት ያብዳል› እንደሚባለው እኛ የነገርናቸውን ካልሰሙ፤ ሰው ሰምቶት የማያውቅ የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥማቸው በጣም መናደዳቸው አይቀርም።
እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ቢነሱም ጊዜው ያልፋል። ምን ያምጣ ድሃ ምን ይግዛ ውሃ ብለው የናቁት ህዝብ በደሉን ስለሚያስብ እርሱም በተራው አልሰማም ማለት ሲጀምር የቤት ሥራውን በአግባቡ ያልሰራው ኃላፊ፤ እንኳን ከሞት በኋላ መልካም ታሪኩ ሊፃፍና ሃውልት ሊቆምለት ቀርቶ ተራ ሆኖ መኖር እንደሰማይ ይርቀበታልና ሁላችንም ከወዲሁ ብናስብ ይሻላል።›› ሲል ዘውዴ የዕለቱን ማሳሰቢያውን ተናግሮ እንደልማዱ የጠጣበትን ሳይከፍል ወደቤቱ ለመሔድ ሲነሳ ተሰማ እጁን ጎትቶ ወንበሩ ላይ አስቀመጠው።
ተሰማ ለዘውዴ፤ ‹‹መጨረሻ ላይ በአንድ ዓረፍተ ነገር ይሔንን ሁሉ የተናገርከው ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ሳታወሳስብ በግልፅ ንገረኝ። ከዛ የዕለቱን የጠጣህበትን ምንም ሳላንገራግር እዘጋዋለሁ ›› አለው። ዘውዴ ቆጣ ብሎ ፤ ‹‹ ወደህ ነው፤ ሕዝብ የሚበላውን እና የሚጠጣውን ማሟላት ባትችሉም በስሱም ቢሆን መክፈል ግዴታችሁ ነው።›› አለ። በድጋሚ ንግግሩን ቀጥሎ ‹‹ ማለት የፈለግኩት መንግስትም ሆነ ምሁራኖቻችን የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማጥፋት ምን ይህል እየተጉ መሆኑን እያወቁ፤ ካወቁም በኋላ ደግሞ ለሕዝብ በትክክል አለመግለፃቸው አደጋ አለው የሚል ነው። ሕዝብ ቢያውቅ ከጎናችሁ ሆኖ ይደግፋችሁ፤ ያለበለዚያ ሕዝብ ያጠፋችኋል ለማለት ነው። ስለኢትዮጵያ ጠላቶች ዓላማ በዝርዝር ማወቅ ከፈለግክ ደግሞ ሰሞኑን የዓለም ዋንጫ እግር ኳስን ስትመለከት በነበረው ሰዓት አንብብበት።›› ብሎ ዘውዴ ከግሮሰሪ ወጣ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2015